በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንዳንድ ሰዎች ጳውሎስ የመርከብ መሰበር አደጋ የደረሰበት ከሲሲሊ በስተ ደቡብ በምትገኘው በማልታ ደሴት ሳይሆን ሌላ ደሴት ላይ ነው ይላሉ። ታዲያ አደጋው የተከሰተው የት ነበር?

ይህ ጥያቄ ሊነሳ የቻለው ሐዋርያው ጳውሎስ የመርከብ መሰበር አደጋ የደረሰበት ማልታ ደሴት ላይ ሳይሆን ከግሪክ በስተ ምዕራብ በአዮንያ ባሕር በምትገኘው ኮርፉ አቅራቢያ ባለችው ሴፋሎኒያ (ወይም ከፋሊኒያ) ላይ ነበር የሚል መላምት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመሰንዘሩ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ ጳውሎስ የሮም የክፍለ ጦር አዛዥ በሆነው ዩልዮስ ጥበቃ ሥር ሆኖ ከጥቂት ወታደሮችና ከጓደኞቹ ጋር ከቂሳርያ ጉዞ እንደጀመረ ይገልጻል። ካርታው ላይ እንደሚታየው ወደ ሲዶና ከዚያም ወደ ሙራ ተጓዙ። ከመጀመሪያው መርከብ ወርደው ከእስክንድርያ ግብፅ የመጣ ትልቅ እህል ጫኝ መርከብ ላይ ከተሳፈሩ በኋላ በስተ ምዕራብ ወደ ቀኒዶስ አመሩ። የኤጂያን ባሕር ለማቋረጥና የግሪክን ጫፍ አልፈው ወደ ሮም ለማምራት የመረጡትን መንገድ ተከትለው መሄድ አቃታቸው። ካጋጠማቸው ኃይለኛ ነፋስ የተነሳ የደቡብ አቅጣጫ ተከትለው ወደ ቀርጤስ መሄድ ግድ ሆነባቸው። ከዚያም የቀርጤስን ዳርቻ ተገን በማድረግ ጉዟቸውን ቀጠሉ። እዚያም መልካም ወደብ በተባለ ቦታ መርከባቸውን አቆሙ። ‘ከቀርጤስ ተነስተው’ ጉዞ ከጀመሩ በኋላ መርከቢቱ ‘“ሰሜናዊ ምሥራቅ” በሚባል ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተያዘች።’ ግዙፏ እህል ጫኝ መርከብ እስከ አሥራ አራተኛው ሌሊት ድረስ ‘ባሕር ላይ ከወዲያ ወዲህ ስትንገላታ’ ቆየች። በመጨረሻ 276 ሰዎች የጫነችው መርከብ፣ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆነው የግሪክኛው ጽሑፍ መላጥያ ብሎ በሚጠራት ደሴት ላይ ተሰባበረች።—የሐዋርያት ሥራ 27:1–28:1

ባለፉት በርካታ ዓመታት መላጥያ የተባለችው ይህች ደሴት የትኛዋ እንደሆነች የተለያየ ሐሳብ ሲሰጥ ቆይቷል። አንዳንዶች ደሴቲቷ በአድርያን ባሕር ላይ በክሮኤሺያ ጠረፍ አካባቢ የምትገኘው የሚለተ ኢሊሪካ ደሴት የአሁኗ መልየት እንደሆነች ይገምታሉ። ሆኖም በስተ ሰሜን አቅጣጫ የምትገኘው መልየት ጳውሎስ በጉዞው ወቅት ካለፈባቸው ከሰራኩስ፣ ከሲሲሊ እና ከኢጣሊያ ምዕራባዊ ዳርቻ ጋር ምንም ግንኙነት ስለሌላት እንደዚያ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።—የሐዋርያት ሥራ 28:11-13

አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መላጥያ በአሁኑ ጊዜ ማልታ ተብላ የምትጠራውን ሚለተ አፍሪካነስ የምትባለውን ደሴት ታመለክታለች የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ጳውሎስ የተሳፈረባት መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ የቆመችው ቀርጤስ በሚገኘው መልካም ወደብ ላይ ነበር። ከዚያም መርከቧ ከኃይለኛው ነፋስ የተነሳ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ቄዳ ለመጓዝ የተገደደች ሲሆን ለበርካታ ቀናትም በነፋስ ስትነዳ ቆየች። ስለዚህ በዐውሎ ነፋስ የተነዳችው መርከብ ወደ ምዕራብ መጓዟን ቀጥላ ማልታ ትደርሳለች ብሎ መደምደሙ በጣም አሳማኝ ነው።

ካኒባር እና ሃውሰን የቅዱስ ጳውሎስ ሕይወትና መልእክቶች (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በአካባቢው በብዛት የሚከሰተውን ነፋስ እንዲሁም መርከቧ የሄደችበትን “አቅጣጫና ፍጥነት” ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በክላውዳ [ወይም ቄዳ] እና በማልታ መካከል ያለው ርቀት 480 ማይል [770 ኪሎ ሜትር] እንኳ አይሞላም። የሁኔታዎቹ መገጣጠም አስገራሚ ከመሆኑ የተነሳ መርከበኞቹ በአሥራ አራተኛው ቀን ሌሊት [የደረሱበት] ቦታ ከማልታ በስተቀር ሌላ ሊሆን አይችልም ብለን እንድናምን ያደርገናል። ቦታው ማልታ የመሆኑ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው።”

የተለያዩ አማራጮች ሊቀርቡ ቢችሉም ካርታው ላይ እንደሚታየው የመርከብ መሰበር አደጋው የተከሰተው ማልታ ላይ ነው መባሉ መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው ዘገባ ጋር ይስማማል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኢየሩሳሌም

ቂሳርያ

ሲዶና

ሙራ

ቀኒዶስ

ቀርጤስ

ቄዳ

ማልታ

ሲሲሊ

ሰራኩስ

ሮም

መልየት

ግሪክ

ሴፋሎኒያ