በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የይሖዋ ምሥክሮች በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን 144,000 የሚለውን ቁጥር በምሳሌያዊ ሁኔታ ሳይሆን ቃል በቃል የሚረዱት ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ዮሐንስ “የታተሙትንም ቊጥር ሰማሁ፤ እነርሱም . . . መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ” ሲል ጽፏል። (ራእይ 7:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘የታተሙት’ የሚለው ቃል በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ገነት የምትሆነውን ምድር ለመግዛት ከመላው የሰው ዘር የተመረጡ ሰዎችን ያመለክታል። (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22፤ ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) መቶ አርባ አራት ሺህ የሚለውን ቁጥር ቃል በቃል እንድንረዳ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉን። አንደኛው ከራእይ 7:4 በታች ይገኛል።

ሐዋርያው ዮሐንስ 144,000 ሰዎች ስለሚገኙበት ስለዚህ ቡድን በራእይ ከተገለጠለት በኋላ አንድ ሌላ ቡድን ተመለከተ። ዮሐንስ ይህን ሁለተኛ ቡድን በሚመለከት “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ቆመው ማየቱን ተናግሯል። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ይህን ክፉ ዓለም ከሚያጠፋው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት የሚተርፉትን ሰዎች ያመለክታሉ።—ራእይ 7:9, 141954 ትርጉም

ይሁን እንጂ ዮሐንስ፣ ራእይ ምዕራፍ 7 ቁጥር 4ን እና ቁጥር 9ን እንዴት እንዳነጻጸራቸው ልብ በል። ‘የታተሙት’ ማለትም የመጀመሪያው ቡድን አባላት የተወሰነ ቁጥር እንዳላቸው ገልጿል። ሁለተኛው ቡድን ይኸውም “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት ግን የተወሰነ ቁጥር የላቸውም። ከዚህ የተነሳ 144,000 የሚለው ቁጥር ቃል በቃል መወሰዱ ምክንያታዊ ነው። ቁጥሩ ምሳሌያዊ ቢሆንና የተወሰነ ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች የሚያመለክት ቢሆን ኖሮ በሁለቱ ቁጥሮች መካከል ያለው ንጽጽር ትርጉም አይኖረውም ነበር። በመሆኑም በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ 144,000 የሚለው ቁጥር ቃል በቃል መወሰድ እንደሚኖርበት በማያሻማ ሁኔታ ያመለክታል።

ጥንትም ሆነ ዛሬ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ቁጥሩ ቃል በቃል መወሰድ ይኖርበታል የሚል ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዶክተር ኢተልበርት ቡሊንገር የተባሉ እንግሊዛዊ የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የዛሬ 100 ዓመት ገደማ ራእይ 7:4, 9ን በሚመለከት “በዚሁ ምዕራፍ ላይ ያልተወሰነ ቁጥር፣ ከተወሰነ ቁጥር ጋር ተነጻጽሮ ስለተገለጸ ሐሳቡ ግልጽና የማያሻማ ነው” ብለዋል። (ዚ አፖካሊፕስ ኦር “ዘ ዴይ ኦቭ ዘ ሎርድ” ገጽ 282) በቅርቡ ደግሞ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ ዘ ማስተርስ ሴሚናሪ በተባለ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ በአዲስ ኪዳን ፕሮፌሰር የሆኑት ሮበርት ቶማስ “ቁጥሩ ምሳሌያዊ ነው ለማለት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት የለም” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም “የተነጻጸሩት [በራእይ 7:4 ላይ የሚገኘው] የተወሰነ ቁጥርና በ[ራእይ] 7:9 ላይ ያለው ያልተወሰነ ቁጥር ናቸው። ቁጥሩ በምሳሌያዊ መንገድ የሚወሰድ ከሆነ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኝ አንድም ቁጥር ቃል በቃል ሊወሰድ አይችልም ማለት ነው” ብለዋል።—ሬቨሌሽን:- አን ኤክሰጄቲካል ኮሜንታሪ፣ ጥራዝ 1 ገጽ 474

አንዳንዶች የዮሐንስ ራእይ ጥልቅ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን ስለሚጠቀም 144,000 የሚለውን ቁጥር ጨምሮ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ቁጥሮች በሙሉ ምሳሌያዊ መሆን አለባቸው በማለት ይከራከራሉ። (ራእይ 1:1, 4፤ 2:10) እንዲህ ብሎ መደምደሙ ግን ትክክል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የራእይ መጽሐፍ በርካታ ምሳሌያዊ ቁጥሮች እንዳሉት የታወቀ ነው፤ ይሁን እንጂ ቃል በቃል ልንረዳቸው የሚገቡ ቁጥሮችም ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሐንስ ስለ ‘ዐሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች’ ተናግሯል። (ራእይ 21:14) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው 12 ቁጥር ምሳሌያዊ ሳይሆን ቃል በቃል የሚወሰድ ነው። በተጨማሪም ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ‘የሺህ ዓመት’ ግዛት ጽፏል። መጽሐፍ ቅዱስን በማስተዋል ካጠናነው ይህንንም ቁጥር ቃል በቃል ልንረዳው እንደሚገባ እንገነዘባለን። a (ራእይ 20:3, 5-7) በመሆኑም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ቁጥሮች ልንረዳቸው የሚገባን ቃል በቃል ይሁን ወይም በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚወስነው የተጻፈበት ዓላማና በቁጥሩ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ነው።

መቶ አርባ አራት ሺህ የሚለው ቁጥር ቃል በቃል መወሰድ ይኖርበታል እንዲሁም የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ይኸውም ‘ከእጅግ ብዙ ሰዎች’ ጋር ሲነጻጸሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ያመለክታል የሚለው መደምደሚያ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ጋር ይስማማል። ለምሳሌ ያህል፣ ከጊዜ በኋላ ለሐዋርያው ዮሐንስ በተገለጠለት ራእይ ውስጥ እነዚህ 144,000 ሰዎች “በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ” መሆናቸው ተገልጿል። (ራእይ 14:1, 4) “በኩራት” የሚለው ቃል መጀመሪያ ከደረሰ የሰብል ፍሬ የተወሰደን ናሙና ያመለክታል። እንዲሁም ኢየሱስ ምድር ሳለ በሰማያዊ መንግሥት ከእርሱ ጋር ስለሚገዙት ሰዎች የተናገረ ሲሆን እነርሱን “ታናሽ መንጋ” በማለት ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 12:321954 ትርጉም፤ 22:29) በእርግጥም በሰማይ ገዥዎች እንዲሆኑ ከሰው ልጆች መካከል የተመረጡት ገነት የምትሆነውን ምድር ከሚወርሱት ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ ጥቂት ናቸው።

በመሆኑም፣ በራእይ 7:4 ዙሪያ የሚገኘው ሐሳብና በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙት ተዛማጅነት ያላቸው አባባሎች 144,000 የሚለው ቁጥር ቃል በቃል መወሰድ እንደሚኖርበት ያረጋግጣሉ። ቁጥሩ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ሆነው ገነት የምትሆነውንና ይሖዋን በሚያመልኩ እጅግ ብዙ ሰዎች የምትሞላውን ምድር የሚገዙትን ሰዎች ያመለክታል።—መዝሙር 37:29

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስለ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 289-90 ተመልከት።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሰማይ ውርሻ ያላቸው ሰዎች ቁጥር 144,000 ነው

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እጅግ ብዙ ሰዎች” ቁጥራቸው የተወሰነ አይደለም

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከዋክብት:- Courtesy of Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin