በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በባሕሮች ውስጥ ያለው የተትረፈረፈ ብልጽግና’

‘በባሕሮች ውስጥ ያለው የተትረፈረፈ ብልጽግና’

ዕጹብ ድንቅ የሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት

‘በባሕሮች ውስጥ ያለው የተትረፈረፈ ብልጽግና’

ጀንበር ስታሽቆለቁል በዝግታ የሚነፍሰው ነፋስ ባሕሩን ወዲያና ወዲህ ያናውጠዋል። ሞገዱም ከባሕሩ ዳርቻ ጋር በቀስታ እየተጋጨ ይመለሳል። ለእረፍትና ለመዝናናት ወደ ባሕሩ ዳርቻ የሚጎርፉ ሰዎች ማዕበሉ በሚፈጥረው ድምፅ መንፈሳቸው ይታደሳል። a

እንደዚህ ያሉ የባህር ዳርቻዎች የሚገኙባቸው ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚሸፍኑ የባሕር ጠረፎች በዓለም ዙሪያ ይገኛሉ። በውኃና በአሸዋው መካከል ያለው ይህ በአንድ ቦታ የማይረጋ ድንበር ለባሕሩ ወሰን ያበጅለታል። ባህሩን በዚህ መልክ ያዘጋጀው ፈጣሪ ነው። ራሱ አምላክ “አሸዋን ለባሕር ድንበር አደረግሁ” ብሏል። አክሎም “ማዕበሉ እየጋለበ ቢመጣ ከዚያ አያልፍም፤ ሞገዱ ቢጮኽም ሊያቋርጠው አይችልም” በማለት ተናግሯል።—ኤርምያስ 5:22፤ ኢዮብ 38:8፤ መዝሙር 33:7

ምድራችን በአብዛኛው በውኃ የተሸፈነች መሆኗ በምንገኝበት ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ካሉት ፕላኔቶች ሁሉ የተለየች ያደርጋታል። ሰባ በመቶ የሚሆነው የፕላኔታችን ክፍል በውኃ የተሸፈነ ነው። ይሖዋ ምድርን ለሰዎች መኖሪያነት ሲያዘጋጃት “‘ከሰማይ በታች ያለው ውሃ በአንድ ስፍራ ይከማች፤ ደረቁ ምድር ይገለጥ’ አለ፤ እንዳለውም ሆነ።” ከዚያም ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] ደረቁን ምድር፣ ‘የብስ’፣ በአንድነት የተሰበሰበውን ውሃ፣ ‘ባሕር’ ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ።” (ዘፍጥረት 1:9, 10) የውቅያኖሶች መኖር ምን ጥቅም አለው?

በውቅያኖሶች ውስጥ የሚገኘው ውኃ በተለያዩ መንገዶች ለሕይወት አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ውኃ ሙቀትን በውስጡ ይዞ የማቆየት ችሎታ አለው። በመሆኑም ውቅያኖሶች ትላልቅ የሙቀት ማጠራቀሚያዎች ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማውን የክረምት ቅዝቃዜ ለማለዘብ ይረዳሉ።

ውኃ ሌላም ጥቅም አለው። ከየትኛውም ፈሳሽ በተሻለ ሁኔታ ንጥረ ነገሮችን በቀላሉ ማሟሟት ይችላል። ከሕይወት ጋር የተያያዙ ዑደቶች በሙሉ ሊከናወኑ የሚችሉት ኬሚካላዊ ለውጦች ሲካሄዱ በመሆኑ አስፈላጊዎቹን ንጥረ ነገሮች ለማሟሟትና ሞለኪውሎቻቸውን በማገናኘት የተለያዩ ውህዶችን ለመፍጠር ውኃ የግድ አስፈላጊ ነው። ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ከሚገኙት ኬሚካላዊ ውህዶች መካከል አብዛኞቹ በውስጣቸው ውኃ ይገኛል። ዘ ሲ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚለው “ሁሉም ዓይነት ሕይወት ሌላው ቀርቶ በየብስ ላይ የሚኖሩት ዕጽዋትና እንስሳት እንኳ ውኃ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ይህ ውኃ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመጣው ከውቅያኖሶች ነው።”

የምድራችን ውቅያኖሶች ከባቢ አየርን በማጣራት ረገድም ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በውቅያኖሶች ላይ የሚንሳፈፉት ፕላንክተን ተብለው የሚጠሩት ጥቃቅን ዕጽዋትና ነፍሳት ካርቦን ዳይኦክሳይድን ወደ ኦክስጅን ይለውጣሉ። አንድ ተማራማሪ “በየዓመቱ ወደ ከባቢ አየር ከሚገባው ኦክስጅን ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በባሕር ላይ ካለው ፕላንክተን ነው ብለዋል።

ከዚህም በላይ የተለያዩ በሽታዎችን ለማከም የሚያስችሉ ተፈጥሯዊ መድኃኒቶችን ከውቅያኖሶች ማግኘት ይቻላል። የዓሣ ተዋጽኦዎች ለብዙ ክፍለ ዘመናት በመድኃኒትነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ኮድ ከተባለው የዓሣ ዝርያ ጉበት ውስጥ የሚገኘውን ዘይት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በቅርብ ዓመታት ደግሞ ከዓሦችና ከሌሎች የባሕር ፍጥረታት የሚገኙ ኬሚካሎች አስምን ለማከምና ልዩ ልዩ ቫይረሶችን ብሎም ካንሰርን ለመዋጋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።

ውቅያኖሶች ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለመገመት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ምንም እንኳን ትክክለኛ አኃዝ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ቢሆንም የፕላኔታችን ጠቅላላ ሥነ ምሕዳር ከሚሰጠን ጥቅም ውስጥ ወደ ሁለት ሦስተኛ የሚጠጋው ከውቅያኖሶች የሚገኝ እንደሆነ ይገመታል። ይህም ውቅያኖሶች የተፈጠሩት በዓላማ፣ ይኸውም ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንደሆነ ያረጋግጥልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ባሕሮች በውስጣቸው የተትረፈረፈ ብልጽግና’ እንደያዙ የሚናገረው ሐሳብ ከዚህ ጋር ምንኛ ይስማማል!—ዘዳግም 33:19

የዚህ ሀብት ታላቅ ንድፍ አውጪና ፈጣሪ ተብሎ ሊወደስ የሚገባው ይሖዋ ነው። በዚህም የተነሳ ነህምያ “አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ። ሰማያትን፣ . . . ባሕሮችንና በውስጣቸው ያሉትንም ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ” በማለት እርሱን ለማወደስ ተገፋፍቷል።—ነህምያ 9:6

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የ2004 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ መስከረም/ጥቅምት የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ውኃ፣ ነፋስና የባሕር ሞገዶች

በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካሊፎርኒያ የተነሳው ይህ ፎቶግራፍ እንደሚያሳየው ውኃና ነፋስ በጋራ የሚፈጥሯቸው ትላልቅ ሞገዶች ከቋጥኞች ጋር ሲላተሙ ጆሮ የሚያደነቁር ድምፅ ይፈጥራሉ። የውቅያኖሶችን ልዩ ገጽታ የሚያሳዩት ማዕበሎች ውኃ ያለውን አስገራሚ ኃይል ያስገነዝቡናል። የፈጣሪንም ወደር የለሽ ኃይል ያስታውሱናል። ይሖዋ “በባሕርም ማዕበል ላይ ይራመዳል” ተብሎለታል። እንዲሁም “በኀይሉ ባሕርን ጸጥ ያደርጋል፤ በጥበቡም ረዓብ የተባለውን ታላቅ አውሬ ያጠፋል” ተብሏል። (ኢዮብ 9:8፤ 26:12 የ1980 ትርጉም) በእርግጥም፣ “ከብዙ ውሆች ድምፅ ይልቅ፣ ከባሕርም ሞገድ ይልቅ፣ ከፍ ብሎ ያለው እግዚአብሔር ኀያል ነው።”—መዝሙር 93:4

አስገራሚ ቅርጽ ያላቸው የአሸዋ ክምሮች

በአንዳንድ አካባቢዎች አስገራሚ ቅርጽ ያላቸው የአሸዋ ክምሮች የባሕር ዳርቻዎችን ተንተርሰው የሚገኙ ሲሆን በሥዕሉ ላይ የሚታየው በደቡብ አፍሪካ፣ ናሚቢያ የባሕር ጠረፍ ላይ የሚገኘው የአሸዋ ክምር ከእነዚህ አንዱ ነው። ለአሸዋው ይህን የመሰለ ልዩ ቅርጽ የሚሰጠው ዋነኛው ኃይል ነፋስ ነው። አንዳንድ የአሸዋ ክምሮች ትናንሽ ጉብታ የሚመስሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ እስከ 400 ሜትር የሚደርስ ከፍታ አላቸው። ይህ ሥፍር ቁጥር የሌለው አሸዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን “እንደ ባሕር ዳር አሸዋ” የሚለውን አባባል ለመረዳት ያስችለናል። ይህ አባባል ሊቆጠር ወይም ሊሰፈር የማይችልን ነገር ለማመልከት ያገለግላል። (ዘፍጥረት 22:17) ፈጣሪ ይህን የአሸዋ ክምር ያዘጋጀው በአስፈሪ ሁኔታ እየጋለበ የሚመጣውን የባሕር ማዕበል በቦታው ለመገደብ እንደሆነ ስንገነዘብ በብልሃቱ እንደመማለን።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በባሕር ዳርቻ ላይ ጀንበር ስትጠልቅ፣ በቢያፍራ ባሕረ ሰላጤ፣ ካሜሩን