በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ”

“የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ”

“የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ”

“የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ።”—ኤፌሶን 6:11

1, 2. ክርስቲያኖች ሊታጠቁት የሚገባውን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ በራስህ አባባል ግለጽ።

 መጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሮም እጅግ ኃያልና ገናና ሆና ነበር። ሮም የነበራት ጠንካራ የጦር ሠራዊት በወቅቱ የሚታወቀውን አብዛኛውን የዓለም ክፍል በቁጥጥሯ ሥር ለማድረግ አስችሏታል። አንድ ታሪክ ጸሐፊ ይህን ሠራዊት በሚመለከት “በታሪክ ውስጥ ከታየው የጦር ሠራዊት ሁሉ በስኬታማነቱ አቻ የለውም” በማለት ተናግረዋል። የሮም ጦር ሠራዊት ከባድ ሥልጠና በወሰዱና በሥነ ምግባር በታነጹ ወታደሮች የተገነባ ነበር፤ ሆኖም በውጊያ ላይ የሚያገኙት ውጤት በሚታጠቁት የጦር መሣሪያ ላይም የተመካ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከዲያብሎስ ጋር የሚያደርጉትን ጦርነት በድል አድራጊነት ለመወጣት የሚስፈልጋቸውን መንፈሳዊ የጦር መሣሪያ ከሮም ወታደር የጦር ትጥቅ ጋር አመሳስሎታል።

2 ይህን መንፈሳዊ ትጥቅ በተመለከተ የሰጠው መግለጫ በኤፌሶን 6:14-17 ላይ ይገኛል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣ በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ። ከእነዚህም ሁሉ ጋር፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንን ራስ ቊር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።” ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ አንድ የሮም ወታደር ጳውሎስ የጠቀሰው ዓይነት የጦር ትጥቅ ማድረጉ ከአደጋ እንደሚጠብቀው እሙን ነው። ወታደሩ ለጨበጣ ውጊያ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የጦር መሣሪያ ይኸውም ሰይፍን ጨምሮ ይይዛል።

3. የኢየሱስ ክርስቶስን መመሪያዎች መታዘዝና ምሳሌውን መከተል የሚኖርብን ለምንድን ነው?

3 አንድ የሮም ጦር ሠራዊት ድል ማድረጉ የተመካው በታጠቀው የጦር መሣሪያና በሚያገኘው ሥልጠና ላይ ብቻ ሳይሆን ወታደሮቹ ለአዝማቻቸው በሚኖራቸው ታዛዥነትም ላይ ነው። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለሕዝቦች የጦር አዝማች’ በማለት ለሚጠራው ለኢየሱስ ክርስቶስ መታዘዝ ይኖርባቸዋል። (ኢሳይያስ 55:4) ኢየሱስ ‘የቤተ ክርስቲያንም ራስ’ ነው። (ኤፌሶን 5:23) ኢየሱስ የተሰለፍንበትን መንፈሳዊ ጦርነት በሚመለከት መመሪያዎችን የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ ትጥቃችንን እንዴት መልበስ እንደሚኖርብን የሚያሳይ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) የክርስቶስ ስብዕና ከመንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን ጋር በጣም ስለሚመሳሰል ቅዱሳን ጽሑፎች እኛም የክርስቶስን አስተሳሰብ “እንደ ዕቃ ጦር” እንድንታጠቅ ይመክሩናል። (1 ጴጥሮስ 4:1 የ1954 ትርጉም) እያንዳንዱን መንፈሳዊ የጦር መሣሪያ በምንመረምርበት ጊዜ ምን ያህል አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ለመረዳት ኢየሱስን በምሳሌነት እናነሳለን።

ወገባችንን፣ ደረታችንንና እግራችንን ከአደጋ መጠበቅ

4. አንድ ወታደር ከሚታጠቀው የጦር ትጥቅ ውስጥ ቀበቶ ምን ጥቅም አለው? ለምን ነገርስ ምሳሌ ነው?

4 ወገብን በእውነት መታጠቅ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ወታደሮች ወገባቸውን ከ5 እስከ 15 ሳንቲ ሜትር ስፋት ባለው ከቆዳ የተሠራ መታጠቂያ ወይም ቀበቶ ይታጠቁ ነበር። አንዳንድ ተርጓሚዎች ጥቅሱ “እንደ ቀበቶ ወገባችሁን በእውነት ታጠቁ” ተብሎ መተርጎም ይኖርበታል ይላሉ። ቀበቶው ወታደሩን በወገቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የሚጠብቀው ከመሆኑም በላይ ሰይፉን ለማንጠልጠል የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ይፈጥርለታል። አንድ ወታደር ወገቡን ሲታጠቅ ለፍልሚያ ዝግጁ ይሆናል። ጳውሎስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሕይወታችን ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚገባ ለማስረዳት የአንድን ወታደር ቀበቶ እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖርና አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ለእውነት ለመሟገት እውነትን ልክ እንደ ቀበቶ አጥብቀን ልንታጠቀው ይገባል። (መዝሙር 43:3፤ 1 ጴጥሮስ 3:15) ይህን ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናትና ባጠናነው ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ኢየሱስ የአምላክ ሕግ ‘በልቡ ውስጥ’ ነበር። (መዝሙር 40:8) በመሆኑም ተቃዋሚዎች ጥያቄ ሲጠይቁት ጥቅሶችን በቃሉ አስታውሶ በመጥቀስ መልስ ሊሰጣቸው ችሏል።—ማቴዎስ 19:3-6፤ 22:23-32

5. የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ፈተና ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ በሚያጋጥመን ወቅት ሊረዳን የሚችለው እንዴት እንደሆነ አስረዳ።

5 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መመሪያችን ካደረግነው ከተሳሳተ አስተሳሰብ ይጠብቀናል፤ እንዲሁም ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ያስችለናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ፈተና ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ በሚያጋጥመን ወቅት ትክክል የሆነውን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል። ታላቁን አስተማሪያችንን ይሖዋን የምናይ እንዲሁም “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚለውን ድምፅ ከበስተ ኋላችን የምንሰማ ያህል ነው።—ኢሳይያስ 30:20, 21

6. ምሳሌያዊው ልባችን መጠበቅ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ጽድቅ ምሳሌያዊ ልባችንን ከጉዳት ሊጠብቅልን የሚችለው እንዴት ነው?

6 የጽድቅ ጥሩር። አንድ ወታደር የሚለብሰው ጥሩር በጣም አስፈላጊ የሆነውን የሰውነቱን ክፍል ይኸውም ልቡን ከጉዳት ይጠብቀዋል። ምሳሌያዊው ልባችን ማለትም ውስጣዊ ማንነታችን ወደ ክፋት ያዘነበለ ስለሆነ ልዩ ጥበቃ ያስፈልገዋል። (ዘፍጥረት 8:21) በመሆኑም የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ማወቅና መውደድ ይኖርብናል። (መዝሙር 119:97, 105) ለጽድቅ ያለን ፍቅር በግልጽ የተቀመጡትን የይሖዋን መመሪያዎች ችላ እንድንል ወይም አቅልለን እንድንመለከት ከሚያደርጉን ዓለማዊ አስተሳሰቦች ይጠብቀናል። ከዚህም በላይ መልካም የሆነውን የምንወድና ክፉውን የምንጠላ ከሆነ ሕይወታችንን ሊያበላሽ የሚችል አካሄድ ከመከተል እንቆጠባለን። (መዝሙር 119:99-101፤ አሞጽ 5:15) ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስን በሚመለከት “ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ” ስለሚሉ በዚህ ረገድ ምሳሌ ይሆነናል።—ዕብራውያን 1:9 a

7. አንድ ሮማዊ ወታደር ጥሩ ጫማ የሚያስፈልገው ለምን ነበር? ጫማ መጫማት የምን ምሳሌ ነው?

7 የሰላምን ወንጌል የተጫሙ እግሮች። የሮም ወታደሮች ለግዳጅ በሚወጡበት ጊዜ 27 ኪሎ ግራም የሚመዝን የጦር መሣሪያና ዕቃ ተሸክመው ብዙውን ጊዜ በየዕለቱ 30 ኪሎ ሜትር ስለሚጓዙ ጠንካራ ጫማ ያስፈልጋቸዋል። ጳውሎስ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት ለመስበክ የተዘጋጀን መሆናችንን ጫማ ከመጫማት ጋር አመሳስሎ መግለጹ ተገቢ ነው። ለመስበክ ዝግጁ ወይም ፈቃደኛ መሆናችን አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እንደዚያ ካልሆንን ሰዎች እንዴት ይሖዋን ሊያውቁ ይችላሉ?—ሮሜ 10:13-15

8. የምሥራቹ ሰባኪ በመሆን ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሰጠው ሥራ ምን ነበር? ለሮማዊው አገረ ገዥ ለጳንጥዮስ ጲላጦስ ‘ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው’ ብሎት ነበር። ኢየሱስ ሰሚ ጆሮ ባገኘበት ቦታ ሁሉ ምሥራቹን ይሰብክ የነበረ ከመሆኑም በላይ አገልግሎቱን በጣም ይወድ ስለነበር ከሥጋዊ ፍላጎቶቹ የበለጠ ቦታ ይሰጠው ነበር። (ዮሐንስ 4:5-34፤ 18:37) እኛም እንደ ኢየሱስ ምሥራቹን ለመስበክ የምንጓጓ ከሆነ ለሌሎች ለመናገር የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን እንፈልጋለን። ከዚህም በላይ አገልግሎታችንን በትጋት ማከናወናችን በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነን እንድንኖር ይረዳናል።—የሐዋርያት ሥራ 18:5

ጋሻ፣ የራስ ቁርና ሰይፍ

9. አንድ የሮማ ወታደር ትልቅ ጋሻ መያዙ ምን ጥቅም አለው?

9 ትልቅ የእምነት ጋሻ። “ጋሻ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አብዛኛውን የሰውነት ክፍል መከለል የሚችልን ትልቅ ጋሻ ያመለክታል። እንዲህ ያለው ጋሻ አንድን ሰው በኤፌሶን 6:16 ላይ እንደተጠቀሰው ካለ ‘የሚንበለበል ፍላጻ’ ይጠብቀዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ወታደሮች ናፍጣ የያዙ አነስተኛ የብረት ዕቃዎች የተገጠሙባቸው ትንንሽ የመቃ ቀስቶችን ይጠቀሙ ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እነዚህን ቀስቶች በሚመለከት “በጥንት ዘመን ጥቅም ላይ ይውሉ ከነበሩ በጣም አደገኛ የጦር መሣሪያዎች መካከል አንዱ ነው” በማለት ተናግረዋል። አንድ ወታደር እንዲህ ካሉት ተወንጫፊ መሣሪያዎች ራሱን የሚከላከልበት ትልቅ ጋሻ ከሌለው ከባድ ጉዳት ሊደርስበት አልፎ ተርፎም ሕይወቱን ሊያጣ ይችላል።

10, 11. (ሀ) እምነታችንን ሊሸረሽሩ የሚችሉት የሰይጣን ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ የትኞቹ ናቸው? (ለ) የኢየሱስ ምሳሌ እምነት በመከራ ጊዜ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

10 ሰይጣን እምነታችንን ለማዳከም የሚጠቀምባቸው ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ ምንድን ናቸው? በቤተሰብ፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ስደት ወይም ተቃውሞ ይቆሰቁስብን ይሆናል። በተጨማሪም ቁሳዊ ሀብት የማካበት ፍላጎትና የጾታ ብልግና ማባበያዎች አንዳንዶችን መንፈሳዊ አደጋ ላይ ጥለዋቸዋል። እንዲህ ካለው አደጋ ራሳችንን ለመጠበቅ ከምንም በላይ ትልቁን ‘የእምነት ጋሻ ማንሳት’ ይኖርብናል። እምነት የሚገኘው ስለ ይሖዋ በመማር፣ ዘወትር ከእርሱ ጋር በጸሎት በመገናኘትና እርሱ እንዴት እንደሚጠብቀንና እንደሚባርከን በመገንዘብ ነው።—ኢያሱ 23:14፤ ሉቃስ 17:5፤ ሮሜ 10:17

11 ኢየሱስ ምድር ሳለ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ጠንካራ እምነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተግባር አሳይቷል። በአባቱ ውሳኔ ላይ ሙሉ በሙሉ ይተማመን የነበረ ከመሆኑም በላይ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ደስ ያሰኘው ነበር። (ማቴዎስ 26:42, 53, 54፤ ዮሐንስ 6:38) ኢየሱስ በጌተሰማኒ የአትክልት ቦታ በጣም ተጨንቆ በነበረ ጊዜም እንኳ “እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” በማለት ወደ አባቱ ጸልዮአል። (ማቴዎስ 26:39) ታማኝነቱን በመጠበቅ የአባቱን ልብ ደስ ማሰኘቱ አስፈላጊ መሆኑን ፈጽሞ አልዘነጋም። (ምሳሌ 27:11) እኛም በተመሳሳይ በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ትችት ወይም ተቃውሞ እምነታችንን እንዲያዳክምብን አንፈቅድም። እንዲያውም በአምላክ የምንታመን፣ እርሱን የምናፈቅርና ትእዛዛቱን የምንጠብቅ ከሆነ እምነታችን ይበልጥ ይጠናከራል። (መዝሙር 19:7-11፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ይሖዋ ለሚያፈቅሩት ሰዎች ካዘጋጀው በረከት ጋር ሊወዳደር የሚችል አንዳች ቁሳዊ ሀብት ወይም ቅጽበታዊ ደስታ የለም።—ምሳሌ 10:22

12. ምሳሌያዊው የራስ ቁር በጣም አስፈላጊ የሆነውን የትኛውን የሰውነታችንን ክፍል ይጠብቅልናል? ይህስ በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

12 የመዳን ራስ ቁር። አንድ ወታደር የሚያደርገው ራስ ቁር የእውቀት ማዕከል የሆነውን ራሱንና አንጎሉን ከአደጋ ይጠብቅለታል። ክርስቲያናዊ ተስፋችን አእምሯችንን ከአደጋ ስለሚጠብቅልን ከራስ ቁር ጋር ተመሳስሏል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) ከአምላክ ቃል በሚገኘው ትክክለኛ እውቀት አእምሯችን የታደሰ ቢሆንም እንኳ አሁንም ደካማና ፍጽምና የሚጎድለን ሰዎች ነን። አእምሯችን በቀላሉ ሊበከል ይችላል። ይህ ዓለም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ግቦች ሐሳባችንን ሊከፋፍሉብን አልፎ ተርፎም አምላክ የሰጠንን ተስፋ ችላ ብለን በእነሱ ላይ እንድናተኩር ሊያደርጉን ይችላሉ። (ሮሜ 7:18፤ 12:2) ዲያብሎስ ለኢየሱስ ‘የዓለምን መንግሥታት ከነክብራቸው’ አሳይቶ የትኩረት አቅጣጫውን ለማሳት ከንቱ ሙከራ አድርጓል። (ማቴዎስ 4:8) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ግብዣውን ያለ አንዳች ማመንታት ተቃውሟል። ጳውሎስ ኢየሱስን በሚመለከት “እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል” ብሏል።—ዕብራውያን 12:2

13. በተሰጠን ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ በአምላክ ላይ ይተማመን የነበረው እንዲያው በደመ ነፍስ አልነበረም። በወደፊቱ ተስፋችን ላይ ከማተኮር ይልቅ አእምሯችንን በዚህ ሥርዓት ሕልሞችና ግቦች የምንሞላ ከሆነ አምላክ ቃል በገባልን ነገሮች ላይ ያለን እምነት እየተዳከመ ይሄዳል። ውሎ አድሮ ተስፋችንን ጨርሶ ልናጣ እንችላለን። በሌላ በኩል ዘወትር አምላክ በሰጠን ተስፋዎች ላይ የምናሰላስል ከሆነ በተስፋው ደስ እንሰኛለን።—ሮሜ 12:12

14, 15. (ሀ) ምሳሌያዊው ሰይፋችን ምንድን ነው? እንዴትስ ልንጠቀምበት እንችላለን? (ለ) የመንፈስ ሰይፍ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

14 የመንፈስ ሰይፍ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የአምላክ ቃል ወይም መልእክት በሁለቱም በኩል እንደተሳለ ሰይፍ ሲሆን የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ለማስወገድና ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች መንፈሳዊ ነጻነት እንዲያገኙ ለመርዳት ያገለግላል። (ዮሐንስ 8:32፤ ዕብራውያን 4:12) በተጨማሪም ይህ መንፈሳዊ ሰይፍ ፈተናዎች የሚያደርሱብንን ተጽዕኖ ወይም እምነታችንን ለማጥፋት የሚሞክሩ ከሃዲዎች የሚሰነዝሩብንን ጥቃት ለመቋቋምና ለመከላከል ያገለግለናል። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) ‘ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ እንድንሆን የሚረዱ የአምላክ መንፈስ ያለባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት’ ስላሉን በጣም አመስጋኞች ነን!—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

15 ኢየሱስ በምድረ በዳ በሰይጣን በተፈተነበት ወቅት የተሳሳተ አስተሳሰብንና ተንኮል የተሞላባቸውን ፈተናዎችን ለመመከት በዚህ የመንፈስ ሰይፍ ተጠቅሟል። ሰይጣን ለሰነዘረው ለእያንዳንዱ ፈተና “ተብሎ ተጽፎአል” የሚል መልስ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 4:1-11) በስፔይን የሚኖር ዴቪድ የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክርም በተመሳሳይ ቅዱሳን ጽሑፎች ፈተናዎችን ለመቋቋም እንደረዱት ተናግሯል። የ19 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት በአንድ የጽዳት ኩባንያ ውስጥ አብራው የምትሠራ አንዲት ቆንጆ ወጣት “ለምን አብረን አንዝናናም?” የሚል ግብዣ አቅርባለት ነበር። ዴቪድ ግብዣዋን ያልተቀበለ ከመሆኑም በላይ ዳግም እንዲህ ያለ ጥያቄ እንዳይነሳበት ሲል አለቃውን ወደ ሌላ ክፍል እንዲያዛውረው ጠየቀ። ዴቪድ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ዮሴፍ የወሰደው እርምጃ ትዝ አለኝ። ዮሴፍ የጾታ ብልግና ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልነበረ ከመሆኑም በላይ ከአካባቢው ሸሽቷል። እኔም ተመሳሳይ እርምጃ ወስጃለሁ።”—ዘፍጥረት 39:10-12

16. ‘የአምላክን ቃል በትክክል ለመጠቀም’ ልምምድ የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ አብራራ።

16 በተጨማሪም ኢየሱስ የመንፈስን ሰይፍ ሰዎችን ከሰይጣን መዳፍ እንዲላቀቁ ለመርዳት ተጠቅሞበታል። “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) የኢየሱስን የማስተማር ችሎታ ለመኮረጅ ሥልጠና ያስፈልገናል። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ የሮም ወታደሮችን በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ወታደር ልክ በጦርነት ላይ እንዳለ አድርጎ ራሱን በመቁጠር በከፍተኛ ትጋት በየዕለቱ ይለማመድ ነበር፤ በጦርነት ላይ የሚያጋጥሟቸውን ውጣ ወረዶች በቀላሉ የሚወጡት ለዚህ ነበር።” እኛም በመንፈሳዊ ጦርነታችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ይኖርብናል። ከዚህም በላይ ‘እንደማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚጠቀም የተመሠከረለት ሠራተኛ፣ ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብ መትጋት’ ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በቅንነት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ቅዱሳን ጽሑፎችን መጠቀማችን ይህ ነው የማይባል ደስታ ያስገኝልናል!

በማንኛውም ሁኔታ ጸልዩ

17, 18. (ሀ) የሰይጣንን ጥቃት ለመቋቋም ጸሎት ምን ሚና ይጫወታል? (ለ) የጸሎትን ጥቅም የሚያስረዳ አንድ ምሳሌ ተናገር።

17 ጳውሎስ የተሟሉ መሣሪያዎችን ስለያዘው መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ከገለጸ በኋላ አንድ አስፈላጊ ምክር አክሎ ተናግሯል። ክርስቲያኖች የሰይጣንን ጥቃት ለመቋቋም ‘ሁሉንም ዐይነት ጸሎትና ልመና’ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ምን ያህል ጊዜ? ጳውሎስ “በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 6:18) ፈተናዎች፣ ችግሮች ወይም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ጸሎት በእጅጉ ሊያበረታን ይችላል። (ማቴዎስ 26:41) ኢየሱስ “ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋር አቀረበ፤ ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት።”—ዕብራውያን 5:7

18 በጠና የታመመ ባሏን ለ15 ዓመታት ያስታመመች ሚላግሮስ የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ትላለች፦ “የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ማንም ቢሆን የእርሱን ያህል ሊረዳኝ አይችልም። እርግጥ ነው፣ ‘አሁንስ ከአቅሜ በላይ ነው’ ያልኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ ኃይሌ ሲታደስና መንፈሴ ሲነቃቃ ይሰማኛል።”

19, 20. ከሰይጣን ጋር ያለብንን ውጊያ በድል አድራጊነት ለመወጣት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 ዲያብሎስ በጣም ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስለሚያውቅ እኛን ለማሸነፍ የሚያደርገውን ጥረት አፋፍሞ ቀጥሏል። (ራእይ 12:12, 17) ይህን ኃይለኛ ባላጋራ መቋቋም ብሎም ‘መልካሙን የእምነት ገድል መጋደል’ ይኖርብናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12) እንዲህ ለማድረግ እጅግ ታላቅ ኃይል እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:7) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታም ስለሚያስፈልገን አምላክን መለመን ይኖርብናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”—ሉቃስ 11:13

20 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ የሚሰጠውን የተሟላ የጦር ትጥቅ መልበሳችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ መልበስ እምነትንና ጽድቅን የመሳሰሉ አምላካዊ ባሕርያትን ማዳበር ይጠይቅብናል። እንዲሁም እውነትን እንድንወደውና እንደ ቀበቶ እንድንታጠቀው፣ በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን ለመስበክ ዝግጁዎች እንድንሆንና ተስፋችንን አቅርበን እንድንመለከት ይጠይቅብናል። የመንፈስን ሰይፍ የመጠቀም ችሎታችንን ማዳበር ይኖርብናል። የአምላክን ሙሉ የጦር ዕቃ በመልበስ ከርኩሳን መንፈሳዊ ሰራዊት ጋር ያለብንን ትግል በድል አድራጊነት መወጣትና የይሖዋን ቅዱስ ስም ማስከበር እንችላለን።—ሮሜ 8:37-39

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ ይሖዋ ራሱ ‘ጽድቅን እንደ ጥሩር’ እንደታጠቀ ተደርጎ ተገልጿል። በመሆኑም የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ፍትሕንና ጽድቅን እንዲያንጸባርቁ ይጠብቅባቸዋል።—ኢሳይያስ 59:14, 15, 17

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• መንፈሳዊውን የጦር ትጥቅ በመልበስ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን ማን ነው? የእርሱን ምሳሌ በጥንቃቄ መመርመር የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?

• አእምሯችንንና ምሳሌያዊ ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• የመንፈስን ሰይፍ የመጠቀም ችሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

• በማንኛውም ሁኔታ ሥር የመጸለይ ልማድ ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት ምሥራቹን በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንድንሰብክ ይገፋፋናል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስተማማኝ የሆነው ተስፋችን የሚደርሱብንን ፈተናዎች እንድንቋቋም ይረዳናል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎት ላይ ‘የመንፈስን ሰይፍ’ ትጠቀማለህ?