በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቼስተር ቢቲን ውድ ቅርሶች መጎብኘት

የቼስተር ቢቲን ውድ ቅርሶች መጎብኘት

የቼስተር ቢቲን ውድ ቅርሶች መጎብኘት

“በታሪክ ዘመን የነበሩ በርካታ ሥልጣኔዎች ያፈሯቸው ውድ ቅርሶች በብዛት ይገኝበታል . . . የቅርጻ ቅርጾቹና የስዕሎቹ ማማር አፍ ያስከፍታል።” ይህን የተናገሩት በአየርላንድ ደብሊን የሚገኘው የቼስተር ቢቲ ቤተ መዘክር የቀድሞው ኃላፊ የነበሩት ሪቻርድ ጄምስ ናቸው። ይህ ቤተ መዘክር በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ጥንታዊ ዕቃዎች፣ አስደናቂ የሥነ ጥበብ ውጤቶች እንዲሁም ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ በጣት የሚቆጠሩ መጻሕፍትና በእጅ የተገለበጡ ጽሑፎች በብዛት የሚገኙበት ቦታ ነው። ይሁንና ቼስተር ቢቲ ማን ነበረ? ምን ዓይነት ውድ ቅርሶችንስ ሰብስቧል?

በ1875 በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተወለደው አልፍሬድ ቼስተር ቢቲ የስኮትላንድ፣ የአየርላንድና የእንግሊዝ ደም አለው። የማዕድን ማውጫ መሐንዲስና አማካሪ የነበረው ቢቲ በ32 ዓመት ዕድሜው የናጠጠ ሀብታም ሆነ። የነበረውን ከፍተኛ ገንዘብ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በጣም የሚያማምሩና ጥራት ያላቸው ዕቃዎች ለመሰብሰብ ተጠቅሞበታል። ቢቲ በ1968 በ92 ዓመቱ ሲሞት የሰበሰባቸውን ቅርሶች በሙሉ ለአየርላንድ ሕዝብ በስጦታ አበረከተ።

ከሰበሰባቸው ዕቃዎች መካከል ምን ምን ይገኛሉ?

ቢቲ የሰበሰባቸው ዕቃዎች እጅግ ብዙ ከመሆናቸውም በላይ በዓይነት በጣም የተለያዩ ናቸው። በአንድ ጊዜ ለኤግዚቢሽን የሚቀርበው ወደ 1 ከመቶ ገደማ ብቻ የሚሆነው ነው። በሺዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በርካታ ኅብረተሰቦች በተለያዩ ዘመናት ያፈሯቸውን በጣም ብርቅ የሆኑ ውድ ዕቃዎችን አሰባስቧል። ይህም በመካከለኛው መቶ ዘመንና በተሐድሶ ዘመን በአውሮፓም ሆነ በበርካታ የእስያና የአፍሪካ አገሮች የነበሩ ዕቃዎችን ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል፣ ካሰባሰባቸው ነገሮች መካከል ከተፈለፈለ እንጨት የተሠራው ጥራት ያለው የጃፓን ስዕል በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ምርጥ እንደሆነ ይነገርለታል።

ድንቅ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ከሆኑት ፍጹም በተለየ፣ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈባቸው ከመቶ በላይ የሚሆኑ ጥንታዊ የባቢሎንና የሱሜራን አስደናቂ የሸክላ ሰሌዳዎች ይገኛሉ። ከ4,000 ዓመታት በፊት በሜሶጶጣሚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሕይወት ታሪካቸውን በእርጥብ የሸክላ ሰሌዳ ላይ በዝርዝር ጽፈው በእሳት ይተኩሱት ነበር። በዘመናችን እንደዚህ ዓይነት በርካታ ሰሌዳዎች በመገኘታቸው እጅ ጽሑፍ በጣም ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ጥበብ መሆኑ በግልጽ ሊታወቅ ችሏል።

ለመጻሕፍት የነበረው ፍቅር

ቼስተር ቢቲ ጥራት ያላቸው መጻሕፍት በሚዘጋጁበት የእጅ ጥበብ ይማረክ የነበረ ይመስላል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖታዊና ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ጽሑፎች ያሰባሰበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በረቀቀ ሁኔታ ያሸበረቁ የቁርዓን ቅጂዎች ይገኙበታል። አንድ ጸሐፊ እንዳሉት “ተለክተው የተጻፉ በሚመስሉት የአረብኛ ፊደላት ቀልቡ የተማረከ ይመስላል . . . ከዚህ በተጨማሪ በወርቅና በብር እንዲሁም ደማቅ ቀለም ባላቸው ሌሎች ማዕድናት ያሸበረቁ የቁም ጽሑፎችን በጣም ይወድ ነበር።”

ቀደም ባሉት መቶ ዘመናት እንደኖሩት ቻይናውያን ነገሥታት ሁሉ ቼስተር ቢቲም ኢያስጲድ ለሚባለው ክቡር ድንጋይ ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። ነገሥታቱ ጥራት ያለው ኢያስጲድ ከማንኛውም ማዕድን በላይ ተፈላጊ እንደሆነና ከወርቅ በጣም የበለጠ ጠቀሜታ እንዳለው ይሰማቸው ነበር። እነዚህ ገዢዎች፣ ላቅ ያለ የዕደ ጥበብ ሙያ ያላቸው ሰዎች ከኢያስጲድ ለስላሳና ስስ ገጾች እንዲያዘጋጁ አዘዟቸው። ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው የእጅ ባለሙያዎች ከኢያስጲድ በተሠሩት በእነዚህ ገጾች ላይ በወርቅ የተቀረጹ ጥራት ያላቸው የቁም ጽሑፎችና ስዕሎች ነደፉባቸው። እስከ ዛሬ ድረስ ከተዘጋጁት ሁሉ በጣም አስደናቂ የሆኑት አንዳንድ መጻሕፍት የተዘጋጁት በዚህ መንገድ ነው። ቢቲ ያሰባሰባቸው እነዚህ መጻሕፍት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ አድናቆት ተችሯቸዋል።

በጣም ውድ የሆኑ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች

ቼስተር ቢቲ ካሰባሰባቸው ውድ ቅርሶች መካከል የመጽሐፍ ቅዱስ አፍቃሪዎች የላቀ ግምት የሚሰጧቸው በጥንትና በመካከለኛው መቶ ዘመን በእጅ ተገልብጠው የተዘጋጁ ብዛት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ይገኙበታል። በሚያምር ሁኔታ ያሸበረቁ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ጸሐፊዎቹ በእጅ ሲገለብጡ ያሳዩትን ትዕግሥትና ጥበብ ያንጸባርቃሉ። በማተሚያ መሣሪያ የተዘጋጁት መጻሕፍት ደግሞ ቀደምት መጽሐፍ ጠራዦችና አታሚዎች የነበራቸውን ጥበብና የእጅ ሙያ ይመሰክራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዮሐንስ ጉተንበርግ ዘመን የኖረውና በ1479 ኑረምበርግ ውስጥ ቢብሊያ ላቲና የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ያተመው አንቶን ኮበርገር “በሕትመት ሥራ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ከያዙትና በመስኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ሰዎች መካከል አንዱ” እንደሆነ ይነገራል።

በቼስተር ቢቲ ቤተ መዘክር ለዕይታ ከሚቀርቡት መካከል በአራተኛው መቶ ዘመን በሶርያዊው ምሑር በኤፍሬም የተዘጋጀው የብራና ጽሑፍ በዓይነቱ ልዩ ነው። ኤፍሬም ቲያቴሳሮን ከተባለ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከተዘጋጀ መጽሐፍ ላይ በብዛት ጠቅሷል። በዚህ መጽሐፍ ላይ ጸሐፊው ቴሸን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የሚናገሩትን አራቱን የወንጌል ዘገባዎች አዋህዶ ስምም የሆነ አንድ ወጥ ታሪክ አስፍሯል። ከዚያ በኋላ የመጡ ጸሐፊዎች ከቲያቴሳሮን ጠቅሰው ቢናገሩም የዚህ መጽሐፍ አንድም ቅጂ አልተገኘም። በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ምሑራን እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ስለመኖሩ እንኳ ጥርጣሬ አድሮባቸው ነበር። ይሁን እንጂ በ1956 ቢቲ፣ ቲያቴሳሮን በተባለው የቴሸን ጽሑፍ ላይ ኤፍሬም ትንታኔ የሰጠበትን መጽሐፍ አገኘ። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነትና እውነተኝነት በይበልጥ ያረጋገጠ ግኝት ነው።

ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የፓፒረስ ጽሑፎች ስብስብ

ቢቲ ሃይማኖታዊና ዓለማዊ ይዘት ያላቸው እጅግ በርካታ የፓፒረስ ጽሑፎችንም አሰባስቧል። ከ50 በላይ የሚሆኑት የፓፒረስ መጻሕፍት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከአራተኛው መቶ ዘመን በፊት የተዘጋጁ ናቸው። ከእነዚህ የፓፒረስ ጽሑፎች መካከል አንዳንዶቹ እንደ ቆሻሻ ወረቀት ተጥለው በግብፅ በረሃ ለበርካታ ዘመናት ተሰውረው ከነበሩ ከፍተኛ የፓፒረስ ክምሮች ውስጥ የተገኙ ናቸው። ለሽያጭ የሚቀርቡት አብዛኞቹ የፓፒረስ ጽሑፎች የተሟሉ አልነበሩም። ሻጮች የፓፒረስ ቁርጥራጮች የታጨቁባቸው ካርቶኖች ይዘው ይመጡ ነበር። ከዚያም “መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች እጃቸውን እንዳመጣላቸው ሰድደው ብዙ ነገር የተጻፈበትን ትልቁን ክፍል ይዘው ይወጣሉ” ሲሉ የቼስተር ቢቲ ቤተ መዘክር የምዕራባውያን ዕቃዎች ስብስብ ኃላፊ የሆኑት ቻርለስ ሆርተን ተናግረዋል።

ሆርተን እንደተናገሩት ቢቲ “ካገኛቸው በጣም አስደናቂ” ነገሮች መካከል ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የፓፒረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች (ኮዴክሶች) የሚገኙበት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ “እጅግ ጥንታዊ የሚባሉት በክርስትና ዘመን የነበሩ አንዳንድ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቅጂዎች ይገኙበታል።” የፓፒረስ መጻሕፍቱን ዋጋማነት የተገነዘቡ ሻጮች የተለያዩ ክፍሎችን ለተለያዩ ገዥዎች ለመሸጥ ሲሉ ገነጣጥለዋቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቢቲ አብዛኞቹን ጥራዞች መግዛት ችሎ ነበር። እነዚህ የፓፒረስ ጽሑፎች ጠቀሜታቸው ምን ያህል ነው? ቲሸንዶርፍ፣ ኮዴክስ ሳይናቲከስን በ1844 ካገኘ በኋላ በነበረው ጊዜ ውስጥ “እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ” እንዳለው የሚቆጠረው የእነዚህ ጽሑፎች መገኘት ነው ሲሉ ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን ተናግረዋል።

እነዚህ የፓፒረስ ጽሑፎች በሁለተኛውና በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ የተዘጋጁ ናቸው። በግሪክኛው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ላይ ካሉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መካከል ሁለት የዘፍጥረት መጽሐፍ ቅጂዎች ይገኛሉ። በአራተኛው መቶ ዘመን በብራና በተዘጋጁት “በቫቲካነስና በሳይናይቲከስ ላይ [የዘፍጥረት] መጽሐፍ አብዛኛው ክፍል ስለማይገኝ” እነዚህ የፓፒረስ ጽሑፎች ልዩ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው ሲሉ ኬንዮን ተናግረዋል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የያዙ ሦስት የፓፒረስ መጻሕፍት (ኮዴክሶች) አሉ። አንደኛው የአራቱን ወንጌሎችና የሐዋርያት ሥራ መጻሕፍትን አብዛኛውን ክፍል ይዟል። ሁለተኛው ኮዴክስ ደግሞ ቢቲ ከጊዜ በኋላ ያገኛቸው ሌሎች ገጾች ተዳምረውበት የዕብራውያንን መልእክት ጨምሮ ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፋቸውን ደብዳቤዎች በሙሉ ይዟል ማለት ይቻላል። ሦስተኛው ኮዴክስ ደግሞ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የራእይ መጽሐፍ ይዟል። ኬንዮን እንዳሉት እነዚህ የፓፒረስ መጻሕፍት “አሁን በእጃችን ላይ የሚገኘው አዲስ ኪዳን ከጥንታዊው ቅጂ ምንም ልዩነት የለውም የሚለውን ጽኑ እምነታችንን ይበልጥ የሚያጠናክሩልን ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው።”

ቼስተር ቢቲ ያሰባሰባቸው በፓፒረስ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ ለአጠቃቀም አመቺ ባልሆነው ጥቅልል ፋንታ ኮዴክስ ወይም ገጾች ያሉት መጽሐፍ መጠቀም የጀመሩት ክርስቲያኖች እንደሆኑ ያሳያሉ። ይህም የሆነው ቀደም ባሉት ዓመታት ምናልባትም ከክርስቶስ ልደት በኋላ መጀመሪያው መቶ ዘመን ከማብቃቱ በፊት ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ መጻሕፍት በወቅቱ ለመጻፊያነት የሚያገለግሉ መሣሪያዎች እጥረት ያጋጥም ስለነበረ ገልባጮች አብዛኛውን ጊዜ ያገለገሉ የፓፒረስ ገጾችን በድጋሚ ይጠቀሙባቸው እንደነበር ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል ኮፕቲክ የሚል ስያሜ የተሰጠው የዮሐንስን ወንጌል የተወሰነ ክፍል የያዘ በእጅ የተገለበጠ ቅጂ የተጻፈው “ግሪክኛ የሒሳብ ስሌት በሰፈረበት የትምህርት ቤት ደብተር በሚመስል” ፓፒረስ ላይ ነው።

እነዚህ የፓፒረስ መጻሕፍት ለዓይን የሚማርኩ ባይሆኑም ተፈላጊነታቸው ግን እጅግ ከፍተኛ ነው። ክርስትና ወደጀመረበት ጊዜ የሚያደርሱን እውንና ተጨባጭ የመገናኛ መስመር ናቸው። “በእነዚህ የፓፒረስ መጻሕፍት አማካኝነት አንዳንድ የቀድሞዎቹ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች የተገለገሉባቸውን እንደ ውድ ሀብት የሚቆጥሯቸውን መጻሕፍት በገዛ ዓይናችሁ ማየት ትችላላችሁ” ሲሉ ቻርለስ ሆርተን ተናግረዋል። (ምሳሌ 2:4, 5) በቼስተር ቢቲ ቤተ መዘክር ከሚገኙት ከእነዚህ ውድ ቅርሶች መካከል አንዳንዶቹን የማየት አጋጣሚ ብታገኙ ፈጽሞ አትቆጩም።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካትሱሺካ ሆኩሲ ከተፈለፈለ እንጨት የሠራው የጃፓን ስዕል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ቢብሊያ ላቲና” ለሕትመት ከበቁት ቀደምት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች መካከል አንዱ ነው

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤፍሬም፣ “ቲያቴሳሮን” በተባለው የቴሸን ጽሑፍ ላይ የሰጠው ማብራሪያ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት አጠናክሯል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቼስተር ቢቲ ፒ45 በአንድ ጥራዝ ላይ የአራቱን ወንጌሎችና የሐዋርያት ሥራ መጻሕፍትን አብዛኞቹን ክፍል የያዘ በዓለም ላይ በጥንታዊነቱ ተወዳዳሪ የሌለው የፓፒረስ መጽሐፍ ነው

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Reproduced by kind permission of The Trustees of the Chester Beatty Library, Dublin

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፎቶዎቹ ወይም ሥዕሎቹ በሙሉ የተወሰዱት፦ Reproduced by kind permission of The Trustees of the Chester Beatty Library, Dublin