በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች ሆይ—ልባችሁን በመጠበቅ ረገድ ወላጆቻችሁ እንዲረዷችሁ ፍቀዱላቸው!

ወጣቶች ሆይ—ልባችሁን በመጠበቅ ረገድ ወላጆቻችሁ እንዲረዷችሁ ፍቀዱላቸው!

ወጣቶች ሆይ—ልባችሁን በመጠበቅ ረገድ ወላጆቻችሁ እንዲረዷችሁ ፍቀዱላቸው!

ርከበኛ የሚያጋጥመው በጣም ከባድ ችግር ምን ይመስልሃል? እጅግ ሰፊ የሆነውን ውቅያኖስ በሰላም ማቋረጥ ነው? አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመው ችግር ይህ አይደለም። በርካታ የመርከብ አደጋዎች የሚከሰቱት ጥልቅ በሆነው የባሕር ክፍል ላይ ሳይሆን በባሕር ዳርቻ አካባቢ ነው። እንዲያውም አውሮፕላን መሬት ላይ ከማሳረፍ ይበልጥ መርከብ ወደብ ላይ ማቆም በጣም አስቸጋሪ ነው። ለምን?

መርከበኛው በሰላም መልሕቁን ለመጣል በወደቡ አካባቢ ካሉት አደገኛ ሁኔታዎች ሁሉ መራቅ ይኖርበታል። ከሌሎች መርከቦች ጋር እንዳይጋጭ እየተጠነቀቀ ወደ ወደቡ በሚጠጋበት ጊዜ በውስጠኛው የውሃ ክፍል ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ፈረሰኛ ውሃ ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። እንዲሁም የአሸዋ ክምር፣ ዓለቶችንና በውሃው ስር የተደበቁ የመርከብ ስብርባሪዎችን ሳይነካ ተጠንቅቆ ማለፍ ይኖርበታል። መርከበኛው ወደዚህ ወደብ ሲመጣ የመጀመሪያ ጊዜው ከሆነ ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል።

በመሆኑም ጥበበኛ የሆነ መርከበኛ እነዚህን ችግሮች ለመወጣት እንዲረዳው ወደቡን ጠንቅቆ የሚያውቅ ረዳት መርከበኛ በሥራው ላይ አብሮት እንዲሠማራ ያደርጋል። ረዳቱ ከዋናው መርከበኛ ጎን በመቆጣጠሪያው ቦታ ላይ በመሆን ሙያዊ መመሪያ ይሰጠዋል። አደገኛ ሁኔታዎችን በንቃት በመከታተል እየተጋገዙ መርከቧን በተገኘው የባሕር ወሽመጥ እየመሩ ወደ ወደብ ያደርሷታል።

ረዳት መርከበኛው የሚሰጠው በጣም ጠቃሚ የሆነ ሙያዊ እገዛ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተቋቁመው ለማለፍ እቅድ ማውጣት የሚጠበቅባቸውን ክርስቲያን ወጣቶች ለመርዳት ለተደረገው በዋጋ የማይተመን ዝግጅት ምሳሌ ይሆናል። ይህ ዝግጅት ምንድን ነው? በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ይህ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

እስቲ ስለ መርከብ ያነሳነውን ምሳሌ ማየታችንን እንቀጥል። በአፍላ የጉርምስና እድሜ ላይ የምትገኝ ከሆነ ልክ እንደ ዋናው መርከበኛ በአንደኛ ደረጃ ለሕይወትህ ኃላፊነት የምትወስደው አንተ ነህ። ወላጆችህ ደግሞ እንደ ረዳት መርከበኛው ሁሉ አይተሃቸው የማታውቃቸው በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙህ ጊዜ አመራር ይሰጡሃል። በእርግጥ በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ ስትሆን ወላጆችህ የሚሰጡህን ምክር መቀበል ይከብድሃል። ለምን ይሆን?

ችግሩ ከልብ ጋር የተያያዘ ነው። ምሳሌያዊ ልብህ የተከለከለውን ነገር የማድረግ ወይም ነፃነትህን የነፈገህ የሚመስልህን ነገር የመቃወም ፍላጎት እንዲያድርብህ ሊገፋፋህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” መሆኑን ይናገራል። (ዘፍጥረት 8:21) ይሖዋ ከባድ ፈተና እንደሚያጋጥምህ ሲያስጠነቅቅ እንዲህ ብሏል:- “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው።” (ኤርምያስ 17:9 የ1954 ትርጉም) ልብ የተሳሳቱ ድብቅ ምኞቶችን ከማብቀሉም በላይ አንድ ወጣት ወላጆቹ ምንም እንኳን ከእርሱ የበለጠ ተሞክሮ ያላቸው ቢሆኑም ከእነርሱ የተሻለ እውቀት እንዳለው አድርጎ እንዲያስብ ሊገፋፋው ይችላል። ነገር ግን መርከብን ወደ አንድ ወደብ ከመምራት ጋር ተመሳስሎ በተገለጸው በአስቸጋሪው የአሥራዎቹ እድሜ የወላጆችህን እርዳታ የምትፈልግበት በቂ ምክንያት አለ።

ወላጆችህን መታዘዝ ያለብህ ለምንድን ነው?

በአንደኛ ደረጃ፣ የቤተሰብ መሥራች የሆነው ይሖዋ ወላጆችህ የሚሰጡህን መመሪያ መታዘዝ እንደሚገባህ ተናግሯል። (ኤፌሶን 3:15) አምላክ አንተን የመንከባከቡን ኃላፊነት ለወላጆችህ የሰጠ በመሆኑ እንዲህ ሲል ይመክርሃል:- “ልጆች ሆይ፤ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና።” (ኤፌሶን 6:1-3፤ መዝሙር 78:5) በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ የምትገኝ ብትሆንም ወላጆችህ ለአንተ መመሪያ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው፤ አንተም የመታዘዝ ግዴታ አለብህ። ሐዋርያው ጳውሎስ ልጆች ወላጆቻቸውን መታዘዝ እንዳለባቸው ለመግለጽ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል በማንኛውም እድሜ ላይ ያሉ ልጆችን ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አብዛኞቹ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አዋቂዎች ቢሆኑም የኢየሩሳሌም ‘ልጆች’ እንደሆኑ አድርጎ እንደገለጻቸው በማቴዎስ 23:37 ላይ ተመዝግቦ እናገኛለን።

በጥንት ጊዜ የነበሩ በርካታ ታማኝ ወንዶች በጉልምስና እድሜ ላይ እያሉም ወላጆቻቸውን ይታዘዙ ነበር። ያዕቆብ ዐዋቂ የነበረ ቢሆንም አባቱ የይሖዋ አምላኪ ያልሆነች ሴት እንዳያገባ በነገረው ጊዜ መታዘዝ እንደሚገባው ተገንዝቦ ነበር። (ዘፍጥረት 28:1, 2) ያዕቆብ ወንድሙ አረማዊ የሆኑ ከነዓናውያን ሴቶችን በማግባቱ የወላጆቹ ልብ በጣም ማዘኑን እንዳስተዋለ ምንም ጥርጥር የለውም—ዘፍጥረት 27:46

ክርስቲያን ወላጆችህ መመሪያ እንዲሰጡህ አምላክ ከሰጣቸው ኃላፊነት በተጨማሪ አማካሪህ ለመሆን ከማንም የበለጠ ብቃት ያላቸው እነሱ ናቸው ሊባል ይችላል። ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ማንነትህን ጥሩ አድርገው ስለሚያውቁና ለበርካታ ዓመታት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅራቸውን ሲለግሱህ ስለኖሩ ነው። ልክ እንደ ረዳት መርከበኛው እነሱም የሚነግሩህ ከልምዳቸው ያገኙትን ነገር ነው። ‘የወጣትነትን ክፉ ምኞት’ በራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ ያውቁታል። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ መሆናቸው መጠን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መተግበር ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ በራሳቸው ሕይወት አይተዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:22

እነዚህን የመሰሉ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ረዳቶች ከጎንህ ስላሉልህ እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሚባሉ ሁኔታዎችን እንኳን ለማሸነፍ ትችላለህ። ከተቃራኒ ጾታ ጋር ሊኖርህ የሚችለውን ግንኙነት እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። በዚህ ከባድ ጉዳይ ረገድ ክርስቲያን ወላጆችህ መመሪያ ሊሰጡህ የሚችሉት እንዴት ነው?

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ያለው መሳሳብ

ረዳት መርከበኛው ለዋናው መርከበኛ ከአሸዋ ክምር ርቆ እንዲጓዝ ይነግረዋል። የአሸዋ ክምር ያን ያህል የሚጎዳ ባይመስልም እንኳን ያለማቋረጥ አቀማመጡን ስለሚቀያይር አደጋ ሊያደርስ ይችላል። በተመሳሳይ ወላጆችህ ስሜትህን ከሚያነሳሱና ወጥመድ ውስጥ እንድትገባ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች እንድትርቅ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ያህል ወላጆች ለተቃራኒ ጾታ የሚኖረው ስሜት በጣም ኃይለኛ እንደሆነና ገልጾ ለማስረዳትም እንደሚያስቸግር ያውቃሉ። ነገር ግን አንዴ ከተቀሰቀሰ አደጋ እንዲደርስብህ ሊያደርግ ይችላል።

የዲና ምሳሌ ራስን ለአደገኛ ሁኔታዎች ማጋለጥ ምን ውጤት እንደሚያስከትል ያስተምረናል። የማወቅ ጉጉቷና የመዝናናት ፍላጎቷ ሥነ ምግባራቸው ካዘቀጠ ከነዓናውያን ሴቶች ጋር ወዳጅነት የመመሥረት ሐሳብ እንዲያድርባት ሳያደርግ አልቀረም። በመጀመሪያ ላይ ምንም ችግር የማያስከትል ይመስል የነበረው ጨዋታ አሳዛኝ ውጤት አመጣ፤ በከተማይቱ ውስጥ “እጅግ የተከበረው” ወጣት ደፈራት።—ዘፍጥረት 34:1, 2, 19

የጾታ ግንኙነት እንደ ትልቅ ነገር በሚታይበት በዛሬው ጊዜ ይህን የመሳሰሉ አደጋዎች እየተባባሱ መጥተዋል። (ሆሴዕ 5:4) ብዙ ወጣቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር መጫወት በጣም አስደሳች ነገር እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። አካላዊ ቁመናዋ ከማረከህ ሴት ጋር ለብቻችሁ ሆናችሁ ጊዜ ስለማሳለፍ ስታስብ ልብህ ይደሰት ይሆናል። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆችህ ግን አምላክ ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች ከማያከብሩ ወጣቶች ጋር ወዳጅነት እንዳትመሠርት ሊከለክሉህ ይችላሉ።

ላውራ በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ያላቸው የማወቅ ጉጉት አደገኛ ሁኔታዎችን እንዳያስተውሉ ሊያደርጋቸው እንደሚችል አምናለች። እንዲህ ብላለች:- “በክፍሌ ውስጥ የሚገኙት ተማሪዎች ከሚያማምሩ ወንዶች ጋር ሲጨፍሩ ማምሸታቸው ፈጽሞ የማይረሳ ትዝታ ጥሎባቸው እንዳለፈ ይነግሩኛል። አብዛኛውን ጊዜ እንደሚያጋንኑ ባውቅም ሄዶ የማየት ጉጉት ያድርብኛል፤ እንዲሁም ብዙ ነገር እንደቀረብኝ አስባለሁ። ወላጆቼ እንዲህ ወዳሉ ቦታዎች እንድሄድ አለመፍቀዳቸው ተገቢ መሆኑን ባምንም እዚያ ቦታ ለመገኘት እጓጓለሁ።”

መርከብ ፍሬን ስለሌለው ለመቆም ረጅም ጊዜ ይፈጅበታል። ወላጆች የጾታ ፍላጎት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ያውቃሉ። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የጾታ ፍላጎቱን መግታት የተሳነው ሰው ሊታረድ እንደሚነዳ በሬ ተደርጎ ተገልጿል። (ምሳሌ 7:21-23) እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ገብተህ መንፈሳዊና ስሜታዊ አደጋ እንዲደርስብህ እንደማትፈልግ የታወቀ ነው። ምናልባት ወላጆችህ በዚህ ረገድ ልብህ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እያመራ መሆኑን ሊገነዘቡና ተገቢውን ምክር ሊለግሱህ ይችላሉ። የሚሉህን ሰምተህ ራስህን ከአደጋ በመጠበቅ ጥበብ ያለበት እርምጃ ትወስዳለህ?—ምሳሌ 1:8፤ 27:12

የእኩዮችን ተጽዕኖ ለመቋቋምም ቢሆን የወላጆችህን ድጋፍ ማግኘት ይኖርብሃል። እንዴት ሊረዱህ ይችላሉ?

እኩዮችህ የሚያደርጉብህ ከባድ ተጽዕኖ

ኃይለኛ ማዕበል ወይም ፈረሰኛ ውሃ መርከቧ አቅጣጫዋን እንድትስት ሊያደርጋት ይችላል። ከዚህ አደገኛ ሁኔታ ለማምለጥ የመርከቧን አቅጣጫ ቀይሮ መንዳት ያስፈልጋል። በተመሳሳይ ወጣቶች የሚያሳድሩብህን አታላይ ተጽዕኖ ለመቋቋም እርምጃ ካልወሰድክ መንፈሳዊ አቅጣጫህን እንድትስት ሊያደርጉህ ይችላሉ።

ከዲና ታሪክ እንደምንማረው “የተላሎች ባልንጀራ ግን ጉዳት ያገኘዋል።” (ምሳሌ 13:20) መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ” የሚለውን ቃል የሚጠቀመው ይሖዋን የማያውቅና በመንገዱ ለመመላለስ የማይፈልግ ሰውን ለማመልከት መሆኑን ልብ በል።

በእርግጥ በክፍልህ ውስጥ ያሉትን ልጆች አስተሳሰብ ወይም የሚያደርጉትን ነገር አለመቀበል ከባድ ሊሆን ይችላል። ማሪያ ሆሴ እንዲህ ትላለች:- “በወጣቶች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እፈልግ ነበር። ከእነርሱ የተለየሁ እንደሆንኩ አድርገው እንዲያስቡ ስለማልፈልግ በተቻለ መጠን እነርሱን ለመምሰል እጥር ነበር።” እኩዮችህ በሙዚቃ ምርጫህ፣ በአለባበስህ አልፎ ተርፎም በአነጋገርህ ላይ አንተ ሳታውቀው ተጽዕኖ ሊያደርጉብህ ይችላሉ። በእድሜ ከሚመጣጠኑህ ወጣቶች ጋር መቀራረብህ ያስደስትህ ይሆናል። ይህ ተፈጥሯዊ ፍላጎት ቢሆንም ጎጂ ለሆነ ከባድ ተጽዕኖ ሊያጋልጥህ ይችላል።—ምሳሌ 1:10-16

ካሮሊን ከጥቂት ዓመታት በፊት አጋጥሟት የነበረውን ችግር እንዲህ ብላ ተናግራለች:- “ከአሥራ ሦስት ዓመቴ ጀምሮ አብረውኝ ከሚውሉት ልጃገረዶች መካከል አብዛኞቹ የወንድ ጓደኞች ነበሯቸው፤ ለበርካታ ዓመታት ያለማቋረጥ የእነርሱን ፈለግ እንድከተል ተጽዕኖ ሲያደርጉብኝ ቆይተዋል። እናቴ ግን በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ አስፈላጊውን መመሪያ ሰጥታኛለች። ስናገር በትዕግሥት ለሰዓታት ታዳምጠኛለች፣ አሳማኝ የሆኑ ሐሳቦችን እያቀረበች ታወያየኛለች እንዲሁም የወንድ ጓደኛ ሊኖረኝ የሚገባው ከጎለመስኩ በኋላ መሆን ያለበት ለምን እንደሆነ እንድገነዘብ ረድታኛለች።”

እንደ ካሮሊን እናት ሁሉ ወላጆችህ ስለ እኩዮች ተጽዕኖ ማስጠንቀቅ፣ አንዳንድ ነገሮችን እንዳታደርግ መከልከልና ልትርቃቸው ስለሚያስፈልግህ ጓደኞችህም ጭምር ውሳኔ ማድረግ እንደሚገባቸው ይሰማቸው ይሆናል። ኔተን በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት ከወላጆቹ ጋር ብዙ ጊዜ ይጋጭ እንደነበር እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ጓደኞቼ ብዙ ጊዜ አብሬያቸው እንድዝናና ይጋብዙኛል፤ ወላጆቼ ግን ከልጆቹ ጋር በመንቀዋለል ጊዜዬን እንዳባክን ወይም ቁጥጥር በማይደረግባቸው ድግሶች ላይ እንድገኝ አይፈቅዱልኝም ነበር። በወቅቱ የሌሎቹ ልጆች ወላጆች ከእኔ ወላጆች ይልቅ ላላ የሚሉበት ምክንያት አይገባኝም ነበር።”

በኋላ ግን ኔተን ምክንያቱ ምን እንደሆነ ተረዳ። እንዲህ ሲል እውነቱን ተናግሯል:- “‘ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል’ የሚሉት ቃላት በእኔ ላይ እንደሚሠሩ ተገንዝቤአለሁ። ወጣት ወንዶች በቡድን ሆነው ጊዜ ሲያሳልፉ ደግሞ እንዲህ ያለው ሞኝነት በቀላሉ ይንጸባረቃል። አንዱ ልጅ መጥፎ ነገር ማድረግ ይጀምራል፤ ቀጥሎ ሌላው ከመጀመሪያው የባሰ መጥፎ ነገር ያደርጋል፤ ሦስተኛው ደግሞ ከሁለቱም የከፋ ነገር ይሠራል። በዚህን ጊዜ ሌሎቹ በድርጊቱ ተካፋይ እንዲሆኑ ግፊት ይደረግባቸዋል። ይሖዋን እናገለግላለን የሚሉ ወጣቶችም ሳይቀሩ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ።”—ምሳሌ 22:15

ኔተንና ማሪያ ሆሴ እኩዮቻቸው የሚሏቸውን ነገር እንዳያደርጉ ወላጆቻቸው በሚከለክሏቸው ጊዜ ከልባቸው ጋር ትግል ይገጥሙ ነበር። ቢሆንም ወላጆቻቸውን መታዘዛቸው የኋላ ኋላ ደስታ አስገኝቶላቸዋል። የምሳሌ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የጠቢባንን ቃል ልብ ብለህ ስማ፤ ልብህም ወደ ትምህርቴ ያዘንብል።”—ምሳሌ 22:17

አክብሮት ይገባቸዋል

መርከብ ወደ አንድ ጎን ዘመም ካለ ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ማንቀሳቀስ ያስቸግራል፤ እንዲያውም በጣም ካዘመመ በቀላሉ ሊገለበጥ ይችላል። በተመሳሳይ ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት ወደ ራስ ወዳድነትና የተከለከልነውን ነገር ወደ ማድረግ እናዘነብላለን። ወጣቶች እነዚህ ዝንባሌዎች ቢያስቸግሯቸውም እንኳን የወላጆቻቸውን መመሪያ በጥንቃቄ የሚከተሉ ከሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደብ ላይ በሰላም ሊደርሱ ይችላሉ።

ለምሳሌ ያህል ወላጆችህ ወደ ሕይወት በሚወስደው ቀጭን መንገድና ወደ ጥፋት በሚያደርሰው ሰፊ ጎዳና መካከል አንድ ሌላ መንገድ አለ የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳይኖርህ ሊረዱህ ይችላሉ። (ማቴዎስ 7:13, 14) ሙሉ በሙሉ የአምላክን ሕግ እስካልጣስኩ ድረስ በተወሰነ ደረጃ ስህተት የሆነ ነገር ብፈጽም ምንም አይደለም ወይም ኃጢአትን “ቀምሼ” ብቻ እስከተውኩት ድረስ ምንም ጉዳት የለውም ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው። በአንድ በኩል ይሖዋን በማገልገል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዓለምንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በመውደድ ‘በሁለት ሐሳብ የሚዋልሉ’ ሰዎች መንፈሳዊነታቸው በቀላሉ ሊዳከም ይችላል። (1 ነገሥት 18:21፤ 1 ዮሐንስ 2:15) ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ወደ ኃጢአት ያዘነበልን በመሆናችን ነው።

ለኃጢአት ፍላጎታችን ቦታ የምንሰጠው ከሆነ ተገዢው ሊያደርገን ይችላል። “ተንኰለኛ” የሆነው ልባችን ተጨማሪ ነገር ይፈልጋል እንጂ ኃጢአትን በመቅመስ ብቻ አይረካም። (ኤርምያስ 17:9) አንድ ጊዜ መንፈሳዊ አቅጣጫችንን ከሳትን ዓለም በጣም ከባድ የሆኑ ተጽዕኖዎችን ይደራርብብናል። (ዕብራውያን 2:1) አንተ ሳታውቀው በመንፈሳዊ እያዘመምክ መሆንህን ክርስቲያን ወላጆችህ ሊያስተውሉ ይችላሉ። አንዳንድ ዘመናዊ የሆኑ ነገሮችን ለመማር ያንተን ያህል ፈጣን ባይሆኑም የልብን አታላይነት ከአንተ ይበልጥ ያውቃሉ። በመሆኑም ‘ልብህን’ ሕይወት ሊያስገኝልህ በሚችለው ‘ትክክለኛ መንገድ’ እንድትመራ ሊረዱህ ይፈልጋሉ።—ምሳሌ 23:19

እርግጥ ነው፣ ወላጆችህ እንደ ሙዚቃ፣ መዝናኛና የልብስ ምርጫ የመሳሰሉ ከባድ ጉዳዮችን በተመለከተ ፍጹም ሚዛናዊ የሆነ መመሪያ ይሰጡኛል ብለህ መጠበቅ የለብህም። ወላጆችህ የሰሎሞንን ያህል ጥበብና እንደ ኢዮብ ዓይነት ትዕግሥት ላይኖራቸው ይችላል። ልክ እንደ ረዳት መርከበኛው ከተገቢው በላይ ጥንቃቄ ያደርጉ ይሆናል። ነገር ግን ‘የአባትህን ምክር የምታዳምጥና የእናትህንም ትምህርት የማትተው’ ከሆነ የሚሰጡህ መመሪያ ምን ያህል ውድ እንደሆነ መገንዘብህ አይቀርም።—ምሳሌ 1:8, 9

ሌሎች ወጣቶች ወላጆቻቸውን የሚያቃልል ነገር ሲናገሩ ትሰማ ይሆናል። ነገር ግን ወላጆችህ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመታዘዝ የሚጥሩ ከሆነ ምንም ዓይነት ፈተና ሲያጋጥምህ ከጎንህ ይቆማሉ። ተሞክሮ ያለው ረዳት መርከበኛ ለዋናው መርከበኛ ምን ማድረግ እንዳለበት እንደሚነግረው ሁሉ አንተም ጥበብ ባለበት ጎዳና እንድትጓዝ የወላጆችህ መመሪያ ያስፈልግሃል። ይህን መመሪያ ከተቀበልክ በእጅጉ ትካሳለህ።

“ጥበብ ልብህ ውስጥ ትገባለችና፤ ዕውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለች፤ የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ ማስተዋልም ይጠብቅሃል። ጥበብ ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች፣ ከክፉዎችም መንገድ ታድንሃለች፤ እነዚህም በጨለማ መንገድ ለመሄድ፤ ቀናውን ጐዳና የሚተዉ ናቸው፤ . . . ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ።”—ምሳሌ 2:10-13, 21

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የወጣቶች ተጽዕኖ መንፈሳዊ አቅጣጫህን ሊያስትህ ይችላል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዲናን ታሪክ አስታውስ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ዋና መርከበኛ ልምድ ያለውን ረዳት መርከበኛ ምክር እንደሚጠይቅ ሁሉ ወጣቶችም የወላጆቻቸውን መመሪያ ለማግኘት መጣር ይኖርባቸዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፎቶ:- www.comstock.com