“በአንድ አፍ” አምላክን አክብሩ
“በአንድ አፍ” አምላክን አክብሩ
“በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት [አክብሩ]።”—ሮሜ 15:6
1. ጳውሎስ የአመለካከት ልዩነቶችን ስለ መፍታት ለእምነት ባልንጀሮቹ የሰጣቸው ትምህርት ምን ነበር?
ሁሉም ክርስቲያኖች አንድ ዓይነት ምርጫ ወይም ፍላጎት የላቸውም። ይሁንና ሁሉም ክርስቲያኖች በሕይወት ጎዳና ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው መጓዝ አለባቸው። ይህ የሚቻል ነው? በመካከላችን ያሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች አጋንነን የማንመለከት ከሆን በእርግጥ ይቻላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ የእምነት ባልንጀሮቹ የሰጣቸው ትምህርት ይህ ነበር። ጳውሎስ ይህን ወሳኝ ጉዳይ ያብራራው እንዴት ነበር? እኛስ በመንፈስ አነሳሽነት የተሰጠውን ይህን ምክር በዛሬው ጊዜ በተግባር ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?
የክርስቲያናዊ አንድነት አስፈላጊነት
2. ጳውሎስ የአንድነትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
2 ጳውሎስ ክርስቲያናዊ አንድነት ወሳኝ ነገር መሆኑን ያውቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ክርስቲያኖች በፍቅር ተቻችለው እንዲኖሩ ለመርዳት ጥሩ ምክር ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:1-3፤ ቆላስይስ 3:12-14) ይሁንና በርካታ ጉባኤዎችን ካቋቋመና ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ጉባኤዎችን ከጎበኘ በኋላ አንድነትን ጠብቆ መኖር በጣም አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተገነዘበ። (1 ቆሮንቶስ 1:11-13፤ ገላትያ 2:11-14) በመሆኑም በሮም የሚኖሩ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን ‘ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ አንድነት ይስጣችሁ’ ሲል አሳሰባቸው። (ሮሜ 15:5, 6) በዛሬው ጊዜ እኛም አንድነት ያለን ሕዝብ በመሆን “በአንድ አፍ” ይሖዋ አምላክን ማክበር ይኖርብናል። በዚህ ረገድ ምን ያህል ተሳክቶልናል?
3, 4. (ሀ) በሮም በነበሩ ክርስቲያኖች መካከል ምን ልዩነት ይታይ ነበር? (ለ) በሮም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ይሖዋን “በአንድ አፍ” ማገልገል የሚችሉት እንዴት ነው?
3 በሮም የሚኖሩ በርካታ ክርስቲያኖች ከጳውሎስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበራቸው። (ሮሜ 16:3-16) የተለያየ አስተዳደግ ቢኖራቸውም እንኳ ጳውሎስ ወንድሞቹን በአጠቃላይ ‘በእግዚአብሔር የተወደዱ’ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። “እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁም አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ” ሲል ጽፏል። በሮም ያሉ ክርስቲያኖች በብዙ መንገዶች ምሳሌ ተደርገው የሚታዩ መሆናቸው ግልጽ ነው። (ሮሜ 1:7, 8፤ 15:14) ይሁንና አንዳንድ የጉባኤው አባላት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የአመለካከት ልዩነት ነበራቸው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በአስተዳደግም ሆነ በባሕል የተለያዩ በመሆናቸው ጳውሎስ የአመለካከት ልዩነቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈውን ምክር ማጥናታቸው “በአንድ አፍ” እንዲናገሩ ሊረዳቸው ይችላል።
4 በሮም ከአይሁድም ሆነ ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች ይገኙ ነበር። (ሮሜ 4:1፤ 11:13) አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ በፊት ይጠብቋቸው የነበሩ በሙሴ ሕግ ሥር የተካተቱ የተወሰኑ ልማዶች ለመዳን አስፈላጊ አለመሆናቸውን ቢገነዘቡም እንኳ መላቀቅ ግን ከብዷቸው እንደነበር ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የኢየሱስ መሥዋዕት ክርስትናን ከመቀበላቸው በፊት ከተጣሉባቸው እገዳዎች ነፃ እንዳወጣቸው አምነው ተቀብለው ነበር። ከዚህም የተነሳ ይከተሏቸው የነበሩትን አንዳንድ ልማዶችና ሥርዓቶች እርግፍ አድርገው ተዉ። (ገላትያ 4:8-11) ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ እንደተናገረው ሁሉም ‘በእግዚአብሔር የተወደዱ’ ናቸው። አንዳቸው ለሌላው ትክክለኛ አመለካከት ካላቸው ሁሉም አምላክን “በአንድ አፍ” ማወደስ ይችላሉ። በዛሬው ጊዜ እኛም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አመለካከት ሊኖረን ስለሚችል ጳውሎስ ይህን አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት እንዴት እንዳብራራው በጥንቃቄ መመርመራችን ተገቢ ነው።—ሮሜ 15:4
“እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ”
5, 6. ሮም ውስጥ በነበረው ጉባኤ የአመለካከት ልዩነት የተፈጠረው ለምን ነበር?
5 ጳውሎስ በሮም ለነበሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የአመለካከት ልዩነት ስለታየበት ጉዳይ ተናግሯል። “የአንድ ሰው እምነቱ ማንኛውንም ነገር እንዲበላ ይፈቅድለታል፤ በእምነቱ ያልጠነከረው ሌላው ሰው ግን አትክልት ብቻ ይበላል” ሲል ጽፏል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? በሙሴ ሕግ ሥር የአሳማ ሥጋ መብላት ክልክል ነበር። (ሮሜ 14:2፤ ዘሌዋውያን 11:7) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ይህ ሕግ ተሻረ። (ኤፌሶን 2:15) ከዚያም ኢየሱስ ከሞተ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ አንድ መልአክ በአምላክ ዓይን የትኛውም ምግብ እርኩስ ተደርጎ እንደማይታይ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ገለጸለት። (የሐዋርያት ሥራ 11:7-12) አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እነዚህን ጉዳዮች ግምት ውስጥ በማስገባት የአሳማ ሥጋም ሆነ በሕጉ ውስጥ ተከልክለው የነበሩ ሌሎች ምግቦችን መብላት እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ይሆናል።
6 ሌሎች አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ደግሞ በፊት እርኩስ ተደርገው ይታዩ የነበሩ ምግቦችን መብላት ይቅርና ሐሳቡ ብቻ እንኳ ሊቀፋቸው ይችላል። ለውጡን ለመቀበል የከበዳቸው እነዚህ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ወንድሞቻቸው የሆኑ አይሁዶች እነዚህን ምግቦች ሲመገቡ ሲያዩ ስሜታቸው ተጎድቶ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ በፊት በነበሩበት ሃይማኖት የፈለጉትን የመብላት ነፃነት የነበራቸው አንዳንድ አሕዛብ ክርስቲያኖች በምግብ ጉዳይ ውዝግብ መፈጠሩ ሳያስገርማቸው አልቀረም። እርግጥ አንድ ሰው ለመዳን ከአንዳንድ ምግቦች መራቅ ያስፈልጋል የሚል አቋም እስካልያዘ ድረስ ከአንዳንድ ምግቦች መራቁ ምንም ስህተት የለውም። ይሁንና የአመለካከት ልዩነት መኖሩ በጉባኤው ውስጥ በቀላሉ ንትርክ ሊፈጥር ይችላል። በሮም የሚኖሩ ክርስቲያኖች እንደዚህ ያሉ ልዩነቶች “በአንድ አፍ” አምላክን ከማክበር እንዳያግዷቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
7. በሳምንቱ ውስጥ ልዩ ተደርጎ የሚታይን ቀን ማክበርን በተመለከተ ምን የአመለካከት ልዩነቶች ነበሩ?
7 ጳውሎስ “አንድ ሰው አንዱን ቀን ከሌላው የተሻለ ቅዱስ አድርጎ ይቈጥራል፤ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኩል እንደ ሆኑ ያስባል” በማለት ሌላም ሁኔታ ጠቅሷል። (ሮሜ 14:5ሀ) በሙሴ ሕግ መሠረት በሰንበት ሥራ መሥራት ክልክል ነበር። ሌላው ቀርቶ ወደ ሩቅ ቦታ መጓዝ ፈጽሞ የተከለከለ ነበር። (ዘፀአት 20:8-10፤ ማቴዎስ 24:20፤ የሐዋርያት ሥራ 1:12) ሕጉ ከተወገደ በኋላ ግን እነዚህ ደንቦች ተሻሩ። ይሁንና አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በፊት ቅዱስ አድርገው ይመለከቱት በነበረው ቀን ማንኛውንም ዓይነት ሥራ መሥራት ወይም ረጅም ርቀት መጓዝ ሳይከብዳቸው አልቀረም። በአምላክ ዓይን ሲታይ የሰንበት ሕግ የተሻረ ቢሆንም እንኳ እነዚህ ሰዎች ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላም ሰባተኛውን ቀን ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ብቻ ለማዋል ወስነው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ማድረጋቸው ስህተት ነበር? ሰንበትን ማክበር መለኮታዊ ግዴታ ነው የሚል አቋም እስካልያዙ ድረስ ስህተት አልነበረም። ስለዚህ ጳውሎስ ለክርስቲያን ወንድሞቹ ሕሊና ከነበረው አሳቢነት የተነሳ “እያንዳንዱ የራሱን ውሳኔ ልብ ብሎ ይወስን” ሲል ጽፏል።—ሮሜ 14:5ለ
8. በሮም የነበሩ ክርስቲያኖች ለሌሎች ሕሊና አሳቢነት ማሳየት የነበረባቸው ቢሆንም ምን ከማድረግ መቆጠብ ነበረባቸው?
8 የሆነ ሆኖ ጳውሎስ ለሕሊና የተተዉ ጉዳዮችን ለመቀበል የተቸገሩ ክርስቲያኖችን በትዕግሥት እንዲይዟቸው ወንድሞቹን አበረታቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ለመዳን የሙሴን ሕግ የግድ መጠበቅ አለባችሁ ብለው የእምነት ጓደኞቻቸውን ለማስገደድ የሞከሩ ክርስቲያኖችን በጥብቅ አውግዟቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ጳውሎስ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ የላቀ ተስፋ ስላላቸው ለሙሴ ሕግ መገዛት ምንም እንደማይጠቅም በግልጽ በማስረዳት ጠንካራ መልእክት የያዘውን የዕብራውያን መጽሐፍ ለአይሁዳውያን ክርስቲያኖች ጽፎላቸዋል።—ገላትያ 5:1-12፤ ቲቶ 1:10, 11፤ ዕብራውያን 10:1-17
9, 10. ክርስቲያኖች ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል? አብራራ።
9 ከላይ እንዳየነው ጳውሎስ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የምርጫ ልዩነት መኖሩ ለአንድነት ስጋት መፍጠር እንደሌለበት ገልጿል። ስለዚህ ጳውሎስ ደካማ ሕሊና ላላቸው ክርስቲያኖች “በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ?” የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው። በእምነት የጎለመሱትን ደግሞ (ምናልባትም ሕጉ ይከለክላቸው የነበሩትን አንዳንድ ምግቦች ለመመገብ ወይም በሰንበት ሥራ ለመሥራት ሕሊናቸው የፈቀደላቸው ክርስቲያኖችን) “ለምንስ ወንድምህን ትንቃለህ?” ሲል ጠየቃቸው። (ሮሜ 14:10) ጳውሎስ ደካማ ሕሊና ያላቸው ክርስቲያኖች ሰፋ ያለ አመለካከት ያላቸው ወንድሞቻቸውን ከመኰነን መቆጠብ ይገባቸዋል ማለቱ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ የሆኑ ክርስቲያኖች በአንዳንድ ጉዳዮች ሕሊናቸው አሁንም ደካማ የሆነውን ክርስቲያኖች በንቀት መመልከት አይኖርባቸውም። ሁሉም የሌሎችን ትክክለኛ ውስጣዊ ዝንባሌ ማክበርና ‘ከሆኑት በላይ ራሳቸውን ከፍ አድርገው እንዳያስቡ’ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።—ሮሜ 12:3, 18
10 ጳውሎስ እንዲህ በማለት ምክንያታዊ የሆነውን አመለካከት ገልጿል፦ “ማንኛውንም የሚበላ የማይበላውን አይናቅ፤ የማይበላውም፣ የሚበላውን አይኰንን፤ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና።” በተጨማሪም ‘ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ተቀብሎናል’ በማለት ገልጿል። ጠንካራውም ሆነ ደካማው በአምላክና በክርስቶስ ፊት ተቀባይነት ስላላቸው እኛም በተመሳሳይ አስተሳሰባችንን ሰፋ በማድረግ ‘እርስ በርሳችን መቀባበል’ ይኖርብናል። (ሮሜ 14:3፤ 15:7) እንዲህ መሆን የለበትም ሊል የሚችል ማን ነው?
ወንድማዊ መዋደድ ዛሬም አንድነት ያስገኛል
11. በጳውሎስ ዘመን የተከሰተው በዓይነቱ ለየት ያለ ሁኔታ ምን ነበር?
11 ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በዓይነቱ ልዩ ስለሆነ ሁኔታ ተናግሯል። ይሖዋ አንድ ቃል ኪዳን አስወግዶ በምትኩ አዲስ ያቋቋመው በቅርቡ ነበር። አንዳንዶች አዲሱን ቃል ኪዳን ተግባራዊ ማድረግ ከበዳቸው። በዛሬው ጊዜ ያን ዓይነት ሁኔታ አናይም፤ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ተመሳሳይ የሆኑ አወዛጋቢ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ።
12, 13. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ለወንድሞቻቸው ሕሊና እንደሚጠነቀቁ ማሳየት የሚችሉባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
12 ለምሳሌ ያህል አንዲት ክርስቲያን ከዚህ በፊት የነበረችበት ሃይማኖት መዘነጥና መኳኳል የሚከለክል ይሆናል። እውነትን ከተቀበለች በኋላ፣ ለአንዳንድ ወቅቶች ልከኛ የሆነ ቆንጆ ልብስ መልበስ ወይም ማጋጌጫዎችን በልኩ መጠቀም ስህተት የለውም የሚለውን ሐሳብ መቀበል በጣም ሊከብዳት ይችላል። ይህን እንድትቀበል የሚያስገድድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ስለሌለ የትኛውም ሰው ቢሆን ይህች ክርስቲያን ሕሊናዋ የማይፈቅድላትን ነገር እንድታደርግ ለማሳመን መሞከሩ ተገቢ አይሆንም። በሌላ በኩል ደግሞ በነፃነታቸው ለመጠቀም ሕሊናቸው የፈቀደላቸውን ክርስቲያን ሴቶች መተቸት እንደሌለባት ትገነዘባለች።
13 ሌላም ምሳሌ ተመልከት። አንድ ክርስቲያን ያደገው የአልኮል መጠጥ መጠጣት እንደ ነውር በሚታይበት አካባቢ ሊሆን ይችላል። እውነትን ካወቀ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ወይን የአምላክ ስጦታ እንደሆነና በልክ መጠጣት እንደሚቻል ይገነዘባል። (መዝሙር 104:15) ይህን አመለካከት ቢቀበልም እንኳ ከአስተዳደጉ የተነሳ የአልኮል መጠጦችን ሙሉ በሙሉ ለመራቅ ይመርጣል። ሆኖም በልክ የሚጠጡ ክርስቲያኖችን አይነቅፍም። በዚህ መንገድ ጳውሎስ “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ” ሲል የሰጠውን ምክር በተግባር ያውላል።—ሮሜ 14:19
14. ክርስቲያኖች ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች የሰጣቸው ምክር የያዘውን መንፈስ በየትኞቹ ሁኔታዎች ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ?
14 ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች የጻፈው ምክር የያዘውን መንፈስ በተግባር እንድናውል የሚያስገድዱ ሌሎች ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። የክርስቲያን ጉባኤ በርካታ ግለሰቦችን ያቀፈ ሲሆን እነርሱም የተለያየ ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም እንደ ልብስና የፀጉር አበጣጠር በመሳሰሉ ጉዳዮች የተለያየ ምርጫ ሊኖራቸው ይችላል። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊያከብሯቸው የሚገቡ ግልጽ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል። ማናችንም ብንሆን አለባበሳችንም ሆነ የፀጉር አበጣጠራችን መረን የለቀቀ ወይም ቅጥ ያጣ አሊያም ከዓለም ክፍል ሊያስመድበን የሚችል ዓይነት መሆን የለበትም። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ክርስቲያኖች በማንኛውም ጊዜ ሌላው ቀርቶ በሚዝናኑበት ጊዜም የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ የሚወክሉ አገልጋዮች መሆናቸውን አይዘነጉም። (ኢሳይያስ 43:10፤ ዮሐንስ 17:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) ይሁን እንጂ በተለያዩ መስኮች ለክርስቲያኖች ተገቢ የሆኑ እጅግ በርካታ ምርጫዎች አሉ። a
ሌሎችን ላለማሰናከል ተጠንቀቁ
15. አንድ ክርስቲያን ለወንድሞቹ በማሰብ፣ መብቱ የሆነውን ነገር ከማድረግ የሚቆጠበው በየትኞቹ ሁኔታዎች ነው?
15 ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ምክር ላይ የጠቀሰው አንድ ተጨማሪ ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት አለ። በሚገባ የሰለጠነ ሕሊና ያለው አንድ ክርስቲያን በመምረጥ ነፃነቱ ላለመጠቀም የሚወስንባቸው ጊዜያት አሉ። ለምን? እንዲህ የሚያደርገው ውሳኔው የሌሎችን ስሜት ሊጎዳ እንደሚችል ስለሚገነዘብ ነው። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጳውሎስ “ለወንድምህ መሰናከል ምክንያት የሚሆነውን ሥጋን አለመብላት፣ ወይንን አለመጠጣት፣ ወይም አንዳች ነገርን አለማድረግ መልካም ነው” ብሏል። (ሮሜ 14:14, 20, 21) በመሆኑም “እኛ ብርቱዎች የሆን፣ የደካሞችን ጉድለት መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም። እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን ለማነጽ፣ እርሱንም ለመጥቀም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይገባናል።” (ሮሜ 15:1, 2) በእኛ አድራጎት የእምነት ጓደኛችን ሕሊና የሚጎዳ ከሆነ ወንድማዊ መዋደድ አሳቢነት እንድናሳይና በመምረጥ ነፃነታችን በገደብ እንድንጠቀም ይገፋፋናል። ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የምናደርገው ውሳኔ ለዚህ ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። አንድ ክርስቲያን ወይን በልክ መጠጣት ይችላል። ሆኖም መጠጥ መጠጣቱ ባልንጀራውን የሚያሰናክል ከሆነ መብቴ ነው በሚል ድርቅ አይልም።
16. በክልላችን ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
16 ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነትም በሥራ ልናውለው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በምንኖርበት አካባቢ ያለው ብዙዎች የሚከተሉት ሃይማኖት ከሳምንቱ ቀናት መካከል አንዱን የእረፍት ቀን አድርገው እንዲመለከቱት ምዕመናኑን ያስተምር ይሆናል። በዚህም ምክንያት ጎረቤቶቻችንን ላለማሰናከልና በስብከቱ ሥራችን ላይ እንቅፋት ላለመፍጠር ስንል በተቻለን መጠን በዕለቱ እነርሱን የሚያስቀይም አንዳች ነገር ላለማድረግ እንጠነቀቃለን። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሀብታም ክርስቲያን እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄዶ ለማገልገል ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ ይዛወር ይሆናል። ይህ ወንድም ተራ ልብስ በመልበስ ወይም የገንዘብ አቅም ቢኖረውም ኑሮውን በጣም ቀላል በማድረግ በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች አሳቢነት ለማሳየት ይመርጥ ይሆናል።
17. አንዳንድ ምርጫዎች ስናደርግ ስለ ሌሎች ስሜት ማሰባችን ምክንያታዊነት የሚሆነው ለምንድን ነው?
17 “ብርቱዎች” የሆኑት እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንዲያደርጉ መጠበቁ ምክንያታዊነት ነው? እስቲ ይህን ምሳሌ ተመልከት፦ በፍጥነት መንዳት በሚቻልበት አውራ ጎዳና ላይ ከፊት ለፊታችን ትንንሽ ልጆች ለሕይወታቸው አደገኛ በሆነ ሁኔታ መንገዱ ላይ ሲሄዱ እናያለን። ሕጉ ስለሚፈቅድልን ብቻ በተፈቀደው ከፍተኛ የፍጥነት መጠን መንዳታችንን እንቀጥላለን? አናደርገውም፤ በልጆቹ ላይ አደጋ ላለማድረስ ስንል ፍጥነታችንን እንቀንሳለን። ከእምነት ባልንጀሮቻችን ወይም ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት የሚያስገድደን ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ፍጥነታችንን ለመቀነስ ወይም መብታችንን ለመሠዋት ፈቃደኛ እንሆናለን። የምናደርገው ነገር ሙሉ በሙሉ መብታችን ሊሆን ይችላል። የጣስነው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት የለም። ይሁን እንጂ ሌሎችን የምናስቀይም ወይም ደካማ ሕሊና ያላቸውን ክርስቲያኖች የምንጎዳ ከሆነ ክርስቲያናዊ ፍቅር የምናደርገውን ነገር በጥንቃቄ እንድናመዛዝን ይገፋፋናል። (ሮሜ 14:13, 15) አንድነታችንን ማስጠበቅና የመንግሥቱን ጥቅሞች ማራመድ በግል መብቶቻችን ከመጠቀም የበለጠ እጅግ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው።
18, 19. (ሀ) ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሁላችንም በጋራ አንድ ዓይነት እርምጃ የምንወስደው በየትኞቹ ጉዳዮች ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
18 ውሳኔ የምናደርገው በዚህ መንገድ ከሆነ ከሁሉ የተሻለውን ምሳሌ እንከተላለን። ጳውሎስ “ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን፣ ‘አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ደረሰብኝ’ ተብሎ እንደ ተጻፈው ሆነበት” ብሏል። ኢየሱስ ሕይወቱን ለእኛ ለመሠዋት ፈቃደኛ ነበር። ‘ደካሞች’ የሆኑት አምላክን ከእኛ ጋር እንዲያወድሱ የሚያስችላቸው ከሆነ አንዳንድ መብቶቻችንን ለመሠዋት ፈቃደኛ እንደምንሆን የታወቀ ነው። በእርግጥም፣ ደካማ ሕሊና ያላቸውን ክርስቲያኖች በትዕግሥት መያዝና ለእነርሱ አሳቢነት ማሳየት በሌላ አባባል የግል ምርጫዎቻችንን በፈቃደኝነት መሥዋዕት ማድረግና መብቴ ነው ብሎ ድርቅ አለማለት ‘ክርስቶስ ኢየሱስን እንደምንከተል’ ያሳያል።—ሮሜ 15:1-5
19 ቀጥተኛ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ባልተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ያለን አመለካከት በመጠኑ የተለያየ ሊሆን ቢችልም አምልኮን በሚመለከቱ ጉዳዮች ግን በመካከላችን ፍጹም አንድነት አለ። (1 ቆሮንቶስ 1:10) ለምሳሌ ያህል እውነተኛውን አምልኮ ለሚቃወሙ ሰዎች በምንሰጠው ምላሽ ረገድ አንድነታችን በግልጽ ይታያል። የአምላክ ቃል እነዚህን ተቃዋሚዎች እንግዳ የሚላቸው ከመሆኑም ሌላ ‘ከእንግዳ ድምፅ’ እንድንርቅም ያስጠነቅቀናል። (ዮሐንስ 10:5) እነዚህን እንግዳ የሆኑ ሰዎች ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ምን ምላሽ ልንሰጣቸው ይገባል? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ መልስ ያገኛሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ለትንንሽ ልጆች ልብስ የሚመርጡላቸው ወላጆቻቸው ይሆናሉ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የግል ምርጫ በሆኑ ጉዳዮች የተለያየ አመለካከት መያዛችን በአንድነታችን ላይ ስጋት ሊፈጥር የማይገባው ለምንድን ነው?
• ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አንዳችን ለሌላው ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
• ጳውሎስ አንድነትን በተመለከተ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? እንዲህ እንድናደርግ የሚገፋፋንስ ምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ አንድነትን በተመለከተ የሰጠው ምክር ለጉባኤው በጣም አስፈላጊ ነበር
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች የተለያየ አስተዳደግ ቢኖራቸውም በመካከላቸው አንድነት አለ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህች አሽከርካሪ በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርባታል?