በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዕድሜ ልክ የዘለቀ ሥልጠና

ዕድሜ ልክ የዘለቀ ሥልጠና

የሕይወት ታሪክ

ዕድሜ ልክ የዘለቀ ሥልጠና

ሃረልድ ግሉየስ እንደተናገረው

በልጅነቴ የተፈጸመው የሚከተለው ሁኔታ ከተከሰተ ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም ከአእምሮዬ አልጠፋም። ወጥ ቤት ቁጭ ብዬ “ሲሎን ሻይ” የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ማሸጊያ እመለከታለሁ። በማሸጊያው ላይ በለምለም የሲሎን (አሁን ስሪ ላንካ ይባላል) እርሻ ውስጥ ሻይ ቅጠል የሚለቅሙ ሴቶች ምስል ይታያል። እኛ ከምንኖርበት ደረቁ የደቡብ አውስትራሊያ ክፍል በጣም ርቆ የሚገኘውን ይህን ቦታ በዓይነ ህሊናዬ በአድናቆት መመልከት ጀመርኩ። ሲሎን የተዋበና አስደሳች አገር መሆን አለበት ስል አሰብኩ! ያን ጊዜ በዚያ ውብ ደሴት ላይ በሚስዮናዊነት ከሕይወት ዘመኔ አርባ አምስቱን ዓመታት እንደማሳልፍ በጭራሽ አልገመትኩም ነበር።

የተወለድኩት በሚያዝያ ወር 1922 ሲሆን በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም አሁን ካለው ፈጽሞ የተለየ ነበር። በሠፊው የአውስትራሊያ አህጉር መሃል ባለው ታላቁ በረሃ ደቡባዊ ጫፍ ላይ በሚገኘው ኪምባ በተባለ የገጠር ከተማ አቅራቢያ የራሳችን የሆነ የእህል እርሻ ነበረን። ክልሉ በድርቅ እንዲሁም በተለያዩ ተባዮችና ነፍሳት የሚጠቃ እጅግ ሞቃታማ የሆነ ሥፍራ በመሆኑ ምክንያት ጫካ ውስጥ ባለው ከቆርቆሮ በተሠራ ጎጆአችን የስጋት ኑሮ እንኖር ነበር። እናቴ እኔን ጨምሮ ስድስት ልጆቿንና አባቴን ለመንከባከብ ጠንክራ ትሠራ ነበር።

ይሁን እንጂ በዚህ ሥፍራ መኖር ለእኔ ደስታና ነጻነት ይሰጠኝ ነበር። በልጅነቴ ኃይለኛ ኮርማዎች መሬቱን እየጎደፈሩ ቁጥቋጦውን ሲያወድሙት ወይም ደግሞ የሚያፏጭ ኃይለኛ ነፋስ አቧራውን እያነሳ አገሩን ሲሸፍነው ስመለከት ምን ያህል እገረም እንደነበር አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል። በመሆኑም እውቀት መቅሰም የጀመርኩት ከቤታችን አምስት ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘውና አንድ አስተማሪ ብቻ ወዳለበት ትንሽ ትምህርት ቤት በእግር እየተመላለስኩ መማር ከመጀመሬ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው።

ወላጆቼ በቦታ ርቀት ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ሄደው ባያውቁም ሃይማኖተኞች ነበሩ። እናቴ በ1930ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ በአደሌድ በሚገኘው የሬዲዮ ጣቢያ በየሳምንቱ የሚተላለፈውን የጀጅ ራዘርፎርድን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ታዳምጥ ነበር። ጀጅ ራዘርፎርድ በአደሌድ የሚገኝ ተራ ሰባኪ ይመስለኝ ስለነበር ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም። እናቴ ግን በባትሪ የሚሠራው አሮጌው ሬዲዮናችን ቁርጥርጥ እያደረገ የሚያሰማውን የራዘርፎርድ ንግግር በየሳምንቱ ሥራዬ ብላ እየተጠባበቀች ትከታተል ነበር።

ዕለቱ ሞቃትና አቧራማ ነበር፤ በዚያን ቀን ከሰዓት በኋላ ላይ አሮጌ የጭነት መኪና በራችን ላይ ቆመና ሁለት ጥሩ አለባበስ ያላቸው ሰዎች ወረዱ። ሰዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እናቴ መልእክታቸውን ካዳመጠች በኋላ የገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ በርከት ያሉ መጻሕፍት ወሰደችና ወዲያውኑ ማንበብ ጀመረች። ባነበበችው ነገር ስሜቷ በጥልቅ በመነካቱ ስላወቀችው ነገር በአካባቢያችን ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ለመወያየት አባቴ በመኪና ይዟት እንዲሄድ ጠየቀችው።

በጎ ተጽዕኖዎች ያስገኙልኝ ጥቅም

የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን ከመጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ አስቸጋሪ የነበረው የአካባቢያችን አየር ጠባይ 500 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው አደሌድ ከተማ መኖሪያችንን እንድንቀይር አስገደደን። ከዚያም ቤተሰባችን በአደሌድ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መሰብሰብና መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጀመረ። ወደ አደሌድ በመዘዋወራችን ምክንያት በ13 ዓመቴ ሰባተኛ ክፍልን ካጠናቀቅኩ በኋላ ትምህርቴን አቋረጥኩ። በተፈጥሮዬ ነገሮችን አቅልሎ የመመልከት ዝንባሌ ስለነበረኝ አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ ጥሩ ወንድሞች በአሳቢነት ባይረዱኝ ኖሮ በመንፈሳዊ እደክም ነበር።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እነዚህ ቀናተኛ ወንድሞች ያሳደሩብኝ በጎ ተጽዕኖ በውስጤ ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንዲተከል አደረገ። ከእነርሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ በጣም ያስደስተኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ታታሪነታቸው እጅግ ያስደንቀኝ ነበር። በመሆኑም በ1940 በአደሌድ ተደርጎ በነበረው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድንካፈል የሚያበረታታ ማስታወቂያ ስሰማ በዚህ አገልግሎት ለመሠማራት ተመዘገብኩ፤ ይህ እኔንም አስገርሞኝ ነበር። በወቅቱ ገና ካለመጠመቄም በላይ በስብከቱ ሥራ ብዙም ተሞክሮ አልነበረኝም። የሆነ ሆኖ ከጥቂት ቀናት በኋላ ዎርነምቡል በሚባል ከአደሌድ በጣም ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ የቪክቶሪያ አዋሳኝ በሆነ ግዛት ካሉ ጥቂት አቅኚዎች ጋር እንዳገለግል ተጋበዝኩ።

በመጀመሪያ ግብዣውን ለመቀበል አንገራግሬ ነበር፤ ደስ የሚለው ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለመስክ አገልግሎት ለዓመታት ያልቀዘቀዘ ፍቅር እያደረብኝ መጣ። እንዲያውም ይህ ሁኔታ በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ በማምጣቱ እውነተኛ የሆነ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ቻልኩ። ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር ካላቸው ሰዎች ጋር መወዳጀት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተምሬያለሁ። ምንም ዓይነት የትምህርት ደረጃ ቢኖረን መልካም ምሳሌነታቸው እንደሚቀርጸንና ይህም በዕድሜያችን ሁሉ እንደሚጠቅመን ተገንዝቤያለሁ።

ፈተናዎች ያስገኙልኝ ጥንካሬ

በአቅኚነት ካገለገልኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአውስትራሊያ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታገደ። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገብቶኝ ወንድሞችን ሳማክራቸው፣ እገዳው ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማነጋገር እንደማይከለክል ገለጹልኝ። ስለዚህ አጭር የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ይዤ ከሌሎች አቅኚዎች ጋር ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመርኩ። ይህም ብዙም ሳይቆይ የገጠመኝን ፈተና ለመወጣት የሚያስችል ብርታት እንዳገኝ ረድቶኛል።

ከአራት ወራት በኋላ 18 ዓመት ስለሞላኝ ለውትድርና አገልግሎት እንድመዘገብ የሚገልጽ መጥሪያ ደረሰኝ። በዚህ አጋጣሚ ለበርካታ የጦር ኃይል ሹማምንትና ለአንድ የሕግ ባለ ሥልጣን ስለ እምነቴ ምሥክርነት መስጠት ቻልኩ። ከዚያም በገለልተኛ አቋማቸው ምክንያት በአደሌድ ታስረው ከነበሩ 20 የሚያህሉ ወንድሞች ጋር ታሰርኩ። እንደ ድንጋይ መፍለጥና መንገድ መሥራት ያሉ ከባድ የጉልበት ሥራዎችን እንድንሠራ ተደረግን። እነዚህ ጊዜያት ጽናትንና ቆራጥነትን የመሳሰሉ ባሕርያት እንዳዳብር ረድተውኛል። የኋላ ኋላ በመልካም ባሕርያችንና በጽኑ አቋማችን ምክንያት ብዙ የእስር ቤት ጠባቂዎች ያከብሩን ጀመር።

ከወራት እስር በኋላ ነፃ ወጣሁና ከታሰርኩ ወዲህ አግኝቼው የማላውቀውን ጥሩ ምግብ ተመግቤ እንደገና የአቅኚነት ሥራዬን ጀመርኩ። አቅኚ የአገልግሎት ጓደኛ በብዛት ስለማይገኝ ብቻዬን ደቡብ አውስትራሊያ በሚገኝ ሩቅ የእርሻ ቦታ እንዳገለግል ተጠየቅኩ። ጥያቄውን ተቀብዬ ብስክሌቴንና ለአገልግሎት የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ብቻ ይዤ በመርከብ ወደ ዮርክ ባህረ ገብ ምድር ተጓዝኩ። እዛም እንደደረስኩ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያለው አንድ ቤተሰብ ወደ አንድ አነስተኛ የእንግዶች ማረፊያ ወሰደኝ፤ በዚያ ቦታ የነበሩ አንዲት በጣም ደግ ሴት ልክ እንደ ልጃቸው ይንከባከቡኝ ነበር። ቀን ቀን አቧራማ በሆነው መንገድ ከዮርክ ባሻገር ተራርቀው ወደሚገኙ ትንንሽ መንደሮች በብስክሌት እየሄድኩ አገለግላለሁ። ራቅ ያሉ የአገልግሎት ክልሎችን ለመሸፈን እንዲያመቸኝ አልፎ አልፎ እዚያው ባሉ ትንንሽ ሆቴሎችና እንግዳ ማረፊያዎች አድራለሁ። በዚህ ሁኔታ በርካታ ኪሎ ሜትሮች በብስክሌት በመጓዝ ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎችን ማግኘት ችያለሁ። ብቻዬን በማገልገሌ ብዙም ቅር አይለኝም ነበር፤ እንዲያውም የይሖዋን እንክብካቤ በማየቴ ይበልጥ ከእርሱ ጋር ተቀራርቤያለሁ።

ብቁ አይደለሁም ከሚል ስሜት ጋር መታገል

በ1946 ተጓዥ የወንድሞች አገልጋይ (አሁን የወረዳ የበላይ ተመልካች ይባላል) ሆኜ እንዳገለግል የሚጋብዝ ደብዳቤ ደረሰኝ። ሥራው በተመደብኩበት ወረዳ የሚገኙ በርካታ ጉባኤዎች መጎብኘትን ይጨምራል። እውነት ለመናገር ይህ ሥራ ያስከተለብኝ ኃላፊነት በጣም ከብዶኝ ነበር። አንድ ቀን አንድ ወንድም እንዲህ ሲል ጆሮዬ ጥልቅ አለ፦ “ሃረልድ ከመድረክ ሲናገር እጅግም ነው፤ በመስክ አገልግሎት ግን የተዋጣለት ሰው ነው።” ይህን ስሰማ በጣም ተበረታታሁ። ምክንያቱም በንግግርም ሆነ በማደራጀት በኩል ብዙም ችሎታ እንደሌለኝ ብገነዘብም ክርስቲያኖች በአንደኛ ደረጃ ማከናወን የሚገባቸው የስብከቱን ሥራ እንደሆነ አውቃለሁ።

በ1947 ወንድም ናታን ኖር እና ሚልተን ሄንሽል ብሩክሊን ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት መጥተው ጎበኙን። ይህም በ1938 ወንድም ራዘርፎርድ ከመጣ በኋላ የተደረገልን የመጀመሪያው ጉብኝት ነበር። ከጉብኝቱ ጋር ተያይዞ በሲድኒ ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ተዘጋጀ። በዚያን ጊዜ ገደማ ሚስዮናውያንን ለማሠልጠን በዩ ኤስ ኤ፣ ኒው ዮርክ፣ ሳውዝ ላንሲንግ ተከፍቶ በነበረው ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድንሠለጥን ግብዣ ቀረበልን፤ እኔም ሆንኩ ሌሎች ወጣት አቅኚዎች ሥልጠናውን ለማግኘት ጓጓን። ነገር ግን በትምህርት ቤቱ ለመመዝገብ የግድ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያስፈልግ ይሆን? የሚለው ነገር አብዛኛውን ተሰብሳቢ አሳስቦት ነበር። ወንድም ኖር መጠበቂያ ግንብ ማንበብና ቁልፍ የሆኑ ነጥቦችን ማስታወስ ከቻልን በጊልያድ መሠልጠን እንደማይከብደን ገለጸልን።

ብዙም ስላልተማርኩ ብቁ ላልሆን እችላለሁ ብዬ አስቤ ነበር። ሆኖም ከበርካታ ወራት በኋላ ለጊልያድ ሥልጠና እንዳመለክት ስጋበዝ ማመን አቃተኝ። ማመልከቻዬ ተቀባይነት አግኝቶ በ1950 በ16ኛው የጊልያድ ክፍል ሰለጠንኩ። በዚህ ትምህርት ቤት መካፈሌ በራሴ እንድተማመን ያደረገኝ ከመሆኑም በላይ ስኬት ለማግኘት የሚያስፈልገው ትልቁ ነገር በቀለም ትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ እንዳልሆነ መገንዘብ ችያለሁ። ከዚህ ይልቅ በዋነኝነት የሚያስፈልጉት ነገሮች ትጋትና ታዛዥነት ናቸው። አስተማሪዎቻችን የተቻለንን ጥረት እንድናደርግ አበረታተውናል። ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋሌ ጥሩ መሻሻል እንዳደርግና መመሪያዎችን በደንብ ማክበርን እንድማር ረድቶኛል።

ከደረቁ አህጉር ወደ ውቧ ደሴት መጓዝ

ከትምህርት ቤቱ ከተመረቅኩ በኋላ ከሁለት አውስትራሊያውያን ወንድሞች ጋር በሲሎን (አሁን ስሪ ላንካ ትባላለች) እንዳገለግል ተመደብኩና መስከረም 1951 ዋና ከተማዋ ኮሎምቦ ደረስን። የአየር ንብረቱ ሞቃታማና እርጥበት አዘል የነበረ ሲሆን የምናያቸው አዳዲስ ነገሮች፣ የምንሰማው ድምፅ እና የሚሸቱት መልካም መዓዛ ያላቸው ነገሮች አንድ ላይ ተዳምረው ትኩረታችንን ሳቡት። ከመርከብ ስንወርድ በሚስዮናዊነት በዚያው ሲያገለግል የነበረ አንድ ወንድም ተቀበለኝና በመጪው እሁድ ዕለት በከተማይቱ አደባባይ የሚቀርበውን የሕዝብ ንግግር የሚያስተዋውቅ መጋበዣ ወረቀት ሰጠኝ። የሚገርመው በመጋበዣ ወረቀቱ ላይ የተጠቀሰው ተናጋሪ እኔ ነበርኩ! ምን ያህል እንደፈራሁና እንደተጨነቅኩ ልትገምቱ ትችላላችሁ። ነገር ግን በአውስትራሊያ በአቅኚነት ባሳለፍኳቸው ዓመታት የተሰጠኝን ሥራ ሁሉ መቀበል እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። በመሆኑም በይሖዋ እርዳታ የሕዝብ ንግግሩን በጥሩ ሁኔታ ማቅረብ ቻልኩ። ሦስታችንም ከእኛ ቀደም ብለው በሲሎን ማገልገል ከጀመሩትና በኮሎምቦ የሚስዮናውያን ቤት ከሚኖሩት አራት ነጠላ ወንድሞች ጋር ሆነን አስቸጋሪውን የሲንሃላ ቋንቋ መማርና በመስክ አገልግሎት መካፈል ጀመርን። አብዛኛውን ጊዜ የምናገለግለው ለየብቻ ሆነን ነበር፤ ያገሬው ሕዝብ ሰው አክባሪና እንግዳ ተቀባይ ሆኖ ማግኘታችን በጣም አስደሰተን። ብዙም ሳይቆይ የተሰብሳቢው ቁጥር እየጨመረ መጣ።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ጊልያድ ትምህርት ቤት ለመሠልጠን በመርከብ ስጓዝ ስለተዋወቅኳት ሲበል የተባለች አንዲት የምታምር አቅኚ ማሰብ ጀመርኩ። እሷ በኒው ዮርክ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለመገኘት እየተጓዘች ነበር። በኋላም በ1953 በተካሄደው የጊልያድ 21ኛ ክፍል ከሰለጠነች በኋላ ሆንግ ኮንግ ተመደበች። በደብዳቤ መገናኘት ጀመርንና እስከ 1955 ድረስ ከተጻጻፍን በኋላ ሲሎን መጥታ ተጋባን።

አብረን በሚስዮናዊነት እንድናገለግል የተመደብንበት የመጀመሪያው ቦታ በሰሜን ስሪ ላንካ ጫፍ የሚገኘው ጃፍና ከተማ ነው። በ1950ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ሲንሃላዎችንና ታሚሎችን የከፋፈለና ለአሥርተ ዓመታት ጦር ያማዘዘ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ተቀሰቀሰ። የሲንሃላና የታሚል የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ አስቸጋሪ ዓመታት እርስ በርሳቸው ሲደጋገፉና ሲረዳዱ መመልከት እንዴት ልብን ደስ ያሰኛል! እነዚህ ፈተናዎች የወንድሞች እምነት እንዲጠራና እንዲጠነክር አድርገዋል።

በስሪ ላንካ መስበክና ማስተማር

ከሂንዱና ከሙስሊም ማኅበረሰቦች ጋር መላመድ ትልቅ ትዕግሥትና ጽናት ይጠይቃል። እየቆየን ግን ባህላቸውንና ድንቅ የሆኑ ባሕርይዎቻቸውን መውደድ ጀመርን። የውጭ አገር ዜጎች በከተማ አውቶቡስ መጓዛቸው ያልተለመደ ነገር በመሆኑ አውቶቡስ ውስጥ ከገባን ብዙውን ጊዜ አፍጥጠው ይመለከቱን ነበር። ሲበል ሰዎቹ ሲያዩን ጥሩ ፈገግታ ለማሳየት አሰበች። በግርምት የሚያዩን መንገደኞች ፈገግ ብለው አጸፋውን ሲመልሱ መመልከት እንዴት ደስ ይላል!

አንድ ቀን ኬላ ላይ ቆመን ሳለ ተረኛ የነበረው ጠባቂ ከየት እንደመጣንና ወዴት እንደምንሄድ ከጠየቀን በኋላ ስለግል ጉዳያችን ያነሳ ጀመር።

“ይህች ሴት ምንህ ናት?”

እኔም “ባለቤቴ ነች” ብዬ መለስኩለት።

“ከተጋባችሁ ስንት ጊዜ ሆናችሁ?”

“ስምንት ዓመት ሆኖናል።”

“ልጆች ወልዳችኋል?”

“አይ፣ አልወለድንም።”

“እንዴት አልወለዳችሁም? ሐኪም አማክራችኋል?”

መጀመሪያ ላይ እንዲህ ያለው የሰውን ገመና የማወቅ ጉጉት በጣም አስገርሞን ነበር፤ በኋላ ግን የአገሬው ሰዎች ለሌሎች ከልብ የመነጨ አሳቢነት እንዳላቸው የሚገልጹት በዚህ መንገድ መሆኑን ተገነዘብን። እንዲያውም ካሏቸው ጥሩ ባሕርያት አንዱ ይሄ ነው። አንድ ሰው ሕዝብ በሚበዛበት አካባቢ ለጥቂት ጊዜ ቢቆም አንዱ ቀረብ ይለውና ሊረዳው የሚችለው ነገር እንዳለ በደግነት ይጠይቀዋል።

ያጋጠሙኝ ለውጦች እና ትውስታዎች

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በስሪ ላንካ ከሚስዮናዊነት አገልግሎት በተጨማሪ በሌሎች ሥራዎችም ላይ መካፈል ችለናል። በወረዳና በአውራጃ የበላይ ተመልካችነት እንዲሁም በቅርንጫፍ ኮሚቴ አባልነት ሠርቻለሁ። ወደ ሰባዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ተዳርሼ በነበርኩበት በ1996፣ በስሪ ላንካ በሚስዮናዊነት አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን ከ45 የሚበልጡ ዓመታት ወደኋላ መለስ ብዬ ስመለከት ልዩ ደስታ ተሰምቶኛል። በኮሎምቦ በተገኘሁበት የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የተገኙት 20 ሰዎች ብቻ ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ግን ቁጥሩ ከ3,500 በላይ ሆኗል! እኔና ሲበል ከእነዚህ ውድ ወንድሞች ውስጥ አብዛኞቹን እንደ መንፈሳዊ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን አድርገን እንመለከታቸዋለን። ሆኖም በአገሪቱ ውስጥ ከእኛ የተሻለ ችሎታና ጉልበት ባላቸው ወጣቶች የሚሠራ ገና ብዙ ሥራ ነበር። ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአስተዳደር አካሉ ወደ አውስትራሊያ እንድንመለስ ያቀረበልንን ጥያቄ ተቀበልን። ስሪ ላንካን ለቅቀን መውጣታችን ብቁ የሆኑ ሌሎች በዕድሜ ከእኛ ያነሱ ባልና ሚስት ሚስዮናውያን እኛን ተክተው እንዲሠሩ መንገድ ከፍቷል።

አሁን 82 ዓመት ሆኖኛል፤ እኔም ሆንኩ ሲበል በቀድሞ መኖሪያዬ በአደሌድ ልዩ አቅኚዎች ሆነን ለማገልገል የሚያስችል ጤንነት ስላለን በጣም ደስተኞች ነን። በአገልግሎት መካፈላችን አእምሯችን ንቁ እንዲሆንና ከአዳዲስ ነገሮች ጋር በቀላሉ እንድንላመድ አስችሎናል። እንዲሁም ከስሪ ላንካ በጣም የሚለየውን የአውስትራሊያ ኑሮ እንደገና እንድንለምድ ረድቶናል።

ይሖዋ በቁሳዊ ነገር ረገድ እኛን መንከባከቡን አላቋረጠም፤ በጉባኤያችን የሚገኙት ወንድሞችና እህቶች ፍቅርና ድጋፍም አልተለየንም። በቅርቡ በጉባኤያችን ጸሐፊ ሆኜ እንዳገለግል ተመድቤያለሁ። ይህም ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል እስከተጣጣርኩ ድረስ የማገኘው ሥልጠና እንደሚቀጥል አስገንዝቦኛል። ነገሮችን አቅልሎ የመመልከት ልማድ የነበረኝ በጫካ ውስጥ ያደግኩ ተራ ልጅ ይህን የመሰለ የዕድሜ ልክ ሥልጠና ማግኘቴን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ሁልጊዜ ያስገርመኛል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1955 በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሬገን ካዲርጋማር ከተባለ የስሪ ላንካ ተወላጅ ወንድም ጋር በ1957 በመስክ አገልግሎት ላይ እያለን

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከሲበል ጋር