ደስተኛ ለመሆን በእርግጥ ምን ያስፈልጋል?
ደስተኛ ለመሆን በእርግጥ ምን ያስፈልጋል?
“ደስተኛ አምላክ” የሆነው ይሖዋና “ደስተኛና ብቻውን ገዥ የሆነው” ኢየሱስ ክርስቶስ ደስተኛ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ ከማንም በላይ ያውቃሉ። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ 6:15 NW) በመሆኑም የደስታ ቁልፍ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መገኘቱ የሚያስደንቅ አይደለም።—ራእይ 1:3፤ 22:7
ኢየሱስ በዝነኛ የተራራ ስብከቱ ላይ ደስተኛ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ ገልጿል። (1) በመንፈስ ድኾች የሆኑ፣ (2) የሚያዝኑ፣ (3) የዋሆች፣ (4) ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ፣ (5) ምሕረት የሚያደርጉ፣ (6) ልባቸው ንጹሕ የሆነ፣ (7) ሰላምን የሚያወርዱ፣ (8) ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ እና (9) በእርሱ ምክንያት የሚሰደቡና የሚሰደዱ “ብፁዓን” ወይም ደስተኞች እንደሆኑ ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:3-11 a
ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች ትክክል ናቸው?
ኢየሱስ የተናገራቸውን አንዳንድ ሐሳቦች ትክክል ናቸው ብሎ ለመቀበል ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ያስፈልጋል። የዋህ፣ መሐሪ፣ ሰላማዊና ንጹሕ ልብ ያለው ሰው ቁጡ፣ ጠበኛና ጨካኝ ከሆነ ሰው ይልቅ ደስተኛ መሆኑን ማን ሊክድ ይችላል?
ይሁን እንጂ፣ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ወይም የሚያዝኑ ሰዎች እንዴት ደስተኛ ይባላሉ ብለን እንጠይቅ ሕዝቅኤል 9:4) ይህ በራሱ ደስተኛ እንደማያደርጋቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ፣ አምላክ በምድር ላይ ጽድቅን የማስፈንና በግፍ ለተደቆሱት ፍትሕን የማምጣት ዓላማ እንዳለው ሲማሩ ደስታቸው ወደር አይኖረውም።—ኢሳይያስ 11:4
ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ስለ ዓለም ሁኔታዎች ትክክለኛ አመለካከት አላቸው። በዘመናችን ‘በሚሠራው ጸያፍ ተግባር ያዝናሉ እንዲሁም ያለቅሳሉ።’ (በተጨማሪም ሰዎች ለጽድቅ ካላቸው ፍቅር የተነሳ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ጥረት አድርገው በተደጋጋሚ አልሳካ ሲላቸው ያዝናሉ። ይህም በመንፈሳዊ የሚጎድላቸው ነገር እንዳለ እንደሚገነዘቡ ያሳያል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ድክመቶቻቸውን እንዲያሸንፉ ሊረዳቸው የሚችለው አምላክ ብቻ መሆኑን ስለሚገነዘቡ አመራሩን ለመቀበል ፈቃደኞች ይሆናሉ።—ምሳሌ 16:3, 9፤ 20:24
የሚያዝኑ፣ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ እንዲሁም በመንፈሳዊ የሚጎድላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ሰዎች ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘባሉ። ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ደስታ እንደሚያስገኝ የታወቀ ነው፤ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ደግሞ ከዚያ የበለጠ ደስታ ያስገኛል። አዎን፣ መለኮታዊውን አመራር ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ፣ ጽድቅን ከልብ የሚያፈቅሩ ሰዎች ደስተኞች መባላቸው የተገባ ነው።
ይሁን እንጂ፣ የሚሰደዱና የሚሰደቡ ሰዎች ደስተኛ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባለውን መቀበል ይከብድህ ይሆናል። ሆኖም ይህን የተናገረው ኢየሱስ በመሆኑ ደስተኛ ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ እነዚህን ቃላት መረዳት ያለብን እንዴት ነው?
እየተሰደዱም ደስተኛ መሆን እንዴት ይቻላል?
ኢየሱስ መሰደብና መሰደድ በራሱ ደስታ ያስገኛሉ እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ “ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ . . . ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁ . . . ብፁዓን ናችሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:10, 11) በመሆኑም አንድ ሰው ብፁዕ ወይም ደስተኛ የሚሆነው ስድብ ወይም ነቀፋ የሚሰነዘርበት የክርስቶስ ተከታይ በመሆኑ እንዲሁም ኢየሱስ ካስተማረው የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖሩ ከሆነ ብቻ ነው።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ነገር ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ሳንሄድሪን የተባለው የአይሁዳውያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አባላት “ሐዋርያትን አስጠርተው አስገረፏቸው፤ ዳግመኛም በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ አዘው ለቀቋቸው።” ሐዋርያት ምን ተሰምቷቸው ይሆን? “ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 5:40-42፤ 13:50-52
ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገረው ሐሳብ በነቀፋና በደስታ መካከል ያለውን ግንኙነት በሚመለከት ተጨማሪ የእውቀት ብርሃን ይፈነጥቅልናል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ፣ የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ብፁዓን ናችሁ።” (1 ጴጥሮስ 4:14) አዎን፣ አንድ ክርስቲያን መሰቃየት ባያስደስተውም እንኳ ሥቃይ የሚደርስበት ትክክል የሆነውን በማድረጉ ምክንያት ከሆነ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንደሚያስገኝለት ስለሚያውቅ ደስ ይለዋል። የአምላክ መንፈስ ከደስታ ጋር ተያይዞ የተገለጸው ለምንድን ነው?
የሥጋ ሥራ ወይስ የመንፈስ ፍሬ?
የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚያርፈው የአምላክን ገዥነት ተቀብለው በሚታዘዙት ሰዎች ላይ ብቻ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 5:32) ይሖዋ ‘የሥጋ ሥራን’ ለሚያደርጉ ሰዎች መንፈሱን አይሰጥም። የሥጋ ሥራ “ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቁጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፤ ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ እንዲሁም እነዚህን የመሰለው ነው።” (ገላትያ 5:19-21) በዚህ ዓለም ‘የሥጋ ሥራዎችን’ ማድረግ በጣም የተለመደ መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ይህን የሚያደርጉ ሰዎች እውነተኛና ዘላቂ ደስታ አያገኙም። እንዲያውም አንድ ሰው የሥጋ ሥራዎችን ማድረጉ ከዘመዶቹ፣ ከጓደኞቹና ከወዳጆቹ ጋር ያለውን ጥሩ ግንኙነት ያበላሽበታል። ከዚህም በላይ የአምላክ ቃል እንደሚናገረው “በእንዲህ ሁኔታ የሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”
በአንጻሩ ግን፣ አምላክ ‘የመንፈስ ፍሬዎችን’ ለሚያዳብሩ ሰዎች መንፈሱን ይሰጣል። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬዎች “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት [“እምነት፣ የ1954 ትርጉም”]፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” ናቸው። (ገላትያ 5:22, 23) እነዚህን ባሕርያት ስናንጸባርቅ ከሰዎችና ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ወዳጅነት ለመፍጠር የሚያስችል ሁኔታ የሚኖረን ሲሆን ይህም እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (ሣጥኑን ተመልከት) ከዚህም በላይ ፍቅርን፣ ቸርነትን፣ በጎነትንና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያትን በማንጸባረቅ ይሖዋን እናስደስታለን፤ እንዲሁም ጽድቅ በሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አስደሳች ተስፋ እናገኛለን።
ደስታ በምናደርገው ምርጫ ላይ የተመካ ነው
በጀርመን የሚኖሩ ቮልፍጋንግ እና ብሪጊት የተባሉ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማጥናት በጀመሩበት ወቅት ሰዎች ለደስታ አስፈላጊ ናቸው የሚሏቸው በርካታ ቁሳዊ ነገሮች ነበሯቸው። ወጣትና ጤናማ የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ በውድ ዋጋ የገዟቸው ልብሶች ነበሯቸው፣ በጣም በሚያምር ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር እንዲሁም ትርፋማ የንግድ ሥራ ነበራቸው። አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ተጨማሪ ቁሳዊ ሀብት በማሳደድ ነበር፤ ሆኖም ይህ እውነተኛ ደስታ አላስገኘላቸውም። ስለዚህ ከጊዜ በኋላ ወሳኝ ምርጫ አደረጉ። መንፈሳዊ እሴቶችን ለማካበት የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ጊዜ የመደቡ ከመሆኑም በላይ ብርቱ ጥረት ማድረግ ጀመሩ፤ እንዲሁም ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የሚያስችሏቸውን መንገዶች ቀየሱ። ውሳኔያቸው ብዙም ሳይቆይ የአመለካከት ለውጥ ወደ ማድረግ የመራቸው ሲሆን ይህም አኗኗራቸውን ቀላል አድርገው አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ወንጌላዊ እንዲሆኑ ገፋፋቸው። በአሁኑ ጊዜ ጀርመን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በፈቃደኛ ሠራተኝነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም በአገራቸው የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንዲማሩ ለመርዳት በእስያ ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል አንዱን በመማር ላይ ናቸው።
እነዚህ ባልና ሚስት እውነተኛ ደስታ አግኝተው ይሆን? ቮልፍጋንግ እንዲህ ይላል:- “ለመንፈሳዊ ነገሮች ይበልጥ ትኩረት መስጠት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ከመቼውም የበለጠ ደስታና እርካታ አግኝተናል። ይሖዋን በፍጹም ልባችን ማገልገላችን የጋብቻ ሰንሰለታችንንም
አጠናክሮልናል። በፊትም ቢሆን አስደሳች ትዳር ነበረን፤ ሆኖም የተለያዩ ግዴታዎችና ፍላጎቶች ስለነበሩን ሁለታችንም በየፊናችን እንሮጥ ነበር። አሁን ግን ሁለታችንም ተመሳሳይ ግብ ላይ ለመድረስ ተባብረን እንሠራለን።”ደስተኛ ለመሆን ምን ያስፈልጋል?
በአጭሩ ‘ከሥጋ ሥራዎች’ ርቆ ‘የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች’ ማፍራት ነው። አንድ ሰው ደስተኛ ለመሆን ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመመሥረት ከፍተኛ ፍላጎት ሊያድርበት ይገባል። እንዲህ ለማድረግ የሚጣጣር ሰው ኢየሱስ የገለጸው ዓይነት ደስታ ያገኛል።
በመሆኑም ፈጽሞ ደስተኛ ልሆን አልችልም የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩል። በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ጤና አይኖርህ ይሆናል፤ ወይም በትዳርህ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች ሊኖሩህ ይችላሉ። ምናልባትም ልጅ ወልደህ ማሳደግ የምትችልበት ዕድሜ አልፎህ ወይም አርኪ ሥራ ለማግኘት ብርቱ ጥረት እያደረግህ ይሆናል። እንዲሁም ኪስህ የበፊቱን ያህል ሙሉ ላይሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ አይዞህ፣ ተስፋ የምትቆርጥበት ምንም ምክንያት የለም! በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር እነዚህና ሌሎች በርካታ ችግሮች ይወገዳሉ። በእርግጥም ይሖዋ አምላክ፣ መዝሙራዊው “መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት . . . አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ” በማለት የተናገረውን ተስፋ በቅርቡ ይፈጽማል። (መዝሙር 145:13, 16) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች እንደሚመሰክሩት አጽናኝ የሆነውን ይህን ተስፋ ማስታወስህ በዛሬው ጊዜም እንኳ ደስተኛ እንድትሆን በእጅጉ ይረዳሃል።—ራእይ 21:3
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ዘጠኝ ዓረፍተ ነገሮች የሚጀምሩት ማካሪይ በሚለው የግሪክኛ ቃል ነው። አዲሲቱ ዓለም ትርጉም እንዲሁም ዘ ጀሩሳሌም ባይብል እና ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርዥን የመሳሰሉ ትርጉሞች ይህንን ቃል “ብፁዕ” ወይም ብሩክ በማለት ከተረጎሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተለየ “ደስተኛ” በማለት በትክክል ተርጉመውታል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች
ፍቅር የምታሳይ ከሆነ ሌሎችም ይወዱሃል።
ደስታ ተፈታታኝ ችግሮችን እንድትቋቋም ብርታት ይሰጥሃል።
ሰላም ከሌሎች ጋር ተስማምተህ እንድትኖር ይረዳሃል።
ትዕግሥት መከራ በሚያጋጥምህ ጊዜም እንኳ ደስታህን እንዳታጣ ይረዳሃል።
ቸርነት ወይም ደግነት ሌሎችን ወደ አንተ ይስባል።
በጎነት የምታሳይ ከሆነ ሌሎች በችግርህ ጊዜ ቶሎ ይደርሱልሃል።
እምነት የአምላክን ፍቅራዊ አመራር ያስገኝልሃል።
ገርነት ወይም የዋህነት የልብ፣ የአእምሮና የአካል መረጋጋት ያጎናጽፍሃል።
ራስን መግዛት ከብዙ ስህተት ይጠብቅሃል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ደስተኛ ለመሆን መንፈሳዊ ጥማትህን ማርካት ያስፈልግሃል