መንፈሳዊ ነገሮችን መከታተል የሚያስገኘው ጥቅም
መንፈሳዊ ነገሮችን መከታተል የሚያስገኘው ጥቅም
“ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም።”—መክብብ 5:10
ከመጠን በላይ በሥራ መጠመድ ለውጥረት ይዳርጋል፤ ውጥረት ደግሞ የጤና ችግሮች ሊያስከትል አንዳንዴም ለሞት ሊዳርግ ይችላል። በብዙ አገሮች ውስጥ ቤተሰቦች በፍቺ ይፈርሳሉ። አብዛኛውን ጊዜ የእነዚህ አሳዛኝ ችግሮች መንስኤ ከመጠን በላይ ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ ነው። ሃብት የማካበት ዝንባሌ የተጠናወተው ሰው ባለው ነገር ከመርካት ይልቅ በደኅንነቱ ላይ የሚያጋጥመውን ቀውስ ግምት ውስጥ ሳያስገባ ምንጊዜም ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ይሯሯጣል። አንድ ራስ አገዝ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “እንደ ጎረቤት መኖር በኅብረተሰቡ ዘንድ በጣም ተስፋፍቷል፤ ጎረቤትየው የሥራ ሱሰኛ ከመሆኑ የተነሳ ገና በአርባ ሦስት ዓመቱ ለልብ ሕመም የተጋለጠ ቢሆን እንኳን ከእርሱ ጋር መወዳደራቸው አይቀርም።”
ተጨማሪ ነገር ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ አንድን ሰው በቃኝ የማይል ሊያደርገውና ባለው ረክቶ ቢኖር ሊያገኘው የሚችለውን ደስታ ሊያሳጣው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ማስታወቂያዎች ይህን የሰዎች ድክመት ይጠቀሙበታል። የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞች ጨርሶ የማያስፈልጉህን ወይም ገቢህ የማይፈቅዳቸውን ነገሮች እንድትገዛ በሚወተውቱ የንግድ ማስታወቂያዎች የተጣበቡ ናቸው። ይህ ሁሉ ቀስ በቀስ ከባድ ጉዳት ሊያስከትልብህ ይችላል።
ምሳሌ 14:30) በተቃራኒው ግን ከመጠን በላይ መሥራት፣ ውጥረትና ቁሳዊ ሃብት ለማካበት የሚደረገው ሩጫ ደስታ ሊያሳጣን ብሎም ጤንነታችንን ሊጎዳው ይችላል። በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ለቁሳዊ ነገሮች ከሆነ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነትም አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። አንድ ሰው የቤተሰብ ሕይወቱና ከሰዎች ጋር ያለው ማኅበራዊ ግንኙነት ከተቃወሰ አጠቃላይ ሕይወቱ ይመሰቃቀላል።
ያየሁት ሁሉ አይቅርብኝ ማለት በቀላሉ ለማይስተዋል ሆኖም ከፍተኛ ለሆነ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሊዳርገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” ብሎ ነበር። (መንፈሳዊ እሴቶች ያላቸው ብልጫ
ሐዋርያው ጳውሎስ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት “ይህን ዓለም አትምሰሉ” የሚል ምክር ሰጥቶ ነበር። (ሮሜ 12:2) በጊዜያችን ትልቅ ግምት የሚሰጣቸውን ነገሮች የሚከተሉ ሰዎች በዓለም ዘንድ ተወዳጅነት ያተርፋሉ። (ዮሐንስ 15:19) ዓለም የማየት፣ የመዳሰስ፣ የመቅመስ፣ የማሽተትና የመስማት ሕዋሳትህን ተጠቅሞ ቀልብህን በመማረክ በፍቅረ ነዋይ ላይ ያተኮረ የሕይወት ዘይቤ እንድትከተል ለማድረግ ይጥራል። አንተም ሆንክ ሌሎች ቁሳዊ ጥቅሞችን እንድታሳድዱ ለመገፋፋት የሚጥርበት ዋነኛው መንገድ ደግሞ ‘የዓይን አምሮት’ ነው።—1 ዮሐንስ 2:15-17
ይሁን እንጂ ከገንዘብ፣ ታዋቂ ከመሆንና ከቁሳዊ ሃብት የላቀ ዋጋ ያላቸው እሴቶች አሉ። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የኖረው ንጉሥ ሰሎሞን ዓለም ሊሰጠው የሚችለውን ቁሳዊ ነገር በሙሉ አግኝቶ ነበር። ቤቶች፣ የአትክልት ቦታዎችና የፍራፍሬ እርሻዎች፣ አገልጋዮች፣ ከብቶች፣ ወንድና ሴት አዝማሪዎች እንዲሁም በርካታ ወርቅና ብር ነበረው። ሃብቱ ከእርሱ በፊት ከተነሱት ሁሉ በእጅጉ የበለጠ ነበር። እንዲያውም ሃብታም የሚለው ቃል ብቻ አይገልጸውም። ሰሎሞን ሰው ሊመኘው የሚችለው ነገር በሙሉ ነበረው። ሆኖም የድካሙን ውጤት ከተመለከተ በኋላ “ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር” ብሏል።—መክብብ 2:1-11
ሰሎሞን ከይሖዋ ባገኘው ከፍተኛ ጥበብ ከሁሉ የላቀው ስኬት የሚገኘው መንፈሳዊ ነገሮችን በማስቀደም እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።”—መክብብ 12:13
የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ሃብት ከወርቅና ከብር የበለጠ ዋጋ አለው። (ምሳሌ 16:16) መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ቆፍረህ ልታወጣቸው የምትችላቸው እንደ እንቁ ያሉ ውድ ሃብቶች ይዟል። እነዚህን እውነቶች ለመፈለግና ቆፍረህ ለማውጣት ጥረት ታደርጋለህ? (ምሳሌ 2:1-6) የዚህ እውነተኛ ሃብት ምንጭ የሆነው ፈጣሪያችን እንደዚህ እንድታደርግ የሚያበረታታህ ሲሆን እንዲሳካልህም ይረዳሃል። እንዴት?
ይሖዋ በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ በኩል ውድ የሆኑ የእውነት እንቁዎችን ይሰጠናል። (መዝሙር 1:1-3፤ ኢሳይያስ 48:17, 18፤ ማቴዎስ 24:45-47፤ 1 ቆሮንቶስ 2:10) እነዚህን በዋጋ ሊተመን የማይችል ጠቀሜታ ያላቸውን ውድ እንቁዎች መመርመርህ ከሁሉ የተሻለውንና ስኬታማ የሚያደርግህን የሕይወት መንገድ በጥበብ ለመወሰን ያስችልሃል። ይህን ውሳኔ ማድረግ ያን ያህል ከባድ አይሆንብህም፤ ምክንያቱም ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ ደስተኛ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልገን ጠንቅቆ ያውቃል።
መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ የሆኑ እሴቶችን ያስተምራል
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጠቃሚ ምክር ተግባራዊ መሆን የሚችልና አቻ የሌለው ነው። ሰዎች የላቁ የሥነ ምግባር እሴቶችን እንዲከተሉ ያበረታታል። የያዘው ምክር ምንጊዜም ጠቃሚና ጊዜ የማይሽረው መሆኑ የተረጋገጠለት ነው። ከእነዚህ ጠቃሚ ምክሮች መካከል ጠንክሮ መሥራት፣ ሐቀኛ መሆን፣ ገንዘብን በአግባቡ መጠቀምና ስንፍናን ማስወገድ ይገኙበታል።—ምሳሌ 6:6-8፤ 20:23፤ 31:16
ከዚህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቆፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።”—ማቴዎስ 6:19, 20
ይህ ምክር ከ2,000 ዓመት በፊት ወቅታዊና ጠቃሚ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ቁሳዊ ሃብት ለማካበት በሚደረግ ሩጫ ከመጠላለፍ ይልቅ ከዚያ የላቀ የአኗኗር ዘይቤ በመከተል ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ለዚህ ቁልፉ መንፈሳዊ ሃብት ማከማቸት ሲሆን ይህም እውነተኛ ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት ለመምራት ያስችላል። ታዲያ መንፈሳዊ ሃብት ማካበት የሚቻለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ያነበብነውን በሥራ ላይ በማዋል ነው።
መንፈሳዊ እሴቶች በረከት ያስገኛሉ
መንፈሳዊ እሴቶች በተገቢው መንገድ በሥራ ላይ ካዋልናቸው አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጥቅም ያስገኙልናል። ከምድር ከባቢ አየር በላይ የሚገኘው የኦዞን ሽፋን ጎጂ የሆኑ የፀሐይ ጨረሮችን እንደሚከላከልልን ሁሉ የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶችም ቁሳዊ ሃብት ማሳደድ ያለውን አደጋ በማጋለጥ ይጠብቁናል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጉጉት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
ፍቅረ ነዋይ ሰዎች የበለጠ ሃብት፣ ሥልጣንና ኃይል እንዲፈልጉ ይገፋፋቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ሐቀኝነት የጎደላቸው ተግባሮችንና የተንኮል ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ቁሳዊ ሃብት የሚያሳድድ ሰው ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ተሰጥኦውን በከንቱ ያባክናል። እንዲያውም እንቅልፍ አጥቶ እንዲያድር ሊያደርገው ይችላል። (መክብብ 5:12) ተጨማሪ ሃብት ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ ለመንፈሳዊ እድገት እንቅፋት እንደሚሆን የታወቀ ነው። በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ኢየሱስ ክርስቶስ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” በማለት የተሻለውን መንገድ በግልጽ አሳይቷል። (ማቴዎስ 5:3 NW) መንፈሳዊ ሃብት ዘላቂ የሆነ በረከት እንደሚያስገኝና ጊዜያዊ ጥቅም ካላቸው ቁሳዊ ነገሮች የበለጠ ዋጋ እንዳለው ያውቅ ነበር።—ሉቃስ 12:13-31
መንፈሳዊ ሃብት በእርግጥ ጠቃሚ ነው?
ግሪግ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ወላጆቼ መንፈሳዊ እሴቶች እርባና እንደሌላቸው እኔን ለማሳመን
ያላደረጉት ጥረት የለም፤ ቢሆንም መንፈሳዊ ግቦችን መከታተሌ ይሄ ነው የማይባል የአእምሮ ሰላም አስገኝቶልኛል። ምክንያቱም ሃብት ለማካበት መሯሯጥ ከሚያስከትለው ውጥረት ነጻ ሆኛለሁ።”መንፈሳዊ እሴቶችን መከታተል ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመገንባትም ያስችላል። እውነተኛ ጓደኞች የሚቀርቡህ በማንነትህ ተስበው እንጂ ሃብትህን ብለው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢባን ጋር ብትወዳጅ ጠቢብ ትሆናለህ” ይላል። (ምሳሌ 13:20 የ1980 ትርጉም) ከዚህም በላይ አስደሳች የሆነ የቤተሰብ ሕይወት መገንባት የሚቻለው በቁሳዊ ሃብት ሳይሆን በፍቅርና በጥበብ ነው።—ኤፌሶን 5:22 እስከ 6:4
በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ነገሮች በሚመለከት ያለን እውቀት ከሌሎች ሰዎች ወይም ከአምላክ ቃል በመማር የምናገኘው ነው እንጂ ይዘን የምንወለደው አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ለቁሳዊ ነገሮች ያለንን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ሊለውጠው ይችላል የምንለው ለዚህ ነው። ዶን የተባለ አንድ የቀድሞ ባለ ባንክ “[የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር] በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጣቸውን ነገሮች ቆም ብዬ ለመመርመር ያስቻለኝ ሲሆን በሚያስፈልጉኝ ነገሮች ብቻ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ” ብሏል።
ዘላቂ ጥቅም ያለውን መንፈሳዊ ሃብት አከማቹ
መንፈሳዊ እሴቶች ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ተድላና ፍስሐ ሳይሆን ዘላቂ ጥቅም ያላቸው በረከቶችን ያስገኛሉ። ጳውሎስ “የሚታየው [ቁሳዊ ነገር] ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው [መንፈሳዊ ነገር] ግን ዘላለማዊ ነው” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 4:18) ቁሳዊ ነገሮች ጊዜያዊ ፍላጎቶቻችንን ሊያሟሉልን እንደሚችሉ አይካድም፤ ሆኖም ስግብግብነት ዘላቂ ጥቅም አያስገኝም። በአንጻሩ መንፈሳዊ እሴቶች ዘላለማዊ ጠቀሜታ አላቸው።—ምሳሌ 11:4፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜያችን ተስፋፍቶ የሚገኘውን ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት የመስጠት ዝንባሌ ያወግዛል። ዓይናችን ጤናማ እንዲሆንና የበለጠ ጠቀሜታ ባለው ነገር ፊልጵስዩስ 1:10) ከስግብግብነት በስተጀርባ ያለው ራስን የማምለክ ዝንባሌ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ከአምላክ ቃል የምንማረውን በሥራ ላይ ስናውል ወደር የለሽ ደስታ እናገኛለን። ስለ መቀበል ሳይሆን ለሌሎች ስለ መስጠት ማሰብ እንጀምራለን። ይህ ለሥጋዊ ፍላጎታችን መገዛታችንን ትተን መንፈሳዊ እሴቶችን እንድንከታተል የሚያነሳሳን ጠንካራ ምክንያት ነው!
ይኸውም በመንፈሳዊ ሃብት ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ሊያድርብን የሚችለውን የራስ ወዳድነት ፍላጎት እንዴት መግታት እንደምንችል ያስተምረናል። (እውነት ነው፣ ገንዘብ በተወሰነ መጠን ከችግር ሊጠብቀን ይችላል። (መክብብ 7:12) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “በሀብት ላይ ዐይንህን ብትጥል፤ ወዲያው ይጠፋል፤ ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር፣ በርግጥ ክንፍ አውጥቶ ይበራል” በማለት እውነታውን ይናገራል። (ምሳሌ 23:5) ሰዎች ቁሳዊ ሃብት ለማካበት ሲሉ ጤናቸውን፣ የቤተሰብ ሕይወታቸውንና ሕሊናቸውን ጨምሮ ብዙ ነገሮችን መሥዋዕት ያደረጉ ሲሆን ይህም ጎጂ ውጤቶችን አስከትሎባቸዋል። በሌላ በኩል ግን መንፈሳዊ ሰው መሆን ይበልጥ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ይኸውም ከሌሎች ጋር በፍቅር የመኖር፣ ዓላማ ያለው ሕይወት የመምራትና አፍቃሪውን አምላካችንን ይሖዋን የማምለክ ፍላጎታችንን ያሟላልናል። በተጨማሪም አምላክ ቃል በገባልን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጽምናን ተላብሶ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ለማግኘት ያስችለናል።
በቅርቡ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ በብልጽግና የመኖር ሕልሙ ሙሉ በሙሉ እውን ይሆናል። (መዝሙር 145:16) በዚያን ጊዜ መላዋ ምድር ‘እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።’ (ኢሳይያስ 11:9) መንፈሳዊ እሴቶች ይስፋፋሉ። ፍቅረ ነዋይና ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች እስከ ወዲያኛው ጨርሰው ይወገዳሉ። (2 ጴጥሮስ 3:13) ከዚያም ለሕይወት ጣዕም የሚሰጡት እንደ አርኪ ሥራ፣ የተሟላ ጤና፣ አስደሳች መዝናኛ፣ ሞቅ ያለ የቤተሰብ ሕይወትና ከአምላክ ጋር ዘላቂ ዝምድና መመሥረት ያሉት ነገሮች ለሰው ዘር ዘላለማዊ የሆነ እውነተኛ ደስታ ያስገኙለታል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ገንዘብህን በጥበብ ተጠቀምበት!
የሚያስፈልጉህን ነገሮች ለይተህ እወቅ። ኢየሱስ “የዕለት እንጀራችንን በየዕለቱ ስጠን” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ሉቃስ 11:3) ዛሬ ቢኖሩኝ ብለህ የምትመኛቸው ነገሮች ነገ ያለ እነርሱ መኖር እንደማትችል እንዲሰማህ እንዳያደርጉህ ጥንቃቄ አድርግ። ሕይወትን አስደሳች የሚያደርገው የሃብትህ መጠን እንዳልሆነ አስታውስ።—ሉቃስ 12:16-21
ባጀት ይኑርህ። በስሜት ተነሳስተህ እቃ አትግዛ። መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) ኢየሱስ ተከታዮቹ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ምንም ነገር ከማድረጋቸው በፊት ወጪውን እንዲያሰሉ አሳስቧቸዋል።—ሉቃስ 14:28-30
አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አትግባ። በተቻለ መጠን ዕቃዎችን በዱቤ ከመውሰድ ይልቅ የሚያስፈልግህን ገንዘብ አስቀድመህ አጠራቅም። የምሳሌ መጽሐፍ “ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው” ይላል። (ምሳሌ 22:7) ራስህን በመቆጣጠርና ከባጀትህ ውጪ ባለመሸመት ትላልቅ ነገሮችን እንኳን ለመግዛት የሚያስፈልግህን ገንዘብ ማጠራቀም ትችላለህ።
አታባክን። ያለህን ንብረት በአግባቡ በመያዝ ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግልህ ማድረግና ብክነትን መቀነስ ትችላለህ። ኢየሱስ ነገሮችን ላለማባከን ጥንቃቄ ያደርግ ነበር።—ዮሐንስ 6:10-13
ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ቅድሚያ ስጥ። ጠቢብ የሆነ ሰው ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜውን ‘ይዋጃል።’—ኤፌሶን 5:15, 16
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል7]
ከራስ ተሞክሮ ከመማር የተሻለ ነገር አለ
በራሳችን ላይ ከደረሱብን ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገሮች ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን ልናገኝ እንችላለን። ይሁን እንጂ ከራስ ተሞክሮ ከመማር የተሻለ ነገር የለም የሚባለው እውነት ነው? በፍጹም። ከዚያ የተሻለ የእውቀት ምንጭ አለ። መዝሙራዊው ዳዊት “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ብሎ በጸለየ ጊዜ የዚህን እውቀት ምንጭ ጠቁሟል።—መዝሙር 119:105
ከራስ ተሞክሮ ከመማር ይልቅ ከአምላክ ቃል መማሩ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የተሻለውን አካሄድ ለማግኘት የተለያዩ መንገዶችን እየሞከሩ መማር ኪሳራና ሐዘን የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ አላስፈላጊ ነው። አምላክ ለጥንት እስራኤላውያን “ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” ብሏቸዋል።—ኢሳይያስ 48:18
የአምላክ ቃል ከሁሉ የተሻለ የእውቀት ምንጭ ነው የምንልበት ሌላው ምክንያት በውስጡ ጥንታዊና ትክክለኛ የሆኑ የሰዎች ተሞክሮዎችን መያዙ ነው። ሰዎች የፈጸሟቸውን ስህተቶች ድጋሚ ሠርቶ ለችግር ከመጋለጥ ከእነርሱ ስኬት ወይም ስህተት መማር እንደሚሻል ሳትገነዘብ አትቀርም። (1 ቆሮንቶስ 10:6-11) ከዚህም በላይ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በአስተማማኝነታቸው ተወዳዳሪ የማይገኝላቸውን ግሩም ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቶናል። “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ . . . የእግዚአብሔር ሥርዓት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።” (መዝሙር 19:7) በእርግጥም አፍቃሪው ፈጣሪያችን ካለው ጥበብ መማር የተሻለ መንገድ ነው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓለም ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረ የአኗኗር ዘይቤ እንድትከተል ይፈልጋል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከወርቅና ከብር የበለጠ ዋጋ ያለው ሃብት ይገኛል