በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘዳግም መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የዘዳግም መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የዘዳግም መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

ጊዜው 1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፃውያን የባርነት ቀንበር ካላቀቃቸው እነሆ አርባ ዓመታት ተቆጥረዋል። እስራኤላውያን እነዚህን ሁሉ ዓመታት በምድረ በዳ ካሳለፉም በኋላ እንኳ የራሳቸው አገር የሌላቸው ሕዝብ ናቸው። አሁን ግን የተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ደርሰዋል። ምድሪቱን አንድ በአንድ እየተቆጣጠሩ ሲሄዱ ምን ያጋጥማቸው ይሆን? ምን ችግሮች ይደቀኑባቸዋል? ችግሮቹንስ መወጣት የሚኖርባቸው እንዴት ነው?

እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ከነዓን ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ታላቅ ሥራ አዘጋጃቸው። እንዴት? ማበረታቻና ማነቃቂያ፣ ምክርና ማስጠንቀቂያ የያዙ ተከታታይ ንግግሮች በማቅረብ ነው። ይሖዋ አምላክን ብቻ ማምለክ እንደሚገባቸውና በዙሪያቸው ያሉ ብሔራትን መከተል እንደሌለባቸው እስራኤላውያንን አሳሰባቸው። የዘዳግም መጽሐፍ አብዛኛው ክፍል እነዚህን ንግግሮች የያዘ ነው። እኛም የምንኖርበት ዓለም ለይሖዋ ፍጹም አምልኮ እንዳናቀርብ ብዙ መሰናክሎች ስለሚደቅንብን ንግግሮቹ የያዟቸው ምክሮች በጣም ይጠቅሙናል።—ዕብራውያን 4:12

ከመጨረሻው ምዕራፍ በስተቀር በሙሴ የተጻፈው ይህ የዘዳግም መጽሐፍ የሚሸፍነው የጊዜ ርዝመት ከሁለት ወር ብዙም አይበልጥም። a (ዘዳግም 1:3፤ ኢያሱ 4:19) መጽሐፉ የያዘው ምክር ይሖዋ አምላክን በሙሉ ልባችን እንድንወድና በታማኝነት እንድናገለግለው እንዴት እንደሚረዳን እስቲ እንመልከት።

“ዐይኖቻችሁ ያዩዋቸውን ነገሮች እንዳትረሱ”

(ዘዳግም 1:1–4:49)

ሙሴ በመጀመሪያው ንግግሩ ላይ በምድረ በዳ ጉዟቸው ያጋጠሟቸውን አንዳንድ ነገሮች በተለይ ደግሞ እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ለመውረስ ለሚያደርጉት ዝግጅት ይበልጥ የሚጠቅሟቸውን ነገሮች ተርኮላቸዋል። ዳኞች ስለ መሾማቸው የሚገልጸው ዘገባ ይሖዋ ሕዝቦቹ ፍቅራዊ እንክብካቤ ማግኘት በሚችሉበት መንገድ እንደሚያደራጃቸው ሳያስገነዝባቸው አልቀርም። ከዚህ በተጨማሪ ሙሴ አሥሩ ሰላዮች ያቀረቡት መጥፎ ሪፖርት የፊተኛው ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ እንቅፋት እንደሆነበት ገለጸላቸው። ተስፋይቱን ምድር ከፊት ለፊታቸው እያዩ ሙሴ የሚነግራቸውን ይህን ማስጠንቀቂያ የያዘ ምሳሌ ሲያዳምጡ ምን ዓይነት ስሜት አሳድሮባቸው እንደሚሆን አስብ።

የዮርዳኖስን ወንዝ ከመሻገራቸው በፊት ይሖዋ ያቀዳጃቸውን ድሎች ማስታወሳቸው ከወንዙ ባሻገር ያሉትን ብሔራት ድል እያደረጉ ለመያዝ በተዘጋጁበት በዚህ ወቅት የድፍረት ስሜት ሳያሳድርባቸው አይቀርም። የሚወርሱት ምድር በጣዖት አምልኮ የተጥለቀለቀ በመሆኑ ሙሴ ጣዖት አምልኮን በተመለከተ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ እጅግ ተገቢ ነው!

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

2:4-6, 9, 19, 24, 31-35፤ 3:1-6—እስራኤላውያን ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩትን አንዳንድ ሕዝቦች ሲደመስሱ ሌሎቹን ያላጠፉት ለምን ነበር? ይሖዋ እስራኤላውያን ከዔሳው ልጆች ጋር ጦርነት እንዳይገጥሙ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። ለምን? የያዕቆብ ወንድም ዝርያዎች ስለሆኑ ነው። ሞዓባውያንና አሞናውያን ደግሞ የአብርሃም ወንድም ልጅ የሎጥ ዝርያዎች በመሆናቸው እስራኤላውያን በእነርሱ ላይ ጥቃት መሰንዘር ወይም ጦርነት ማወጅ አልነበረባቸውም። ይሁን እንጂ አሞራውያን ነገሥታት የሆኑት ሴዎንና ዐግ ከእስራኤላውያን ጋር የሥጋ ዝምድና ስለሌላቸው ምድሩ የእኛ ነው ሊሉ አይችሉም። በመሆኑም ሴዎን እስራኤላውያን በከተማው እንዳያልፉ በመከልከሉና ዐግ ደግሞ እነርሱን ለመዋጋት በመነሳቱ ይሖዋ ከተሞቻቸውን እንዲደመስሱና አንድም ሰው እንዳያስተርፉ እስራኤላውያንን አዘዛቸው።

4:15-20, 23, 24—ምስል መሥራት የተከለከለ መሆኑ የአንዳንድ ዕቃዎችን ምስል ሠርቶ በጌጥ መልክ መጠቀም ስህተት ነው ማለት ነው? አይደለም። ሕጉ የሚከለክለው ምስሎችን ለአምልኮ መሥራትን ይኸውም ለምስል ‘መስገድንና አምልኮ ማቅረብን’ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች በጌጣ ጌጥነት የሚያገለግሉ የአንዳንድ ነገሮችን ምስል መቅረጽ ወይም መሳል አይከለክሉም።—1 ነገሥት 7:18, 25

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:2, 19 “በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ [አሥርቱ ትእዛዛት በተሰጡበት በሲና ተራራ አካባቢ የሚገኝ ተራራማ ክልል] እስከ ቃዴስ በርኔ ዐሥራ አንድ ቀን” ብቻ የሚፈጅ ቢሆንም እስራኤላውያን ለ38 ዓመታት ያህል በምድረ በዳ ተንከራትተዋል። በእርግጥም፣ በይሖዋ አምላክ ላይ ማመጻቸው ከባድ መዘዝ አስከትሎባቸዋል!—ዘኍልቁ 14:26-34

1:16, 17 አምላክ ፍርድ የሚሰጥበት መሥፈርት ዛሬም አልተለወጠም። በፍርድ ኮሚቴ ውስጥ ገብተው እንዲያገለግሉ ኃላፊነት የሚጣልባቸው ወንድሞች ወገናዊነት ወይም ሰውን መፍራት የሚሰጡትን ውሳኔ እንዲያዛባባቸው መፍቀድ የለባቸውም።

4:9 እስራኤላውያን ሕይወታቸው የተሳካ እንዲሆን ‘ዐይኖቻቸው ያዩዋቸውን ነገሮች እንዳይረሱ’ መጠንቀቃቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። ቃል የተገባልን አዲሱ ዓለም እየቀረበ ሲመጣ እኛም ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመሆን ይሖዋ ባከናወናቸው አስደናቂ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል።

ይሖዋን ውደዱ፤ ትእዛዛቱንም አክብሩ

(ዘዳግም 5:1–26:19)

ሙሴ በሁለተኛው ንግግሩ ላይ በሲና ተራራ ሕጉ የተሰጠበትን ሁኔታ በዝርዝር የገለጸ ከመሆኑም ሌላ አሥርቱን ትእዛዛት በድጋሚ ጠቅሷል። ፈጽሞ መደምሰስ ያለባቸውን ሰባት ብሔራት በስም ጠቅሷል። እስራኤላውያን በምድረ በዳ የተማሩትን አንድ ዐቢይ ጉዳይ ይኸውም “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር” አስታውሷቸዋል። እስራኤላውያን አዲስ ሕይወት በሚጀምሩበት ጊዜ ‘ትእዛዞችን ሁሉ መጠበቅ’ ይኖርባቸዋል።—ዘዳግም 8:3፤ 11:8

እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ውስጥ ተደላድለው መኖር ከጀመሩ በኋላ አምልኮን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን ፍርድን፣ መስተዳድርን፣ ውጊያን እንዲሁም የየዕለቱን ማኅበራዊ ኑሮንም ሆነ የግል ሕይወትን የሚመለከቱ ሕጎች ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ሙሴ እነዚህን ሕጎች የከለሰላቸው ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን የመውደድንና ትእዛዛቱን የማክበርን አስፈላጊነት አበክሮ ገልጾላቸዋል።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

8:3, 4—እስራኤላውያን በምድረ በዳ በተጓዙበት ወቅት ልብሳቸው አላረጀም እግራቸውም አላበጠም ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? በየዕለቱ እንደሚሰጣቸው መና ሁሉ ይህም ተአምራዊ ዝግጅት ነበር። እስራኤላውያን ጉዞ በጀመሩበት ወቅት አድርገውት የነበሩትን ያንኑ ጫማና ልብስ ተጠቅመዋል። ይህም በዕድሜ የገፉት ሲሞቱ ልጆቻቸው አድገው ልብስና ጫማውን በመውረሳቸው ሊሆን ይችላል። በጉዟቸው መጀመሪያና በምድረ በዳ ጉዞው ማብቂያ ላይ የተካሄደው የሕዝብ ቆጠራ እንደሚያሳየው እስራኤላውያን በቁጥር ስላልጨመሩ መጀመሪያ ላይ የነበሩት ልብሶችና ጫማዎች ለሁሉም ሊዳረሱ ይችላሉ።—ዘኍልቁ 2:32፤ 26:51

14:21—እስራኤላውያን እነርሱ ራሳቸው የማይበሉትን ደሙ ሳይፈስስ የሞተ እንስሳ በአገራቸው ለሚኖር መጻተኛ እንዲሰጡ ወይም ለውጭ አገር ዜጋ እንዲሸጡ የተፈቀደላቸው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መጻተኛ” የሚለው ቃል የአይሁድን እምነት የተቀበለ እስራኤላዊ ያልሆነን ሰው ወይም የይሖዋ አምላኪ ባይሆንም መሠረታዊ የሆኑትን ሕጎች የሚያከብርን ሰፋሪ ሊያመለክት ይችላል። የአይሁድን እምነት ያልተቀበሉ የውጭ አገር ዜጎችና መጻተኞች በሕጉ ሥር ስላልሆኑ ደሙ ሳይፈስ የሞተን እንስሳ በልዩ ልዩ መንገዶች ሊጠቀሙ ይችላሉ። እስራኤላውያን በዚህ መልክ የሞተን እንስሳ ለእነርሱ እንዲሰጡ ወይም እንዲሸጡ ተፈቅዶላቸዋል። በሌላ በኩል ግን የአይሁድን እምነት የተቀበለ ሰው የቃል ኪዳኑን ሕግ የማክበር ግዴታ ነበረበት። ዘሌዋውያን 17:10 ላይ እንደተገለጸው እንዲህ ዓይነቱ ሰው የእንስሳ ደም እንዳይበላ ተከልክሏል።

24:6—“ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም እንኳ ቢሆን፣ የብድር መያዣ” አድርጎ መውሰድ “የሰውን ነፍስ” መያዣ አድርጎ እንደመውሰድ የተቆጠረው ለምንድን ነው? ወፍጮና መጅ የአንድን ሰው “ነፍስ” በሌላ አባባል መተዳደሪያውን ያመለክት ነበር። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዱን መውሰድ መላው ቤተሰብ የዕለት ጉርስ እንዳያገኝ ያደርጋል።

25:9—የወንድሙን ሚስት ለማግባት የማይፈልግ ሰው ጫማው ከእግሩ ላይ መውለቁና ፊቱ ላይ መተፋቱ ምን ትርጉም ነበረው? “በጥንት ዘመን በእስራኤል የመቤዠት . . . ጉዳይ የሚጸናው አንዱ ወገን ጫማውን አውልቆ ለሌላው ወገን ሲሰጠው ነው።” (ሩት 4:7) የወንድሙን ሚስት ለማግባት ፈቃደኛ ያልሆነን ሰው ጫማ ማውለቅ ለሟች ወንድሙ ዘር ለመተካት ያለውን አጋጣሚና መብት ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነበር። ይህ ደግሞ በጣም አሳፋሪ ጉዳይ ነው። (ዘዳግም 25:10) ፊት ላይ መትፋት ለማዋረድ ተብሎ የሚደረግ ነገር ነው።—ዘኍልቁ 12:14

ምን ትምህርት እናገኛለን?

6:6-9 እስራኤላውያን ሕጉን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ታዝዘው እንደነበረ ሁሉ እኛም የአምላክን ትእዛዛት በሚገባ ማወቅ፣ ምንጊዜም በአእምሯችን መያዝና በልጆቻችን አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ ይኖርብናል። እጆቻችን የምናደርጋቸውን ነገሮች ስለሚወክሉ ሕጎቹን ‘በእጃችን ላይ ምልክት አድርገን በማሰር’ ለይሖዋ ታዛዥ መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናል። እንዲሁም ‘በግንባራችን ላይ መሆናቸው’ ታዛዥነታችን ለሰው ሁሉ በግልጽ የሚታይ መሆን እንዳለበት ያሳያል።

6:16 እምነት የለሾቹ እስራኤላውያን በማሳህ ውኃ አጣን ብለው በማጉረምረም ይሖዋን እንደተፈታተኑት ይሖዋን ፈጽሞ አንፈታተን።—ዘፀአት 17:1-7

8:11-18 ፍቅረ ነዋይ ይሖዋን እንድንረሳ ሊያደርገን ይችላል።

9:4-6 በራሳችን ጽድቅ ከመመካት መቆጠብ ይኖርብናል።

13:6 ማንኛውም ሰው ከይሖዋ አምልኮ እንዲያርቀን መፍቀድ የለብንም።

14:1 ሰውነትን መቦጨቅ ለአካላችን አድናቆት እንደሌለን የሚያሳይ ስለሆነና ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ግንኙነት ሊኖረው ስለሚችል መቅረት ያለበት ልማድ ነው። (1 ነገሥት 18:25-28) የትንሣኤ ተስፋ ስላለን ሰው ቢሞትብን እንኳ እንዲህ ያለ ቅጥ ያጣ የሐዘን መግለጫ ማሳየቱ ተገቢ አይሆንም።

20:5-7፤ 24:5 መከናወን ያለበት አንገብጋቢ ሥራ ቢኖርም ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ አስተያየት ማድረግ አስፈላጊ ነው።

22:23-27 አንዲት ሴት ተገድዶ የመደፈር አደጋ ሲደቀንባት ራሷን ለማዳን ማድረግ የምትችለው ከሁሉ የተሻለው ነገር መጮህ ነው።

“ሕይወትን ምረጥ”

(ዘዳግም 27:1—34:12)

ሙሴ ባቀረበው ሦስተኛ ንግግር ላይ እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ ሕጉን በትልልቅ ድንጋዮች ላይ እንዲጽፉ እንዲሁም አለመታዘዝ የሚያስከትላቸውን እርግማኖችና ታዛዥነት የሚያስገኛቸውን በረከቶች እንዲናገሩ አዟቸው ነበር። አራተኛው ንግግር የሚጀምረው ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የተጋባው ቃል ኪዳን መታደሱን በሚገልጹ ቃላት ነው። በዚህ ጊዜም ቢሆን ሙሴ በይሖዋ ላይ እንዳያምጹ ያስጠነቀቃቸው ከመሆኑም ሌላ ‘ሕይወትን እንዲመርጡ’ አበረታቷቸዋል።—ዘዳግም 30:19

ሙሴ አራቱን ንግግሮች ከማቅረቡም በተጨማሪ የተደረገውን የአመራር ለውጥ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል። በተጨማሪም ይሖዋን ከፍ ከፍ የሚያደርግና ታማኝነት ማጉደል የሚያስከትለውን መከራ የሚያጎላ አንድ ግሩም መዝሙር አስተምሯቸዋል። ሙሴ የእስራኤልን ነገዶች ከባረከ በኋላ በ120 ዓመቱ ሞቶ ተቀበረ። የለቅሶው ጊዜ የቆየው ለ30 ቀናት ሲሆን ይህም የዘዳግም መጽሐፍ የሚሸፍነውን ግማሽ ያህሉን ጊዜ ይይዛል።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

32:13, 14 (የ1954 ትርጉም)እስራኤላውያን ስብ እንዳይበሉ ተከልክለው ስለነበር ‘የጠቦት ስብ’ መብላታቸው ምን ያመለክታል? እዚህ ላይ ቃሉ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተሠራበት ሲሆን ከመንጋው ውስጥ ምርጥ የሆኑትን ያመለክታል። ይህ አነጋገር ቅኔያዊ መሆኑን እዚያው ጥቅስ ላይ ‘የወይን ደም’ ከሚለው አባባል መረዳት ይቻላል።

33:1-29—ሙሴ የእስራኤልን ነገዶች ሲባርክ ስምዖንን ያልጠቀሰው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት ስምዖንም ሆነ ሌዊ “እጅግ አስፈሪ የሆነ” እርምጃ በመውሰዳቸውና ንዴታቸው “ጭከና የተሞላ” በመሆኑ ነው። (ዘፍጥረት 34:13-31፤ 49:5-7) ያገኙት ውርስ ለሌሎቹ ነገዶች የተሰጠውን ያህል አያክልም ነበር። ሌዊ ያገኘው 48 ከተሞችን ሲሆን የስምዖን ድርሻ ደግሞ የሚገኘው በይሁዳ ግዛት ውስጥ ነው። (ኢያሱ 19:9፤ 21:41, 42) በመሆኑም ሙሴ ስምዖንን በስም ጠቅሶ አልባረከውም። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በአጠቃላይ ሲባረኩ ስምዖንም በዚያ አጋጣሚ ተባርኳል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

31:12 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ልጆች ከትልልቆች ጋር አንድ ላይ ተቀምጠው ለማዳመጥና ለመማር ጥረት ማድረግ አለባቸው።

32:4 ይሖዋ ፍትሑን፣ ጥበቡን፣ ፍቅሩንና ኃይሉን የሚገልጠው ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስለሆነ ሥራዎቹ ሁሉ እንከን የለሽ ናቸው።

ከዘዳግም መጽሐፍ የምናገኘው ጥቅም

የዘዳግም መጽሐፍ ይሖዋን “አንድ ይሖዋ” በማለት ይገልጸዋል። (ዘዳግም 6:4 NW) ዘዳግም ከአምላክ ጋር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዝምድና ስለነበራቸው ሕዝቦች የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የዘዳግም መጽሐፍ ከጣዖት አምልኮ የመራቅንና እውነተኛውን አምላክ ብቻ የማምለክን አስፈላጊነት አበክሮ ይገልጻል።

በእርግጥም የዘዳግም መጽሐፍ ከፍተኛ ጥቅም ይዞልናል! በሕጉ ሥር ባንሆንም እንኳ ‘አምላካችንን ይሖዋን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ኀይላችን እንድንወድ’ የሚያስችል ከፍተኛ ትምህርት እናገኝበታለን።—ዘዳግም 6:5

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስለ ሙሴ ሞት የሚዘግበውን የመጨረሻውን ምዕራፍ የጻፈው ኢያሱ ወይም ሊቀ ካህኑ አልዓዛር ሳይሆን አይቀርም።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሴይር

ቃዴስ በርኔ

ሲና ተራራ (ኮሬብ)

ቀይ ባሕር

[ምንጭ]

Based on maps copyrighted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዘዳግም መጽሐፍ በአብዛኛው የያዘው ሙሴ ያቀረባቸውን ንግግሮች ነው

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ሕዝቡን መና መመገቡ ምን ትምህርት ይዟል?

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወፍጮን ወይም መጁን የብድር መያዣ አድርጎ መውሰድ “የሰውን ነፍስ” መያዣ አድርጎ እንደመውሰድ ተቆጥሯል