በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለልጆቻችሁ ማውረስ የሚገባችሁ ምንድን ነው?

ለልጆቻችሁ ማውረስ የሚገባችሁ ምንድን ነው?

ለልጆቻችሁ ማውረስ የሚገባችሁ ምንድን ነው?

በደቡብ አውሮፓ የሚኖረው ፓቭሎስ 7 ዓመት የሆነው አንድ ወንድና 11 እና 13 ዓመት የሆናቸው ሁለት ሴቶች ልጆች ቢኖሩትም ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር ጊዜ የሚያሳልፈው ግን ከስንት አንዴ ነው። የወደፊት ሕልሙን ለማሳካት ሲል በሳምንት ውስጥ ሰባቱንም ቀናት፣ በየቀኑ በሁለት ፈረቃዎች ይሠራል። ፓቭሎስ ለሁለቱም ሴቶች ልጆቹ አፓርታማ የመግዛትና ለወንድ ልጁ ደግሞ አነስተኛ ንግድ የማቋቋም እቅድ አለው። ባለቤቱ ሶፊያ ደግሞ ልጆቹ አድገው ጎጆ ሲወጡ የሚጠቀሙባቸው የአልጋ ልብሶችና የጠረጴዛ ጨርቆች፣ የሸክላ ዕቃዎች እንዲሁም የወጥ ቤትና የገበታ ዕቃዎች ለማጠራቀም ትደክማለች። ባልና ሚስቱ ይህን ያህል የሚለፉት ለምን እንደሆነ ሲጠየቁ “ለልጆቻችን ስንል ነው!” በማለት ይመልሳሉ።

እንደ ፓቭሎስና ሶፊያ ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው አድገው የራሳቸውን ኑሮ ሲመሠርቱ ጥሩ ጅምር እንዲኖራቸው በማሰብ የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። አንዳንዶች ልጆቹ ወደፊት እንዲጠቀሙበት በሚል ገንዘብ ያስቀምጣሉ። ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙና ለወደፊት ሕይወታቸው የሚጠቅማቸው ሞያ እንዲማሩ ያደርጋሉ። አብዛኞቹ ወላጆች እንደዚህ ያለው ስጦታ ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ እንደሆነ ቢሰማቸውም በዚህ ረገድ ዘመዶቻቸው፣ ወዳጆቻቸውና ኅብረተሰቡ የሚጠብቁባቸውን ለማሟላት የሚያደርጉት ጥረት ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ጫና ይፈጥርባቸዋል። በዚህም የተነሳ ጉዳዩ ያሳሰባቸው አንዳንድ ወላጆች ‘ለልጆቻችን ልናወርሳቸው የሚገባን ምን ያህል ነው?’ በማለት ተገቢ ጥያቄ ያነሳሉ።

ለልጆቻችሁ የወደፊት ሕይወት ዝግጅት ማድረግ

ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው የወደፊት ሕይወት አስበው ዝግጅት ማድረጋቸው ተገቢ ከመሆኑም በላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ወላጆች ለልጆች ገንዘብ ያከማቻሉ እንጂ ልጆች ለወላጆች አያከማቹም” ብሏቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 12:14) አክሎም ወላጆች ልጆቻቸውን የመንከባከብ ግዴታቸውን በቁም ነገር ሊመለከቱት እንደሚገባ አመልክቷል። “አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ከውርስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አክብደው ይመለከቷቸው እንደነበረ የሚያሳዩ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሰፈሩ በርካታ ዘገባዎች አሉ።—ሩት 2:19, 20፤ 3:9-13፤ 4:1-22፤ ኢዮብ 42:15

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ለልጆቻቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት ለማውረስ ስለሚፈልጉ በጣም ይጨነቃሉ። ከደቡብ አውሮፓ ወደ አሜሪካ የሄደ ማኖሊስ የተባለ አባት ይህ የሆነበትን አንዱን ምክንያት ሲገልጽ “በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ችግር የደረሰባቸው እንዲሁም ረሃብና ድህነትን የቀመሱ ወላጆች ልጆቻቸው የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ” ብሏል። አክሎም “ወላጆች ኃላፊነታቸውን በጣም አክብደው ስለሚመለከቱትና ልጆቻቸው በሕይወታቸው ውስጥ ጥሩ ጅምር እንዲኖራቸው ስለሚፈልጉ አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን ይጎዳሉ” ይላል። በእርግጥም አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ቁሳዊ ነገሮችን ለማከማቸት ሲሉ መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን በመተው ራሳቸውን ጨቁነው የችግር ኑሮ ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ወላጆች እንደዚህ ማድረጋቸው ጥበብ ይሆናል?

“ከንቱና ትልቅ ጉዳት”

የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ውርስን አስመልክቶ ሊታሰብበት የሚገባ ጥሩ ነጥብ ገልጿል:- “ከፀሓይ በታች የደከምሁበትን ነገር ሁሉ ጠላሁት፣ ከኋላዬ ለሚመጣው የግድ እተውለታለሁና። እርሱ ጠቢብ ወይም ሞኝ ይሆን እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም ከፀሓይ በታች ድካሜንና ችሎታዬን ባፈሰስሁበት ሥራ ሁሉ ላይ ባለቤት ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። . . . ምክንያቱም ሰው ሥራውን በጥበብ፣ በዕውቀትና በብልኀት ሠርቶ፣ ከዚያ ያለውን ሁሉ ለሌላ ላልለፋበት ሰው ይተውለታል። ይህም ደግሞ ከንቱና ትልቅ ጉዳት ነው።”—መክብብ 2:18-21

ሰሎሞን እንደገለጸው ወራሾች የሚሆኑት ልጆች እነርሱ ራሳቸው የደከሙበት ስላልሆነ ያገኙት ውርስ ምን ያህል እንደተለፋበት አይገነዘቡ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ወላጆቻቸው ስንት ደክመው ያወረሷቸውን ሃብት በአግባቡ ላይዙት ይባስ ብሎም ሊያባክኑት ይችላሉ። (ሉቃስ 15:11-16) ይህ በእርግጥም “ከንቱና ትልቅ ጉዳት” ይሆናል!

ውርስና ስግብግብነት

ወላጆች ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርባቸው ሌላም ነገር አለ። በውርስ ለሚገኝ ንብረትና የጋብቻ ስጦታ ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጥባቸው ባህሎች ልጆች ስግብግብነት ሊጠናወታቸውና የወላጆቻቸው አቅም ከሚፈቅደው በላይ ጥሎሽ ወይም ንብረት እንዲሰጣቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። በግሪክ የሚኖረው ሉካስ የተባለ አባት “ሁለት ወይም ሦስት ሴቶች ልጆች ያሉት ሰው ጉድ ፈላበት” ብሏል። አክሎም እንዲህ ይላል:- “ሴቶቹ ልጆች አባታቸው ሊሰጣቸው የሚችለውን ስጦታ ሌሎች ወላጆች ለልጆቻቸው ‘በለጋስነት’ ከሚያከማቹት ሃብት ጋር ያወዳድሩ ይሆናል። በቂ ጥሎሽ መስጠት ካልቻሉ የማግባት ዕድላቸው የተመናመነ እንደሚሆን ይናገሩ ይሆናል።”

ቀደም ሲል የተገለጸው ማኖሊስ እንዲህ ይላል:- “አንድ ወጣት ሊያገባት ያሰባት ልጅ አባት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወይም ንብረት እንደሚሰጣት ቃል እስኪገባለት ድረስ በመጠናናት የሚያሳልፉትን ጊዜ ያራዝመው ይሆናል። ነገሩ እንደ ማስፈራሪያ ሊሆን ይችላል።”

መጽሐፍ ቅዱስ በማንኛውም መልኩ ከስግብግብነት እንድንርቅ ያሳስባል። ሰሎሞን “ከጅምሩ ወዲያው [“በስግብግብነት፣” NW] የተገኘ ርስት፣ በመጨረሻ በረከት አይኖረውም” ብሏል። (ምሳሌ 20:21) ሐዋርያው ጳውሎስም “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው” በማለት አበክሮ ተናግሯል።—1 ጢሞቴዎስ 6:10፤ ኤፌሶን 5:5

“ጥበብ ከርስት ጋር”

ውርስ ጥቅም እንዳለው ባይካድም ጥበብ ግን ከቁሳዊ ሃብት በጣም የላቀ ዋጋ አለው። ንጉሥ ሰሎሞን “ጥበብ እንደ ርስት [“ከርስት ጋር፣” የ1954 ትርጉም] መልካም ነገር ነው፤ . . . ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው” በማለት ጽፏል። (መክብብ 7:11, 12፤ ምሳሌ 2:7 የ1980 ትርጉም፤ 3:21 የ1980 ትርጉም) ገንዘብ ያለው ሰው የፈለገውን ማግኘት ስለሚችል የመተማመን ስሜት ቢያድርበትም ገንዘቡ ሊጠፋ እንደሚችል ግን መዘንጋት የለበትም። በሌላ በኩል ጥበብ ማለትም ችግሮችን ለመፍታት ወይም አንድ ግብ ላይ ለመድረስ እውቀትን የመጠቀም ችሎታ አንድን ሰው የሞኝነት እርምጃ ከመውሰድ ይጠብቀዋል። በአምላካዊ ፍርሃት ላይ የተመሠረተ ጥበብ በቅርቡ በሚመጣው የአምላክ አዲስ ዓለም የዘላለም ሕይወት ያስገኛል፤ ይህ በእርግጥም ከፍተኛ ዋጋ ያለው ውርስ ነው!—2 ጴጥሮስ 3:13

ክርስቲያን ወላጆች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠትና ልጆቻቸውም እንዲሁ እንዲያደርጉ በማበረታታት እንደዚህ ያለውን ጥበብ ያሳያሉ። (ፊልጵስዩስ 1:10) ለልጆች ቁሳዊ ሃብት ማከማቸት ከመንፈሳዊ ነገሮች የበለጠ ቦታ ሊሰጠው አይገባም። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” በማለት አበረታቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:33) ለቤተሰባቸው መንፈሳዊ ግቦች የሚያወጡ ክርስቲያን ወላጆች የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያጭዱ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጻድቅ ሰው አባት እጅግ ደስ ይለዋል፤ ጠቢብ ልጅ ያለውም በእርሱ ሐሤት ያደርጋል። አባት እናትህ ደስ ይበላቸው፤ ወላጅ እናትህም ሐሤት ታድርግ።”—ምሳሌ 23:24, 25

ዘላለማዊ ውርስ

በጥንቶቹ እስራኤላውያን ዘንድ በውርስ የተገኘ ንብረት ትልቅ ቦታ ይሰጠው ነበር። (1 ነገሥት 21:2-6) ያም ሆኖ ይሖዋ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷቸዋል:- “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።” (ዘዳግም 6:6, 7) በተመሳሳይም ክርስቲያን ወላጆች “[ልጆቻችሁን] በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” ተብለዋል።—ኤፌሶን 6:4

መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ወላጆች ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ማቅረብ መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማርንም እንደሚጨምር ይገነዘባሉ። የሦስት ልጆች አባት የሆነው አንዝሪአስ “ልጆቻችሁ በአምላካዊ ሥርዓቶች መሠረት መመላለስ ከተማሩ ለወደፊት ሕይወታቸው የተሻለ መሠረት ይኖራቸዋል” ብሏል። እንደዚህ ያለው ውርስ ከፈጣሪያቸው ጋር የግል ዝምድና እንዲመሠርቱና ይህንን ዝምድና እያሳደጉት እንዲሄዱ መርዳትንም ይጨምራል።—1 ጢሞቴዎስ 6:19

ለልጆቻችሁ መንፈሳዊ ውርስ ስለማውረስ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ለምሳሌ፣ ወላጆች ልጃቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈል ከሆነ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቅም ሆነ መጠበቅ ባይኖርበትም አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች በአገልግሎቱ መቀጠል እንዲችል ‘በሚያስፈልገው ሊረዱት’ ይችላሉ። (ሮሜ 12:13 የ1954 ትርጉም፤ 1 ሳሙኤል 2:18, 19፤ ፊልጵስዩስ 4:14-18) እንደዚህ ያለው የደጋፊነት መንፈስ ይሖዋን እንደሚያስደስተው ምንም ጥያቄ የለውም።

እንግዲያው ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያወርሷቸው የሚገባው ምንድን ነው? ክርስቲያን ወላጆች የልጆቻቸውን ቁሳዊ ፍላጎት ከማሟላት በተጨማሪ ዘላለማዊ ጥቅም የሚያስገኝላቸውን መንፈሳዊ ውርስም ይሰጧቸዋል። እንዲህ ካደረጉ በመዝሙር 37:18 ላይ የሚገኘው “እግዚአብሔር የንጹሐንን የሕይወት ዘመን ያውቃል፤ ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል” የሚለው ጥቅስ ይፈጸምላቸዋል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለልጆቻችሁ ምን ዓይነት ግብ አውጥታችሁላቸዋል?