በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ’

‘እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ’

‘እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ’

“እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።”—ሮሜ 12:10

1, 2. በዚህ ዘመን የኖረ አንድ ሚስዮናዊም ሆነ ጳውሎስ ከወንድሞቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?

 ን በሩቅ ምሥራቅ በሚስዮናዊነት ባገለገለባቸው 43 ዓመታት በብዙዎች ዘንድ በአፍቃሪነቱ ይታወቅ ነበር። ታሞ በሞት አፋፍ ላይ በነበረበት ወቅት ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው በመምጣት በኮሪያ ቋንቋ “ኮምሶሆምኒዶ፣ ኮምሶሆምኒዶ!” ማለትም “እናመሰግንሃለን! እናመሰግንሃለን!” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸውለታል። ዶን ለእነርሱ በነበረው ጥልቅ ፍቅር ልባቸው ተነክቶ ነበር።

2 እንዲህ ያለ ፍቅር ያሳየው ዶን ብቻ አልነበረም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ቃል ላስተማራቸው ሰዎች ጥልቅ ፍቅር ነበረው። ጳውሎስ ሙሉ በሙሉ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ሰው ነበር። በቆራጥነቱ ይታወቅ የነበረ ሰው ቢሆንም ‘ልጆቿን እንደምትንከባከብ እናት’ የዋህና አሳቢ ነበር። በተሰሎንቄ ለነበረው ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ።” (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ለኤፌሶን ወንድሞቹ ዳግም እንደማያዩት በነገራቸው ጊዜ “ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም አንገቱን ዐቅፈው ሳሙት።” (የሐዋርያት ሥራ 20:25, 37) ከዚህ በግልጽ እንደምናየው በጳውሎስና በወንድሞቹ መካከል የነበረው ግንኙነት አንድ ዓይነት እምነት ከመጋራት አልፎ የሚሄድ ነበር። እርስ በርሳቸው ከልብ ይዋደዱ ነበር።

ከልብ መዋደድ

3. ርኅራኄንና አሳቢነትን የመሳሰሉ ባሕርያት ከፍቅር ጋር ምን ተዛማጅነት አላቸው?

3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ርኅራኄ፣ አሳቢነትና አዛኝነት የላቀ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ከሆነው ከፍቅር ጋር የቅርብ ተዛማጅነት እንዳላቸው ተገልጿል። (1 ተሰሎንቄ 2:8፤ 2 ጴጥሮስ 1:7) የተለያዩ ገጽታዎች እንዳሉት አንድ የሚያምር ዕንቁ እነዚህ አምላካዊ ባሕርያትም አንድ ላይ ሲቀናጁ ውበት ያለው ባሕርይ ይፈጥራሉ። እነዚህ ባሕርያት ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ብቻ ሳይሆን ከሰማዩ አባታቸው ጋርም እንዲቀራረቡ ያስችሏቸዋል። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ . . . እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” ሲል የእምነት ባልንጀሮቹን አጥብቆ መክሯቸዋል።—ሮሜ 12:9, 10

4. “አጥብቃችሁ ተዋደዱ” የሚለው አገላለጽ ምን መልእክት ያስተላልፋል?

4 “አጥብቃችሁ ተዋደዱ” ተብሎ የተተረጎመው ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆን አንደኛው ወዳጅነት ሌላው ደግሞ የተፈጥሮ ፍቅር የሚል ፍቺ አለው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንደገለጹት ይህ ማለት ክርስቲያኖች “እርስ በርሱ እንደሚቀራረብ፣ እንደሚረዳዳና እንደሚተሳሰብ ቤተሰብ እርስ በርስ ከልብ መፋቀር ይኖርባቸዋል።” አንተስ ክርስቲያን ወንድሞችህንና እህቶችህን በሚመለከት እንዲህ ይሰማሃል? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደ ሥጋ ዘመድ የመዋደድ መንፈስ ሊሰፍን ይገባል። (ገላትያ 6:10) በመሆኑም በጄ ቢ ፊሊፕስ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ሮሜ 12:10ን “እንደ ሥጋ ወንድማማቾች እርስ በርሳችን ከልብ እንዋደድ” ሲል ተርጉሞታል። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል ደግሞ “ሥጋዊ ወንድማማቾች የሚዋደዱትን ያህል እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ይላል። አዎን፣ ክርስቲያኖች እርስ በርስ መዋደድ የሚኖርባቸው ግዴታ ወይም ኃላፊነት እንዳለባቸው ስለሚሰማቸው ብቻ መሆን የለበትም። ‘ግብዝነት በሌለው ፍቅር እርስ በርስ ከልብ አጥብቀን መዋደድ’ አለብን።—1 ጴጥሮስ 1:22 የ1954 ትርጉም

‘እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ከእግዚአብሔር ተምራችኋል’

5, 6. (ሀ) ይሖዋ ክርስቲያናዊ ፍቅርን ለሕዝቦቹ ለማስተማር ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎችን የተጠቀመባቸው እንዴት ነው? (ለ) ወንድሞችን የሚያስተሳስራቸው ሰንሰለት በጊዜ ሂደት ይበልጥ የሚጠነክረው እንዴት ነው?

5 ምንም እንኳ በዚህ ባለንበት ዓለም “የብዙ ሰዎች ፍቅር” እየቀዘቀዘ ቢሆንም ይሖዋ ‘እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ’ ሕዝቦቹን እያስተማረ ነው። (ማቴዎስ 24:12፤ 1 ተሰሎንቄ 4:9) የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ለዚህ ሥልጠና እንደ አንድ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህ ወቅት ስብሰባው በሚደረግበት አገር ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከሩቅ አገር ከመጡ ወንድሞቻቸው ጋር የመገናኘት አጋጣሚ የሚኖራቸው ሲሆን ብዙዎቹ ቤታቸው እንዲያርፉ በማድረግ በደስታ ያስተናግዷቸዋል። በቅርቡ በተደረገ እንዲህ ያለ ስብሰባ ላይ በእንግድነት ከተገኙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የመጡት ስሜታቸውን በመግለጽ ረገድ በተፈጥሯቸው ቁጥብ የሆኑ ሰዎች ከሚኖሩባቸው አገሮች ነበር። በመስተንግዶ ክፍል ይሠራ የነበረ አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እነዚህ እንግዶች መጀመሪያ እዚህ ሲደርሱ ትንሽ የመረበሽና የፍርሃት ስሜት ይነበብባቸው ነበር። ሆኖም ከስድስት ቀን በኋላ ወደ አገራቸው ለመሄድ ሲነሱ በእንግድነት ከተቀበሏቸው ወንድሞች ጋር አንገት ላንገት ተቃቅፈው ይላቀሱ ነበር። እንዲህ ያለው ክርስቲያናዊ ፍቅር መቼም ቢሆን ከአእምሯቸው የሚጠፋ አይደለም።” ከየትኛውም አገር የመጡ ቢሆኑ ወይም አስተዳደጋቸው ምንም ይሁን ምን ወንድሞችን በእንግድነት መቀበል ለአስተናጋጁም ሆነ ለእንግዳው ትልቅ በረከት ያስገኛል።—ሮሜ 12:13

6 ለአጭር ቀናት የቆዩት እነዚህ ስብሰባዎች እንኳ ይህን የመሰለ ተሞክሮ ካስገኙ ክርስቲያኖች ይሖዋን ረዘም ላለ ጊዜ አብረው ባገለገሉ መጠን በመካከላቸው ያለው ፍቅር ይበልጥ እየዳበረ እንደሚሄድ ግልጽ ነው። ወንድሞቻችንን ይበልጥ እየቀረብናቸው ስንሄድ እንድንወዳቸው የሚገፋፉ ግሩም ባሕርያት እንዳሏቸው እንገነዘባለን። ሐቀኝነታቸው፣ ታማኝነታቸው፣ ደግነታቸው፣ ለጋስነታቸው፣ አሳቢነታቸው፣ ርኅሩኅነታቸውና ገርነታቸው ጎልቶ ይታየናል። (መዝሙር 15:3-5፤ ምሳሌ 19:22) በምሥራቅ አፍሪካ በሚስዮናዊነት ያገለገለው ማርክ “ከወንድሞቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ማገልገላችን በማይበጠስ ሰንሰለት ያስተሳስረናል” በማለት ተናግሯል።

7. በጉባኤ ውስጥ በክርስቲያናዊ ፍቅር ለመተናነጽ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

7 በጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያለ ትስስር እንዲፈጠርና ጸንቶ እንዲቀጥል የጉባኤው አባላት እርስ በርስ ይበልጥ መቀራረብ አለባቸው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን በመገኘት ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት እናጠናክራለን። ከወንድሞች ጋር በሚገባ መጫወት እንድንችል ስብሰባዎች ላይ ቀደም ብለን በመገኘትና ዘግይተን በመውጣት እንዲሁም ስብሰባው በሚካሄድበት ጊዜ ተሳትፎ በማድረግ እርስ በርሳችን “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ” መነቃቃትና መበረታታት እንችላለን። (ዕብራውያን 10:24, 25) በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “ልጅ ሳለሁ ከወንድሞቻችን ጋር እየተጫወትንና ቁም ነገር እያወራን ስለምንቆይ ሁልጊዜ ከመንግሥት አዳራሹ መጨረሻ ከሚወጡት ቤተሰቦች አንዱ የእኛ ቤተሰብ እንደነበረ አስታውሳለሁ” በማለት ተናግሯል።

‘ልባችሁን መክፈት’ ይኖርባችሁ ይሆን?

8. (ሀ) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ‘ልባችሁን ክፈቱ’ ብሎ ሲመክራቸው ምን ማለቱ ነበር? (ለ) በጉባኤ ውስጥ ፍቅር እንዲሰፍን ምን ማድረግ እንችላለን?

8 እንዲህ ዓይነቱን ክርስቲያናዊ ፍቅር ይበልጥ ለማሳየት ‘ልባችንን መክፈት’ ያስፈልገን ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ ለነበሩ ክርስቲያኖች “ልባችንንም ወለል አድርገን ከፍተንላችኋል። . . . ፍቅራችንን አልነፈግናችሁም” ሲል ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም በአጸፋው ‘ልባቸውን ወለል አድርገው እንዲከፍቱ’ አሳስቧቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13) አንተስ ለሌሎች ፍቅር ለማሳየት ‘ልብህን መክፈት’ ይኖርብህ ይሆን? ሌሎች ወደ አንተ እስኪመጡ ድረስ መጠበቅ አያስፈልግህም። ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እርስ በርስ የመዋደድን አስፈላጊነት በገለጸበት ወቅት “እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ” የሚል ምክር አክሎ ሰጥቷል። (ሮሜ 12:10 የ1980 ትርጉም) በስብሰባዎች ላይ ሌሎች መጥተው ሰላም እስኪሉህ ድረስ ከመጠበቅ አንተ ቀዳሚ በመሆን አክብሮት ማሳየት ትችላለህ። አብረውህ እንዲያገለግሉ ወይም ለስብሰባ አንድ ላይ ሆናችሁ እንድትዘጋጁ ልትጋብዛቸው ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ በመካከላችሁ ያለው ፍቅር እያደገ እንዲሄድ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

9. አንዳንዶች ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር ምን አድርገዋል? (ከአካባቢህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ የምትፈልገው ካለ መናገር ትችላለህ።)

9 በጉባኤ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቤተሰቦች እርስ በርስ በመጠያየቅ፣ ምናልባትም ትንሽ ነገር አዘጋጅቶ በመገባበዝና አብሮ በመዝናናት ለሌሎች ‘ልባቸውን መክፈት’ ይችላሉ። (ሉቃስ 10:42፤ 14:12-14) ሃኮፕ የሚባል አንድ ወንድም አልፎ አልፎ የተወሰኑ ወንድሞች አብረውት ሽርሽር እንዲሄዱ ዝግጅት ያደርጋል። “ነጠላ ወላጆችን ጨምሮ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወንድሞችንና እህቶችን ለማካተት ጥረት አደርጋለሁ። ሁላችንም የማይረሳ ጊዜ አብረን የምናሳልፍ ከመሆኑም በላይ እርስ በርስ ያለን ፍቅር ከምንጊዜውም ይበልጥ ይጠናከራል” በማለት ተናግሯል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አንድ እምነት መጋራት ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ወዳጆች መሆን ይገባናል።—3 ዮሐንስ 14

10. ከወንድሞችና እህቶች ጋር አለመግባባት ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንችላለን?

10 ይሁን እንጂ ፍጽምና የጎደለን መሆናችን ወዳጅነታችንን እንዳናጠናክር አልፎ አልፎ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን? በመጀመሪያ ደረጃ ከወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዲኖረን መጸለይ እንችላለን። አምላክ አገልጋዮቹ እርስ በርስ ተስማምተው እንዲኖሩ ስለሚፈልግ እንዲህ ያለውን ጸሎት ይሰማል። (1 ዮሐንስ 4:20, 21፤ 5:14, 15) በተጨማሪም ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ ተግባር ሊኖረን ይገባል። በምሥራቅ አፍሪካ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግለው ሪክ አስቸጋሪ ጠባይ ከነበረው አንድ ወንድም ጋር መግባባት ቸግሮት እንደነበር ያስታውሳል። “ይህን ወንድም ከመራቅ ይልቅ ይበልጥ ቀርቤው ስለ እርሱ ለማወቅ ወሰንኩ። ከዚያም አባቱ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ምንም ሳያፈናፍን እንዳሳደገው ተረዳሁ። እንዲያውም ባሕርይውን ለማሻሻል ምን ያህል ጥረት እንዳደረገና እንደተለወጠ ስረዳ በጣም አደነቅሁት። ከዚያም የቅርብ ጓደኛሞች ሆንን” በማለት ተናግሯል።—1 ጴጥሮስ 4:8

ስሜታችሁን አትደብቁ!

11. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ፍቅር እንዲስፋፋ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? (ለ) ከልክ በላይ ከሰው መራቅና ቁጥብ መሆን በመንፈሳዊ ጎጂ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

11 በዛሬው ጊዜ ሕይወታቸውን ሙሉ አንድም የልብ ጓደኛ የሌላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው! በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግን እንዲህ ያለ ሁኔታ መከሰት አይኖርበትም። እውነተኛ የወንድማማች ፍቅር ሲባል እንዲያው በአክብሮት ሰላም መባባልና ጥቂት መጨዋወት ማለት ብቻ አይደለም፤ ወይም ደግሞ ዝም ብሎ ማውካካት ማለትም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዳደረገው ለወንድሞቻችን የሆዳችንን አውጥተን ማጫወት እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻችን ደኅንነት ከልብ እንደሚያሳስበን ማሳየት ይኖርብናል። ምንም እንኳ ሁሉም ሰው በተፈጥሮው ተጫዋች ወይም ተግባቢ ይሆናል ማለት ባይሆንም ከልክ በላይ ከሰው መራቅና ቁጥብ መሆን ጎጂ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውን ፍርድ ሁሉ ይቃወማል” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 18:1

12. የልብን አውጥቶ መጨዋወት በጉባኤ ውስጥ ያለውን ቅርርብ ይበልጥ በማጠናከር ረገድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ምንም ሳይደብቁ የልብን አውጥቶ መጨዋወት ለእውነተኛ ወዳጅነት ወሳኝ ነው። (ዮሐንስ 15:15) ሁላችንም የውስጣችንን አውጥተን የምንነግራቸው ወዳጆች ያስፈልጉናል። ከዚህም በላይ እርስ በርስ ይበልጥ በተዋወቅን መጠን በቀላሉ እንግባባለን። በዚህ መንገድ እርስ በርስ የምንተሳሰብ ከሆነ በጉባኤው ውስጥ ያለው ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንዲሄድ የምናደርግ ከመሆኑም በላይ ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በማለት የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ማየት እንችላለን።—የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ ፊልጵስዩስ 2:1-4

13. ለወንድሞቻችን ከልብ የመነጨ ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

13 ፍቅራችን በጎ ውጤት እንዲኖረው ከፈለግን ሰውረን ልንይዘው አይገባም። (ምሳሌ 27:5) ፍቅራችን እውነተኛ መሆን አለመሆኑ በፊታችን ላይ መነበቡ አይቀርም። ይህ ደግሞ ሌሎችም አጸፋውን እንዲመልሱ ይገፋፋቸዋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ብሩህ ገጽታ ልብን ደስ ያሰኛል” ይላል። (ምሳሌ 15:30) በተጨማሪም አሳቢነት በተግባር ሲገለጽ ፍቅርን ይበልጥ ያጠናክራል። ምንም እንኳ እውነተኛ ፍቅር በገንዘብ የሚገዛ ባይሆንም ከልብ የተሰጠ ስጦታ ትልቅ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ካርድ መስጠት፣ ደብዳቤ መጻፍ እንዲሁም በትክክለኛው ጊዜ “የተነገረ ቃል” ከልብ የመነጨ ፍቅርን ሊገልጽ ይችላል። (ምሳሌ 25:11፤ 27:9) አንዴ ወዳጅነት ከመሠረትን በኋላ ደግሞ ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር በማሳየት ወዳጅነታችን ቀጣይ እንዲሆን መጣር ይኖርብናል። በተለይ ወዳጆቻችን ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ ልንደርስላቸው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል።—ምሳሌ 17:17

14. ከአንድ ሰው ጋር የምንፈልገውን ያህል ልንቀራረብ ባንችል ምን ማድረግ እንችላለን?

14 በጉባኤ ውስጥ ካሉት ሁሉ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንመሠርታለን ማለት እንደማይቻል የታወቀ ነው። በተፈጥሯችን ከሌሎች አብልጠን ልንቀርባቸው የምንችላቸው ይኖራሉ። ለምሳሌ አንድን ሰው የምትፈልገውን ያህል ልትቀርበው ባትችል በአንተ ወይም በዚያ ሰው ላይ አንድ ችግር እንዳለ አድርገህ ለመደምደም አትቸኩል። ጓደኛ ካልሆንን ብለህም ለማስገደድ አትሞክር። ሁኔታው የፈቀደልህን ያህል ከቀረብከው ከጊዜ በኋላ የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት የምትችሉበት አጋጣሚ ክፍት እንዲሆን ታደርጋለህ።

“በአንተ ደስ ይለኛል”

15. አድናቆትን መግለጽ በሌሎች ላይ ምን ውጤት ያመጣል? ከማድነቅ መቆጠብስ?

15 ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት “በአንተ ደስ ይለኛል” የሚሉትን ቃላት ከሰማይ ሲሰማ በጣም ተደስቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም! (ማርቆስ 1:11) ኢየሱስ እነዚህን የአድናቆት ቃላት መስማቱ አባቱ እንደሚወደው ያለውን እምነት ይበልጥ አጠናክሮለት መሆን አለበት። (ዮሐንስ 5:20) የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶች ከሚያከብሯቸውና ከሚወዷቸው ሰዎች እንዲህ ያለ የአድናቆት ቃል ሰምተው አያውቁም። አን የተባለች አንዲት ወጣት “እንደ እኔ ያሉ ብዙ ወጣቶች እምነታቸውን በማይጋራ ቤተሰብ ውስጥ ይኖራሉ። ቤታችን ከትችት በስተቀር ሌላ ነገር አንሰማም። ይህ ደግሞ በጣም ያሳዝነናል” በማለት ተናግራለች። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ ወጣቶች የጉባኤው አባል ሲሆኑ እርስ በርሱ በሚረዳዳና በሚተሳሰብ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ እንደታቀፉ ስለሚሰማቸው ይደሰታሉ። በሌላ አባባል መንፈሳዊ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች ያገኛሉ።—ማርቆስ 10:29, 30፤ ገላትያ 6:10

16. ሌሎችን የመንቀፍ ዝንባሌ ጎጂ የሚሆነው ለምንድን ነው?

16 በአንዳንድ ባሕሎች ወጣቶችን ማመስገን የበለጠ ጥረት እንዳያደርጉ ወይም እንዲኮሩ ያደርጋቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ወላጆች፣ ትላልቅ ሰዎችና አስተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ለወጣቶች ያላቸውን አድናቆት ከመግለጽ ይቆጠባሉ። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በአንዳንድ ክርስቲያን ቤተሰቦችም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ይንጸባረቅ ይሆናል። አንድ ወጣት ንግግር ካቀረበ ወይም አንድ ዓይነት ሥራ ካከናወነ በኋላ ትላልቆች “ጥሩ ነው፤ ግን ከዚህ የበለጠ ማድረግ ትችል ነበር” በማለት አስተያየት ይሰጡ ይሆናል። ወይም ደግሞ በልጁ ሁኔታ እምብዛም እንዳልረኩ በተለያዩ መንገዶች ያሳያሉ። ብዙዎች እንዲህ ማድረጋቸው ወጣቶችን የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ እንደሚያነሳሳቸው ይሰማቸዋል። ነገር ግን ይህ ወጣቶች ተስፋ እንዲቆርጡ ወይም ብቃት እንደሌላቸው እንዲሰማቸው ስለሚያደርግ ብዙውን ጊዜ ጎጂ ውጤት ይኖረዋል።

17. ሌሎችን ለማመስገን የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?

17 ይሁን እንጂ አድናቆት ወይም ምስጋና ሁልጊዜ ምክር ለመለገስ እንደ መንደርደሪያ ተደርጎ ብቻ መሰጠት አይኖርበትም። እርስ በርስ ከልብ መመሰጋገን በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ፍቅር እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህ ደግሞ ወጣቶች የጎለመሱ ወንድሞችንና እህቶችን ቀርበው ምክር እንዲጠይቁ ይገፋፋቸዋል። ስለዚህ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ በአካባቢው ባሕል ከመመራት ይልቅ “እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው [እንልበስ]።” እኛም እንደ ይሖዋ አመስጋኞች እንሁን።—ኤፌሶን 4:24

18. (ሀ) ወጣቶች፣ ከትላልቆች ለሚሰጣችሁ ምክር ምን አመለካከት ሊኖራችሁ ይገባል? (ለ) ትላልቆች ምክር ከመስጠታቸው በፊት የሚያስቡበትና የሚጸልዩበት ለምንድን ነው?

18 በሌላ በኩል ግን እናንተ ወጣቶች፣ ትላልቅ ሰዎች እርማት ወይም ምክር ሲሰጧችሁ ይህን የሚያደርጉት ስለሚጠሏችሁ እንደሆነ አድርጋችሁ አታስቡ። (መክብብ 7:9) እንዲያውም ይህን ማድረጋቸው እንደሚወዷችሁ የሚያሳይ ማስረጃ ነው! ምክር ወይም እርማት ለመስጠት የተገፋፉት ስለሚያስቡላችሁና ከልብ ስለሚወዷችሁ ሊሆን ይችላል። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ እናንተን ለመምከር ይህን ያህል ምን አደከማቸው? ትላልቆች በተለይ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌዎች በጥሩ ሁኔታ የተሰጠ ምክር የሚያስገኘውን ውጤት ስለሚረዱ ብዙውን ጊዜ ምክር ከመስጠታቸው በፊት በደንብ ያስቡበታል እንዲሁም ይጸልዩበታል። ምንጊዜም ቢሆን ፍላጎታቸው መልካም ማድረግ ነው።—1 ጴጥሮስ 5:5

‘ይሖዋ እጅግ አፍቃሪ ነው’

19. አፍቃሪ በመሆናቸው ምክንያት በሌሎች የተጎዱ ሰዎች ይሖዋ እንደሚደግፋቸው እርግጠኞች መሆን የሚችሉት ለምንድን ነው?

19 አንዳንዶች በሌሎች በመጎዳታቸው ምክንያት ፍቅር ማሳየት ራስን ለተጨማሪ ጉዳት ከመዳረግ ውጪ ምንም ፋይዳ እንደማይኖረው ይሰማቸው ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ልባቸውን እንደገና ለመክፈት ድፍረትና ጠንካራ እምነት ጠይቆባቸዋል። ይሁንና ይሖዋ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ እንዳልሆነ’ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርባቸውም። ይሖዋ ሁላችንንም ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27፤ ያዕቆብ 4:8) በተጨማሪም ዳግም ላለመጎዳት ያለብንን ፍርሃት የሚረዳልን ከመሆኑም በላይ ከጎናችን በመቆም ሊደግፈን ቃል ገብቶልናል። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—መዝሙር 34:18

20, 21. (ሀ) ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት እንደምንችል እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስፈልገው ብቃት ምንድን ነው?

20 ከይሖዋ ጋር የሚኖረን የጠበቀ ወዳጅነት ልንመሠርተው ከምንችለው ከማንኛውም ዓይነት ግንኙነት በእጅጉ የላቀ ነው። ይሁንና ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ ወዳጅነት መመሥረት ይቻላል? አዎን፣ ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሰማዩ አባታችን ጋር የቀረበ ወዳጅነት ስለመሠረቱ ጻድቅ ወንዶችና ሴቶች ይናገራል። እነዚህ ሰዎች የተናገሩት ሐሳብ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ የቆየልን እኛም ወደ ይሖዋ መቅረብ እንደምንችል ለማበረታታት ነው።—መዝሙር 23, 34, 139፤ ዮሐንስ 16:27፤ ሮሜ 15:4

21 ማንም ቢሆን ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ማሟላት ከአቅም በላይ አይሆንበትም። ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል?” በማለት ጠይቆ ነበር። ከዚያም “አካሄዱ ንጹሕ የሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር” በማለት መልስ ሰጥቷል። (መዝሙር 15:1, 2፤ 25:14) አምላክን ማገልገል መልካም ፍሬ እንድናፈራ እንዲሁም የእርሱን አመራርና ጥበቃ እንድናገኝ ያስችለናል፤ ይህ ደግሞ ‘ይሖዋ እጅግ አፍቃሪ’ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል።—ያዕቆብ 5:11 NW

22. ይሖዋ ሕዝቦቹ ምን ዓይነት ዝምድና እንዲመሠርቱ ይፈልጋል?

22 ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ሆነን ሳለ ይሖዋ ከእኛ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ለመመሥረት መፈለጉ ለእኛ ትልቅ መብት ነው! ታዲያ እኛስ እርስ በርሳችን ከልብ መዋደድ አይኖርብንም? እያንዳንዳችን በይሖዋ እርዳታ የክርስቲያን ወንድማማች ማኅበር ዓይነተኛ መለያ የሆነው ፍቅር እንዲዳብር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ይህን ፍቅር ለዘላለም ያንጸባርቃል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ መስፈን ይኖርበታል?

• እያንዳንዳችን በጉባኤ ውስጥ ፍቅር እንዲሰፍን ምን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን?

• እርስ በርስ ከልብ መመሰጋገን ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዲዳብር የሚያደርገው እንዴት ነው?

• ይሖዋ አፍቃሪ መሆኑ ብርታት የሚጨምርልን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች እርስ በርስ የሚዋደዱት እንደዚያ የማድረግ ኃላፊነት ስላለባቸው ብቻ አይደለም

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንተስ ለሌሎች ፍቅር ለማሳየት ‘ልብህን መክፈት’ ትችል ይሆን?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚቀናህ ምንድን ነው? መተቸት ወይስ ማበረታታት?