በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያለ ምክንያት መጠላት

ያለ ምክንያት መጠላት

ያለ ምክንያት መጠላት

“ያለ ምክንያት ጠሉኝ።”—ዮሐንስ 15:25

1, 2. (ሀ) ክርስቲያኖች ሲሰደቡ አንዳንዶች ግራ የሚገባቸው ለምንድን ነው? ሆኖም እንዲህ ያለው ስድብ ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንመረምረው “ጥላቻ” ለሚለው ቃል የተሰጠውን የትኛውን ትርጉም ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

 የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለመከተል ይጥራሉ። በዚህም ምክንያት በብዙ አገሮች ውስጥ መልካም ስም አትርፈዋል። አንዳንድ ጊዜ ግን ስለ እነርሱ ማንነት የተሳሳተ ወሬ ይናፈሳል። ለምሳሌ ያህል፣ ሩሲያ ውስጥ በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ የሚኖሩ አንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣን “የይሖዋ ምሥክሮች በምሥጢር የሚንቀሳቀሱ፣ ሕጻናትን የሚያርዱና የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሕቡዕ ድርጅት ናቸው ተብሎ ይነገረን ነበር” ብለዋል። ይሁን እንጂ እኚህ ባለ ሥልጣን ከአንድ የአውራጃ ስብሰባ ጋር በተያያዘ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተቀራርበው ከሠሩ በኋላ እንዲህ ብለዋል፦ “አሁን ከማንኛውም ሰው ያልተለዩ፣ ፈገግታ የማይለያቸው . . . ሰዎች መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ። ሰላማውያንና ስክን ያሉ ሰዎች ናቸው። እንዲሁም እርስ በርሳቸው በጣም ይዋደዳሉ።” አክለውም “ሰዎች ስለ እነርሱ እንዲህ ያለ ውሸት ለምን እንደሚናገሩባቸው ሊገባኝ አይችልም” በማለት ተናግረዋል።—1 ጴጥሮስ 3:16

2 የአምላክ አገልጋዮች መጥፎ ሰዎች ተደርገው መቆጠራቸው ፈጽሞ አያስደስታቸውም። ሆኖም ኢየሱስ ተከታዮቹን “ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ። . . . ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው” በማለት አስጠንቅቋቸው ስለነበር ሰዎች ስለ እነርሱ ክፉ መናገራቸው አያስደንቃቸውም። a (ዮሐንስ 15:18-20, 25፤ መዝሙር 35:19፤ 69:4) ከዚያ ቀደም ሲል ደቀ መዛሙርቱን “ባለቤቱን ‘ብዔልዜቡል’ ካሉት ቤተ ሰዎቹንማ እንዴት አብልጠው አይሏቸውም!” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:25) ክርስቲያኖች እንዲህ ያለው ነቀፋ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸው የሚያስከትልባቸው መከራ ክፍል እንደሆነ ይገነዘባሉ።—ማቴዎስ 16:24

3. በእውነተኛ አምላኪዎች ላይ የሚደርሰው ስደት በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

3 በእውነተኛ አምላኪዎች ላይ የሚደርሰው ስደት ረጅም ዘመን አስቆጥሯል፤ እንዲያውም “ከጻድቁ ከአቤል” ጀምሮ ነው ለማለት ይቻላል። (ማቴዎስ 23:34, 35) እንዲህ ያለው ስደት በተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ የሚደርስ አይደለም። ኢየሱስ በእርሱ ስም የተነሳ ተከታዮቹን ‘ሰዎች ሁሉ እንደሚጠሏቸው’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:22) ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እኛን ጨምሮ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ስደት ይደርስብናል ብለው መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ይህ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?

የጥላቻው ቆስቋሽ

4. በአምላክ ሕዝቦች ላይ መሠረተ ቢስ ጥላቻ የሚቆሰቁሰው ማን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው እንዴት ነው?

4 የአምላክ ቃል፣ ከጅምሩ አንስቶ በእውነተኛ አምላኪዎች ላይ ጥላቻ የሚቆሰቁስ አንድ በዓይን የማይታይ ፍጡር እንደነበረ ይናገራል። የመጀመሪያው የእምነት ሰው አቤል እንዴት በጭካኔ እንደተገደለ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ የወንድሙን ነፍስ ያጠፋው ቃየን “የክፉው” ማለትም የሰይጣን “ወገን” እንደሆነ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:12) ቃየን የሰይጣንን ባሕርይ ያንጸባረቀ ሲሆን ዲያብሎስም እኩይ ዓላማውን ለማስፈጸም ተጠቅሞበታል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በኢዮብና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ለተሰነዘረው አረመኔያዊ ጥቃት የሰይጣን እጅ እንዳለበት ይናገራል። (ኢዮብ 1:12፤ 2:6, 7፤ ዮሐንስ 8:37, 44፤ 13:27) የራእይ መጽሐፍ “ዲያብሎስ ሊፈትናችሁ አንዳንዶቻችሁን ወደ እስር ቤት ይጥላል” በማለት በኢየሱስ ተከታዮች ላይ የሚደርሰውን ስደት የሚቆሰቁሰው ማን እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦታል። (ራእይ 2:10) አዎን፣ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ለሚሰነዘረው መሠረተ ቢስ ጥላቻ ዋነኛው ምንጭ ሰይጣን ነው።

5. ሰይጣን የአምላክ አገልጋዮችን የሚጠላበት ምክንያት ምንድን ነው?

5 ሰይጣን እውነተኛ አምላኪዎችን የሚጠላበት ምክንያት ምንድን ነው? ሰይጣን ለራሱ ካለው ከፍተኛ ግምት የተነሳ ‘ዘላለማዊውን ንጉሥ’ ይሖዋ አምላክን ተገዳደረ። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ 3:6) አምላክ ፍጥረታቱን የሚገዛበት መንገድ ፈጽሞ የማያፈናፍን ነው፣ ይሖዋን በንጹሕ ልብ ተገፋፍቶ የሚያገለግል ሰው የለም እንዲሁም ሰዎች እርሱን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስተው ነው በማለት ይከራከራል። ሰዎችን የመፈተን አጋጣሚ ቢሰጠው እያንዳንዱን ሰው አምላክን እንዳያገለግል ማድረግ እንደሚችል ይናገራል። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-7) ሰይጣን ይሖዋን ጨቋኝና ውሸታም እንደሆነና ውጥኑ እንዳልሰመረ አድርጎ በመግለጽ ራሱን ተቀናቃኝ ሉዓላዊ ገዥ አድርጎ ለማቅረብ ይጥራል። በመሆኑም በአምላክ አገልጋዮች ላይ የሚቆጣው ለመመለክ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ነው።—ማቴዎስ 4:8, 9

6. (ሀ) የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በሚመለከት የተነሳው ጥያቄ እኛን በግለሰብ ደረጃ የሚነካን እንዴት ነው? (ለ) የተነሳውን አከራካሪ ጉዳይ መረዳታችን ጽኑ አቋማችንን ጠብቀን እንድንኖር የሚረዳን እንዴት ነው? (በገጽ 16 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

6 ይህ አወዛጋቢ ጉዳይ አንተን እንዴት እንደሚነካ አስተውለሃል? የአምላክ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝም ሳትገነዘብ አትቀርም። ሆኖም፣ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህ ሁኔታዎች ከይሖዋ ሕግና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖሩን አስቸጋሪ እንዲያውም መከራ የሚያስከትል ቢያደርጉብህስ? ደግሞም አንዳች ጥቅም እንዳላስገኘልህ ቢሰማህስ? ይሖዋን ማገልገል ጥቅም የለውም የሚል መደምደሚያ ላይ ትደርሳለህ? ወይስ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና ግሩም ለሆኑት ባሕርያቱ ያለህ አድናቆት በመንገዱ መሄድህን እንድትቀጥል ይገፋፋሃል? (ዘዳግም 10:12, 13) ይሖዋ ሰይጣን በተወሰነ መጠን እንዲፈትነን በመፍቀድ እያንዳንዳችን ለሰይጣን ግድድር መልስ እንድንሰጥ የሚያስችል አጋጣሚ እንድናገኝ አድርጓል።—ምሳሌ 27:11

‘ሰዎች ሲነቅፏችሁ’

7. ሰይጣን እኛን ከይሖዋ ለማራቅ ከሚጠቀምባው ዘዴዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው?

7 ሰይጣን በይሖዋና በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ያነሳው ክስ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ከሚጠቀምባቸው የተንኮል ዘዴዎች መካከል አንዱን በሰፊው እንመልከት። ይህ ዘዴ የሐሰት ውንጀላ ነው። ኢየሱስ ሰይጣንን ‘የሐሰት አባት’ በማለት ጠርቶታል። (ዮሐንስ 8:44) “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም ያለው ዲያብሎስ የሚለው የተግባር ስሙ ሰይጣን አምላክን፣ ጠቃሚ የሆነውን ቃሉንና ቅዱስ ስሙን በማጉደፍ ረገድ ቀንደኛ መሆኑን ያሳያል። ዲያብሎስ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመገዳደር አሉባልታ፣ የሐሰት ውንጀላና ዓይን ያወጣ ውሸት የሚጠቀም ሲሆን የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ለማሳጣትም ተመሳሳይ ዘዴ ይጠቀማል። በእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ በነቀፋ ላይ ነቀፋ በመደረብ ከባድ የሆነውን ፈተናቸውን መሸከም እስከማይችሉ ድረስ ያከብድባቸዋል።

8. ሰይጣን ኢዮብን የነቀፈው ምን በማድረግ ነው? ውጤቱስ?

8 ስሙ “የጥላቻ ዒላማ” የሚል ትርጉም ያለው ኢዮብ ምን እንደደረሰበት ተመልከት። ሰይጣን ኢዮብ መተዳደሪያውን፣ ልጆቹንና ጤንነቱን እንዲያጣ ከማድረጉም በላይ ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት አምላክ እየቀጣው እንደሆነ ለማስመሰል ሞክሯል። ኢዮብ እጅግ የተከበረ ሰው የነበረ ቢሆንም በዘመዶቹና በቅርብ ወዳጆቹ ሳይቀር ተዘልፏል። (ኢዮብ 19:13-19፤ 29:1, 2, 7-11) ከዚህም በላይ ሰይጣን የሐሰት አጽናኞችን ተጠቅሞ በመጀመሪያ አንድ ዓይነት ኃጢአት እንደሠራ የሚያስመስል ነገር በመናገር ከዚያም በቀጥታ ኃጢአት ሠርቷል በማለት ‘በቃላት ደቁሶታል።’ (ኢዮብ 4:6-9፤ 19:2፤ 22:5-10) ይህ ኢዮብን በጣም አሳዝኖት መሆን አለበት!

9. ኢየሱስን ኃጢአተኛ ለማስመሰል ምን ተደርጓል?

9 የአምላክ ልጅ የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ ረገድ የላቀ በመሆኑ የሰይጣን ጥላቻ ዋነኛ ዒላማ ሆኗል። ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ሰይጣን ልክ በኢዮብ ላይ እንዳደረገው ኃጢአተኛ እንደሆነ በመናገር መልካም ስሙን ለማጉደፍ ጥሯል። (ኢሳይያስ 53:2-4፤ ዮሐንስ 9:24) ሰዎች ሰካራምና ሆዳም ብለው የሰደቡት ከመሆኑም በላይ ‘ጋኔን አድሮበታል’ ብለውታል። (ማቴዎስ 11:18, 19፤ ዮሐንስ 7:20፤ 8:48፤ 10:20) አምላክን ሰድቧል ተብሎም በሐሰት ተወንጅሏል። (ማቴዎስ 9:2, 3፤ 26:63-66፤ ዮሐንስ 10:33-36) ኢየሱስ ይህ ሁኔታ በአባቱ ላይ ተገቢ ያልሆነ ነቀፋ እንደሚያስከትል ያውቅ ስለነበር አስጨንቆታል። (ሉቃስ 22:41-44) በመጨረሻም ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ተሰቅሎ ተገደለ። (ማቴዎስ 27:38-44) ኢየሱስ “ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ” በመታገሥ ጸንቶ ቆሟል።—ዕብራውያን 12:2, 3

10. በዛሬው ጊዜ ቅቡዓን ቀሪዎች የሰይጣን ጥቃት ዒላማ የሆኑት እንዴት ነው?

10 በዘመናችንም የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎች የዲያብሎስ ጥላቻ ዒላማ ሆነዋል። ሰይጣን ‘ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከሳቸው የነበረው፣ የክርስቶስ ወንድሞች ከሳሽ’ ተብሎ ተገልጿል። (ራእይ 12:9, 10) ሰይጣን ከሰማይ ተጥሎ በምድር አካባቢ ከተወሰነበት ጊዜ አንስቶ የክርስቶስ ወንድሞች እንዲናቁና እንዲገለሉ የሚያደርገውን ጥረት አፋፍሞ ቀጥሏል። (1 ቆሮንቶስ 4:13) በአንዳንድ አገሮች ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አደገኛ ኑፋቄ ተብለው ተሰድበዋል። (የሐዋርያት ሥራ 24:5, 14፤ 28:22) በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ስማቸውን ለማጉደፍ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ይነዛባቸዋል። ይሁንና የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ‘ክብርና ውርደት፣ መመስገንና መሰደብ’ ቢደርስባቸውም አጋሮቻቸው በሆኑት “ሌሎች በጎች” እየታገዙ ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመጠበቅና ስለ ኢየሱስ ለመመስከር’ በትሕትና ጥረት አድርገዋል።—2 ቆሮንቶስ 6:8፤ ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 12:17

11, 12. (ሀ) ክርስቲያኖች ነቀፋ የሚሰነዘርባቸው በምን ምክንያቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል? (ለ) አንድ ክርስቲያን በእምነቱ ምክንያት እንዴት ያለ ፍትሕ የጎደለው ሁኔታ ሊደርስበት ይችላል?

11 እርግጥ ነው፣ የአምላክ አገልጋዮች ሁልጊዜ ነቀፋ የሚሰነዘርባቸው ‘ለጽድቅ ሲባል’ ነው ማለት አይደለም። (ማቴዎስ 5:10) አንዳንድ ጊዜ ችግሮች የሚደርሱብን ከራሳችን አለፍጽምና የተነሳ ሊሆን ይችላል። ‘ክፉ ሥራ ሠርተን ብንቀጣና ብንታገሥ’ ማንም አበጀህ አይለንም። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ‘ስለ እግዚአብሔር ሲል የግፍ መከራን ቢቀበል’ በይሖዋ ፊት “ምስጋና ያገኛል።” (1 ጴጥሮስ 2:19, 20) ክርስቲያኖች ግፍና መከራ የሚደርስባቸው እንዴት ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ነው?

12 አንዳንዶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ በሌላቸው የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት በደል ተፈጽሞባቸዋል። (ዘዳግም 14:1) ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ከይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው በመኖራቸው ነጋ ጠባ የስድብ ናዳ ይወርድባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 4:4) አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ደም አልባ ሕክምና እንዲያገኙ ስለጠየቁ ብቻ “ደንታ ቢሶች” ወይም “ግፈኞች” ተብለው በሐሰት ተከሰዋል። (የሐዋርያት ሥራ 15:29) አንዳንዶች ደግሞ የይሖዋ አገልጋዮች ስለሆኑ ብቻ ዘመዶቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ዓይንህ ላፈር ብለዋቸዋል። (ማቴዎስ 10:34-37) እንደነዚህ ያሉ ክርስቲያኖች ተገቢ ያልሆነ ሥቃይ በመቀበል ረገድ የነቢያትንና የኢየሱስን ፈለግ ይከተላሉ።—ማቴዎስ 5:11, 12፤ ያዕቆብ 5:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:21

የሚደርስብንን ነቀፋ ችሎ መኖር

13. ከባድ ተቃውሞ ሲያጋጥመን መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንዳንስት ምን ሊረዳን ይችላል?

13 በእምነታችን ምክንያት ከባድ ትችት ሲሰነዘርብን እኛም እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ተስፋ ልንቆርጥና አምላክን ማገልገላችንን መቀጠል እንደማንችል ሊሰማን ይችላል። (ኤርምያስ 20:7-9) መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንዳንስት ምን ሊረዳን ይችላል? ነገሩን በይሖዋ ዓይን ለማየት ሞክሩ። ይሖዋ ፈተና ሲደርስባቸው ታማኝነታቸውን የጠበቁትን የሚመለከታቸው የክፉዎች የጥቃት ሰለባ እንደሆኑ ብቻ አድርጎ ሳይሆን እንደ አሸናፊዎች ነው። (ሮሜ 8:37) ዲያብሎስ ክብራቸውን የሚነካ ማንኛውንም ዓይነት ፈተና ቢያመጣባቸውም የይሖዋን ሉዓላዊነት በታማኝነት የደገፉትን እንደ አቤል፣ ኢዮብና የኢየሱስ እናት ማርያም ያሉ የጥንት ታማኝ አገልጋዮችና በዚህ ዘመን ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች ለማስታወስ ሞክር። (ዕብራውያን 11:35-37፤ 12:1) ጽኑ አቋማቸውን ላለማላላት ስለወሰዱት እርምጃ አስብ። እንደ ደመና ያሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እኛም ዓለምን በእምነታችን ድል አድርገን ሽልማቱን ለመቀበል በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ እንድንቆም ይጋብዙናል።—1 ዮሐንስ 5:4

14. ልባዊ ጸሎት ማድረጋችን ታማኝነታችንን ጠብቀን እንድንኖር ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

14 ‘የውስጣችን ጭንቀት ከበዛ’ ይሖዋ እንዲረዳን ከልብ መጸለይ የምንችል ሲሆን እርሱም ያጽናናናል እንዲሁም ያበረታናል። (መዝሙር 50:15፤ 94:19) ፈተናውን እንድንቋቋም የሚያስፈልገንን ጥበብ የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ በአገልጋዮቹ ላይ ለሚደርሰው ጭፍን ጥላቻ ምክንያት የሆነውን ከሉዓላዊነቱ ጋር የተያያዘውን ወሳኝ ጥያቄ እንዳንዘነጋ ይረዳናል። (ያዕቆብ 1:5) ይሖዋ ‘ከማስተዋል በላይ የሆነውን ሰላሙንም’ ሊሰጠን ይችላል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ከአምላክ የሚገኘው ይህ ሰላም ከፍተኛ ውጥረት በሚያጋጥመን ጊዜ እንድንረጋጋ እንዲሁም ሳንጠራጠር ወይም ሳንፈራ በቆራጥነት እንድንጋፈጠው ያስችለናል። ይሖዋ በእኛ ላይ እንዲደርስ የሚፈቅደውን ማንኛውንም ፈተና ችለን እንድናልፍ በመንፈሱ አማካኝነት ይረዳናል።—1 ቆሮንቶስ 10:13

15. ሥቃይ ሲደርስብን እንዳንመረር ምን ሊረዳን ይችላል?

15 ያለ ምክንያት በሚጠሉን ሰዎች እንዳንመረር ምን ሊረዳን ይችላል? ቀንደኞቹ ጠላቶቻችን ሰይጣንና አጋንንቱ መሆናቸውን አትዘንጉ። (ኤፌሶን 6:12) አንዳንድ ሰዎች አውቀውና ሆነ ብለው የሚያሳድዱን ቢሆንም የአምላክን ሕዝቦች ከሚቃወሙት መካከል ብዙዎቹ ይህን የሚያደርጉት ካለማወቅ ወይም በሌሎች ግፊት ነው። (ዳንኤል 6:4-16፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:12, 13) ይሖዋ ‘ሰዎች ሁሉ የሚድኑበትና እውነትን የሚሰሙበት’ አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) እንዲያውም ቀድሞ ተቃዋሚዎች የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንከን የማይወጣለትን ምግባራችንን ተመልክተው የእምነት ወንድሞቻችን ሆነዋል። (1 ጴጥሮስ 2:12) በተጨማሪም ከያዕቆብ ልጅ ከዮሴፍ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። ዮሴፍ በወንድሞቹ ምክንያት ብዙ መከራ ቢደርስበትም ለእነርሱ የጥላቻ ስሜት አላደረበትም። ለምን? ምክንያቱም በጉዳዩ ውስጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበትና ዓላማውን በዚህ መንገድ ሊያስፈጽም እንዳሰበ ተገንዝቦ ስለነበር ነው። (ዘፍጥረት 45:4-8) በተመሳሳይ ይሖዋ የሚደርስብንን ማንኛውንም ተገቢ ያልሆነ ሥቃይ ለስሙ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል።—1 ጴጥሮስ 4:16

16, 17. ተቃዋሚዎች የስብከቱን ሥራ ለማስተጓጎል የሚያደርጉት ጥረት ሊያስጨንቀን የማይገባው ለምንድን ነው?

16 ተቃዋሚዎች ምሥራቹ እንዳይስፋፋ የሚያደርጉት ጥረት ለጊዜውም ቢሆን የተሳካላቸው በሚመስልበት ወቅት እንኳ ከልክ በላይ መጨነቅ አያስፈልገንም። ይሖዋ በዓለም ዙሪያ እየተሰጠ ባለው ምሥክርነት አማካኝነት ሕዝቦችን እያናወጠ በመሆኑ የተመረጡ ዕቃዎች ወደ ቤቱ በመምጣት ላይ ናቸው። (ሐጌ 2:7 የ1954 ትርጉም) መልካሙ እረኛ ክርስቶስ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ . . . ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም።” (ዮሐንስ 10:27-29) ቅዱሳን መላእክትም በታላቁ መንፈሳዊ የመከር ሥራ በመካፈል ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 13:39, 41፤ ራእይ 14:6, 7) በመሆኑም ተቃዋሚዎች ያሻቸውን ቢናገሩ ወይም ቢያደርጉ የአምላክን ዓላማ ሊያጨናግፉ አይችሉም።—ኢሳይያስ 54:17፤ የሐዋርያት ሥራ 5:38, 39

17 ብዙውን ጊዜ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉት ጥረት ያልተጠበቀ ውጤት ያስገኛል። በአንድ የአፍሪካ አገር ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በርካታ የሐሰት ወሬዎች ይናፈሱ ነበር። ከእነዚህ መካከል የዲያብሎስ አምላኪዎች ናቸው የሚለው ይገኝበታል። በዚህ ምክንያት ግሬስ የተባለች አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች እቤቷ በመጡ ቁጥር ወደ ጓሮ ትሮጥና እነርሱ እስኪሄዱ ድረስ ትደበቃለች። አንድ ቀን የቤተ ክርስቲያኗ ቄስ ከጽሑፎቻችን መካከል አንዱን ከፍ አድርጎ እያሳየ እምነታቸውን እንዳያስቀይራቸው ጽሑፉን እንዳያነቡ እዚያ የተገኙትን ሁሉ አስጠነቀቀ። ይህ ሁኔታ ግሬስን የማወቅ ፍላጎት አሳደረባት። በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷ ሲመጡ እንደ በፊቱ ሳትደበቅ ያነጋገረቻቸው ከመሆኑም በላይ ያንን ጽሑፍ ወሰደች። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምራ በ1996 ተጠመቀች። አሁን ግሬስ ጊዜዋን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተዛባ ግንዛቤ ያላቸውን ሰዎች ለመፈለግ ትጠቀምበታለች።

እምነታችሁን ከወዲሁ አጠናክሩ

18. ከባድ ፈተናዎች ከመምጣታቸው በፊት እምነታችንን ማጠናከራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

18 ሰይጣን በጭፍን ጥላቻ ተነሳስቶ በማንኛውም ጊዜ ድንገተኛ ጥቃት ሊከፍትብን ስለሚችል እምነታችንን ከወዲሁ ማጠናከራችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የይሖዋ ሕዝቦች ይሰደዱበት ከነበረ አንድ አገር የተላከ ሪፓርት እንዲህ ይላል፦ “አንድ ነገር በጣም ግልጽ ሆኖልናል፦ ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶችና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥልቅ አድናቆት ያላቸው ክርስቲያኖች በፈተና ጊዜ ጸንቶ ለመቆም ምንም ችግር አያጋጥማቸውም። ይሁን እንጂ ‘አመቺ በሆነ ጊዜ’ ከጉባኤ የሚቀሩ፣ በመስክ አገልግሎት አዘውትረው የማይካፈሉና ጥቃቅን በሚመስሉ ጉዳዮች አቋማቸውን የሚያላሉ ከባድ ፈተና ሲያጋጥማቸው ብዙውን ጊዜ ጸንተው መቆም አይችሉም።” (2 ጢሞቴዎስ 4:2) አንተም ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ጥረት አድርግ።—መዝሙር 119:60

19. የአምላክ አገልጋዮች ያለ ምክንያት ሲጠሉ ከአቋማቸው ፍንክች አለማለታቸው ምን ውጤት ያስገኛል?

19 እውነተኛ አምላኪዎች ከሰይጣን የመረረ ጥላቻ ሲያጋጥማቸው ጽኑ አቋማቸውን ጠብቀው መኖራቸው የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክል፣ ተገቢና ጽድቅ የተሞላበት ለመሆኑ ሕያው ምሥክር ነው። ታማኝነታቸው የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል። ሰዎች ክፉኛ ቢነቅፏቸውም ክብሩ ከምድርና ከሰማይ በላይ የሆነው ይሖዋ ‘አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አያፍርም።’ በእርግጥም፣ እነዚህን ታማኝ አገልጋዮች በሚመለከት “ዓለም ለእነርሱ አልተገባቻቸውም” መባሉ ትክክል ነው።—ዕብራውያን 11:16, 38

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጥላቻ” የሚለው ቃል የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከሌላው ባነሰ መጠን መውደድ የሚል ትርጉም አለው። (ዘዳግም 21:15, 16) ከዚህ በተጨማሪ “ጥላቻ” የሚለው ቃል አንድ ሰው ጉዳት የማድረስ ዓላማ ባይኖረውም እንኳ አንድን ነገር መጸየፉን ወይም መራቁን ሊያመለክት ይችላል። ይሁን እንጂ “ጥላቻ” የሚለው ቃል የማጥቃት ፍላጎት የታከለበት ሥር የሰደደን የጠላትነት ስሜት ሊያመለክትም ይችላል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንመረምረው እንዲህ ያለውን ጥላቻ ነው።

ልታብራራ ትችላለህ?

• በእውነተኛ አምላኪዎች ላይ ለተነጣጠረው መሠረተ ቢስ ጥላቻ ምክንያቱ ምንድን ነው?

• ሰይጣን ኢዮብንና ኢየሱስን በመንቀፍ አቋማቸውን እንዲያላሉ ለማድረግ የሞከረው እንዴት ነው?

• ይሖዋ ለሰይጣን ጥላቻ እንዳንንበረከክ የሚያበረታን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሚሰደዱበት ዋነኛው ምክንያት ገብቷቸዋል

የአምላክን መንግሥት የመስበኩ ሥራ ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ታግዶ በነበረበት በዩክሬን የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታ ሰዎች ለእነርሱ ባላቸው አመለካከት ብቻ ሊመዘን አይገባውም። . . . አብዛኞቹ ባለ ሥልጣናት ሥራቸው የሚጠይቅባቸውን ግዴታ እየተወጡ ነበር። መንግሥት ሲለወጥ ባለ ሥልጣናቱም አቋማቸውን ለወጡ። እኛ ግን ያው ነበርን። የመከራችን ዋነኛ ምንጭ ማን መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተገንዝበናል።

“ራሳችንን የምንመለከተው የጨቋኞች ጥቃት ዒላማ የሆንን ምስኪን ሰዎች አድርገን አይደለም። እንድንጸና የረዳን የአምላክን የመግዛት መብት በሚመለከት በዔድን ገነት የተነሳውን አከራካሪ ጥያቄ በሚገባ መገንዘባችን ነበር። . . . ከሰዎች የግል ፍላጎት ጋር ብቻ ሳይሆን ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ፍላጎት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ አቋም ወስደናል። ስለተነሱት ዋነኛ አከራካሪ ጉዳዮች ከማንም የተሻለ ግንዛቤ አለን። ብርቱዎች እንድንሆንና በጣም አሰቃቂ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ ጽኑ አቋማችንን እንድንጠብቅ ያስቻለን ይህ ነው።”

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1970 የታሰረው ቪክቶር ፖፖቪች

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ለተሰነዘረበት ነቀፋ በዋነኝነት የሚጠየቀው ማን ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብና ማርያም እንዲሁም ስታንሊ ጆንስን የመሳሰሉ በዘመናችን የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፈዋል