በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ምክር ማግኘት ያስፈልገን ይሆን?

ጥሩ ምክር ማግኘት ያስፈልገን ይሆን?

ጥሩ ምክር ማግኘት ያስፈልገን ይሆን?

በዛሬው ጊዜ ብዙዎች መልካሙን ከክፉው የመለየት ብቃትና ያሻቸውን የማድረግ መብት እንዳላቸው ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ አንድ ሰው ደስታ የሚያስገኝለት ከሆነ የፈለገውን ነገር ቢያደርግ ችግር የለውም ይላሉ። በዚህም ሳቢያ ለዘመናት የሰብዓዊው ኅብረተሰብ ምሰሶ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ የነበሩት ጋብቻና የቤተሰብ ሕይወት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው ነው።—ዘፍጥረት 3:5

በሜክሲኮ የምትኖረው ቬሮኒካ a ያጋጠማትን ተመልከት። እንዲህ ትላለች:- “በትዳር ውስጥ ወደ 15 የሚጠጉ ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ባለቤቴ ከሌላ ሴት ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመሩን ነገረኝ። ወጣት ስለሆነችና ስለምታስደስተው ሊተዋት እንደማይፈልግ ገለጸልኝ። እንደ ልብ ጓደኛዬ የማየው ባሌ ከዚህ በኋላ ከጎኔ እንደማይኖር ሳውቅ በጣም ደነገጥኩ። የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት ከማጣት የበለጠ የሚያሳዝን ነገር ያለ አይመስለኝም ነበር። የባለቤቴ ማመንዘር ግን ከዚያም የከፋ ሆኖብኛል፤ ከልቤ የምወደው ሰው ጥሎኝ መሄዱ ሳያንስ ስሜቴን የሚጎዳውን ነገር ሆን ብሎ እያደረገ መሆኑ ይበልጥ ያንገበግበኛል።”

በ22 ዓመቱ ትዳሩ የፈረሰውንና ወንድ ልጁን የማሳደግ የአባትነት ኃላፊነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነውን የ22 ዓመት ወጣት ሁኔታ ደግሞ እንመልከት። እናቱ እሱንም ሆነ ልጁን እንድትንከባከባቸው ይፈልጋል። የጠየቃትን ነገር ሁሉ ካላደረገችለት እንደ ቀበጥ ሕፃን ይበሳጭና ሊሰድባት ይጀምራል። በቁጣ በሚገነፍልበት ወቅት እናቱ ምን እንደምታደርግ ግራ ይገባታል።

እነዚህ ያልተለመዱ ሁኔታዎች አይደሉም። በሕግ መለያየትና ፍቺ በየቦታው እየተስፋፋ ነው። ብዙ ልጆች ከወላጆቻቸው አንዱ አዲስ ሕይወት ለመጀመር በሚል ቤቱን ትቶ ሲሄድ ይመለከታሉ። አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ለወላጆቻቸውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች አክብሮት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ቀደም ባሉ ጊዜያት ጨርሶ የማይታሰቡ በነበሩ ድርጊቶች ይካፈላሉ። ልቅ የጾታ ብልግና፣ አደገኛ ዕፅ መውሰድ፣ በወጣቶች የሚፈጸሙ ጥቃቶችና የመምህራን ወይም የወላጆች በልጆች መገደል በብዙ አገሮች የዕለት ተዕለት ክስተቶች ሆነዋል። ችግሮች እያጋጠሙ ያሉት በልጆች አስተዳደግና በትዳር ሕይወት ዙሪያ ብቻ እንዳልሆነ አንተም ሳታስተውል አትቀርም።

እንዲህ ያሉ ክስተቶችን ስንመለከት ኅብረተሰባችን ወዴት እያመራ ነው? የሚል ጥያቄ ይደቀንብናል። ሰዎች መልካሙን ከክፉ መለየት የሚችሉ ከሆነ እነዚህ ሁሉ ችግሮች መፍትሔ የማያገኙት ለምንድን ነው? ጥሩ ምክር ማግኘት ያስፈልገን ይሆን? ከሆነስ አስተማማኝነቱ የተረጋገጠለት ጠቃሚ ምክር ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው? ብዙዎች በአምላክና በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ እንደሚያምኑ ቢናገሩም ይህ በውሳኔዎቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሲያደርግ አይታይም። ይሁን እንጂ የአምላክን ምክር ለመስማት ጥረት ስናደርግ ምን ጥቅሞች እናገኛለን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህን እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሟ ተቀይሯል።