በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን የምትጠባበቀው ምን ዓይነት ዝንባሌ ይዘህ ነው?

ይሖዋን የምትጠባበቀው ምን ዓይነት ዝንባሌ ይዘህ ነው?

ይሖዋን የምትጠባበቀው ምን ዓይነት ዝንባሌ ይዘህ ነው?

በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ምንም ነገር ለመጠበቅ ትዕግሥት የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የአምላክ ሕዝቦች በትዕግሥት ‘የመጠበቅን’ ባሕርይ እንዲኮተኩቱ ያበረታታል። ነቢዩ ሚክያስ በዙሪያው ከነበሩት ሰዎች በተቃራኒ “አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ” በማለት ተናግሯል።—ሚክያስ 7:7፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26 NW

ይሖዋን መጠበቅ ሲባል ግን ምን ማለት ነው? አንድ ክርስቲያን አምላክን መጠበቅ ያለበት ምን ዓይነት ዝንባሌ ይዞ ነው? በዚህ ረገድ ትክክለኛና የተሳሳተ ዝንባሌ አለ? ከክርስቶስ ልደት በፊት በዘጠነኛው መቶ ዘመን በነቢይነት ያገለግል የነበረው የዮናስ ታሪክ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ትምህርት ይሰጠናል።

የተሳሳተ ዝንባሌ ይዞ መጠበቅ

ይሖዋ አምላክ የአሦር ግዛት ዋና ከተማ ለነበረችው ለነነዌ ነዋሪዎች እንዲሰብክ ዮናስን ላከው። ነነዌ በጣም ጨካኝና ክፉ ስለነበረች ‘የደም ከተማ’ ተብላ ተጠርታለች፤ ይህ ነገር እውነት መሆኑን ታሪክ ጸሐፊዎችና የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል። (ናሆም 3:1) መጀመሪያ ላይ ዮናስ ከተሰጠው ተልእኮ ለመሸሽ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ይሖዋ ወደ ነነዌ እንዲሄድ አድርጎታል።—ዮናስ 1:3-3:2

“ዮናስም ወደ ከተማዪቱ ገብቶ የመጀመሪያውን ቀን ከተጓዘ በኋላ ‘ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች’ ብሎ ዐወጀ።” (ዮናስ 3:4) የዮናስ ጥረት አስደናቂ ውጤት አስገኘ፦ “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾምንም ዐወጁ፤ ሰዎቹም ሁሉ ከትልቁ እስከ ትንሹ ማቅ ለበሱ።” (ዮናስ 3:5) ይሖዋ “ማንም እንዳይጠፋ” እና “ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ” የሚፈልግ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ለከተማዪቱ ምህረት አደረገላት።—2 ጴጥሮስ 3:9

በዚህ ጊዜ ዮናስ ምን ተሰማው? ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “ዮናስ ግን ፈጽሞ አልተደሰተም፤ ስለዚህም ተቆጣ።” (ዮናስ 4:1) ለምን? ዮናስ ከተወሰነ ቀን በኋላ ጥፋት እንደሚመጣ የተናገረው ትንቢት ሳይፈጸም መቅረቱ የነቢይነቱን ክብር እንደሚነካበት ሳይሰማው አልቀረም። እሱን አሳስቦት የነበረው የሌሎች ምህረት ማግኘትና መዳን ሳይሆን የራሱ ክብር እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

እርግጥ ነው፣ ዮናስ የነቢይነት ሥራውን እስከማቆም ደረጃ አልደረሰም። እንዲያውም ‘በከተማዪቱ የሚሆነውን ለማየት’ ይጠባበቅ ነበር። ሆኖም ይህን ያደረገው በቁጭትና በብስጭት ነበር። ነገሮች እሱ ባሰበው መንገድ ባለመፈጸማቸው ተበሳጭቶና አዝኖ በሠራው ዳስ ጥላ ሥር ተቀምጦ የሚሆነውን ነገር ይጠባበቅ ጀመር። ይሖዋ ግን በዮናስ ዝንባሌ ባለመደሰቱ አመለካከቱን እንዲያስተካክል ፍቅራዊ እርማት ሰጠው።—ዮናስ 4:5, 9-11

ይሖዋ ለምን ይታገሳል?

ነነዌ ንስሐ በመግባቷ ምህረት ቢደረግላትም ከጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ ክፉ መንገዷ ተመለሰች። ይሖዋ በነቢያቱ በናሆምና በሶፎንያስ በኩል ስለ ጥፋቷ ትንቢት አስነገረ። ይሖዋ አሦርን በማጥፋትና ነነዌን ባድማ በማድረግ ይህችን ‘የደም ከተማ’ ከሕልውና ውጪ እንደሚያደርጋት ገልጿል። (ናሆም 3:1፤ ሶፎንያስ 2:13) በ632 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነነዌ ዳግም ላታንሰራራ ወደመች።

በተመሳሳይም ዛሬ ያለንበት ዓለም ከጥንቷ ነነዌ በበለጠ ይህ ነው የማይባል የደም ዕዳ ተከምሮበታል። በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ ይሖዋ ይህ ክፉ ሥርዓት ታይቶ በማያውቅ “ታላቅ መከራ” እንዲጠፋ በይኖበታል።—ማቴዎስ 24:21, 22

ሆኖም ይሖዋ ጥፋቱን ቶሎ ባለማምጣቱ ዛሬ ያሉ ቅን ሰዎች ልክ እንደ ተጸጸቱት የነነዌ ነዋሪዎች ንስሐ ሊገቡና ከጥፋቱ ሊድኑ ይችላሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ የአምላክን ትዕግሥት እንደሚከተለው ሲል ገልጾታል፦ “አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።”—2 ጴጥሮስ 3:9, 10, 13

ትክክለኛ ዝንባሌ ይዞ መጠበቅ

ጴጥሮስ ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል።” (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) የይሖዋን ቀን ስንጠባበቅ ‘ቅድስናና እውነተኛ መንፈሳዊነት’ ማሳየት እንደሚገባን ልብ እንበል፤ እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለን ሳይሆን እንቅስቃሴ እያደረግን መጠባበቅ ያስፈልገናል።

አዎን፣ ትክክለኛ ዝንባሌ ይዘን የምንጠባበቅ ከሆነ የይሖዋ ቀን እሱ ካሰበው ጊዜ ለአፍታም ሳይዘገይ እንደሚመጣ እርግጠኞች እንሆናለን። እንዲህ ያለው እምነት ቅዱስ የሆኑ ተግባራትን እንድናከናውን የሚያነሳሳን ሲሆን ከእነዚህ ቅዱስ ተግባራት ትልቁን ቦታ የሚይዘው ደግሞ የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ነው። ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ በመሥራት በኩል ግሩም ምሳሌ የተወልን ከመሆኑም በላይ ለቅቡዓን ተከታዮቹ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸዋል፦ “በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ ጌታቸው ከሰርግ ግብዣ እስኪመለስ እንደሚጠባበቁና መጥቶም በር ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት ዝግጁ የሆኑ ሰዎች[ን] ምሰሉ። ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው።”—ሉቃስ 12:35-37

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ባሮች ወገባቸውን ‘በመታጠቅ’ እና የልብሳቸውን ጫፍ ወደ ላይ በመሰብሰብ አድካሚ የሆኑ ሥራዎችን በቅልጥፍና ይሠሩ ነበር። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን መልካም ሥራዎችን ለመሥራት ታታሪና ቀናተኛ መሆን ይገባዋል። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ “ወደ ኋላ” የማለትን ዝንባሌ መዋጋት ይኖርበታል፤ ምናልባትም ኃይሉን ተድላንና ቁሳዊ ሃብትን ለማሳደድ እየተጠቀመበት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ‘በጌታ ሥራ ዘወትር እየተጋ’ ታላቁንና የሚያስፈራውን የይሖዋ ቀን መጠባበቅ አለበት።—ሮሜ 12:11፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58

በሥራ ተጠምደን መጠባበቅ

የይሖዋ ምሥክሮች የይሖዋን ቀን የሚጠባበቁት ራሳቸውን በመንፈሳዊ ሥራ አስጠምደው ነው። በ2003 የአገልግሎት ዓመት በየቀኑ በአማካይ 3,383,000 ሰዓቶችን የይሖዋን ቃል በመስበክ አሳልፈዋል። እስቲ አስበው፤ አንድ ሰው ለስብከቱ ሥራ የዋለውን ይህን ያህል ሰዓት ላገልግል ቢል ያለማቋረጥ 386 ዓመታት መስበክ አለበት!

ነገር ግን ራሳችንን እንዲህ እያልን ብንጠይቅ ጥሩ ነው፦ ‘እኔ በበኩሌ ይሖዋን እየተጠባበቅኩ ያለሁት በምን ዓይነት ዝንባሌ ነው?’ ኢየሱስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ታታሪነት የሚጠበቅባቸው መሆኑን የሚገልጽ አንድ ምሳሌ ሰጥቷል። ስለ ሦስት ባሮች እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “[ጌታው] ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጉዞውን ቀጠለ። አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ። የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ።”—ማቴዎስ 25:15-19

ሦስቱም ባሮች የጌታቸውን መመለስ ይጠባበቁ ነበር። እርሱም ሲመለስ፣ ራሳቸውን በሥራ በማስጠመድ መምጣቱን ይጠባበቁ የነበሩትን ሁለቱን ባሮች በየተራ “ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ” ብሎ አመሰገናቸው። እጁን አጣጥፎ ቁጭ ብሎ ይጠብቅ የነበረው ባሪያ የገጠመው ነገር ግን የተለየ ነበር። ጌታው “ይህን የማይረባ አገልጋይ . . . በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት” አለ።—ማቴዎስ 25:20-30

ምንም እንኳ ይህ ምሳሌ የሚሠራው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆንም ተስፋችን ምንም ይሁን ምን ለሁላችንም የሚሆን ትምህርት ይዟል። በጌታው የተመሰለው ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዳችን የይሖዋ ታላቅ ቀን የሚመጣበትን ጊዜ በትጋት እየሠራን እንድንጠባበቅ ይፈልግብናል። እያንዳንዱ ሰው “እንደ ችሎታው” እና ሁኔታው የፈቀደለትን ያህል የሚያደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። የምንጠባበቅበት ጊዜ አብቅቶ ጌታው “ደግ አድርገሃል” ሲለን መስማት እንዴት ያስደስታል!

የጌታችን ትዕግሥት መዳን ያስገኛል

የዚህ ክፉ ሥርዓት ጥፋት ባሰብነው ጊዜ ባይመጣስ? ሥርዓቱ የቆየበት ምክንያት አለ። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደሆነ አስቡ።” (2 ጴጥሮስ 3:15) ስለ አምላክ ዓላማ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችንና ከዓላማው መፈጸም አንጻር ሲታይ የእኛ መዳን ያን ያህል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር አለመሆኑን በትሕትና አምነን መቀበላችን ይሖዋ ይህን አሮጌ ሥርዓት የታገሠውን ያህል እኛም በትዕግሥት እንድንጠባበቅ ያስችለናል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ያዕቆብ ክርስቲያኖችን በትዕግሥት እንዲጠብቁ ለማበረታታት የሚከተለውን ምሳሌ ሰጥቷል፦ “ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። እናንተም እንዲሁ ታገሱ፤ ልባችሁን አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአል።”—ያዕቆብ 5:7, 8

ይሖዋ አምላክ በትዕግሥት በምንጠባበቅበት ጊዜ እንድንዝል ወይም ተስፋ እንድቆርጥ አይፈልግም። የምንሠራው ሥራ የሰጠን ሲሆን በዚህ ሥራ ተጠምደን ብንጠብቀው ይደሰትብናል። ይሖዋ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደተገለጹት ሰዎች እንድንሆን ይፈልጋል፤ “የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።”—ዕብራውያን 6:11, 12

ስለሆነም አንታክት። ከዚህ ይልቅ ከይሖዋ ጋር ያለን የግል ዝምድና፣ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ያለን እምነትና አስደሳች የሆነው የመጪው አዲስ ሥርዓት ተስፋ አበረታች ኃይል ይሁንልን። “እኔ . . . ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በምስጋና ላይ ምስጋና አቀርብልሃለሁ” እንዳለው መዝሙራዊ እኛም አምላካችንን የማመስገኑ ሥራ የበዛልን በመሆን ልክ እንደ ‘መልካሙ ታማኝ አገልጋይ’ የሚያስመሰግነንን እና ሽልማት የሚያስገኝልንን ነገር እናድርግ።—መዝሙር 71:14

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮናስ ነነዌ የሚደርስባትን ነገር ለማየት በብስጭት ተጠባብቋል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋን ቀን በምንጠባበቅበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ያደርን መሆናችንን እናሳይ