በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጉ’

‘ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጉ’

‘ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጉ’

ደማስቆ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የበለጸገች ከተማ ነበረች። በፍራፍሬ ዛፎች የተከበበች በመሆኗ ከበስተ ምሥራቅ ለሚመጡ የግመል ቅፍለቶች ጥሩ የማረፊያ ቦታ ሆና ታገለግል ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በደማስቆ የክርስቲያን ጉባኤ ተመሠረተ። ከጉባኤው አባላት መካከል አንዳንዶቹ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢየሩሳሌም በተከበረው የጴንጠቆስጤ በዓል ላይ ክርስትናን የተቀበሉ አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይቀሩም። (የሐዋርያት ሥራ 2:5, 41) አንዳንድ በይሁዳ የሚኖሩ ደቀ መዛሙርትም እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ ከተገደለ በኋላ ስደት ሲነሳ ወደ ደማስቆ ሄደው ሊሆን ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 8:1

በ34 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሐናንያ የተባለ አንድ በደማስቆ የሚኖር ክርስቲያን እንግዳ የሆነ ተልእኮ ተሰጠው። ጌታ ኢየሱስ “ተነሣና ‘ቀጥተኛ ጎዳና’ በተባለው መንገድ ይሁዳ ወደተባለ ሰው ቤት ሂድ፤ እዚያም ሳውል የሚባል አንድ የጠርሴስ ሰው እየጸለየ ነውና ፈልገው” ብሎ ላከው።—የሐዋርያት ሥራ 9:11

ቀጥተኛ ጎዳና ተብሎ የሚጠራው መንገድ 1 ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርዝመት ሲኖረው ደማስቆን መሃል ለመሃል ሰንጥቆ ያልፋል። በዚህ ገጽ ላይ ያለው የ19ኛው መቶ ዘመን ምስል ይህ መንገድ በጥንት ጊዜ ምን ይመስል እንደነበር ፍንጭ ይሰጠናል። ከመንገዱ አሠራር የተነሳ ሐናንያ የይሁዳን ቤት ለማግኘት የተወሰነ ፍለጋ ማድረግ ሳይጠይቅበት አልቀረም። ሆኖም ቤቱን አግኝቶ ሳውልን ያነጋገረው ሲሆን በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው ሳውልም ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ ሊሆን ችሏል።—የሐዋርያት ሥራ 9:12-19

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሲልካቸው ምሥራቹን ለመስማት ‘ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጉ’ ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:11) ሐናንያ ሳውልን ለማግኘት ቃል በቃል መፈለግ የነበረበት ይመስላል። በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ሐናንያ ምሥራቹ የሚገባቸውን ሰዎች የሚፈልጉ ሲሆን ለመስማት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ሲያገኙ ይደሰታሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎችን ማግኘታችን ጥረታችንን የሚክስ ያደርገዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:58

[በገጽ32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ቀጥተኛ ጎዳና” የተባለው መንገድ በዘመናችን

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

From the book La Tierra Santa, Volume II, 1830