ተስፋ መቁረጥን እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?
ተስፋ መቁረጥን እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?
ተስፋ የቆረጥክበት ጊዜ አለ? በበርካታ ችግሮች በተሞላውና ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ በማይታወቅበት በዚህ ዘመን በርካታ ሰዎች ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። አንዳንዶች ሥራ ማጣት ሌሎች ደግሞ በአደጋ ምክንያት የደረሰባቸው ጉዳት ተስፋ እንዲቆርጡ ያደርጋቸዋል። ከቤተሰብ ችግሮች፣ ከከባድ ሕመም ወይም ከብቸኝነት ስሜት ጋር እየታገሉ የሚኖሩም አሉ።
ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ሲያጋጥምህ እርዳታ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ማጽናኛ አግኝተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። . . . እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ሲያነብቡ ይጽናናሉ። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ለምን በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንንና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አታነብም? እንዲህ ማድረግህ ‘ልብህን ሊያጽናናውና ሊያበረታህ’ ይችላል።—2 ተሰሎንቄ 2:17
ይሖዋን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በመቀራረብም የተስፋ መቁረጥን ስሜት ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ማግኘት ይቻላል። ምሳሌ 12:25 “ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” ይላል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ “ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለዐጥንትም ፈውስ” የሆነውን “ደስ የሚያሰኝ ቃል” እንሰማለን። (ምሳሌ 16:24) እንዲህ ያለው ስብሰባ ምን ያህል የሚያበረታታ እንደሆነ ለማየት ለምን በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ አትገኝም?
ጸሎት ከሚሰጠው ኃይልም ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙህ ውጣ ውረዶች ከአቅምህ በላይ ከሆኑብህ ውስጣዊ ስሜትህን ‘ጸሎትን ለሚሰማው ለይሖዋ’ አካፍለው። (መዝሙር 65:2) እኛ ራሳችንን ከምናውቀው የበለጠ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ያውቀናል። በእርሱ እርዳታ መተማመን እንችላለን። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም” የሚል ተስፋ ይሰጠናል። (መዝሙር 55:22) አዎን፣ “እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኃይላቸውን ያድሳሉ።”—ኢሳይያስ 40:31
ይሖዋ አምላክ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችን በተሳካ ሁኔታ ለመቋቋም የሚረዱ ዝግጅቶችን አድርጎልናል። በእነዚህ ዝግጅቶች እየተጠቀምክ ነው?