በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሁሉ የላቀውን ጠቃሚ ምክር ማግኘት

ከሁሉ የላቀውን ጠቃሚ ምክር ማግኘት

ከሁሉ የላቀውን ጠቃሚ ምክር ማግኘት

ሁሉም ሰው የተሳካ ሕይወት እንዲኖረው እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። በዚህ ውጥንቅጡ በወጣ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ሕይወት ለመኖር ጥሩ ምክር ማግኘትና ያንን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ጠቃሚ የሆነ ምክርን ለመስማት ብዙውን ጊዜ ፈቃደኞች አይደሉም። ብዙዎች እያንዳንዱ ሰው ሕይወቱን እንደፈለገው መምራት አለበት ይላሉ። እንዲያውም በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ተቃውሞ ያነሳው የመጀመሪያው ጠላት ሰይጣን ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለአዳምና ሔዋን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመሩ ሐሳብ አቅርቦላቸው እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያሳያል። ዘፍጥረት 3:5 ለሔዋን ምን እንዳላት ይናገራል:- ‘መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ፍሬ በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካሙንና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ያውቃል።’

አዳምና ሔዋን ፍሬውን ከበሉ በኋላ በራሳቸው አስተሳሰብ ብቻ እየተመሩ ያለምንም ችግር በተሳካ ሁኔታ መኖር ችለዋል? በፍጹም። መልካሙንና ክፉውን የሚለዩ መስሏቸው የወሰዱት እርምጃ ባስከተለባቸው ውጤት የተቆጩት ወዲያውኑ ነበር። የአምላክን ሞገስ ያጡ ሲሆን የድርጊታቸው የመጨረሻ ውጤት የሆነውን ሞትን እስኪቀምሱ ድረስ ፍጽምናቸውን አጥተው በመከራ የተሞላ ሕይወት ለመኖር ተገደዋል። (ዘፍጥረት 3:16-19, 23) ሞት ሁላችንንም ይነካናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] በኩል ወደ ዓለም እንደገባ ሁሉ፣ ሞትም በኃጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋል” ይላል።—ሮሜ 5:12

አዳምና ሔዋን ያደረጉት ምርጫ ያስከተለው የከፋ መዘዝ በግልጽ የሚታይ ቢሆንም አሁንም የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው አምላክ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ያለው ጥቅም ለብዙዎች አይታያቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትና ጠቃሚ’ መጽሐፍ መሆኑን እንዲሁም ‘ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆነን እንድንገኝ’ ሊረዳን እንደሚችል ራሱ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በውስጡ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ደስተኞች እንደምንሆን አያጠራጥርም። ይህ በተለይ የቤተሰብን ሕይወት በሚመለከት ይሠራል።

ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አምላክ የጋብቻን ዝግጅት ሲያቋቁም ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን አስቦ ነበር። (ዘፍጥረት 2:22-24፤ ማቴዎስ 19:6) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች “ጋብቻ . . . መኝታውም ንጹሕ ይሁን” የሚሉ ሲሆን ይህ የጋብቻ ጥምረት ከትዳር ውጪ በሚፈጸም የጾታ ግንኙነት መርከስ የለበትም። (ዕብራውያን 13:4) ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ብዙ ትዳሮች ይህን መመሪያ እንደማይከተሉ ሳታስተውል አትቀርም። አንዳንድ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር በሥራ ቦታቸው የመዳራት ልማድ አላቸው። ሌሎች ደግሞ ከትዳር ውጪ ከፍቅረኛቸው ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ ቤተሰባቸውን ይዋሻሉ። ይባስ ብሎ ደግሞ አንዳንዶች ባለፈው ርዕስ ላይ የጠቀስናት ቬሮኒካ እንዳጋጠማት ደስተኛ እንድሆንና ወጣት እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል በሚል ወጣት ከሆነ ግለሰብ ጋር ለመኖር ሲሉ የትዳር ጓደኛቸውን ጥለው ይሄዳሉ።

ይሁን እንጂ የተከፈለው መሥዋዕትነት ተከፍሎ ራስን ለማስደሰት የሚደረግ ጥረት ዘላቂ ደስታ አያመጣም። የሮናልድ ታሪክ ለዚህ ማስረጃ ሊሆን ይችላል። ሕይወቱን እንደሚያሻሽል ስለተሰማው ለ6 ዓመታት ውሽማው ከነበረችና ሁለት ልጆች ከወለደችለት ሴት ጋር አዲስ ቤተሰብ ለመመሥረት ሲል የቀድሞ ሚስቱን ትቷት ሄደ። ይሁን እንጂ ጎጆውን ካፈረሰ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውሽማው ጥላው ሄደች። በመጨረሻ ሮናልድ ከወላጆቹ ጋር መኖር ጀመረ። ስለደረሰበት ሁኔታ ሲናገር “በጣም የሚያሳፍር ነው” ይላል። በርካታ የእርሱ ዓይነት ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። በራስ ወዳድነት ሳቢያ የሚመጣው እንዲህ ያለው ድርጊት ፍቺና የቤተሰብ መፈራረስ ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ እንደ ሰደድ እሳት እንዲዛመት ያደረገ ከመሆኑም በላይ ልጅ አዋቂ ሳይባል ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ለመከራ ዳርጓል።

በአንጻሩ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እውነተኛ ደስታ ያስገኛል። ይህን ከራሱ ተሞክሮ ያየው ሮቤርቶ እንዲህ ይላል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው ምክር ምስጋና ይግባውና ሚስቴን ከማጣት ድኛለሁ። ማራኪ ቁመና ቢኖራቸው እንኳን የትዳር ጓደኛችን ካልሆኑ ሰዎች ጋር በመቅበጥ እውነተኛ ደስታ አናገኝም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምክር ለበርካታ ዓመታት ከጎኔ ያልተለየችውን ባለቤቴን በአድናቆት እንድይዛት ረድቶኛል።” መጽሐፍ ቅዱስ “ከወጣትነት ሚስታችሁም ጋር ያላችሁን ታማኝነት አታጓድሉ” በማለት የሚሰጠው ምክር በሮቤርቶ ሕይወት ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። (ሚልክያስ 2:15) ከመለኮታዊ ምክር ጥቅም ማግኘት የምንችልባቸው ሌሎች ዘርፎችስ ምንድን ናቸው?

ልጆቻችንን በማሳደግ ረገድ

ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ብዙ ገደቦች ሊያደርጉባቸው አይገባም የሚለው አስተሳሰብ ተስፋፍቶ ነበር። ልጆች አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን በሚመለከት የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ መተዉ ተገቢ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ይህ አስተሳሰብ የመጣው የልጆችን እድገት ላለመግታት በሚል ነው። እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች በፕሮግራም ያልተዋቀሩ የትምህርት መርሐ ግብሮች የተዘረጉ ሲሆን ተማሪዎቹ ክፍል ገብተው መማር አለመማራቸውን፣ በመዝናኛ የሚያሳልፉትን ጊዜ እንዲሁም የሚማሩትን የትምህርት ዓይነት የመወሰንና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች መብቶች ተሰጥቷቸው ነበር። በዚህ መልክ የተደራጀ አንድ ትምህርት ቤት “ልጆች በሚያደርጓቸው ውሳኔዎች አዋቂዎች አስተያየታቸውን ሳይሰነዝሩ ወይም ጣልቃ ሳይገቡባቸው ፍላጎታቸውን ያለገደብ እንዲገልጹ ማስቻል” የሚል ፖሊሲ ነበረው። በዛሬው ጊዜ የሰዎችን ባሕርይ የሚያጠኑ አንዳንድ ባለሞያዎች ወላጆች በፍቅር ላይ የተመሠረተ ተግሣጽ መስጠቱ አስፈላጊ እንደሆነ በሚሰማቸው ጊዜ እንኳን አንዳንድ የተግሣጽ ዓይነቶችን መስጠቱ ያለው ጥቅም አይታያቸውም።

እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ምን ውጤት አስከትሏል? ልል የሆነ የልጆች አስተዳደግ ለልጆች ‘ከልክ ያለፈ’ ነጻነት ይሰጣቸዋል ብለው የሚያምኑ ሰዎች በርካታ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ አስተዳደግ ለወንጀልና ለአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚዎች መበራከት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይሰማቸዋል።” በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው አስተያየታቸውን ከሰጡት ሰዎች መካከል ወደ 70 በመቶ የሚሆኑት በዛሬው ጊዜ ልጆችና ወጣቶች የሚያስፈልጋቸውን ያህል የወላጅ ቁጥጥር እንደማያገኙ ተሰምቷቸዋል። ብዙዎች በትምህርት ቤት የሚፈጸሙ ግድያዎችና ሌሎች ከባድ ወንጀሎች መንስኤያቸው “ልጆች መረን ተለቀው ማደጋቸው” እንደሆነ ይናገራሉ። ውጤቱ ይህን ያህል የከፋ በማይሆንበትም ጊዜ እንኳን ልጆችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ማሳደግ የሚያስከትለውን መዘዝ ወላጆችም ሆኑ ልጆች መቅመሳቸው አይቀርም።

መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን ይላል? ቅዱሳን ጽሑፎች ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን ጥብቅ መሆን እንዳለባቸውም ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቅለታል” ይላል። (ምሳሌ 22:15) እርግጥ ነው፣ ወላጆች የሚሰጡት ተግሣጽ ምንጊዜም ከሁኔታው ጋር ተስማሚ መሆን አለበት። ተግሣጽ በደግነት፣ ራስን በመግዛትና በአሳቢነት መሰጠት ይኖርበታል። በዚህ መንገድ የሚሰጥ ተግሣጽ ፍቅርን የሚያንጸባርቅ ይሆናል። ወላጆች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሳይሆን በፍቅር የሚሰጡት ተግሣጽ የበለጠ ግቡን ይመታል።

ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኛቸው ጉልህ ውጤቶች አሉ። በቅርቡ ትዳር የመሠረተ አርቱሮ የተባለ በሜክሲኮ የሚኖር የ30 ዓመት ሰው እንዲህ ይላል:- “አባቴ ቤተሰቡን የሚመሩት እሱና እናቴ መሆናቸውን ለእኔና ለወንድሞቼ ግልጽ አድርጎልናል። እኛን ከመገሠጽ ወደኋላ ብለው አያውቁም። ሆኖም ምንጊዜም ቢሆን ጊዜ ወስደው ያነጋግሩናል። አሁን ካደግሁ በኋላ የምመራውን የተረጋጋ ሕይወት ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ፤ ለዚህ በዋነኝነት አስተዋጽኦ ያደረገው በልጅነቴ ያገኘሁት ጥሩ አመራር እንደሆነ አውቃለሁ።”

ከሁሉ የላቀውን ጠቃሚ ምክር በሚገባ ተጠቀምበት

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ሊያገኘው የሚችለውን ከሁሉ የላቀ ጠቃሚ ምክር ይዟል። በውስጡ የያዘው መመሪያ በቤተሰብ ዙሪያ ብቻ ያተኮረ አይደለም። ብዙዎች የላቀ የጥበብ ምንጭ ከሆነው አካል በሚገኝ ምክር ሕይወታቸውን መምራት የሚያስገኘውን ጥቅም በማይገነዘቡበት ዓለም ውስጥ ስንኖር እንዴት መመላለስ እንደሚኖርብን ስለሚያስተምረን በብዙ መንገዶች ያስታጥቀናል።

የሰው ዘር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ በመዝሙራዊው ዳዊት በኩል “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝሙር 32:8) እኛን ከአደጋ ለመጠበቅ ምንጊዜም በትኩረት የሚከታተለን ፈጣሪ እንዳለ ማወቁ አያስደስትም? እንግዲያው ሁላችንም ‘ይሖዋ እኔን ከችግር ለመጠበቅ የሚሰጠኝን መመሪያ በትሕትና እቀበላለሁ?’ እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል” በማለት ፍቅራዊ ማበረታቻ ይሰጠናል።—ምሳሌ 3:5, 6

ይሖዋን ማወቅ ጥረትና ትጋት ይጠይቃል፤ ሆኖም የሰው ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ አምላክን ማወቅ ይችላሉ። ይሖዋ እንድንከተለው የሚያበረታታን የሕይወት መንገድ “ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ” አለው። በእርግጥም ከሚያስገኝልን ጥቅም አኳያ ትልቅ ትርፍ አለው ሊባል ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ 6:6

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥልቅ ማስተዋል ለመረዳትና ከዚያ ጋር ተስማምቶ መኖር ከሚያስገኘው በረከት ተካፋይ ለመሆን ከፈለግህ የአምላክን ቃል ማንበብንና ባነበብከው ነገር ላይ ማሰላሰልን በሕይወትህ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ ስጠው። እንዲህ ማድረግህ ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት እንድትችል ይረዳሃል። በተጨማሪም ሁሉም የሰው ዘር ከይሖዋ የተማረ በሚሆንበትና ሰላም በሚትረፈረፍበት የአምላክ አዲስ ዓለም ስለሚኖረው ሕይወት ትማራለህ።—ኢሳይያስ 54:13

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የትዳር ሰንሰለትን ለማጠናከር ያስችላል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጥሩ መመሪያ ለመስጠት መሠረት ሆኖ ያገለግላል፣ ሆኖም መዝናናትን አይከለክልም

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ የሚያውሉ የተረጋጋ ሕይወት መምራት ይችላሉ