በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግጠኝነት ልታገኘው የምትችለው ውርስ

በእርግጠኝነት ልታገኘው የምትችለው ውርስ

በእርግጠኝነት ልታገኘው የምትችለው ውርስ

“ከአንድ ሰው፣ ፈጽሞ ያልጠበቅከው ውርስ ልታገኝ እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ ከደረሰህ ተጠንቀቅ። የአታላዮች ሲሳይ ልትሆን ትችላለህ።”

ይህ የዩናይትድ ስቴትስ ፖስታ ምርመራ አገልግሎት ድርጅት በድህረ ገጹ ላይ ያወጣው ማስጠንቀቂያ ነው። ማስጠንቀቂያው ለምን አስፈለገ? በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ‘አንድ ዘመድህ ሲሞት የተናዘዘልህ ውርስ አለ’ የሚል መልእክት እየደረሳቸው ስለነበረ ነው። በዚህ ምክንያት በርካታ ሰዎች ውርሱ የት እንደሚገኝና እንዴት መውሰድ እንደሚቻል ለማወቅ መልእክቱን ለላከላቸው ሰው 30 ወይም ከዚያ የሚበልጥ የአሜሪካ ዶላር የአገልግሎት ክፍያ ልከዋል። የሚያሳዝነው ግን ነገሩ እንዳሰቡት አልሆነም። ሁሉም ምንም ውርስ እንደሌላቸው የሚገልጽ ተመሳሳይ መልስ ደረሳቸው።

አጭበርባሪዎች የሰዎችን ውርስ የማግኘት ተፈጥሯዊ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይህን የመሳሰሉ የረቀቁ ዘዴዎች ይጠቀማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “ደግ ሰው ለልጅ ልጆቹ ውርስ ትቶ ያልፋል” በማለት በእርግጠኝነት ውርስ ሊያወርሱ የሚችሉት እነማን እንደሆኑ ይናገራል። (ምሳሌ 13:22) እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” የሚለውን ተወዳጅና በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ተስፋ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 5:5

ኢየሱስ የሰጠው ይህ ተስፋ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” በማለት በመንፈስ አነሳሽነት የተናገረውን ትንቢት ያስታውሰናል።—መዝሙር 37:11

‘ምድርን መውረስ’ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ሆኖም ይህ ተስፋ ሰዎችን አታልሎ አንድ ነገር ለመቀማት ታስቦ በተንኮል የተዶለተ ዘዴ አለመሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን? ይሖዋ ፈጣሪና የሁሉም ነገሮች ባለቤት እንደመሆኑ መጠን እጹብ ድንቅ ከሆኑት ፍጥረታት መካከል አንዷ የሆነችውን ምድርን ለፈለገው የማውረስ ሕጋዊ መብት አለው። ይሖዋ በንጉሥ ዳዊት በኩል ለሚወደው ልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ትንቢታዊ ይዘት ያለው ቃል ገብቶለት ነበር:- “ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፤ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ።” (መዝሙር 2:8) በዚህ ምክንያት አምላክ ኢየሱስን ‘ሁሉን ወራሽ እንዳደረገው’ ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። (ዕብራውያን 1:2) ስለዚህ ኢየሱስ የዋሆች “ምድርን ይወርሳሉ” ብሎ ሲናገር በእርግጥ የማውረስ ዓላማ እንደነበረውና ቃሉንም ለመፈጸም የሚያስችል የተሟላ ሥልጣን እንዳለው ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—ማቴዎስ 28:18

አሁን የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ ይህ ቃል ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? የሚለው ነው። በዛሬው ጊዜ በሁሉም ቦታዎች ኃይለኛና እብሪተኛ የሆኑ ሰዎች የተሳካላቸው መስለው የሚታዩ ከመሆኑም በላይ የሚፈልጉትን ሁሉ በእጃቸው ያስገባሉ። ታዲያ የዋሆች ምን የሚወርሱት ነገር ይተርፍላቸዋል? ከዚህም በላይ ምድር ክፉኛ እየተበከለች ሲሆን ስግብግቦችና ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ምድርን እየቦጠቦጧት ነው። ታዲያ ምድር በውርስነት ብትሰጥ ምን ትረባለች? ለእነዚህና ለሌሎች አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነተኛ ውርስ ለማግኘት ትበቃ ይሆን?