በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን ካልሆኑ አንዳንድ ሰዎች ጋር መጋባትን የሚከለክል ትእዛዝ ይዞ እያለ እስራኤላውያን ወንዶች በምርኮ የተያዙ የባዕድ አገር ሴቶችን እንዲያገቡ የተፈቀደላቸው ለምን ነበር?—ዘዳግም 7:1-3፤ 21:10, 11

ይህ የተፈቀደበት ምክንያት በዓይነታቸው ለየት ያሉ ሁኔታዎች ስለነበሩ ነው። ይሖዋ እስራኤላውያን በከነዓን ምድር የሚኖሩ የሰባት ብሔራትን ከተሞች እንዲያወድሙና ነዋሪዎቹን በሙሉ እንዲደመስሱ አዝዟቸው ነበር። (ዘዳግም 20:15-18) ሌሎች ብሔራትን የተመለከትን እንደሆነ ሙሉ ሰው ከሆኑት መካከል የመትረፍ አጋጣሚ የነበራቸው በምርኮ የተያዙ ወንድ ያላወቁ ልጃገረዶች ብቻ ነበሩ። (ዘኍልቁ 31:17, 18፤ ዘዳግም 20:14) አንድ እስራኤላዊ እንዲህ ዓይነት ሴት ማግባት ይችላል፤ የሚያገባት ግን አንዳንድ ሁኔታዎችን ካሟላች ብቻ ነው።

ይህች ሴት እንድታሟላ የሚጠበቁባትን ነገሮች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ጠጉሯን ትላጭ፤ ጥፍሯንም ትቁረጥ። ስትማረክ የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፤ እቤትህ ተቀምጣ ለአባትና ለእናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፣ ልትደርስባትና ባል ልትሆናት፣ እርሷም ሚስት ልትሆንህ ትችላለች።”—ዘዳግም 21:12, 13

አንድ እስራኤላዊ ሚስቱ ሊያደርጋት ፈልጎ የወሰዳት ምርኮኛ ልጃገረድ ራሷን መላጨት ነበረባት። ፀጉርን መላጨት የሐዘን ወይም የመከራ መግለጫ ነበር። (ኢሳይያስ 3:24) ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ ልጆቹንና ንብረቱን በሙሉ ካጣ በኋላ ሐዘንተኛ መሆኑን ለመግለጽ ራሱን ተላጭቷል። (ኢዮብ 1:20) ከዚህ በተጨማሪ ተማርካ የተያዘችው ሴት ጥፍር ቀለም የተቀባች ቢሆንም እንኳ እጆቿ አምረው እንዳይታዩ ‘ጥፍሯን መቆረጥ’ ነበረባት። (ዘዳግም 21:12) ይህች ሴት ማውለቅ የነበረባት ‘ስትማረክ የለበሰችው ልብስ’ ምንድን ነው? የአረማውያን ከተሞች በጠላት እጅ ሊወድቁ ሲቃረቡ በዚያ የሚኖሩ ሴቶች የክት ልብሳቸውን የመልበስ ልማድ ነበራቸው። እንዲህ የሚያደርጉት ማርከው የሚይዟቸውን ሰዎች በውበታቸው ለመማረክ ነበር። ለቅሶ የተቀመጠች ምርኮኛ እንዲህ ዓይነቱን ልብስ አውልቃ ማስቀመጥ ነበረባት።

አንድ እስራኤላዊ ሚስቱ ለማድረግ የወሰዳት ምርኮኛ ሴት በሞት ለተለዩዋት የቤተሰቧ አባላት አንድ ወር ሙሉ ማልቀስ ነበረባት። በጦርነቱ የተሸነፉት ከተሞች ላይ የሚደርሰው ጥፋት እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ይህች ሴት ቤተሰቧንም ሆነ ወዳጆቿን በሙሉ በሞት ታጣለች። የእስራኤል ወታደሮች የአማልክቷን ምስሎች አቃጥለውባት ሊሆን ስለሚችል ለአምልኮ ትጠቀምባቸው የነበሩት ዕቃዎች ተወግደዋል። ከዚህ በተጨማሪ በምርኮ የተያዘችው ሴት ሐዘን የምትቀመጥበት የአንድ ወር ጊዜ፣ በፊት ትከተለው በነበረው ሃይማኖት ውስጥ ታከብራቸው ከነበሩት ልማዶች በሙሉ በመላቀቅ ራሷን የምታነጻበት ወቅት ነው።

ይሁን እንጂ በጥቅሉ የባዕድ አገር ሴቶችን በተመለከተ ሁኔታው ከዚህ የተለየ መልክ ነበረው። በዚህ ረገድ ይሖዋ ይህን ትእዛዝ ሰጥቷል:- “ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ።” (ዘዳግም 7:3) ይህ እገዳ የተጣለበት ምክንያት ምንድን ነው? ዘዳግም 7:4 ‘እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉ ነው’ ይላል። ስለዚህ እገዳው የተጣለበት ምክንያት እስራኤላውያንን ከሃይማኖታዊ ብክለት ለመጠበቅ ነበር። ይሁን እንጂ ዘዳግም 21:10-13 ላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ አንዲት የባዕድ አገር ሴት በዚህ ረገድ የምትፈጥረው ስጋት አይኖርም። ዘመዶቿ በሙሉ ሞተዋል እንዲሁም የአማልክቷ ምስሎች ተወግደዋል። የሐሰት ሃይማኖት ተከታይ ከሆኑ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላትም። አንድ እስራኤላዊ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የምትገኝን የባዕድ አገር ሴት ማግባት ይችላል።