“እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት” የተባለው ማን ነው?
“እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት” የተባለው ማን ነው?
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይሖዋ እውነተኛ አምላክ ነው። ለሚወዱት የዘላለም ሕይወት የሚሰጠው ፈጣሪ እሱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡና የሚያምኑ በርካታ ሰዎች በርዕሱ ላይ ለተጠየቀው ጥያቄ ይህን መልስ ይሰጣሉ። አዎን፣ ኢየሱስ ራሱ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሎ ተናግሯል።—ዮሐንስ 17:3 የ1954 ትርጉም
ሆኖም በርካታ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች በርዕሱ ላይ ያለውን አገላለጽ የሚረዱት ለየት ባለ መንገድ ነው። ይህ ሐሳብ የተወሰደው ከ1 ዮሐንስ 5:20 ነው፤ ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይላል:- “እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።”
በሥላሴ የሚያምኑ ሰዎች “እርሱ” (ሆውቶስ) የሚለው ተውላጠ ስም የሚያመለክተው ከዚህ ቃል አጠገብ የተጠቀሰውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው ብለው ይናገራሉ። በመሆኑም ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው” ብለው ይከራከራሉ። ነገር ግን ይህ የሥላሴ አማኞች የሚያቀርቡት ማብራሪያ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች ጋር የሚቃረን ከመሆኑም በላይ በርካታ ታዋቂ ምሑራን አይስማሙበትም። የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ምሑር የሆኑት ቢ ኤፍ ዌስኮት እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “ሐዋርያው [ሆውቶስ የሚለውን ተውላጠ ስም] የጠቀሰው ከቃሉ አጠገብ ያለውን ባለቤት በማሰብ ሳይሆን ቀደም ብሎ በዋነኝነት የገለጸውን ባለቤት በአእምሮው በመያዝ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው።” ስለሆነም ሐዋርያው ዮሐንስ “እርሱ” ሲል በአእምሮው ይዞ የነበረው የኢየሱስን አባት ይሖዋን ነው። ጀርመናዊው የሃይማኖት ምሑር ኤሪሽ ሀዉፕት እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “ቃሉ [ሆውቶስ] የተጠቀሰው ከቃሉ አጠገብ የተገለጸውን ባለቤት ለማመልከት ይሁን . . . አሊያም ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን አምላክ ለማመልከት በትክክል ማወቅ ያስፈልጋል። . . . በመጨረሻ ላይ ከጣዖት ስለመራቅ ከተሰጠው ማስጠንቀቂያ መረዳት እንደምንችለው ሐሳቡ የአምላክን እውነተኝነት ለማረጋገጥ እንጂ የኢየሱስን መለኮትነት ለማሳወቅ ተብሎ የገባ አይደለም።”
በሮም የሚገኘው የጳጳሳት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተቋም ያሳተመው ኤ ግራማቲካል አናሊሲስ ኦቭ ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት ይህንኑ ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል:- “[ከቁጥር] 18-20 ለተጠቀሰው ሐሳብ መደምደሚያ ሆኖ የተገለጸው [ሆውቶስ] የሚያመለክተው ከጣዖታት በተቃራኒ ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ነው (ቁጥር 21)።”
“እርሱ” ተብሎ የተተረጎመው ሆውቶስ የሚለው ቃል በአብዛኛው አጠገቡ ያለውን ባለቤት አያመለክትም። ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ 4:10, 11 ላይ ሉቃስ ይህን ተውላጠ ስም እንዴት እንደተጠቀመበት እንመልከት:- “እናንተ በሰቀላችሁት፣ እግዚአብሔር ግን ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መዳኑንና ፊታችሁ መቆሙን እናንተም ሆናችሁ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይህን ይወቅ። እርሱም [ሆውቶስ]፣ ‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማእዘን ራስ የሆነው ድንጋይ’ ነው።” ምንም እንኳን ሆውቶስ የሚለው ቃል የተጻፈው ፈውስ ያገኘው ሰው ከተገለጸ በኋላ ቢሆንም “እርሱም” የተባለው ይህ ሰው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በቁጥር 11 ላይ “እርሱም” የተባለው ክርስቲያን ጉባኤ የተመሠረተበት “የማእዘን ድንጋይ” የሆነው የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው።—ኤፌሶን 2:20፤ 1 ጴጥሮስ 2:4-8
እንደነዚህ ያሉት ማስረጃዎች ግሪካዊው ምሑር ዳንኤል ዋላስ ያሉትን የሚከተለውን ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጡልናል:- “ጸሐፊው” የግሪክኛ ገላጭ ተውላጠ ስሞችን የሚጠቀመው “ከተውላጠ ስሙ አጠገብ ያለውን ባለቤት በአእምሮው ይዞ ላይሆን ይችላል።”
“እውነተኛ አምላክ”
ሐዋርያው ዮሐንስ እንደጻፈው “እውነተኛ አምላክ” የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነው ይሖዋ ነው። ብቸኛው እውነተኛ አምላክና ፈጣሪ እርሱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን” በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 8:6፤ ኢሳይያስ 42:8) በተጨማሪም የእውነት ምንጭ ስለሆነ በ1 ዮሐንስ 5:20 ላይ “እውነተኛ አምላክ” ተብሎ ተገልጿል። ይሖዋ በሥራው ሁሉ የታመነና ሊዋሽ የማይችል በመሆኑ መዝሙራዊው “የእውነት አምላክ” ብሎታል። (መዝሙር 31:5፤ ዘፀአት 34:6፤ ቲቶ 1:2) ኢየሱስ ስለ ሰማያዊ አባቱ ሲናገር “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። እንዲሁም የሚያስተምረውን ትምህርት በተመለከተ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው።”—ዮሐንስ 7:16፤ 17:17
በተጨማሪም ይሖዋ “የዘላለም ሕይወት ነው።” በክርስቶስ በኩል ያገኘነው የማይገባን የሕይወት ስጦታ ምንጭ ይሖዋ ነው። (መዝሙር 36:9፤ ሮሜ 6:23) ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ “ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ” ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዕብራውያን 11:6) በእርግጥም አምላክ ልጁን ከሞት በማስነሳት ዋጋውን ከፍሎታል፤ በሙሉ ልባቸው የሚያገለግሉትንም የዘላለም ሕይወት በመስጠት ዋጋቸውን ይከፍላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 26:23፤ 2 ቆሮንቶስ 1:9
ከላይ ካየናቸው ሐሳቦች አንጻር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ ይኖርብናል? “እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት” ከይሖዋ በስተቀር ማንም ሊሆን አይችልም። ከፍጥረታቱ፣ በሙሉ ልብ የቀረበ አምልኮ ሊቀበል የሚገባው እርሱ ብቻ ነው።—ራእይ 4:11