በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በገነት ተስፋ እንድታምን የሚያደርግ ምክንያት አለህ?

በገነት ተስፋ እንድታምን የሚያደርግ ምክንያት አለህ?

በገነት ተስፋ እንድታምን የሚያደርግ ምክንያት አለህ?

‘በክርስቶስ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ እርሱም ወደ ገነት ተነጠቀ።’—2 ቆሮንቶስ 12:2-4

1. አስደሳች የሆኑት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች የትኞቹ ናቸው?

 ገነት። አምላክ ምድርን ገነት እንደሚያደርግ ስለሰጠው ተስፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሰማ ምን ተሰምቶህ እንደነበር ታስታውሳለህ? ‘የዕውር ዓይን እንደሚገለጥ፣ የደንቆሮ ጆሮ እንደሚከፈትና ምድረ በዳው’ ውበት እንደሚላበስ ስለ ተማርክበት ጊዜ እስቲ አስብ። ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር እንደሚኖር ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር እንደሚተኛ ስለሚናገረው ትንቢት ስትማር ምን ተሰምቶህ ነበር? በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች እንደገና ሕያው ሆነው በዚያች ገነት ውስጥ መኖር እንደሚችሉ ስታውቅ አልተደሰትክም?—ኢሳይያስ 11:6፤ 35:5, 6፤ ዮሐንስ 5:28, 29

2, 3. (ሀ) ስለ ገነት የሚናገረው ተስፋ ባዶ ተስፋ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን ተጨማሪ ማስረጃ ምንድን ነው?

2 ይህ ተስፋ እንዲሁ ባዶ ተስፋ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ገነት በተመለከተ በሰጠው ተስፋ እንድታምን የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለህ። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አብሮት ተሰቅሎ ለነበረው ወንጀለኛ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ሲል የገባለት ቃል እንደሚፈጸም አትጠራጠርም። (ሉቃስ 23:43) “እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን” የሚለው ተስፋም ቢሆን እንደሚፈጸም እርግጠኛ ነህ። አምላክ እንባን ሁሉ ከዓይናችን እንደሚያብስ እንዲሁም ሞትን፣ ሐዘንን፣ ልቅሶንና ሥቃይን እንደሚያስወግድ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም አትጠራጠርም። ይህ ማለት ደግሞ ምድር እንደገና ገነት ትሆናለች ማለት ነው።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:4

3 ከዚህም በላይ ደግሞ ክርስቲያኖች አሁን ያሉበት ሁኔታ ስለ ገነት የሚናገረው ተስፋ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሆነናል። ይህ ሁኔታ ምንድን ነው? አምላክ መንፈሳዊ ገነት በማቋቋም ሕዝቦቹ በዚህ ገነት ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓል። “መንፈሳዊ ገነት” የሚለው አነጋገር ትንሽ ግር ሊል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነት ገነት እንደሚኖር አስቀድሞ በትንቢት የተነረገ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እውን ሆኗል።

የገነት ራእይ

4. በ2 ቆሮንቶስ 12:2-4 ላይ ምን ራእይ ተገልጿል? ይህን ራእይ ያየውስ ማን መሆን አለበት?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ገነት በተመለከተ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ የተነጠቀ በክርስቶስ አንድ ሰው ዐውቃለሁ፤ . . . ይህ ሰው በሥጋ ይሁን ወይም ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ግን ያውቃል፤ እርሱም ወደ ገነት እንደ ተነጠቀ፣ በዚያም በሰው አንደበት ሊገለጥ የማይችል፣ ሰውም እንዲናገረው ያልተፈቀደለት ነገር ሰማ።” (2 ቆሮንቶስ 12:2-4) ጳውሎስ ይህን የተናገረው ሐዋርያነቱን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ከሰጠ በኋላ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ በየትም ቦታ ላይ እንዲህ ያለ ሁኔታ ስላጋጠመው ሰው አይናገርም። ስለዚህ ጉዳይ የተናገረው ጳውሎስ ብቻ ነው። በመሆኑም ራእዩን የተመለከተው ጳውሎስ መሆን አለበት። ታዲያ ይህንን እንግዳ የሆነ ራእይ ባየበት ወቅት የገባበት “ገነት” ምንድን ነው?—2 ቆሮንቶስ 11:5, 23-31

5. ጳውሎስ በራእይ ያየው ነገር ምንን አያመለክትም? ታዲያ የተመለከተው “ገነት” ምንድን ነው?

5 ከራእዩ ይዘት እንደምንረዳው “ሦስተኛው ሰማይ” በምድራችን አካባቢ የሚገኘውን ህዋ ወይም ሳይንቲስቶች አለ የሚሉትን ከዚያ ራቅ ብሎ የሚገኘውን የጠፈር ክፍል አያመለክትም። መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ሦስት ቁጥርን አንድን ነገር አጠንክሮ ወይም አበክሮ ለመግለጽ ይጠቀምበታል። (መክብብ 4:12፤ ኢሳይያስ 6:3፤ ማቴዎስ 26:34, 75፤ ራእይ 4:8) በመሆኑም ጳውሎስ በራእይ ያየው ነገር አንድን ከፍ ያለ ወይም የላቀ መንፈሳዊ ሁኔታ የሚያመለክት ነው።

6. ጳውሎስ ያየውን ራእይ በተመለከተ ማስተዋል እንድናገኝ የሚረዱን የትኞቹ ታሪካዊ ክንውኖች ናቸው?

6 ቀደም ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ይህን ሁኔታ በተመለከተ ማስተዋል እንድናገኝ ይረዱናል። አምላክ ጥንት ሕዝቦቹ የነበሩት እስራኤላውያን ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ባቢሎናውያን ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን እንዲወርሩና እንዲያጠፉ ወስኖ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ይህ ሁኔታ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ተፈጽሟል። በትንቢቱ መሠረት ምድሪቱ ለ70 ዓመታት ባድማ ሆና ትቆያለች። ከዚያም አምላክ ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ ዳግም እንዲያቋቁሙ ይፈቅዳል። ይህ ደግሞ ፍጻሜውን ያገኘው በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። (ዘዳግም 28:15, 62-68፤ 2 ነገሥት 21:10-15፤ 24:12-16፤ 25:1-4፤ ኤርምያስ 29:10-14) ምድሪቱስ ምን ሆና ነበር? በእነዚያ 70 ዓመታት ዳዋ ወርሷትና የቀበሮዎች መፈንጫ ሆና ነበር። (ኤርምያስ 4:26፤ 10:22) ያም ሆኖ “እግዚአብሔር ጽዮንን በእርግጥ ያጽናናታል፤ ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤ ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣ በረሓዋንም እንደ እግዚአብሔር ተክል ቦታ [ወይም በሴፕቱጀንት ትርጉም መሠረት ‘ገነት’] ያደርጋል” የሚል ተስፋ ተሰጥቶ ነበር።—ኢሳይያስ 51:3

7. ከ70 ዓመት ባድማነት በኋላ ምን ይፈጸማል?

7 ይህ ትንቢት ከ70 ዓመት በኋላ ፍጻሜውን አግኝቷል። አምላክ በረከቱን ስላፈሰሰ በዚያ የነበረው ሁኔታ ተለወጠ። እስቲ የሚከተለውን በዓይነ ኅሊናህ ለመመልከት ሞክር፦ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤ በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤ እንደ አደይም ያብባል። በደስታና በዝማሬ ሐሤት ያደርጋል . . . አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል፤ ውሃ ከበረሓ ይወጣል፤ ምንጮችም ከምድረ በዳ ይፈልቃሉ። ንዳዳማው ምድር ኩሬ ይሆናል፤ የተጠማው መሬት ውሃ ያመነጫል። ቀበሮዎች በተኙባቸው ጉድጓዶች፣ ሣር፣ ሸምበቆና ደንገል ይበቅልበታል።”—ኢሳይያስ 35:1-7

ወደ አገራቸው የተመለሱና የተለወጡ ሰዎች

8. ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 በይበልጥ ያተኮረው በሰዎች ላይ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?

8 ይህ በእርግጥም ታላቅ ለውጥ ነው! ባድማ የነበረችው ምድር ተለውጣ ገነት ሆናለች። ይሁን እንጂ፣ ይህም ሆነ አስተማማኝ የሆኑ ሌሎች ትንቢቶች በሕዝቡም ላይ ከዚህ የማይተናነስ ለውጥ እንደሚኖር ይጠቁማሉ። እንዲህ ልንል የምንችለው ለምንድን ነው? ኢሳይያስ በይበልጥ ያተኮረው ‘በፍሥሓና በሐሴት እየዘመሩ’ ወደ አገራቸው በተመለሱት ‘ይሖዋ በዋጃቸው’ ሰዎች ላይ ነበር። (ኢሳይያስ 35:10) እንዲህ የሚያደርጉት ሰዎች እንጂ ግዑዟ ምድር ልትሆን እንደማትችል ግልጽ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ በሌላ ቦታ ላይ ወደ ጽዮን የሚመለሱትን ሰዎች በተመለከተ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ . . . ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣ . . . እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣ ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።” እንዲሁም ስለ አምላክ ሕዝቦች ሲናገር “እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል . . . ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ . . . ትሆናለህ” ብሏል። (ኢሳይያስ 58:11፤ 61:3, 11፤ ኤርምያስ 31:10-12) የምድሪቱ ገጽታ እንደተለወጠ ሁሉ ወደ አገራቸው የሚመለሱት አይሁዳውያንም ትልቅ ለውጥ ያደርጋሉ።

9. ጳውሎስ ያየው “ገነት” ምን ነበር? ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው?

9 እንደ ተምሳሌት የሆነው ይህ ታሪካዊ ክንውን ጳውሎስ በራእይ ያየው ሁኔታ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን የሚረዳ ሲሆን ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ዕርሻ” ሲል የተናገረለትንና ፍሬ ማፍራት የሚጠበቅበትን የክርስቲያን ጉባኤም ይጨምራል። (1 ቆሮንቶስ 3:9) ይህ ራእይ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነበር? ጳውሎስ ያየውን ነገር ‘ራእይ’ ሲል ጠርቶታል። ይህ ደግሞ ወደፊት የሚፈጸም መሆኑን ያመለክታል። ጳውሎስ ከእርሱ ሞት በኋላ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ክህደት እንደሚነሳ ተገንዝቦ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 12:1፤ የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3, 7) ክህደቱ ተስፋፍቶ ክርስቲያኖችን ሙሉ በሙሉ የዋጣቸው ይመስል በነበረበት ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ ፍሬያማ የአትክልት ሥፍራ ተደርገው ሊገለጹ አይችሉም። ሆኖም እውነተኛው አምልኮ ዳግም ወደ ላቀ ደረጃ ይደርሳል። ‘ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ እንዲያበሩ’ የአምላክ ሕዝቦች እንደገና ይቋቋማሉ። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43) ይህ የተፈጸመው የአምላክ መንግሥት በሰማይ ከተቋቋመ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነው። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የአምላክ ሕዝቦች ጳውሎስ በራእይ ተመልክቶት የነበረውን መንፈሳዊ ገነት እንዳገኙ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በግልጽ ይታዩ ጀመር።

10, 11. ፍጽምና የሚጎድለን ሰዎች ብንሆንም በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነን ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

10 ሁላችንም ፍጽምና የሚጎድለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን በጳውሎስ ዘመን በነበሩት ክርስቲያኖች ዘንድ እንደነበረው ሁሉ አልፎ አልፎ ችግሮች ሊነሱ ቢችሉ የሚያስደንቅ አይሆንም። (1 ቆሮንቶስ 1:10-13፤ ፊልጵስዩስ 4:2, 3፤ 2 ተሰሎንቄ 3:6-14) ይሁን እንጂ አሁን ስላለንበት መንፈሳዊ ገነት እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ዛሬ ቀደም ሲል ከነበርንበት መንፈሳዊ ሕመም ተፈውሰናል። በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ረሃብተኞች ነበርን፤ አሁን ግን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እናገኛለን። የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ምድረ በዳ በሆነ ዓለም ውስጥ መንከራተታቸው አክትሞ የእርሱ ሕዝቦች በመሆን በረከቱን በማግኘት ላይ ናቸው። (ኢሳይያስ 35:1, 7) ዓይናችንን ካሳወረው መንፈሳዊ ጨለማ ወጥተን የነጻነት ብርሃን ለማየትና የአምላክን ሞገስ ለማግኘት በቅተናል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጆሯችን የተደፈነ ያህል የነበርን ሰዎች ዛሬ ጆሯችን ተከፍቶ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሉትን ለመስማትና ለማስተዋል ችለናል። (ኢሳይያስ 35:5) ለምሳሌ ያህል፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የዳንኤልን ትንቢት ጥቅስ በጥቅስ አጥንተውታል። ከዚያ ደግሞ የኢሳይያስን ትንቢት እያንዳንዱን ምዕራፍ በጥልቀት ለመመርመር የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተዋል። ታዲያ ይህ በእርግጥ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ አይሆንም?

11 እስቲ ደግሞ ቅን ልብ ያላቸው የተለያዩ ሰዎች የአምላክን ቃል ለመረዳትና ተግባራዊ ለማድረግ በመጣራቸው የተገኘውን የባሕርይ ለውጥ እንመልከት። እንደ አውሬ ሊያስቆጥሯቸው የሚችሉ መጥፎ ባሕርያትን ለመተው ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል። አንተም ትልቅ የባሕርይ ለውጥ አድርገህ ይሆናል። ሌሎች መንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህም እንዲሁ አድርገው እንደሚሆን የታወቀ ነው። (ቆላስይስ 3:8-14) ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ይበልጥ በተቀራረብህና አብረህ በተሰበሰብህ መጠን ሰላማዊና ጥሩ ሰዎች መሆናቸውን መገንዘብህ አይቀርም። እነዚህ ሰዎች ፍጹማን ናቸው ማለት አይደለም፤ ሆኖም እንደ አንበሳና እንደ ሌሎች የዱር አራዊት ያለ አስፈሪ ባሕርይ የላቸውም። (ኢሳይያስ 35:9) በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚታየው እንዲህ ያለው ሰላም የሰፈነበት መንፈስ ምን ያሳያል? መንፈሳዊ ገነት ብለን በምንጠራው መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን በግልጽ የሚያሳይ ነው። ይህ መንፈሳዊ ገነት ደግሞ ለአምላክ ታማኝ ሆነን እስከቀጠልን ድረስ ወደፊት ለምንገባባት ምድራዊ ገነት አምሳያ ነው።

12, 13. ከመንፈሳዊ ገነት እንዳንወጣ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

12 ያም ሆኖ ልብ ልንለው የሚገባን አንድ ነገር አለ። አምላክ እስራኤላውያንን “ወደምትወርሷት ምድር ለመግባትና ለመያዝ ብርታት እንድታገኙ፣ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ” ብሏቸው ነበር። (ዘዳግም 11:8) ይህች ምድር በዘሌዋውያን 20:22, 24 ላይም ተገልጻለች፦ “እንድትኖሩባት እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ አድርጉም። . . . እናንተ ግን፣ ‘ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ማርና ወተት የምታፈሰውን አገር ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ’ አልኋችሁ።” አዎን፣ ተስፋ የተገባላቸውን ምድር ማግኘታቸው ከይሖዋ አምላክ ጋር በሚኖራቸው መልካም ግንኙነት ላይ የተመካ ነበር። አምላክ፣ ባቢሎናውያን እስራኤላውያንን ድል አድርገው ከምድራቸው እንዲያፈናቅሏቸው የፈቀደው ሳይታዘዙት በመቅረታቸው ነበር።

13 ይህን መንፈሳዊ ገነት ማራኪ የሚያደርጉት በርካታ ነገሮች አሉ። በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የሚታየው ነገር ሁሉ የሚያስደስትና መንፈስን የሚያድስ ነው። አውሬ መሰል ባሕርያቸውን ከለወጡ ክርስቲያኖች ጋር ሰላም የሰፈነበት ግንኙነት አለን። እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት ደጎችና አሳቢዎች ናቸው። ሆኖም በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ መቀጠላችን የተመካው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ባለን መልካም ግንኙነት ላይ ብቻ አይደለም። ከይሖዋ ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖረንና ፈቃዱን ልናደርግ ይገባናል። (ሚክያስ 6:8) ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት የገባነው በፍላጎታችን ነው፤ ሆኖም ከአምላክ ጋር ያለን ግንኙነት እንዳይበላሽ እስካልተጠነቀቅን ድረስ ሳይታወቀን ከዚህ መንፈሳዊ ገነት ልንወጣ ወይም ልንባረር እንችላለን።

14. በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ እንድንቀጥል ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?

14 በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ እንድንቀጥል የሚረዳን አንዱ ወሳኝ ነገር በአምላክ ቃል አማካኝነት መንፈሳዊነታችንን ማጠናከር ነው። በመዝሙር 1:1-3 ላይ የተገለጸውን ምሳሌያዊ ሁኔታ ልብ በል፦ “በክፉዎች ምክር የማይሄድ . . . ሰው ብፁዕ ነው። ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” በተጨማሪም በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ታማኝና ልባም ባሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል።—ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም

ስለ ገነት ያለህን አመለካከት አጠናክር

15. ሙሴ እስራኤላውያንን እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ ያልተፈቀደለት ለምን ነበር? ሆኖም ምን ተመልክቷል?

15 ለዚህ ገነት አምሳያ የሆነ ሌላም ነገር አለ። እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ሲንከራተቱ ከቆዩ በኋላ ሙሴ ሕዝቡን ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ወደ ሞዓብ ሜዳ ወሰዳቸው። ሙሴ ቀደም ሲል በፈጸመው ስህተት ምክንያት እስራኤላውያንን እየመራ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ አልተፈቀደለትም ነበር። (ዘኍልቍ 20:7-12፤ 27:12, 13) “ከዮርዳኖስ ማዶ ያለችውን ያችን መልካሚቱን ምድር . . . እንዳይ ፍቀድልኝ” በማለት አምላክን ተማጸነ። ሙሴ ተስፋይቱ ምድር መግባት ባይችልም ወደ ፈስጋ ተራራ ወጥቶ የምድሪቱን የተለያዩ ገጽታዎች ከተመለከተ በኋላ ምድሪቱ ምን ያህል ‘መልካም’ እንደሆነች ተገንዝቦ መሆን አለበት። አንተስ ይህች ምድር ምን ትመስል እንደነበረ ታውቃለህ?—ዘዳግም 3:25-27

16, 17. (ሀ) ጥንት ተስፋይቱ ምድር የነበረችበት አካባቢ አሁን ካለው የአካባቢው ገጽታ የሚለየው በምንድን ነው? (ለ) ይህ አካባቢ በአንድ ወቅት በእርግጥም ገነት ይመስል እንደነበረ እንድናምን የሚያደርገን ምንድን ነው?

16 ይህን አካባቢ ዛሬ ካለው ገጽታ አንጻር ከተመለከትከው ወደ አእምሮህ የሚመጣው አሸዋና ዓለት የሞላበት በፀሐይ ትኩሳት የነደደ ምድረ በዳ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አካባቢ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከአሁኑ ፈጽሞ የተለየ ገጽታ እንደነበረው የሚያሳምን በቂ ማስረጃ አለ። በውኃና በአፈር ምርምር ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ዋልተር ላውደርሚልክ ሳይንቲፊክ አሜሪካን በተባለው መጽሔት ላይ በዚያ የሚገኘው ምድር “በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በደረሰበት ጉስቁልና ምክንያት ተራቁቷል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። አክለውም “በአንድ ወቅት ውበት ተላብሶ የነበረውን ምድር ‘በምድረ በዳ’ የተካው ተፈጥሮ ሳይሆን የሰው ልጅ ነው” በማለት ጽፈዋል። እንዲያውም “ይህ ምድር በአንድ ወቅት ገነት የሚመስል የግጦሽ ቦታ” እንደነበረ ካደረጉት ጥናት ለመረዳት ይቻላል። የሰው ልጅ ‘ገነት ይመስል የነበረውን’ ይህን ምድር እንዳልነበር አድርጎታል። a

17 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባነበብከው ነገር ላይ ስታሰላስል ተስፋይቱ ምድር በእርግጥ ገነት ትመስል እንደነበር መገንዘብህ አይቀርም። ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ በሙሴ አማካኝነት እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶ ነበር፦ “ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት። ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር የሚንከባከባት . . . ናት።”—ዘዳግም 11:8-12

18. በኢሳይያስ 35:2 ላይ የሚገኘው ትንቢት በግዞት ለነበሩ እስራኤላውያን የተስፋይቱን ምድር ገጽታ በሚመለከት ምን አስገንዝቧቸው መሆን አለበት?

18 መላዋ ተስፋይቱ ምድር ውበት የተላበሰችና ለም ስለነበረች ስለተወሰኑ ቦታዎች እንኳ ሲጠቀስ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የገነት ገጽታ ነው። በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ላይ ከሚገኘውና ከባቢሎን ምርኮ በተመለሱ እስራኤላውያን ላይ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ካገኘው ትንቢት ይህን በግልጽ መረዳት ይቻላል። ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በደስታና በዝማሬ ሐሤት ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር ይሰጠዋል፤ የቀርሜሎስንና የሳሮንን ግርማ ይለብሳል። የአምላካችንን ታላቅ ግርማ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ያያሉ።” (ኢሳይያስ 35:2) እስራኤላውያን ስለ ሊባኖስ፣ ስለ ቀርሜሎስና ስለ ሳሮን ሲሰሙ በዓይነ ኅሊናቸው አስደሳችና ውብ እይታ ስለው መሆን አለበት።

19, 20. (ሀ) የጥንቱ የሳሮን አካባቢ ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ። (ለ) የገነት ተስፋችንን ማጠናከር የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

19 እስቲ በሰማርያ ኮረብታና በታላቁ ባሕር ወይም በሜድትራንያን መካከል የሚገኘውን የሳሮንን የተንጣለለ ምድር እንመልከት። (በገጽ 10 ላይ የሚገኘውን ፎቶ ግራፍ ተመልከት።) ይህ አካባቢ በውበቱና በለምነቱ የታወቀ ከመሆኑም በላይ ውኃ በደንብ ስለሚያገኝ ለግጦሽ ምቹ ነበር። ሆኖም በስተ ሰሜን በኩል እንደ ወርካ ባሉ ትላልቅ ዛፎች የተሸፈነ ነው። (1 ዜና መዋዕል 27:29፤ ማሕልየ መሓልይ 2:1፤ ኢሳይያስ 65:10) በመሆኑም ኢሳይያስ 35:2 እስራኤላውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ እንዲሁም ምድሪቱም እንደምታብብና ገነት እንደምትመስል የሚገልጽ ትንቢት ነው። ጳውሎስ ባየው ራእይ መሠረት ደግሞ ይህ ትንቢት አስደሳች ስለሆነ መንፈሳዊ ገነት የሚጠቁም ነው። እንደ ሌሎቹ ትንቢቶች ሁሉ ይህም ትንቢት ምድር ገነት እንደምትሆን ያለንን ተስፋ ያጠናክርልናል።

20 በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ስንኖር ለዚህ ገነት ያለንን አድናቆት ከፍ ማድረግና ምድር ገነት እንደምትሆን ያለንን ተስፋ ማጠናከር እንችላለን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለምናነባቸው ነገሮች ያለንን ግንዛቤ በማስፋት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መግለጫዎችና ትንቢቶች አንዳንድ ቦታዎችን በስም ይጠቅሳሉ። እነዚህ ቦታዎች የት እንደሚገኙና ከሌሎች አካባቢዎች አንጻር ስላላቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዴኒስ ባሊ ዘ ጂኦግራፊ ኦቭ ዘ ባይብል በተባለው ጽሑፋቸው ላይ “በአካባቢው የነበረው የዕጽዋቱ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበረው በእጅጉ ተለውጧል” ብለዋል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? “ሰዎች ደኑን እየጨፈጨፉ ለማገዶና ለግንባታ ስለተጠቀሙበት . . . ምድሩ ለመጥፎ የአየር ጠባይ ሊጋለጥ ችሏል። የአካባቢው ገጽታ ቀስ በቀስ እንዲለወጥና እንዲበላሽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው የሰው ልጅ ተፈጥሮን በዚህ መንገድ መጠቀሙ ነው።”

ታስታውሳለህ?

• ሐዋርያው ጳውሎስ በራእይ የተመለከተው “ገነት” ምንድን ነው?

የኢሳይያስ ምዕራፍ 35 የመጀመሪያ ፍጻሜ ምን ነበር? ጳውሎስ ካየው ራእይ ጋር ያለውስ ግንኙነት ምንድን ነው?

• ስላለንበት መንፈሳዊ ገነት ያለንን አድናቆት ከፍ ማድረግና ምድር ገነት እንደምትሆን ያለንን ተስፋ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የሚገኘው የተንጣለለው የሳሮን አካባቢ ለም ነበር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙሴ ተስፋይቱ ምድር ‘መልካም’ እንደነበረች ተገንዝቧል