በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት የጸኑ ክርስቲያኖች

ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት የጸኑ ክርስቲያኖች

ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት የጸኑ ክርስቲያኖች

ፖላንድ ከስሎቫኪያና ከቼክ ሪፑብሊክ ጋር በምትዋሰንበት ደቡባዊ ጠረፍ አቅራቢያ ቪስዋ ተብላ የምትጠራ አነስተኛ ከተማ ትገኛለች። ከዚህ ቀደም ስለዚህች ከተማ ሰምተህ የማታውቅ ቢሆንም እንኳ በቪስዋ የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ያሳዩት ቅንዓትና ጽናት የእውነተኛ ክርስቲያኖችን ትኩረት የሚስብ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ቪስዋ ድንቅ ተፈጥሯዊ ውበት በሚንጸባረቅበት ተራራማ አካባቢ የምትገኝ ከተማ ናት። በዚህች ከተማ ውስጥ በደን የተሸፈኑ ተራሮችንና ሸለቆዎችን አቋርጦ እየተጠማዘዘ ከሚፈስሰው የቪስቹላ ወንዝ ጋር የሚቀላቀሉ ጅረቶችና ሁለት ገባር ወንዞች አሉ። የነዋሪዎቹ ወዳጃዊ አቀራረብና የአካባቢው ልዩ የአየር ንብረት ቪስዋ ታዋቂ የሕክምና ማዕከል ከመሆንም አልፋ በበጋ ወቅት ለእረፍት ጊዜ ማሳለፊያነት የምትመረጥና በክረምትም የምትዘወተር እንድትሆን አስተዋጽኦ አድርጓል።

ቪስዋ የተቆረቆረችው በ1590ዎቹ ዓመታት ሳይሆን አይቀርም። በመንደሯ የእንጨት መሰንጠቂያ ከተቋቋመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በጎችና ከብቶች በማርባትና በእርሻ የሚተዳደሩ ሰዎች በደን ባልተሸፈኑት ተራራማ ቦታዎች መኖር ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ ግን ፈጣን ሃይማኖታዊ ለውጦች ይታዩ ጀመር። ማርቲን ሉተር ያካሄደው ሃይማኖታዊ ተሃድሶ በቪስዋ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ሲሆን ተመራማሪው አንጄ ኦትቼክ እንደገለጹት “ከ1545 [ጀምሮ የሉተራን እምነት] የመንግሥት ሃይማኖት” ሆኖ ነበር። ሆኖም የሠላሳ ዓመቱ ጦርነትና ከጦርነቱ በኋላ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያካሄደችው የጸረ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ለውጥ አስከተለ። ኦትቼክ አክለው እንደገለጹት “በ1654 ሁሉም የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የተወረሱ ሲሆን ሃይማኖታዊ ስብሰባ እንዳያደርጉ ታገዱ፤ መጽሐፍ ቅዱሶችና ሌሎች ሃይማኖታዊ መጽሐፎቻቸውም ተወሰዱባቸው።” ያም ሆኖ አብዛኛው የኅብረተሰቡ ክፍል የሉተራንን እምነት መከተሉን ቀጠለ።

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የመጀመሪያ ዘር

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ግን በቪስዋ ከዚህ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ተካሄደ። በ1928 ሁለት ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (የይሖዋ ምሥክሮች በወቅቱ የሚታወቁበት ስም ነው) የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በቪስዋ ዘሩ። በቀጣዩ ዓመት ያን ጎሞላ የተባለ ወንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች የተቀረጹበት የሸክላ ማጫወቻ ይዞ ወደ ቪስዋ ሄደ። ከዚያም በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሸለቋማ አካባቢ የተሻገረ ሲሆን በዚህ ቦታ ያነጋገረው አንጄ ራሽካ የተባለ አጠር ያለና ፈርጠም ያለ ሰውነት ያለው የደጋ ሰው ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ሰጠ። ራሽካ ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱሱን አውጥቶ በሸክላ ማጫወቻው የሚሰማውን ንግግር ትክክለኛነት አረጋገጠ። ባገኘው ነገር በመርካቱ “ወንድሜ ሆይ፣ በመጨረሻ እውነትን አገኘሁ! በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ምሽግ ውስጥ ከነበርኩበት ጊዜ አንስቶ በአእምሮዬ የሚመላለሱ ጥያቄዎች ነበሩ” በማለት በደስታ ተናገረ።

ባገኘው እውነት በጣም የተደሰተው ራሽካ፣ ይርዝሃ እና አንጄ ፒልክ የተባሉ ጓደኞቹን ከጎሞላ ጋር አገናኛቸው፤ እነርሱም ምሥራቹን በደስታ ተቀበሉ። በፈረንሳይ እውነትን የሰማ አንጄ ታይርና የተባለ ሌላ ወንድም የአምላክን ቃል በጥልቀት ያስጠናቸው ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ራሳቸውን ወስነው ተጠመቁ። በ1930ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ በቪስዋ የነበረውን አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ለመርዳት በአጎራባች ከተሞች የሚኖሩ ወንድሞች እየመጡ ይጠይቋቸው የነበረ ሲሆን በዚህም አስደናቂ ውጤት ተገኝቷል።

ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች በብዛት ይጎርፉ ነበር። በቪስዋ የሚኖሩ የሉተራን ሃይማኖት ተከታዮች መጽሐፍ ቅዱስን በየቤታቸው የማንበብ ልማድ ነበራቸው። ስለዚህ የሲኦል እሳትና የሥላሴ መሠረተ ትምህርቶች የተሳሳቱ መሆናቸውን የሚያሳይ አሳማኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ሲያገኙ አብዛኞቹ እውነቱን ከሐሰቱ መለየት አላስቸገራቸውም። በርካታ ቤተሰቦች ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ለመላቀቅ ወሰኑ። በመሆኑም በቪስዋ የነበረው ጉባኤ እያደገ የሄደ ሲሆን በ1939 140 ያህል አባላት ነበሩት። የሚያስገርመው ግን በዚያ ጉባኤ ከነበሩት አዋቂዎች አብዛኞቹ አልተጠመቁም ነበር። በዚያ ዘመን ከነበሩት ክርስቲያኖች አንዷ የሆነችው ሄለና እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ሲባል ግን እነዚህ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ከይሖዋ ጎን አልቆሙም ማለት አይደለም፤ ብዙም ሳይቆይ የገጠማቸውን የእምነት ፈተና በጽናት መወጣታቸው ይህንን ያረጋግጣል።”

ልጆቹስ? ወላጆቻቸው እውነትን እንዳገኙ ተገንዝበው ነበር። ፍራንቺሼክ ብራንዝ እንዲህ ይላል፦ “አባቴ እውነትን እንዳገኘ ሲያውቅ በእኔና በወንድሜ ልብ ውስጥ ይህን እውነት ለመቅረጽ ጥረት ያደርግ ጀመር። እኔ ስምንት ወንድሜ ደግሞ አሥር ዓመቱ ነበር። አባባ ‘አምላክ ማን ነው? ስሙስ? ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ታውቃላችሁ?’ እንደሚሉ ያሉ ቀላል ጥያቄዎችን ይጠይቀናል። መልሶቻችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አስደግፈን በወረቀት ላይ እንድናሰፍር ይጠበቅብን ነበር።” ሌላ የይሖዋ ምሥክር ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ወላጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብለው በ1940 በፈቃዳቸው ከሉተራን ቤተ ክርስቲያን በመውጣታቸው በትምህርት ቤት ተቃውሞ ይደርስብኝ አልፎ ተርፎም ይደበድቡኝ ነበር። ወላጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ስላስተማሩኝ አመሰግናቸዋለሁ። እነዚያን አስቸጋሪ ጊዜያት መቋቋም የቻልኩት ከእነርሱ ባገኘሁት ሥልጠና ነው።”

እምነታቸው ተፈተነ

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ናዚዎች አካባቢውን የተቆጣጠሩት ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮችን ለማጥፋት ቆርጠው ተነሱ። መጀመሪያ ላይ አዋቂዎቹ በተለይም አባቶች አንዳንድ ጥቅሞች ማግኘት እንዲችሉ ጀርመኖች መሆናቸውን በሚገልጽ መዝገብ ላይ እንዲፈርሙ ይበረታቱ ነበር። ምሥክሮቹ ከናዚዎች ጎን ለመሰለፍ ፈቃደኛ አልሆኑም። ዕድሜያቸው ለውትድርና የደረሰ በርካታ ወንድሞችና ለእውነት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች አስቸጋሪ ሁኔታ ተደቀነባቸው፦ ወይ ከሠራዊቱ ጋር መቀላቀል አሊያም የገለልተኝነት አቋማቸውን በመጠበቅ የሚመጣውን ከባድ ቅጣት መቀበል ነበረባቸው። በ1943 ጌስታፖዎች አስረውት የነበረ አንጄ ሻልቦ የተባለ ወንድም ሁኔታውን እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው የሚጠብቀው ዕጣ ወደ ማጎሪያ ካምፕ (በአብዛኛው ወደ ኦሽዊትዝ) መላክ ነበር። በወቅቱ ባልጠመቅም ኢየሱስ በማቴዎስ 10:28, 29 ላይ የሰጠውን ማበረታቻ አውቅ ነበር። በይሖዋ ላይ ባለኝ እምነት ምክንያት ብሞት እንኳ እንደገና ሊያስነሳኝ እንደሚችል አውቅ ነበር።”

በ1942 መጀመሪያ ላይ ናዚዎች በቪስዋ ከነበረው ጉባኤ 17 ወንድሞችን ያሰሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 15ቱ በሦስት ወራት ውስጥ በኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ ሞቱ። በቪስዋ የቀሩት ወንድሞች ይህንን ሲያውቁ ምን ተሰማቸው? ይህ ሁኔታ እምነታቸውን እንዲያላሉ አላደረጋቸውም፤ እንዲያውም በአቋማቸው ጸንተው ከይሖዋ ጎን እንዲቆሙ አበረታታቸው! በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ በቪስዋ የሚገኙ አስፋፊዎች ቁጥር በእጥፍ ጨመረ። ብዙም ሳይቆይ ተጨማሪ ሰዎች ታሰሩ። በአጠቃላይ 83 ያህል ወንድሞች፣ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችና ልጆች ሂትለር የይሖዋ ምሥክሮችን ለመደምሰስ ባሰማራው ኃይል ጥቃት ደርሶባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 53ቱ ወደ ማጎሪያ ካምፖች (በዋነኝነት ኦሽዊትዝ) ወይም የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው በፖላንድ፣ ጀርመንና ቦሂሚያ የሚገኙ የማዕድን ማውጫና የድንጋይ መፍለጫ ካምፖች ተልከዋል።

በታማኝነት ጸንተዋል

ናዚዎች በኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ ያሰሯቸውን ምሥክሮች አቋማቸውን ቢያላሉ ወዲያው እንደሚፈቱ በመናገር ሊያግባቧቸው ይሞክሩ ነበር። አንድ የኤስ ኤስ ጠባቂ ለአንድ ወንድም “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንዳልሆንክ በመግለጽ ከፈረምክ በነፃ ተለቅቀህ ወደ ቤትህ መሄድ ትችላለህ” ብሎት ነበር። ወንድም ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢቀርብለትም ለይሖዋ ያለውን የታማኝነት አቋም አላላላም። በዚህም የተነሳ ይደበድቡትና ይሳለቁበት የነበረ ከመሆኑም በላይ በኦሽዊትዝና በጀርመን በሚገኘው በሚቴልባው ዶራ ካምፕ የጉልበት ሥራ እንዲሠራ ተደረገ። ይህ ወንድም ልክ ነፃ ሊወጣ አካባቢ የነበረበት ካምፕ በቦምብ በመደብደቡ ከሞት ያመለጠው ለጥቂት ነው።

በቅርቡ የሞተው ፓቬል ዛልቦት በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጌስታፖዎች ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉልኝ በጀርመን ጦር ሠራዊት ውስጥ ለመሰለፍና ሂትለርን የሚያወድስ መፈክር ለማሰማት እንቢተኛ የሆንኩት ለምን እንደሆነ ደጋግመው ይጠይቁኝ ነበር።” ክርስቲያኖች ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ የሚሆኑበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ ካስረዳቸው በኋላ በጦር መሣሪያ ማምረቻ ውስጥ እንዲሠራ ተፈረደበት። “እንደዚህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ሕሊናዬ እንደማይፈቅድልኝ ግልጽ ነበር፤ ስለዚህ በማዕድን ማውጫ ውስጥ እንድሠራ ላኩኝ።” ሆኖም የታማኝነት አቋሙን አላላላም።

ሴቶቹና ልጆቹ ስላልታሰሩ በኦሽዊትዝ ማጎሪያ ካምፕ ላሉት ወንድሞች ምግብ ይልኩ ነበር። በወቅቱ ልጅ የነበረ አንድ ወንድም እንዲህ ይላል፦ “በበጋ ወራት ክራንቤሪ (እንደ እንጆሪ ያለ ፍሬ) ከዱር እንለቅምና በስንዴ እንለውጠው ነበር። ከዚያም እህቶች ሙልሙል ዳቦ ጋግረው ቅባት ውስጥ ይነክሩታል። ይህንን ዳቦ በትንሽ በትንሹ እያደረግን ወኅኒ ቤት ለሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቻችን እንልክላቸው ነበር።”

ከቪስዋ በአጠቃላይ 53 ምሥክሮች ወደ ማጎሪያ ካምፖችና የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ቦታዎች የተላኩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 38ቱ ለይሖዋ ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ አንቀላፍተዋል።

አዲስ ትውልድ ተተካ

በናዚዎች ጭቆና የይሖዋ ምሥክሮች ልጆችም ተነክተዋል። አንዳንዶቹ ከእናቶቻቸው ጋር በቦሂሚያ ወደሚገኙ ጊዜያዊ ካምፖች ተላኩ። ሌሎቹ ደግሞ ከወላጆቻቸው ተነጥለው በአስከፊነቱ ወደሚታወቀው በሎድዝ ወደሚገኘው የልጆች ካምፕ ተልከዋል።

ከእነዚህ ልጆች ሦስቱ እንዲህ ሲሉ የደረሰባቸውን ያስታውሳሉ፦ “በመጀመሪያው ዙር ጀርመኖች ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት የሚሆነንን አሥር ልጆች ከወላጆቻችን ለይተው ወደ ሎድዝ ወሰዱን። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶች ላይ በመወያየትና በመጸለይ እርስ በርስ እንበረታታ ነበር። በዚያን ወቅት መጽናት ቀላል አልነበረም።” በ1945 እነዚያ ልጆች በሙሉ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። በሕይወት ቢተርፉም ሰውነታቸው መንምኖና ስሜታቸው ተጎድቶ ነበር። ያም ሆኖ ምንም ነገር አቋማቸውን እንዲያላሉ አላደረጋቸውም።

ከጦርነቱ በኋላስ?

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ መገባደጃው ሲቃረብ በቪስዋ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸው እንደቀድሞው ጠንካራ ከመሆኑም በላይ የስብከቱን ሥራቸውን በቅንዓትና በቆራጥነት ለማከናወን ተዘጋጅተው ነበር። ወንድሞች በቡድን እየሆኑ ከቪስዋ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው ወደሚኖሩ ሰዎች በመሄድ ይሰብኩና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ያሰራጩ ነበር። ያን ዞክ “ብዙም ሳይቆይ በመንደራችን ጥሩ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሦስት ጉባኤዎች ተቋቋሙ” ይላል። ሆኖም ያገኙት ሃይማኖታዊ ነፃነት ለረዥም ጊዜ አልዘለቀም።

በፖላንድ ናዚዎችን ተክቶ ሥልጣን የያዘው የኮሚኒስት አገዛዝ በ1950 የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ አገደው። በዚህም ምክንያት ወንድሞች አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ ዘዴኞች መሆን ነበረባቸው። አንዳንድ ጊዜ ከብት ወይም እህል የሚገዙ በማስመሰል ወደ ሰዎች ቤት ይሄዱ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚደረጉት በምሽት ሲሆን የሚሰበሰቡትም በትናንሽ ቡድኖች ሆነው ነበር። ያም ሆኖ የደህንነት ወኪሎች በርካታ የይሖዋ አምላኪዎችን ለባዕድ የስለላ ድርጅት ትሠራላችሁ በሚል ክስ አሰሯቸው። ይህ ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ክስ ነበር። አንዳንድ ባለ ሥልጣናት ፓቬል ፒልክ የተባለውን ወንድም “ሂትለር አቋምህን ሊያስለውጥህ አልቻለም፤ እኛ ግን እንችላለን” በማለት ዝተውበት ነበር። ወንድም ፒልክ ለአምስት ዓመታት ቢታሰርም ለይሖዋ በታማኝነት ጸንቷል። አንዳንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በሶሻሊስት ፖለቲካዊ ሰነድ ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከትምህርት ቤት ወይም ከሥራቸው ተባርረዋል።

ይሖዋ አልተዋቸውም

በ1989 በፖላንድ ፖለቲካዊ ለውጥ በመደረጉ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ሕጋዊ እውቅና አገኘ። በቪስዋ ያሉት አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ቁጥር እንደሚያሳየው በዚህች ከተማ ያሉት ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች እንቅስቃሴያቸውን ይበልጥ አጠናክረው ቀጥለዋል። በዚህ አካባቢ የሚኖሩ 100 ያህል ወንድሞችና እህቶች በአቅኚነት አገልግሎት ተሰማርተዋል። ይህቺ ከተማ የአቅኚዎች ማምረቻ በሚል ቅጽል ስም መሰየሟ አያስገርምም።

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በጥንት ዘመን ለሕዝቦቹ ስላደረገው ድጋፍ ሲገልጽ “ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ኖሮ፣ . . . በቁመናችን በዋጡን ነበር” ይላል። (መዝሙር 124:2, 3) በዘመናችንም ግዴለሽነትና ሥነ ምግባር የጎደለው ዓለማዊ አኗኗር በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተስፋፍቶ የሚገኝ ቢሆንም በቪስዋ የሚገኙ የይሖዋ አምላኪዎች ታማኝነታቸውን ለመጠበቅ ይጥራሉ፤ እንዲህ በማድረጋቸውም በእጅጉ ተባርከዋል። ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ በዚያች ከተማ የኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስ አባባል እውነተኝነት መመስከር ይችላሉ።—ሮሜ 8:31

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤሚሊያ ረዞክ ከልጆቿ ከሄለና፣ ከኤሚሊያና ከያን ጋር በቦሂሚያ ወደሚገኘው ጊዜያዊ ካምፕ ተልካ ነበር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓቬል ዛልቦት በውትድርና አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ በማዕድን ማውጫ ካምፕ እንዲሠራ ተልኳል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ኦሽዊትዝ የተላኩት ወንድሞች ቢገደሉም በቪስዋ የነበረው ሥራ እድገት ማድረጉን አላቆመም

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓቬል ፒልክና ያን ፖልክ በሎድዝ ወደሚገኘው የወጣቶች ካምፕ ተወስደው ነበር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የቤሪ ፍሬዎችና አበባዎች፦ © R.M. Kosinscy / www.kosinscy.pl