በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለክፍል ጓደኞቿ ስለ እምነቷ ተናገረች

ለክፍል ጓደኞቿ ስለ እምነቷ ተናገረች

ለክፍል ጓደኞቿ ስለ እምነቷ ተናገረች

የክፍል ጓደኞችህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው እምነትህ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለመርዳት ትፈልጋለህ? በፖላንድ የምትኖር የአንዲት የ18 ዓመት ወጣት የይሖዋ ምሥክርን ተሞክሮ ተመልከት። ማግዳሌና የተባለችው ይህቺ ወጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን ብዙውን ጊዜ ስለ እምነቷ ለክፍል ጓደኞቿ ትናገራለች። በዚህም ምክንያት ‘የይሖዋ ምሥክር መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?’ እና ‘በኢየሱስ ክርስቶስ አታምኑም?’ እንደሚሉ ያሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይቀርቡላት ነበር። የክፍል ጓደኞቿን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችል ይሆን? ማግዳሌና ይሖዋ እንዲመራት ጸለየችና ከጸሎቷ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወሰደች።—ያዕቆብ 1:5

አንድ ቀን ማግዳሌና እምነቷን የምታከብርላትን አንዲት መምህርት የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት a የተባለውን የቪዲዮ ፊልም ለክፍሏ ተማሪዎች ማሳየት ትችል እንደሆነ ጠየቀቻት። መምህሯም በጥያቄው ተስማማች። ከዚያም ማግዳሌና የክፍል ጓደኞቿን “አንድ ጓደኛዬ የ90 ደቂቃ ፕሮግራም እንዲያቀርብላችሁ ዝግጅት አድርጌያለሁ። በፕሮግራሙ ላይ የቪዲዮ ፊልም የሚታይ ሲሆን ስለ የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ማብራሪያ ይሰጣል። በዝግጅቱ ላይ መገኘት ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀቻቸው። ሁሉም እንደሚፈልጉ ገለጹላት። ከዚያም ማግዳሌና እና ቮይጸይክ የተባለ አንድ ተሞክሮ ያለው የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ዝግጅታቸውን ጀመሩ።

ፕሮግራሙን የይሖዋ ምሥክሮች—እነማን ናቸው? ምን ብለው ያምናሉ?* (እንግሊዝኛ) በተባለው ብሮሹር ላይ ተመሥርቶ በሚቀርብ የ20 ደቂቃ ንግግር ለመጀመርና ከዚያም የጥያቄና መልስ ውይይት ለማድረግ ወሰኑ። ከዚያ በኋላም ፊልሙን በትምህርት ቤቱ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ለማሳየት አሰቡ። ለእያንዳንዱ የክፍሉ ተማሪም የተወሰኑ ብሮሹሮችን፣ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና—ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች* የተባለውን መጽሐፍ እንዲሁም አንዳንድ ትራክቶችንና መጽሔቶችን የያዘ ትልቅ ፖስታ በስጦታ ለማበርከት ዝግጅት ተደረገ።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት 14 የክፍል ጓደኞቿ፣ መምህሯና በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ የነበሩ ሌሎች 4 ተማሪዎች ነበሩ። በመጀመሪያ ቮይጸይክ በርካታ ፖላንዳውያን ባለቅኔዎችና ደራሲያን በሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው ውስጥ ይሖዋ የተባለውን መለኮታዊ ስም መጠቀማቸውን ተናገረ። በተጨማሪም መለኮታዊውን ስም የያዙ አንዳንድ የቆዩ የካቶሊክ ሃይማኖት ማስተማሪያ ጽሑፎችን ጠቀሰ። የይሖዋ ምሥክሮች በዘመናችን ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሲገልጽ የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን የሚያሳዩ ብሮሹሮችንና በርካታ ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን የያዙ ፎቶግራፎችን አሳየ።

ከዚያም አስደሳች ውይይት ቀጠለ። ማግዳሌና እና ቮይጸይክ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቀሙ ነበር። ይህ አድማጮቻቸውን ከማስደነቁም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት ራሳቸው የፈጠሩትን ሐሳብ እንዳልሆነም አስገንዘቧቸዋል። ከቀረቡት ጥያቄዎችና ከመልሶቻቸው መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-

ጥያቄ:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያየ መንገድ ሊተረጎሙ የሚችሉ አሻሚ አባባሎችና ምሳሌያዊ አነጋገሮች በብዛት ይገኛሉ። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ጋር እንዴት ተስማምቶ መኖር ይቻላል?

መልስ:- አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ድምፅ እንዲያወጣ አድርገህ ልትጫወተው እንደምትችለው የሙዚቃ መሣሪያ ነው ይላሉ። ሆኖም እስቲ አስቡት:- አንድ ደራሲ የጻፈውን ሐሳብ ትርጉም ለመረዳት ከፈለጋችሁ እርሱ ራሱን መጠየቁ የተሻለ አይሆንም? በጊዜያችን በሕይወት ከሌሉት የተለያዩ ደራሲዎች በተለየ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሕያው ነው። (ሮሜ 1:20፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) የአንድን ጥቅስ ትክክለኛ አተረጓጎም በዙሪያው ያለው ሐሳብ ሊጠቁመን ይችላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ስለ አንድ ጉዳይ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ስለሚናገር እነዚህን ሐሳቦች ማወዳደር ትርጉማቸውን ለመረዳት ያስችለናል። በዚህ መንገድ አምላክ ራሱ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዳብራራልን ያህል አስተሳሰባችንን እንዲቀርጸው ማድረግ እንችላለን። እንዲህ በማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ፈቃዱን መረዳትና ከዚያ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ሕይወታችንን መምራት የምንችል አይመስላችሁም?

ጥያቄ:- በክርስቲያኖችና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

መልስ:- እኛ ክርስቲያኖች ነን! ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያን ነን በማለት ብቻ ሳይወሰኑ ከሚያምኑበትና አምላክ ለራሳቸው ጥቅም ብሎ ከሚያስተምራቸው ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) የሚያስተምሯቸው ትምህርቶች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ስለሆኑ እውነት ያለው እነርሱ ጋር እንደሆነ ያውቃሉ።—ማቴዎስ 7:13, 14, 21-23

ጥያቄ:- ፈጽሞ የማታውቋቸውን ሰዎች ቀርባችሁ ካላነጋገርናችሁ የምትሉት ለምንድን ነው? ይህ ሌሎች እምነታችሁን እንዲቀበሉ ማስገደድ አይሆንም?

መልስ:- አንድ ሰው በመንገድ ላይ በትሕትና አስቁሟችሁ በአንድ ጉዳይ ላይ ያላችሁን አመለካከት ቢጠይቃችሁ ድርጊቱ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማችኋል? (ኤርምያስ 5:1፤ ሶፎንያስ 2:2, 3) (ከዚያም ቮይጸይክ እና ማግዳሌና በመንገድ ላይ የሚተላለፉ ሰዎችን አምላክ በቅርቡ በፖላንድ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ያስብ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዴት እንደሚጠይቋቸው የሚያሳይ ሠርቶ ማሳያ አቀረቡ።) የግለሰቡን አመለካከት ካዳመጥን በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናነብለታለን። አንድ ሰው ሊያናግረን ፈቃደኛ ካልሆነ በሰላም እንሰናበተውና መንገዳችንን እንቀጥላለን። (ማቴዎስ 10:11-14) ይህ ሰዎችን በግድ እንደማነጋገር ሊቆጠር ይችላል? ወይስ ሰዎች ጨርሶ እርስ በርስ መነጋገር የለባቸውም?

ጥያቄ:- በዓላትን የማታከብሩት ለምንድን ነው?

መልስ:- መጽሐፍ ቅዱስ እንድናከብረው ያዘዘንን ብቸኛ በዓል ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት መታሰቢያ እናከብራለን። (1 ቆሮንቶስ 11:23-26) ዓመት በዓላትን በሚመለከት ግን ኢንሳይክሎፒዲያዎችንና ሌሎች ተአማኒ ጽሑፎችን በማንበብ ስለ አመጣጣቸው ለማወቅ ትችላላችሁ። እንዲያ ብታደርጉ እነዚህን በዓላት የማናከብርበትን ምክንያት በቀላሉ ትገነዘባላችሁ።—2 ቆሮንቶስ 6:14-18

ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው መልስ ተሰጥቶባቸዋል። ውይይቱ በጣም ረጅም ሰዓት ከመፍጀቱ የተነሳ ፊልሙ በሌላ ቀን እንዲታይ ተወሰነ።

የተማሪዎቹ ምላሽ ምን ነበር? እስቲ ከራሷ ከማግዳሌና አንደበት እንስማ:- “አብዛኛውን ጊዜ የማይረባ ነገር የሚያደርጉና በሌሎች ላይ የሚያፌዙ ተማሪዎች ቁም ነገር ያዘሉ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ መመልከቴ አስገርሞኛል። አምላክ የለም ባዮች ነን ቢሉም በውይይቱ ወቅት በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል!” በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የተዘጋጀላቸውን ስጦታ በደስታ የተቀበሉ ሲሆን በድምሩ 35 መጻሕፍት፣ 63 ብሮሹሮችና 34 መጽሔቶች ተበርክተውላቸዋል።

በትምህርት ቤት ከመመሥከር የተገኘ እንዴት ያለ ግሩም ውጤት ነው! የማግዳሌና የክፍል ጓደኞች የይሖዋ ምሥክሮችን ይበልጥ እንዲያውቋቸውና እንዲረዷቸው ከማድረጉም በላይ በርካታ ወጣቶችን ስለ ሕይወት ዓላማ በቁም ነገር እንዲያስቡ አበረታቷቸዋል። የክፍል ጓደኞችህ ስለ እምነትህ ይበልጥ እንዲያውቁ ለመርዳት ለምን ጥረት አታደርግም?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማግዳሌና እና ቮይጸይክ ለውይይቱ ሲዘጋጁ