በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የራስን ጥቅም መሠዋት የሚያስገኘው አርኪና አስደሳች ሕይወት

የራስን ጥቅም መሠዋት የሚያስገኘው አርኪና አስደሳች ሕይወት

የሕይወት ታሪክ

የራስን ጥቅም መሠዋት የሚያስገኘው አርኪና አስደሳች ሕይወት

ማሪያን እና ሮዛ ዙሚጋ እንደተናገሩት

መዝሙር 54:6 “በበጎ ፈቃድ መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ” ይላል። እነዚህ ቃላት በፈረንሳይ በሚኖሩት በማሪያን ዙሚጋና በባለቤቱ ሮዛ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። በቅርቡ በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፉት ረጅምና አስደሳች ሕይወት ውስጥ ያጋጠሟቸውን ጉልህ ክንውኖች እንደሚከተለው ተርከዋል።

ማሪያን፦ ወላጆቼ ከፖላንድ ወደ ፈረንሳይ የፈለሱ የሮማ ካቶሊኮች ነበሩ። አባቴ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር አጋጣሚ ባያገኝም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በምሽግ ውስጥ ሆኖ ባሳለፋቸው ጊዜያት ማንበብና መጻፍ ተምሯል። አባቴ አምላክን የሚፈራ ሰው ቢሆንም ብዙ ጊዜ በሃይማኖቱ ውስጥ ቅር የሚያሰኙት ነገሮች ያጋጥሙት ነበር።

አንድ ወቅት ያጋጠመውን ነገር መቼም አይረሳውም። አንደኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት አንድ ቄስ አባቴ የነበረበትን ክፍለ ጦር በመጎብኘት ላይ ነበሩ። በአቅራቢያው የመድፍ ፍንዳታ ሲሰማ ቄሱ ተደናግጠው ፈረሳቸውን የኢየሱስ ምስል በተቀረጸበት መስቀል እየገረፉ ፈረጠጡ። አባቴ የአምላክ “ወኪል” እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩ ሰው ፈረሳቸው እንዲፈጥን ለማድረግ እንደ “ቅዱስ” ነገር በሚታየው መስቀል መጠቀማቸው ክፉኛ አስደነገጠው። ሆኖም እነዚህን የመሳሰሉ ገጠመኞችና በጦርነቱ ወቅት የተመለከታቸው አሰቃቂ ነገሮች በአምላክ ላይ የነበረውን እምነት እንዲያጣ አላደረጉትም። እንዲያውም ከጦርነቱ ያተረፈው አምላክ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገር ነበር።

“ትንሿ ፖላንድ”

በ1911 አባቴ በአቅራቢያው በሚገኝ መንደር የምትኖር አና ጸሶቭስኪ የተባለች አንዲት ልጃገረድ አገባ። አንደኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ብዙም ሳይቆይ በ1919 ወላጆቼ ወደ ፈረንሳይ ተጓዙና በዚያ አባቴ በከሰል ማዕድን ማውጫ ውስጥ ሥራ አገኘ። እኔም በመጋቢት ወር 1926 በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ በምትገኘው ካንያክ ሌ ሚን ከተማ ተወለድኩ። ከዚያ በኋላ ወላጆቼ በርካታ ፖላንዳውያን በሚኖሩበት በሰሜን ፈረንሳይ በሌንስ አቅራቢያ በምትገኝ ሎሳንጎኤል በተባለች መንደር መኖር ጀመሩ። የመንደሯ ባለ ዳቦ ቤት፣ ባለ ሥጋ ቤቱና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሰብከው ቄስ በሙሉ ፖላንዳውያን ስለነበሩ አካባቢው “ትንሿ ፖላንድ” ይባል ነበር። ወላጆቼ በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር። አባቴ ብዙ ጊዜ ተውኔቶችን፣ ሙዚቃዎችንና መዝሙሮችን ያካተቱ ትርኢቶች ያዘጋጅ ነበር። እንዲሁም ከቄሱ ጋር ዘወትር ውይይት ያደርግ ነበር። ነገር ግን ቄሱ አብዛኛውን ጊዜ “በርካታ የማናውቃቸው ምስጢሮች አሉ” በማለት የሚሰጠው መልስ አያረካውም።

በ1930 አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሁለት ሴቶች (በጊዜው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚጠሩበት ስም ነው) በራችንን አንኳኩ። ለአባቴ ለብዙ ዓመታት ሊያነበው ሲመኝ የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አበረከቱለት። እሱና እናቴ መጽሐፍ ቅዱሱን ጨምሮ እነዚህን ጽሑፎች በጉጉት ያነበቧቸው ሲሆን ባገኙት እውቀት ልባቸው በጥልቅ ተነካ። ወላጆቼ ሥራ ይበዛባቸው የነበረ ቢሆንም እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያዘጋጅዋቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። አባቴ ከቄሱ ጋር የሚያደርጋቸው ውይይቶች ይበልጥ እየከረሩ ሄዱ። ከዚያም አንድ ቀን ቄሱ ወላጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን ካላቆሙ እህቴን ስቴፋኒን ከሰንበት ትምህርት ቤት እንደሚያባርሯት ተናገሩ። አባቴም “አትቸገር፤ እንዲያውም ከአሁን በኋላ ስቴፋኒም ሆነች ሌሎቹ ልጆች ከእኛ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደሚያደርጉት ስብሰባ ይሄዳሉ” አላቸው። አባቴ የቤተ ክርስቲያን አባልነቱን የሰረዘ ሲሆን በ1932 መጀመሪያ ላይ ከእናቴ ጋር ተጠመቁ። በወቅቱ በፈረንሳይ የነበሩት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር 800 ያህል ብቻ ነበር።

ሮዛ፦ ወላጆቼ የመጡት ከሃንጋሪ ሲሆን እንደ ማሪያን ቤተሰቦች ሁሉ እነርሱም በከሰል ማዕድን ማውጫ ውስጥ ለመስራት በሰሜን ፈረንሳይ ሰፈሩ። እኔም በ1925 ተወለድኩ። በ1937 አባባ ኦጉስት እያልን የምንጠራው ኦጉስት ቡጌን የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለወላጆቼ በሃንጋሪ ቋንቋ የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ ያመጣላቸው ጀመር። ወላጆቼ መጽሔቶቹን ማንበብ ቢያስደስታቸውም አንዳቸውም የይሖዋ ምሥክር አልሆኑም።

ምንም እንኳን ትንሽ ልጅ የነበርኩ ቢሆንም በመጠበቂያ ግንብ ላይ የማነባቸው ነገሮች ልቤን ይነኩት ነበር። የአባባ ኦጉስት ምራት የሆነችው ሱዛን ቡጌን በጣም ታስብልኝ የነበረ ሲሆን ወላጆቼ ወደ ስብሰባዎች ይዛኝ እንድትሄድ ፈቀዱላት። ከጊዜ በኋላ ግን ሥራ መሥራት ስጀምር እሁድ እሁድ ወደ ስብሰባ መሄዴ አባቴን ያበሳጨው ጀመር። ጥሩ ሰው የነበረ ቢሆንም አንድ ቀን በምሬት “በሳምንቱ ቀናት ቤት አትውይም፤ እሁድ እሁድ ደግሞ ስብሰባ ብለሽ ትሄጃለሽ!” አለኝ። ሆኖም መሰብሰቤን አላቋረጥኩም። ስለዚህ አንድ ቀን “ጓዝሽን ጠቅልይና ውጪ!” አለኝ። ምሽቱ ከመግፋቱም በላይ ገና 17 ዓመቴ ነበር። ወዴት እንደምሄድ ግራ ገባኝ። በመጨረሻም እያለቀስኩ ወደ ሱዛን ቤት ሄድኩ። እዚያም ለአንድ ሳምንት ያህል ከተቀመጥኩ በኋላ አባቴ ወደ ቤት እንድመለስ እህቴን ላከብኝ። በተፈጥሮዬ ዓይን አፋር ብሆንም በ1 ዮሐንስ 4:18 ላይ ያለው “ፍጹም ፍቅር . . . ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል” የሚለው ጥቅስ በአቋሜ እንድጸና ረድቶኛል። ከዚያም በ1942 ተጠመቅኩ።

ውድ መንፈሳዊ ውርሻ

ማሪያን፦ በ1942 እኔና ወንድሜ ስቴፋን እንዲሁም እህቶቼ ስቴፋኒና ሜላኒ አብረን ተጠመቅን። የቤተሰባችን ሕይወት በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነበር። በጠረጴዛ ዙሪያ እንቀመጥና አባታችን መጽሐፍ ቅዱስን በፖላንድ ቋንቋ ያነብልናል። አብዛኛውን ጊዜ ምሽቱን የምናሳልፈው ወላጆቻችን የመንግሥቱን ምሥራች ሲሰብኩ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች በመስማት ነበር። በመንፈሳዊ ማበረታቻ የምናገኝባቸው እነዚህ አስደሳች ጊዜያት ይሖዋን እንድንወደውና በእርሱ ላይ ያለን እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ እንዲሄድ ረድቶናል። አባቴ በጤና እክል ምክንያት ሥራ ቢያቆምም እኛን በመንፈሳዊና በቁሳዊ መንከባከቡን አላቋረጠም።

በዚህ ወቅት አባቴ በቂ ጊዜ ስለነበረው በጉባኤው ውስጥ ያለነውን ወጣቶች በሳምንት አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስን በፖላንድ ቋንቋ ያስጠናን ጀመር። በፖላንድ ቋንቋ ማንበብ የተማርኩት በዚህ አጋጣሚ ነው። አባቴ በሌሎች መንገዶችም ወጣቶችን ያበረታታ ነበር። በአንድ ወቅት በፈረንሳይ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ ይመራ የነበረው ወንድም ጉስታቭ ሶፕፌር ጉባኤያችንን ሲጎበኝ አባቴ አንድ የመዝሙር ቡድንና ንጉሥ ብልጣሶር ስላዘጋጀው ግብዣና በግድግዳ ላይ ስለታየው የእጅ ጽሑፍ በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ድራማ አዘጋጀ። (ዳንኤል 5:1-31) የድራማው ተዋንያን ጥንታዊ አለባበስ ለብሰው የሚጫወቱ ሲሆን ዳንኤልን ሆኖ የተወነው ከጊዜ በኋላ በናዚዎች የደረሰበትን ስደት በጽናት የተቋቋመው ልዊ ፒሆታ ነበር። a የልጅነት ሕይወታችንን ያሳለፍነው ይህን በመሰለ ሁኔታ ነው። ወላጆቻችን ሁልጊዜ በመንፈሳዊ ጉዳዮች የተጠመዱ መሆናቸውን እንመለከት ነበር። አሁን መለስ ብዬ ሳስበው ወላጆቼ ውድ የሆነ መንፈሳዊ ውርሻ ትተውልን እንዳለፉ ይሰማኛል።

በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ በፈረንሳይ በይሖዋ ምሥክሮች የስብከት እንቅስቃሴ ላይ እገዳ ተጣለ። አንድ ቀን በመንደራችን ፍተሻ ይደረግ ነበር። ቤቶቹ ሁሉ በጀርመን ወታደሮች ተከበቡ። አባቴ በአንድ ቁም ሣጥን ውስጥ የማስመሰያ ወለል በመሥራት እቃ ለመደበቅ እንዲያመች አድርጎ አዘጋጅቶት ስለነበር የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን በዚያ ውስጥ ደበቅናቸው። ይሁን እንጂ ፋሺዝም ወይስ ነጻነት የተባለው ቡክሌት በርካታ ቅጂዎች በብፌው መሳቢያ ውስጥ ተቀምጠው ነበር። አባቴ ቡክሌቶቹን በፍጥነት ከብፌው ውስጥ አውጥቶ በኮሪደሩ ላይ በተሰቀለ አንድ ጃኬት ኪስ ውስጥ ደበቃቸው። ሁለት ወታደሮችና አንድ የፈረንሳይ ፖሊስ ቤታችንን መፈተሽ ጀመሩ። በጭንቀት ተውጠን የሚሆነውን በመጠባበቅ ላይ ሳለን አንዱ ወታደር በኮሪደሩ ላይ የተሰቀሉትን ልብሶች መፈተሽ ጀመረ። ወዲያውም ቡክሌቶቹን በእጁ ይዞ ወደነበርንበት ወጥ ቤት ገባና አፈጠጠብን። ከዚያም ቡክሌቶቹን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ ሌሎች ክፍሎችን ለመፈተሽ ወጣ። እኔም ቀልጠፍ ብዬ ቡክሌቶቹን አነሳሁና ወታደሮቹ ፈትሸው ባለፉት መሳቢያ ውስጥ አስቀመጥኳቸው። ወታደሩ ፈጽሞ ረስቶት ሳይሆን አይቀርም ስለ ቡክሌቶቹ ምንም አልጠየቀም!

ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት

በ1948 አቅኚ ሆኜ ይሖዋን በሙሉ ጊዜዬ ለማገልገል ወሰንኩ። ከጥቂት ቀናት በኋላ በፈረንሳይ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ አንድ ደብዳቤ ደረሰኝ። ደብዳቤው በቤልጂየም አቅራቢያ በምትገኘው በሴዳን ከተማ ባለው ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት እንዳገለግል መመደቤን የሚገልጽ ነበር። ወላጆቼ ለይሖዋ አገልግሎት ራሴን በማቅረቤ ደስተኞች ነበሩ። እንዲያም ሆኖ አባቴ አቅኚነት መዝናኛ እንዳልሆነና በርትቶ መስራትን የሚጠይቅ እንደሆነ አስገነዘበኝ። ወደ ቤት መመለስ ከፈለግሁ ግን ምንጊዜም በደስታ እንደሚቀበለኝና ችግር ካጋጠመኝ ሊረዳኝ ፈቃደኛ መሆኑን ነገረኝ። ወላጆቼ ብዙ ገንዘብ ባይኖራቸውም አዲስ ብስክሌት ገዝተው ሰጡኝ። ደረሰኙ እስከ አሁን ድረስ አብሮኝ ያለ ሲሆን ባየሁት ቁጥር እንባዬ በዓይኖቼ ግጥም ይላል። ወላጆቼ በ1961 የሞቱ ቢሆንም የአባቴን ጥበብ ያዘሉ ምክሮች እስከ አሁን ድረስ አልረሳቸውም። በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው ዓመታት ማበረታቻና ማጽናኛ ሆነውልኛል።

የብርታት ምንጭ የሆኑልኝ ሌላዋ እህት ደግሞ በሴዳን ጉባኤ የሚገኙት ኤሊዝ ሞት የተባሉ የ75 ዓመት አረጋዊት ክርስቲያን ነበሩ። በበጋ ወራት ራቅ ወዳሉ መንደሮች በብስክሌት እየሄድኩ በማገለግልበት ጊዜ እህት ኤሊዝ በባቡር ይመጡና አብረውኝ ያገለግሉ ነበር። አንድ ቀን ግን የባቡሩ መሐንዲሶች የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው ምክንያት እህት ኤሊዝ ወደ ቤት መመለስ አልቻሉም። የነበረኝ ብቸኛ አማራጭ ምቹ ባይሆንም እንኳን በብስክሌቱ ዕቃ መጫኛ ላይ አስቀምጫቸው ቤታቸው ማድረስ ነበር። በማግስቱ ጠዋት ትራስ ይዤ ወደ እህት ኤሊዝ ቤት ሄድኩና በብስክሌቱ ዕቃ መጫኛ ላይ አስቀምጫቸው ወደምናገለግልበት ቦታ አመራን። ከዚያ በኋላ በባቡር መጓዛቸውን አቆሙ፤ ለባቡር መጓጓዣ ይከፍሉት የነበረውንም ገንዘብ በምሳ ሰዓታችን ትኩስ ነገር ገዝተን እንጠጣበት ነበር። ብስክሌቴ እንደ ሕዝብ መጓጓዣ ሆኖ ያገለግላል ብሎ ማን ያሰበ ነበር?

ተጨማሪ ኃላፊነቶች ተሰጡኝ

በ1950 በመላው ሰሜናዊ ፈረንሳይ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተጠየቅኩ። ገና የ23 ዓመት ወጣት እንደመሆኔ መጀመሪያ ላይ በጣም ፈርቼ ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው የሆነ ስህተት ሠርቶ መሆን አለበት ብዬ አሰብኩ! ‘በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ለሥራው ብቁ ነኝ? በየሳምንቱ በተለያዩ ቦታዎች ማደሩስ ይሆንልኛል?’ የሚሉት ጥያቄዎች በአእምሮዬ ይመላለሱ ነበር። ከዚህም በላይ የስድስት ዓመት ልጅ ሳለሁ የጀመረኝ ዳይቨርጀንት ስትራቢዝመስ የተባለ የዓይን በሽታ ነበረብኝ። በዚህም ምክንያት አንዱ ዓይኔ ሸውረር ያለ ስለነበር ሌሎች ሲመለከቱኝ ምን ይሰማቸው ይሆን የሚለው ያሳስበኝና ያስጨንቀኝ ነበር። ደስ የሚለው ግን የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ምሩቅ የሆነው ስቴፋን ቤሁኒክ በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ትልቅ እርዳታ አበርክቶልኛል። ወንድም ቤሁኒክ በስብከቱ ሥራ ምክንያት ከፖላንድ በመባረሩ በፈረንሳይ እንዲያገለግል ተመድቦ ነበር። ድፍረቱ በጣም ያስገርመኝ ነበር። ለይሖዋና ለእውነት ጥልቅ አክብሮት ነበረው። አንዳንዶች በእኔ ላይ በጣም ጥብቅ እንደሚሆንብኝ ይሰማቸው የነበረ ቢሆንም ከእርሱ በርካታ ነገሮችን ተምሬአለሁ። ደፋርነቱ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዳዳብር ረድቶኛል።

የጉብኝት ሥራ አንዳንድ አስደሳች የመስክ አገልግሎት ተሞክሮዎች እንዳገኝ አስችሎኛል። በ1953 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ኮንትራት የነበረውን ሚስተር ፓኦሊ የተባለ በደቡብ ፓሪስ የሚገኝ አንድ ሰው እንዳነጋግር ተጠየቅኩ። ስንገናኝ ከውትድርና ሥራው በጡረታ የተገለለ መሆኑንና መጠበቂያ ግንብን በጣም እንደሚወደው ነገረኝ። በቅርብ ጊዜ በወጣ እትም ላይ ስለ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚናገር ርዕሰ ትምህርት ካነበበ በኋላ በዓሉን ብቻውን እንዳከበረና ቀሪውን ምሽት የመዝሙር መጽሐፍን በማንበብ እንዳሳለፈ ነገረኝ። ውይይታችን የከሰዓት በኋላው ጊዜ እስኪገባደድ ድረስ ቀጠለ። ከመለያየታችን በፊት ስለ ጥምቀት አጠር ያለ ውይይት አደረግን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በ1954 መጀመሪያ አካባቢ በምናደርገው የወረዳ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ የግብዣ ወረቀት ላክሁለት። በስብሰባው ላይ የተገኘ ሲሆን በዚያን ዕለት ከተጠመቁት 26 ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ይህን የመሰሉ ተሞክሮዎች አሁንም ድረስ ያስደስቱኛል።

ሮዛ፦ በጥቅምት ወር 1948 በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። በቤልጂየም አቅራቢያ በምትገኝ አኖር የተባለች ከተማ ካገለገልኩ በኋላ ኢሬን ኮላንስኪ (አሁን ኢሬን ለርዋ ትባላለች) ከተባለች አቅኚ ጋር ሆኜ በፓሪስ እንዳገለግል ተመደብኩ። በከተማዋ መሃል ባለ ሴን ዠርሜን ዴ ፕሬ በሚባል ሠፈር በትንሽ ክፍል ውስጥ እንኖር ነበር። ያደግኩት በገጠር ስለነበር የፓሪስ ነዋሪዎች በጣም ያስገርሙኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሁሉም ሥልጡኖችና አስተዋዮች ይመስሉኝ ነበር። ምሥራቹን ስነግራቸው ግን ከማንም ያልተለዩ ሰዎች መሆናቸውን ብዙም ሳይቆይ ተረዳሁ። ብዙውን ጊዜ የአፓርትማ ጠባቂዎች ወደ ውስጥ እንዳንገባ ስለሚከለክሉን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ቀላል አልነበረም። ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች መልእክታችንን ይቀበሉ ነበር።

በ1951 በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ እኔና ኢሬን በአቅኚነት ስለምናከናውነው አገልግሎት ቃለ መጠይቅ ተደረገልን። ቃለ መጠይቁን ያደረገልን ማን ይመስላችኋል? ማሪያን ዙሚጋ የሚባል ወጣት የወረዳ የበላይ ተመልካች ነበር። ከማሪያን ጋር ከዚህ በፊት አንድ ጊዜ ተገናኝተን ነበር፤ ከዚህ ስብሰባ በኋላ ግን ደብዳቤ መጻጻፍ ጀመርን። እኔና ማሪያን በአንድ ዓመት መጠመቃችንንና በተመሳሳይ ዓመት የአቅኚነት አገልግሎት መጀመራችንን ጨምሮ በርካታ የምንመሳሰልባቸው ነገሮች ነበሩ። ትልቁ ጉዳይ ግን ሁለታችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል የምንፈልግ መሆኑ ነበር። ስለዚህ ጉዳዩን በጸሎት ካሰብንበት በኋላ ሐምሌ 31, 1956 ተጋባን። ከዚያ በኋላ ፍጹም አዲስ የሆነ ሕይወት ጀመርኩ። ከትዳር ሕይወት ጋር መላመድ ብቻ ሳይሆን ማሪያን የጉብኝት ሥራውን ሲያከናውን አብሬው መጓዝ ነበረብኝ፤ ይህም በየሳምንቱ በተለያየ ቦታ ማደርን ይጨምራል። መጀመሪያ ላይ በጣም ከብዶኝ የነበረ ቢሆንም ከፊታችን በርካታ አስደሳች ነገሮች ይጠብቁን ነበር።

አርኪ ሕይወት

ማሪያን፦ ባለፉት ዓመታት በርካታ ስብሰባዎችን በማዘጋጀቱ ሥራ የመካፈል ልዩ መብት አግኝተናል። በተለይ በ1966 በቦርዶ የተደረገውን ስብሰባ በተመለከተ አንድ አስደሳች ትዝታ አለኝ። በወቅቱ በፖርቱጋል የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እገዳ ተጥሎበት ነበር። ስለዚህ ከፖርቱጋል ለሚመጡት ምሥክሮች ሲባል ስብሰባውን በፖርቱጋል ቋንቋ ጭምር ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ከፖርቱጋል መጡ፤ የት እናሳርፋቸው የሚለው ጉዳይ ግን አሳሳቢ ነበር። በቦርዶ የሚኖሩ ምሥክሮች ለእንግዳ ማረፊያ የሚሆን በቂ ቤት ስላልነበራቸው አንድ አገልግሎት መስጠት ያቆመ የፊልም አዳራሽ ተከራየን። መቀመጫዎቹን በሙሉ አነሳናቸው፤ በመድረኩ መጋረጃ አዳራሹን ለሁለት ከፈልነውና አንዱን ክፍል ለእህቶች ሌላውን ደግሞ ለወንድሞች ማደሪያ አደረግነው። እንዲሁም መታጠቢያ ቤትና ገንዳ አዘጋጀን። በአዳራሹ ወለል ላይ የሳር ድርቆሽ ጎዘጎዝንና ሸራ አለበስነው። ሁሉም በተደረገላቸው ዝግጅት በጣም ተደስተው ነበር።

ከስብሰባው በኋላ በፊልም አዳራሹ ውስጥ ወዳረፉት ወንድሞችና እህቶች ሄደን እንጫወት ነበር። በቦታው የነበረው መንፈስ በጣም ደስ የሚል ነበር። ለበርካታ ዓመታት ተቃውሞ የነበረባቸው ቢሆንም ያገኟቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች መስማታችን በጣም አበረታቶናል። ስብሰባው አልቆ ወደ አገራቸው ሲመለሱ የተለያየነው በልቅሶ ነበር።

ይህ ከመሆኑ ሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ ማለትም በ1964 የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ የማገልገል መብት ቀርቦልኝ ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ለሥራው ብቁ እሆን? የሚለው ጉዳይ አሳስቦኝ ነበር። ነገር ግን ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ሥራውን ከሰጡኝ ብቁ እንደሆንኩ ቢሰማቸው ነው ስል አሰብኩ። ከሌሎች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር አብሬ መሥራቴ የሚያስደስት አጋጣሚ ነበር። ከእነርሱ ብዙ ነገሮችን ተምሬአለሁ። አብዛኞቹ በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን እንደ ትዕግሥትና ትጋት ያሉ ባሕርያትን በማሳየት በኩል ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። በትዕግሥት ከጠበቅነው ይሖዋ ፈልጎ እንደሚያገኘን ተገንዝቤአለሁ።

በ1982 ቅርንጫፍ ቢሮው በፓሪስ ዳርቻ በቡሎንቢያንኩር የሚገኝ 12 ፖላንዳውያን አስፋፊዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን እንድንረዳ ጠየቀን። ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነበር። ምክንያቱም በፖላንድ ቋንቋ ቲኦክራሲያዊ ቃላትን ባውቅም እንኳን ቃላቱን አሰካክቼ መናገር አልችልም ነበር። ቢሆንም ወንድሞች በፈቃደኝነትና በደግነት ተነሳስተው በሚያደርጉልኝ ትብብር ችግሩን ልወጣው ችያለሁ። በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ ባለው ጉባኤ ወደ 60 የሚጠጉ አቅኚዎችን ጨምሮ 170 የሚያህሉ አስፋፊዎች ይገኛሉ። ከጊዜ በኋላም ከሮዛ ጋር ሆኜ በኦስትሪያ፣ በዴንማርክና በጀርመን የሚገኙ የፖላንድ ቋንቋ ቡድኖችንና ጉባኤዎችን ጎብኝቻለሁ።

የሁኔታዎች መለዋወጥ

የተለያዩ ጉባኤዎችን መጎብኘት የሕይወታችን ክፍል ሆኖ የነበረ ቢሆንም ባጋጠመኝ የጤና እክል የተነሳ በ2001 ላይ የጉብኝት ሥራችንን ለማቆም ተገደድን። እህቴ ሩት በምትኖርበት በፒቲቭዬ ከተማ ለመኖሪያ የሚሆነን አፓርትማ አገኘን። ቅርንጫፍ ቢሮው አቅማችን የፈቀደውን ያህል ሰዓት እየሠራን ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ፈቀደልን።

ሮዛ፦ የጉብኝት ሥራችንን ካቆምን በኋላ የነበረው የመጀመሪያው ዓመት በጣም ከባድ ሆኖብኝ ነበር። ያደረግነው ለውጥ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር። ነገር ግን ራሴን እንዲህ በማለት አጽናናሁ:- ‘አሁንም ቢሆን አቅኚ ሆነሽ በማገልገል ያለሽን ጊዜና ጉልበት በአግባቡ መጠቀም ትችያለሽ።’ አሁን በጉባኤያችን ካሉት አቅኚዎች ጋር ማገልገል መቻሌ በጣም ያስደስተኛል።

የይሖዋ እንክብካቤ ተለይቶን አያውቅም

ማሪያን፦ ባለፉት 48 ዓመታት ጥሩ አጋር የሆነችልኝን ሮዛን ስለሰጠኝ ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ። በጉብኝት ባሳለፍኳቸው በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ትልቅ ድጋፍ ሰጥታኛለች። አንድም ቀን ‘ምነው የራሳችን ቤት ኖሮን ተረጋግተን በተቀመጥን’ ስትል ሰምቻት አላውቅም።

ሮዛ፦ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች “የምትኖሩት ጥሩ ኑሮ አይደለም። ሁልጊዜ የምትኖሩት በሌሎች ሰዎች ቤት ነው” ይሉኛል። ሆኖም “ጥሩ ኑሮ” የሚባለው ምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ አላስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ከታጠርን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን እንዳናከናውን እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። የሚያስፈልጉን ነገሮች ምቹ አልጋ፣ ጠረጴዛና አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ብቻ ናቸው። አቅኚ እንደመሆናችን መጠን በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሆች ነን፤ ሆኖም የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስፈልጉን ነገሮች ተጓድለውብን አያውቁም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ “የራሳችሁ ቤት የላችሁም፤ ጡረታም አታገኙም፤ ስታረጁ ምን ልትሆኑ ነው?” የሚል ጥያቄ ይቀርብልኛል። በዚህ ጊዜ መዝሙር 34:10 ላይ የሚገኘውን “እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጐድልባቸውም” የሚለውን ሐሳብ እጠቅስላቸዋለሁ። የይሖዋ እንክብካቤ ምንጊዜም ተለይቶን አያውቅም።

ማሪያን፦ እውነት ነው! እንዲያውም ይሖዋ ከሚያስፈልገን በላይ ብዙ ነገሮችን አድርጎልናል። ለምሳሌ በ1958 ወረዳችንን ወክዬ በኒው ዮርክ በሚደረግ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ተመረጥኩ። ነገር ግን ለሮዛ ትኬት መግዣ የሚሆን ገንዘብ አልነበረንም። አንድ ቀን ምሽት አንድ ወንድም “ኒው ዮርክ” የሚል ጽሑፍ ያለበት ፖስታ ሰጠን። በውስጡ ሮዛ አብራኝ እንድትጓዝ የሚያስችል ስጦታ ነበረበት!

እኔም ሆንኩ ሮዛ በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፍናቸው ዓመታት በጭራሽ ተቆጭተን አናውቅም። ምንም ያጣነው ነገር የለም። እንዲያውም ይሖዋን በሙሉ ጊዜ በማገልገል አርኪና አስደሳች ሕይወት ለመምራት ችለናል። ይሖዋ ድንቅ አምላክ ነው። በእርሱ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን እንዳለብን የተገነዘብን ከመሆኑም በላይ ለእርሱ ያለን ፍቅር ይበልጥ እየጨመረ ሄዷል። አንዳንድ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ታማኝነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገዋል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በይሖዋ አገልግሎት በሚያሳልፋቸው ብዙ ዓመታት ሕይወቱን ቀስ በቀስ መሥዋዕት ሊያደርግ ይችላል ብዬ አምናለሁ። እኔና ሮዛ እስከ አሁን እንዲህ ለማድረግ ስንጥር ቆይተናል፤ ወደፊትም ቢሆን በዚሁ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የልዊ ፒሆታ የሕይወት ታሪክ “‘ከሞት ጉዞ’ ተረፍኩ” በሚል ርዕስ በነሐሴ 15, 1980 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1930 ፍራንስዋና አና ዙሚጋ ከልጆቻቸው ከስቴፋኒ፣ ስቴፈን፣ ሜላኒና ማሪያን ጋር። በርጩማው ላይ የቆመው ማሪያን ነው

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ:- በ1950 በሰሜን ፈረንሳይ በምትገኘው አርመንቲየርስ በገበያ ቦታ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ስናስተዋውቅ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስተግራ:- በ1950 ስቴፋን ቤሁኒክ ከማሪያን ጋር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሪያንና ሮዛ ከሠርጋቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1951 ሮዛ (በስተግራ መጀመሪያ ያለችው) አቅኚ ከሆነችው የአገልግሎት ጓደኛዋ ከኢሬን ጋር (በስተግራ አራተኛዋ) የስብሰባ ማስታወቂያ አንግበው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጉባኤዎችን ስንጎበኝ በዋነኝነት የምንጓዘው በብስክሌት ነበር