በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዛሬው ጊዜ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው?

በዛሬው ጊዜ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው?

በዛሬው ጊዜ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው?

“ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11

1, 2. (ሀ) ሰዎች ተፈጥሮን እንደሚኮርጁ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ምን ጥያቄ ይነሳል? መልሱስ ምንድን ነው?

 በ1940 ጆርጅ ደ መስትራል የተባለ ስዊሳዊ መሃንዲስ አንድ ቀን ውሻውን ይዞ ለመንሸራሸር ወጣ። ከዚያም ቤቱ ሲመለስ ልብሱና የውሻው ፀጉር ጭጎጎት እንደወረሰው ተመለከተ። ይህ ተክል እንዴት ልብሱ ላይ ሊጣበቅ እንደቻለ የማወቅ ጉጉት ስላደረበት ጭጎጎቱን በማጉያ መነጽር ተመለከተው። ከዚያም ጭጎጎቱ በማንኛውም ነገር ላይ መጣበቅ የሚያስችሉት እንደ መንጠቆ ያሉ ጭረቶች እንዳሉት አስተዋለ። ይህ መሃንዲስ ከጊዜ በኋላ ልብስንም ሆነ ሌሎች ነገሮችን እርስ በርስ ሊያያይዝ የሚችል ቬልክሮ የሚባል ነገር ፈለሰፈ። ከተፈጥሮ በመኮረጅ ረገድ ደ መስትራል የመጀመሪያው ሰው አልነበረም። በዩናይትድ ስቴትስ ይኖሩ የነበሩት ዊልበር እና ኦርቪል የሚባሉ ወንድማማቾች ትልልቅ አሞራዎች እንዴት እንደሚበሩ በማጥናት አውሮፕላን ፈልስፈዋል። አሌክሳንድር ጉስታቭ ኢፌል የተባለው ፈረንሳዊ መሃንዲስ ደግሞ የታፋ አጥንት የሰውነትን ክብደት እንዴት ሊሸከም እንደቻለ በማጥናት በፓሪስ የሚገኘውንና በስሙ የተሰየመውን ኢፌል ታወር የተባለውን ማማ ንድፍ ሊያወጣ ችሏል።

2 እነዚህ ምሳሌዎች የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለመኮረጅ ምን ያህል ጥረት እያደረገ እንዳለ የሚያሳዩ ናቸው። ይሁን እንጂ፣ እነዚህ የፈጠራ ሰዎች አስመስለው ለሠሯቸው ነገሮች መሠረት የሆኗቸውን እንደ ጭጎጎት፣ አሞራ፣ የሰው የታፋ አጥንት ያሉ አስደናቂ ፍጥረታትን ከራሱ አመንጭቶ ለሠራው ፈጣሪ ክብር ሰጥተው ያውቃሉ? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው። በጣም የሚያሳዝነው በዚህ ባለንበት ዓለም አብዛኞቹ ሰዎች ለአምላክ የሚገባውን ክብር ወይም ምስጋና አይሰጡም።

3, 4. “ክብር” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ፍቺ ምንድን ነው? ይህ ቃል ከይሖዋ ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ምን ያመለክታል?

3 አንዳንዶች ‘አምላክ ምንጊዜም ቢሆን የተከበረ ነው። ታዲያ ለእርሱ ክብር መስጠት ለምን አስፈለገ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ይሖዋን በክብር የሚተካከለው የለም። ይሁን እንጂ ሰዎች ሁሉ ይህን ታላቅ ክብሩን ይገነዘባሉ ማለት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ክብር” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ከክብደት” ጋር የተያያዘ መልእክት ያስተላልፋል። ቃሉ አንድን ሰው በሌሎች ዘንድ ሞገስ ወይም ከፍ ያለ ቦታ የሚያሰጠውን ማንኛውንም ነገር ያመለክታል። ከአምላክ ጋር በተያያዘ ሲጠቀስ አምላክ በሰዎች ፊት እንዲከበር የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ያመለክታል።

4 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች አምላክ የላቀ ክብር እንዲሰጠው የሚያደርጉትን ነገሮች አያስተውሉም። (መዝሙር 10:4፤ 14:1) እንዲያውም በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ግለሰቦች፣ ሰዎች ክብር የተጎናጸፈውን የአጽናፈ ዓለሙን ፈጣሪ እንዳያከብሩ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እንዴት?

“ማመካኛ የላቸውም”

5. በርካታ ሳይንቲስቶች አስደናቂ ፍጥረታት ወደ ሕልውና ስለመጡበት መንገድ ምን ማብራሪያ ለመስጠት ይሞክራሉ?

5 ብዙ ሳይንቲስቶች አምላክ የለም በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ታዲያ የሰውን ልጅ ጨምሮ አስደናቂ ፍጥረታት በሙሉ ከየት መጡ? እነርሱ እንደሚሉት እነዚህ ሁሉ ነገሮች እንዲያው በአጋጣሚ በዝግመተ ለውጥ የተገኙ ናቸው? ለምሳሌ ያህል የዝግመተ ለውጥ አራማጅ የሆኑት ስቴፈን ጄይ ጉልድ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “እኛ ወደ ሕልውና የመጣነው እንግዳ የሆኑ የዓሣ ዝርያዎች ክንፋቸው በመቀየሩና በየብስ ላይ ለሚኖሩ እንስሳት ተስማሚ የሆነ እግር በማውጣታቸው ነው። . . . ከዚህ ‘የረቀቀ’ ማብራሪያ ማግኘት እንፈልግ ይሆናል። ሆኖም ልናገኝ አንችልም።” በተመሳሳይም ሪቻርድ ሊኪ እና ሮጀር ሉዊን “የሰው ልጅ ዝርያ የተገኘው በድንገት በተፈጠረ ባዮሎጂያዊ ክስተት ሳይሆን አይቀርም” በማለት ጽፈዋል። የተፈጥሮን ውበትና ንድፍ ከልብ የሚያደንቁ አንዳንድ ሳይንቲስቶች እንኳ ለዚህ ሁሉ ክብር ሊሰጠው የሚገባው አምላክ መሆኑን ይዘነጋሉ።

6. ብዙዎች አምላክን እንደ ፈጣሪነቱ እንዳያከብሩት ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ምንድን ነው?

6 በጣም ተምረናል የሚሉ ሰዎች ዝግመተ ለውጥ ተጨባጭ ሃቅ ነው ብለው ሲከራከሩ ይህን ትምህርት የማይቀበል ሁሉ ከድንቁርና አልተላቀቀም ማለታቸው ነው። ታዲያ ይህ በብዙዎች ላይ ምን ስሜት አሳድሯል? ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ ስለ ዝግመተ ለውጥ የጠለቀ እውቀት ያለው አንድ ሰው በዚህ ንድፈ ሐሳብ ለሚያምኑ ሰዎች ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር። ያገኘውን ውጤት በተመለከተ “አብዛኞቹ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ይህን ንድፈ ሐሳብ የተቀበሉት የተማሩ ሰዎች ሁሉ በዚህ እንደሚያምኑ ስለተነገራቸው መሆኑን ተረድቻለሁ” ብሏል። አዎን፣ የተማሩ ናቸው የሚባሉ ሰዎች በአምላክ መኖር የማያምኑ መሆናቸውን በተመለከተ የሚሰጡት አስተያየት ሌሎች አምላክን እንደ ፈጣሪነቱ እንዳያከብሩት ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል።—ምሳሌ 14:15, 18

7. በሮሜ 1:20 መሠረት በዙሪያችን ካሉት የፍጥረት ሥራዎች ምን ነገር በግልጽ መገንዘብ ይቻላል? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው?

7 ሳይንቲስቶች እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ማስረጃዎቹ ሁሉ ዝግመተ ለውጥን የሚደግፉ ሆነው ስላገኟቸው ነው? በፍጹም! እንዲያውም በዙሪያችን ያለው ነገር ሁሉ የፈጣሪን ሕልውና የሚያስረግጥ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን በሚመለከት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ዓለም [የሰው ዘር] ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም።” (ሮሜ 1:20) በእርግጥም የእጁ ሥራዎች ፈጣሪነቱን የሚያስረዱ አሻራዎች ናቸው። እዚህ ላይ ጳውሎስ የሰው ዘር ከተፈጠረ ጀምሮ ሰዎች የአምላክን ሕልውና ‘በግልጽ እንዲረዱ’ የሚያስችሏቸው ማስረጃዎች በዙሪያቸው ሞልተዋል ማለቱ ነው። እነዚህ ማስረጃዎች የሚገኙት የት ነው?

8. (ሀ) ግዑዙ ሰማይ ስለ አምላክ ኃይልና ጥበብ የሚመሠክረው እንዴት ነው? (ለ) አጽናፈ ዓለም አንድ ያስጀመረው ኃይል እንዳለ የሚያሳየው ምንድን ነው?

8 በከዋክብት የተሞላው ሰማይ ለአምላክ ሕልውና አንዱ ማስረጃ ነው። መዝሙር 19:1 “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ” ይላል። “ሰማያት” ማለትም ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት አምላክ ላለው ኃይልና ጥበብ ትልቅ ማስረጃዎች ናቸው። ስለ ከዋክብት ብዛት ብቻ እንኳ ማሰብ በአድናቆት እንድንደመም ሊያደርገን ይችላል። እንዲሁም እነዚህ ሁሉ የሰማይ አካላት በሕዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት በዘፈቀደ ሳይሆን ዝንፍ የማይለውን የተፈጥሮ ሕግ ጠብቀው ነው። a (ኢሳይያስ 40:26) ይህ ሊሆን የቻለው እንዲያው በአጋጣሚ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው? የሚያስገርመው ብዙ ሳይንቲስቶች አጽናፈ ዓለም ድንገት ወደ ሕልውና መምጣት እንደጀመረ ይናገራሉ። አንድ ፕሮፌሰር ይህን አባባል ሲያብራሩ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “አምላክ የለም ወይም ስለ እርሱ ማወቅ አይቻልም ብለው የሚያምኑ ሰዎች አጽናፈ ዓለም ዘላለማዊ ነው ቢሉ ይቀላቸው ነበር። አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ አለው ከተባለ ያንን የሚያስጀምር ማስፈለጉ የግድ ነው፤ ታዲያ እንዲህ ያለ አስደናቂ ውጤት ያለ በቂ ምክንያት እንዴት ሊገኝ ይችላል?”

9. የይሖዋ ጥበብ በእንስሳት አፈጣጠር ላይ የተንጸባረቀው እንዴት ነው?

9 በምድር ላይም ቢሆን ስለ አምላክ ሕልውና የሚመሠክሩ ማስረጃዎች አሉ። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። (መዝሙር 104:24) እንስሳትን ጨምሮ ሁሉም ‘ፍጥረታት’ ይሖዋ ከፍተኛ ጥበብ እንዳለው የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። በመግቢያችን ላይ እንደተመለከትነው ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተሠሩበት ንድፍ እጅግ አስደናቂ በመሆኑ ብዙውን ጊዜ ሳይንቲስቶች ተፈጥሮን ለመኮረጅ ጥረት ሲያደርጉ ይታያል። ሌሎች ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት። ተመራማሪዎች ይበልጥ ጠንካራ የሆነ የራስ ቁር ለመሥራት በቀንድ ላይ ጥናት እያካሄዱ ነው። እንዲሁም የመስማት ችግር ላለባቸው ሰዎች የሚረዱ መሣሪያዎችን ጥራት ለማሻሻል ከፍተኛ የመስማት ችሎታ ባላቸው የዝንብ ዝርያዎች ላይ ምርምር በማድረግ ላይ ናቸው። ከራዳር ዕይታ የሚሰወሩ አውሮፕላኖችን ይበልጥ አሻሽሎ ለመሥራት በጉጉት ክንፍ ላባዎች ላይ ጥናት እያደረጉ ነው። የሰው ልጆች ተፈጥሮን ለመኮረጅ የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉም አስመስለው ይሠሩ እንደሆነ እንጂ ያንኑ ነገር መሥራት አይችሉም። ባዮሚሚክራይ—ኢኖቬሽን ኢንስፓየርድ ባይ ኔቸር የተባለው መጽሐፍ “ሕይወት ያላቸው ነገሮች የነዳጅ ዘይት መጠቀም ሳያስፈልጋቸው፣ አካባቢያቸውን ሳይበክሉ ወይም የወደፊት ሕልውናቸውን አደጋ ላይ ሳይጥሉ እኛ ማድረግ የምንፈልገውን ሁሉ ያደርጋሉ” ሲል አስተያየት ሰጥቷል። እንዴት የሚያስደንቅ ጥበብ ነው!

10. የታላቁን ንድፍ አውጪ ሕልውና መካድ ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

10 ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ብትመለከት ወይም እዚሁ ምድር ላይ ያሉትን ፍጥረታት ብትቃኝ ያለምንም ጥርጥር የፈጣሪን መኖር የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ታገኛለህ። (ኤርምያስ 10:12) የሰማይ ፍጥረታት “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና” በማለት ያስተጋቡትን ሐሳብ ከልብ መቀበል ይኖርብናል። (ራእይ 4:11) ሆኖም በርካታ ሳይንቲስቶች በሥጋዊ ዓይናቸው በሚያዩአቸው ፍጥረታት ንድፍ ቢደመሙም ‘በልባቸው ዓይኖች’ ማስተዋል ተስኗቸዋል። (ኤፌሶን 1:18) ይህን ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፦ የተፈጥሮን ውበትና ንድፍ አድንቆ ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያለውን ታላቅ ንድፍ አውጪ ሕልውና አለመቀበል አንድን ግሩም ሥዕል አድንቆ በባዶ ሸራ ላይ ይህን ውብ ሥዕል የሳለውን ሰዓሊ ሕልውና ከመካድ ተለይቶ አይታይም። በአምላክ ሕልውና አናምንም የሚሉ ሰዎች “ማመካኛ የላቸውም” መባላቸው ምንም አያስደንቅም።

“ዕውር መሪዎች” ብዙዎችን ያሳስታሉ

11, 12. ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በየትኛው ግምታዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው? ይህስ ለአምላክ ክብር እንደማያመጣለት የሚያሳየው ምንድን ነው?

11 ብዙ የሃይማኖት ሰዎች አምልኮታቸው ለአምላክ ክብር እንደሚሰጥ ከልብ ያምናሉ። (ሮሜ 10:2, 3) ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ ሃይማኖት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ ክብር እንዳይሰጡ እንቅፋት ሆኗል። እንዴት? ይህን የሚያደርግበትን ሁለት መንገዶች እንመልከት።

12 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሃይማኖቶች የሐሰት ትምህርቶችን በማስተማር የሰው ልጆች ለአምላክ ክብር እንዳይሰጡ አድርገዋል። ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን ትምህርት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ መሠረተ ትምህርት አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታ እስካለው ድረስ የማንኛውንም ነገር የወደፊት ዕጣ አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል በሚል ግምታዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ጽንሰ ሐሳብ አምላክ የእያንዳንዱን ሰው ዕድል (ጥሩም ይሁን መጥፎ) ከረጅም ዘመናት በፊት ወስኗል የሚል መልእክት ያስተላልፋል። እንደዚያ ከሆነ በዚህ ዓለም ላይ ለሚደርሰው ሥቃይና መከራ ሁሉ ተወቃሹ አምላክ መሆን አለበት። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት የሚጠራው የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን ሆኖ ሳለ ጥፋቱን በአምላክ ላይ ማላከኩ ለአምላክ ክብር እንደማያመጣ ግልጽ ነው።—ዮሐንስ 14:30፤ 1 ዮሐንስ 5:19

13. አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታውን የሚጠቀምበት እንደ አስፈላጊነቱ ብቻ ነው ብሎ መናገር ምክንያታዊ የሚሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

13 ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የሌለውና አምላክን የሚያሰድብ ነው። ማድረግ መቻል እና ማድረግ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባዋል። አምላክ ስለወደፊቱ ጊዜ ማወቅ እንደሚችል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። (ኢሳይያስ 46:9, 10) ይህን ችሎታውን ግን ሁልጊዜ ይጠቀምበታል ወይም ለሁሉም ነገር ተጠያቂው እርሱ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ ገና ለገና ጉልበት አለኝ ብለህ ያገኘኸውን ነገር ሁሉ እያነሳህ ትሸከማለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታ ስላለው ብቻ እያንዳንዱን ነገር አስቀድሞ ያውቃል ወይም አስቀድሞ ወስኗል ማለት አይደለም። ይህን ችሎታውን የሚጠቀምበት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብቻ ነው። b ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው ጽንሰ ሐሳብም ሆነ ሌሎች የሐሰት ትምህርቶች ለአምላክ ክብር እንደማያመጡ ግልጽ ነው።

14. ሃይማኖቶች አምላክን የሚያስነቅፉበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

14 ሃይማኖቶች አምላክን የሚያስነቅፉበት ሁለተኛው መንገድ የአባላቶቻቸው ሥነ ምግባር ነው። ክርስቲያኖች የኢየሱስን ትምህርቶች መከተል ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘እርስ በርስ እንዲዋደዱ’ እና ‘የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ’ አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:12፤ 17:14-16) ታዲያ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በዚህ ረገድ ያላቸው አቋም ምንድን ነው? በእርግጥ እነዚህን ትእዛዛት ይከተላሉ?

15. (ሀ) ቀሳውስት በብሔራት መካከል በተካሄዱት ጦርነቶች ረገድ ምን ታሪክ አስመዝግበዋል? (ለ) የቀሳውስት ሥነ ምግባር በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?

15 ቀሳውስት በጦርነት ረገድ ያስመዘገቡትን ታሪክ እስቲ እንመልከት። በብሔራት መካከል የተደረጉትን አብዛኞቹን ጦርነቶች ደግፈዋል፣ በቸልታ ተመልክተዋል አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹን በግንባር ቀደምትነት መርተዋል። ወታደሮችን ባርከው ወደ ጦርነት የሸኙ ከመሆኑም በላይ ጦር ሜዳ ሄዶ መግደል ትክክል እንደሆነ ለማስረዳት ሞክረዋል። ‘በሌላው ጎራ ያሉት የዚያ ሃይማኖት ቀሳውስትም እንዲሁ እንደሚያደርጉ እንዴት ቆም ብለው አያስቡም?’ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው። (“አምላክ የሚወግነው ለየትኛው ጎራ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ቀሳውስት ደም አፋሳሽ በሆኑ ጦርነቶች ውስጥ አምላክ ከጎናቸው እንደሆነ መናገራቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው ማለታቸው እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት የጾታ ብልግና በቸልታ ማለፋቸው ለአምላክ ክብር እንደማያመጣ ግልጽ ነው። ይህ ሁኔታ ኢየሱስ “እናንት ክፉዎች” እና “ዕውር መሪዎች” በማለት የተናገራቸውን በወቅቱ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች ያስታውሰናል። (ማቴዎስ 7:15-23፤ 15:14) የቀሳውስቱ የሥነ ምግባር ሁኔታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል።—ማቴዎስ 24:12

በእርግጥ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው?

16. በዛሬው ጊዜ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

16 ታዋቂ የሆኑና ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ለአምላክ ክብር የማይሰጡ ከሆነ ታዲያ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን መመርመራችን የግድ ነው። ደግሞም አምላክ እንዴት መከበር እንዳለበት የመናገር መብት ያለው ከመሆኑም በላይ ይህን መሥፈርት በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሯል። (ኢሳይያስ 42:8) ለአምላክ ክብር መስጠት የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት፤ ይህን ስናደርግ እግረ መንገዳችንን በዛሬው ጊዜ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን እንደሆኑ እናያለን።

17. ይሖዋ የስሙ መቀደስ የፈቃዱ ዓብይ ገጽታ እንደሆነ ያሳወቀው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ በምድር ዙሪያ የአምላክን ስም እያወደሱ ያሉት እነማን ናቸው?

17 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ስሙን በማወደስ ለአምላክ ክብር መስጠት እንችላለን። ይህን ማድረጉ የአምላክ ፈቃድ ዓብይ ገጽታ መሆኑን ይሖዋ ለኢየሱስ ከተናገረው ነገር መረዳት ይቻላል። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ “አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው” በማለት ጸልዮ ነበር። ከዚያም “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ሰማ። (ዮሐንስ 12:28) ይህን የተናገረው ይሖዋ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ለስሙ መቀደስ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ ከዚህ መረዳት እንችላለን። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ስሙን በማሳወቅና በምድር ዙሪያ እንዲወደስ በማድረግ ለይሖዋ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው? በ235 አገሮች ይህን በማድረግ ላይ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው!—መዝሙር 86:11, 12

18. አምላክን “በእውነት” የሚያመልኩትን ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ሲያስተምሩ የቆዩት እነማን ናቸው?

18 በሁለተኛ ደረጃ፣ ስለ አምላክ እውነት የሆነውን በማስተማር ለእርሱ ክብር መስጠት እንችላለን። ኢየሱስ እውነተኛ አምላኪዎች ‘ለአምላክ በእውነት መስገድ’ እንደሚኖርባቸው ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:24) አምላክን “በእውነት” እያመለኩ ያሉት እነማን እንደሆኑ እንዴት ማወቅ እንችላለን? እውነተኛ አምላኪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌሉና ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው በሚያደርጉ ትምህርቶች ማመን አይኖርባቸውም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ያልተበረዙ እውነቶች ማስተማር ይገባቸዋል። ከእነዚህ ትምህርቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ ሲሆን እንዲህ ያለ ክብር ሊሰጠው የሚገባው እርሱ ብቻ ነው። (መዝሙር 83:18) ኢየሱስ የአምላክ ልጅና በአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ላይ የተሾመ ንጉሥ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:27, 28) የአምላክ መንግሥት የይሖዋን ስም ያስቀድሳል እንዲሁም ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ዳር ያደርሳል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የዚህ መንግሥት ምሥራች በምድር ዙሪያ መሰበክ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 24:14) ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እንዲህ ያለውን ውድ እውነት በታማኝነት ሲያስተምር የኖረው አንድ የሃይማኖት ቡድን ብቻ ነው። እነርሱም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።

19, 20. (ሀ) የአንድ ክርስቲያን መልካም ምግባር አምላክን ሊያስከብር የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ በመልካም ምግባራቸው አምላክን በማስከበር ላይ ያሉት እነማን መሆናቸውን እንድናውቅ የሚረዱን የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?

19 በሦስተኛ ደረጃ፣ የሥነ ምግባር ሕጎቹን በመጠበቅ ለአምላክ ክብር መስጠት እንችላለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ።” (1 ጴጥሮስ 2:12) የአንድ ክርስቲያን ምግባር ምን ዓይነት እምነት እንዳለው ይጠቁማል። ሰዎች የአንድን ክርስቲያን መልካም ምግባር ሲመለከቱ እምነቱ ለዚያ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገነዘባሉ፤ ይህ ደግሞ አምላክን ያስከብራል።

20 ታዲያ በዛሬው ጊዜ በጥሩ ምግባራቸው አምላክ እንዲከበር እያደረጉ ያሉት እነማን ናቸው? በሰላም ወዳድነታቸውም ሆነ የሚፈለግባቸውን ግብርና ቀረጥ በመክፈል ረገድ ሕግ አክባሪ በመሆናቸው በብዙ መንግሥታት ዘንድ አድናቆትን ያተረፉት የየትኛው ሃይማኖት አባላት ናቸው? (ሮሜ 13:1, 3, 6, 7) የዘር፣ የብሔርና የጎሣ ልዩነት ሳይገድባቸው በዓለም ዙሪያ ባላቸው አንድነት የሚታወቁት እነማን ናቸው? (መዝሙር 133:1፤ የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ሰዎች ሕግ አክባሪዎች እንዲሆኑ፣ በቤተሰባቸው ውስጥ መልካም ምግባርን እንዲያንጸባርቁና የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች እንዲከተሉ በዓለም ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር የሚታወቁት እነማን ናቸው? በእነዚህና በሌሎች መስኮች ጥሩ ስም ያተረፉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው!

አንተስ ለአምላክ ክብር እየሰጠህ ነው?

21. ለይሖዋ ክብር እየሰጠን መሆን አለመሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን መመርመር የሚኖርብን ለምንድን ነው?

21 እያንዳንዳችን ‘ለይሖዋ ክብር እየሰጠሁ ነው?’ እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። በመዝሙር 148 መሠረት ፍጥረት ሁሉ ለማለት ይቻላል ለአምላክ ክብር እየሰጠ ነው። መላእክት፣ ግዑዙ ሰማይ፣ ምድርና በውስጧ ያሉት እንስሳት ሁሉ ይሖዋን ያወድሳሉ። (ከቁጥር 1-10) አብዛኞቹ ሰዎች እንደዚያ አለማድረጋቸው በጣም የሚያሳዝን ነው! አንተም አምላክን በሚያስከብር መልካም አኗኗር ከቀሩት ፍጥረታቱ ጋር በመሆን ይሖዋን ማወደስ ትችላለህ። (ከቁጥር 11-13) በሕይወትህ ውስጥ ከዚህ የተሻለ ልታደርገው የሚገባ ነገር የለም።

22. ለይሖዋ ክብር በመስጠት ምን በረከቶችን ታገኛለህ? ቁርጥ ውሳኔህስ ምን መሆን አለበት?

22 ለይሖዋ ክብር መስጠትህ ብዙ በረከቶች ያስገኝልሃል። በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የምታምን ከሆነ ከአምላክ ጋር መታረቅ የምትችል ከመሆኑም በላይ ከሰማዩ አባትህ ጋር ሰላማዊና አስደሳች ግንኙነት ይኖርሃል። (ሮሜ 5:10) ለአምላክ ክብር እንድትሰጥ የሚገፋፉህ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ በተገነዘብህ መጠን ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት ይኖርሃል፤ እንዲሁም አድናቆትህ እየጨመረ ይሄዳል። (ኤርምያስ 31:12) እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ሌሎች አስደሳችና ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲመሩ መርዳት ትችላለህ። ይህም በአጸፋው ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልሃል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) አሁንም ሆነ ለዘላለም ለአምላክ ክብር ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ ካደረጉት ሰዎች መካከል እንድትሆን ከልብ እንመኝልሃለን!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ግዑዙ ሰማይ የአምላክ ጥበብና ኃይል ነጸብራቅ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 እና 17⁠ን ተመልከት።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 853 ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• በአጠቃላይ ሲታይ ሳይንቲስቶች ሰዎች ለአምላክ ክብር እንዲሰጡ እያበረታቱ አይደሉም ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?

• ሃይማኖቶች ሰዎች ለአምላክ ክብር እንዳይሰጡ ያደረጉባቸው ሁለት መንገዶች ምንድን ናቸው?

• ለአምላክ ክብር መስጠት የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

• ለይሖዋ ክብር እየሰጠህ መሆን አለመሆንህን ለማወቅ ራስህን መመርመርህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“አምላክ የሚወግነው ለየትኛው ጎራ ነው?”

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን የአየር ኃይል አባል የነበረና በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ሰው እንደሚከተለው ሲል በወቅቱ ያጋጠመውን ሁኔታ ይገልጻል፦

“በእነዚያ የጦርነት ዓመታት የካቶሊክ፣ የሉተራንና የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶችን ጨምሮ የሁሉም ሃይማኖት ቀሳውስት ለማለት ይቻላል ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችንም ሆነ የአውሮፕላኑን አብራሪዎች ባርከው ወደ ግዳጅ ሲሸኙ መመልከቴ ሁልጊዜ አእምሮዬን ይረብሸው ነበር። ብዙውን ጊዜ ‘አምላክ የሚወግነው ለየትኛው ጎራ ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር።

“የጀርመን ወታደሮች ጎት ሚት ኡንስ (አምላክ ከእኛ ጋር ነው) የሚል ጽሕፈት የተቀረጸበት ዘለበት ያለው ቀበቶ ይታጠቁ ነበር። ‘አምላክ የዚያው ሃይማኖት አባላት ከሆኑትና ወደ ተመሳሳይ አምላክ ከሚጸልዩት በተቃራኒ ጎራ ከተሰለፉት ወታደሮች ጋር የማይሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር።”

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምድር ዙሪያ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው