የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ ለተከታዮቹ “መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ” የሚል መመሪያ ሲሰጣቸው ካበደሩት ገንዘብ ዋናውም እንኳ እንዲመለስላቸው መጠየቅ እንደሌለባቸው መናገሩ ነበር?
በሉቃስ 6:35 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት በተሻለ መልኩ ለመረዳት የሙሴን ሕግ መመልከቱ ጠቃሚ ነው። በዚህ ሕግ ላይ እስራኤላውያን ከወንድሞቻቸው አንዱ ቢደኸይና እርዳታ ቢያስፈልገው ያለ ወለድ እንዲያበድሩት አምላክ አዝዟቸው ነበር። (ዘፀአት 22:25፤ ዘሌዋውያን 25:35-37) እንደዚህ ያለ ብድር የሚሰጠው የንግድ እንቅስቃሴ ለማካሄድ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እስራኤላውያን ያለ ወለድ የሚያበድሩት ችግር ላይ የወደቀው ሰው ከድህነት መላቀቅ ወይም ኑሮውን ማሸነፍ እንዲችል ለመርዳት ነው። ደግሞም ኢኮኖሚያዊ ችግር ከደረሰበት ሰው አጋጣሚውን በመጠቀም ትርፍ ለማግኘት መሞከር ለባልንጀራቸው ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ አይደለም። ያም ቢሆን ግን አበዳሪው የሰጠውን ገንዘብ መልሶ የማግኘት መብት የነበረው ሲሆን አንዳንድ ጊዜም መያዣ (እንደ ዋስትና የሚያገለግል ዕቃ) ይወስድ ነበር።
ኢየሱስ ከሕጉ ጋር ቢስማማም እርዳታ የሚያደርገው ሰው ገንዘቡን ‘መልሶ ለመቀበል’ ተስፋ ማድረግ እንደሌለበት በመናገር ሕጉ ይበልጥ ሰፋ ባለ መንገድ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል። እንደ እስራኤላውያን ሁሉ ክርስቲያኖችም አንዳንድ ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ሊደኸዩ ይችላሉ። እንደዚህ ያለ ከባድ ችግር የገጠመው አንድ ክርስቲያን ገንዘብ ቢፈልግ በደግነት መርዳቱ ተገቢ አይሆንም? በእርግጥም አንድ ክርስቲያን ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት ከባድ የገንዘብ ችግር ላይ ቢወድቅ የእምነት ባልንጀሮቹ ለእርሱ ያላቸው እውነተኛ ፍቅር እርዳታ እንዲያደርጉለት ሊያነሳሳቸው ይገባል። (ምሳሌ 3:27) አሊያም ደግሞ እንደዚህ ያለ ችግር ላጋጠመው ወንድማችን ልናበድረው ከምንችለው ያነሰም ቢሆን በስጦታ መልክ ልንሰጠው እንችላለን።—መዝሙር 37:21
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ በይሁዳ ለነበሩት በረሃብ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቻቸው በትንሿ እስያ ከነበሩ ክርስቲያኖች የተላከውን እርዳታ የማድረስ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 11:28-30) ዛሬም በተመሳሳይ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ክርስቲያኖች ችግር ለደረሰባቸው ወንድሞቻቸው ስጦታ ይልካሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ለሰዎች ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠትም ያስችላል። (ማቴዎስ 5:16) እርግጥ ነው፣ እርዳታ የፈለገው ሰው አመለካከትና ያለበት ሁኔታ ሊጤን ይገባል። እርዳታ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ጳውሎስ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” ብሎ ሲናገር ልብ ልንለው የሚገባ ነጥብ አስቀምጧል።—2 ተሰሎንቄ 3:10
አንድ ወንድም ብድር የጠየቀው በጣም ተቸግሮ ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም በገንዘብ ረገድ የገጠመውን ችግር አሸንፎ እንደገና ለመቋቋም ጊዜያዊ እርዳታ ብቻ አስፈልጎት ከሆነ ለዚህ ወንድም አለወለድ ማበደሩ ተገቢ ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም አበዳሪው ሙሉው ገንዘብ እንደሚመለስለት አስቦ ማበደሩ ኢየሱስ በሉቃስ 6:35 ላይ ከሰጠው ሐሳብ ጋር የሚጋጭ አይደለም። ስምምነታቸውን በጽሑፍ ሊያሰፍሩት የሚገባ ሲሆን ብድሩን የወሰደው ወንድምም በስምምነቱ መሠረት ገንዘቡን ለመመለስ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። አበዳሪው ወንድም በክርስቲያናዊ ፍቅር ተነሳስቶ በችግሩ እንደደረሰለት ሁሉ ተበዳሪውም ብድሩን ለመክፈል ይኸው ፍቅር ሊገፋፋው ይገባል።
ገንዘብ ለማበደር (ወይም በስጦታ ለመስጠት) ያሰበው ወንድም የራሱን ቤተሰብ ሁኔታም ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። ለምሳሌ፣ እንደዚህ ያለ እርዳታ ሲያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዘው መሠረት የገዛ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ይቸገራል? (2 ቆሮንቶስ 8:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) ክርስቲያኖች ከላይ የተመለከትናቸውን ነጥቦች በአእምሯቸው በመያዝ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መልኩ ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር ማሳየት የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ይፈልጋሉ።—ያዕቆብ 1:27፤ 1 ዮሐንስ 3:18፤ 4:7-11