በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዘመናችን የሚሆነው ብቃት ያለው መሪ ማን ነው?

ለዘመናችን የሚሆነው ብቃት ያለው መሪ ማን ነው?

ለዘመናችን የሚሆነው ብቃት ያለው መሪ ማን ነው?

በ1940 በብሪታንያ ፓርላማ ውስጥ አመራርን በተመለከተ ውዝግብ ተነስቶ ነበር። በስብሰባው ላይ ከነበሩት ሰዎች መካከል ብሪታንያ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ድል እንድትቀዳጅ ያስቻሏት የሰባ ሰባት ዓመቱ አረጋዊ ዴቪድ ሎይድ ጆርጅ ይገኙበታል። እኚህ ሰው ለረዥም ዓመታት ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ሥራ በማከናወናቸው የባለ ሥልጣናቱን ሥራ ለመገምገም ብቃት ነበራቸው። ግንቦት 8 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ባቀረቡት ንግግር እንዲህ ብለዋል፦ “ሕዝቡ ጥሩ መሪ እስካገኘ፣ ብሔሩን የሚመሩት ሰዎች አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን እስከቻለና መንግሥት ዓላማውን በግልጽ እስካስቀመጠ ድረስ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው።

ሎይድ ጆርጅ የሰጡት ሐሳብ ሕዝቡ ነገሮችን ለማስተካከል ከልባቸው የሚጥሩና ብቃት ያላቸው መሪዎች እንደሚፈልግ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ከምርጫ ዘመቻ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚሠሩ አንዲት ሴት ሁኔታውን እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፦ “ሰዎች ፕሬዚዳንት ሲመርጡ ሕይወታቸውን፣ የወደፊት ተስፋቸውንና ልጆቻቸውን በአደራ የሚሰጡት ሰው እየመረጡ ነው።” እንደዚህ ያለውን አደራ መወጣት ደግሞ ከባድ ኃላፊነት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ዓለማችን መፍትሔ የሚገኝላቸው በማይመስሉ ችግሮች የተሞላ ነው። ወንጀልንና ጦርነትን ለማስወገድ የሚያስችል ብልሃትም ሆነ ኃይል ያለው የትኛው መሪ ነው? በዛሬው ጊዜ ካሉት መሪዎች መካከል ሁሉም ሰው ምግብ፣ ንጹሕ ውኃና ሕክምና እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስፈልገው አቅምም ሆነ ርኅራኄ ያለው ማን ነው? አካባቢያችንን ለመንከባከብና ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ የሚያስፈልገው እውቀትም ሆነ ቁርጠኝነት ያለው ማን ነው? የሰው ዘር በሙሉ ደስተኛ ሆኖ ለረዥም ዘመን እንዲኖር ለማድረግ ብቃቱም ሆነ ኃይሉ ያለው የትኛው ገዢ ነው?

የሰው ልጆች ብቃቱ የላቸውም

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ መሪዎች በተወሰነ መጠን እንደተሳካላቸው አይካድም። ሆኖም የሥልጣን ዘመናቸው በዛ ቢባል ከጥቂት አሥርተ ዓመታት የማያልፍ ከመሆኑም በላይ በእነርሱ እግር የሚተካው መሪ ማን እንደሚሆን አይታወቅም። በምድር ላይ ከኖሩት መሪዎች ሁሉ በብቃቱ ተወዳዳሪ የሌለው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ይህ ጉዳይ አሳስቦት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ከፀሓይ በታች የደከምሁበትን ነገር ሁሉ ጠላሁት፣ ከኋላዬ ለሚመጣው የግድ እተውለታለሁና። እርሱ ጠቢብ ወይም ሞኝ ይሆን እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም ከፀሓይ በታች ድካሜንና ችሎታዬን ባፈሰስሁበት ሥራ ሁሉ ላይ ባለቤት ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።”—መክብብ 2:18, 19

ሰሎሞን ቀጣዩ ንጉሥ እርሱ ሲያከናውን የኖረውን መልካም ሥራ ይግፋበት ወይም ያበላሸው ማወቅ አይችልም ነበር። በእርሱ አመለካከት የቀድሞ መሪዎችን በአዲሶች እየተኩ የማለፉ ሂደት “ከንቱ” ነበር። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህንን ሁኔታ “እርባና ቢስ” ወይም “ትርጉም የለሽ” ብለውታል።

አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ የኃይል እርምጃ ይወሰዳል። ብቃት ያላቸው መሪዎች በሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ ተገድለዋል። ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፦ “ለአጭር ጊዜም ቢሆን አስፈላጊ የሆነ ሥራ እንዳከናውን መርጣችሁኛል፤ አሁን በእናንተ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያለኝ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ እንደማጣው የታወቀ ነው።” እውነትም ደግሞ የሥልጣን ዘመናቸው አጭር ነበር። ፕሬዚዳንት ሊንከን ሕዝቡን ለማገልገል ብዙ ከመድከማቸውም በላይ ሊያከናውኗቸው የሚፈልጓቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም አገራቸውን መምራት የቻሉት ለአራት ዓመታት ብቻ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠው ሥራቸውን እንደጀመሩ የአመራር ለውጥ በፈለገ አንድ ሰው ተገደሉ።

የተዋጣላቸው የተባሉት ሰብዓዊ መሪዎችም እንኳ ስለ ራሳቸው ሕይወት እርግጠኞች መሆን አይችሉም። ታዲያ ለእነዚህ መሪዎች ሕይወትህን በአደራ ልትሰጣቸው ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ። መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።”—መዝሙር 146:3, 4

በሰብዓዊ መሪዎች እንዳንታመን የተሰጠንን ምክር መቀበል ይከብደን ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ዘር ብቃት ያለውና አስተማማኝ መሪ ጨርሶ አያገኝም አይልም። ኢሳይያስ 32:1 “እነሆ፤ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል” ይላል። የሰው ዘር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ በቅርቡ ምድርን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠራት “ንጉሥ” ወይም መሪ አዘጋጅቷል። ይህ መሪ ማን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መልሱን ይሰጠናል።

ብቃት ያለው መሪ

ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት አንድ መልአክ ማርያም ለተባለች አንዲት አይሁዳዊት ወጣት እንዲህ ብሏት ነበር፦ “ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” (ሉቃስ 1:31-33) ይህ ትንቢት የተነገረለት ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው።

ሃይማኖታዊ ሥዕሎች በአብዛኛው ኢየሱስን እንደ ሕፃን፣ ደካማና ኮስማና እንደሆነ ሰው ወይም ምንም ነገር ቢያጋጥመው በቀላሉ እጁን እንደሚሰጥ ባሕታዊ አድርገው ያቀርቡታል። እነዚህ ምስሎች በኢየሱስ መሪነት እንድንተማመን አያደርጉም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው እውነተኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ቅንዓትና ወኔ ያለው፣ ብርቱና ኃያል ሰው ነው። ለመሪነት ብቁ የሚያደርጉት ሌሎች ባሕርያትም አሉት። (ሉቃስ 2:52) ግሩም ከሆኑት ባሕርያቱ መካከል ጥቂቶቹ ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፦

ፈጽሞ ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር። ሐቀኛና መልካም ምግባር ያለው ሰው ስለነበር ጠላቶቹ በማስረጃ ሊከሱት ይችሉ እንደሆነ በሕዝብ ፊት ቢጠይቃቸውም አንዳች እንከን አላገኙበትም። (ዮሐንስ 8:46) ትምህርቶቹ ከግብዝነት የራቁ በመሆናቸው ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ተከታዮቹ ሆነዋል።—ዮሐንስ 7:46፤ 8:28-30፤ 12:19

ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ሰጥቶ ነበር። ከአምላክ የተሰጠውን ሥራ ለማከናወን ቆርጦ ስለነበር የሰዎችም ሆነ የአጋንንት ተቃውሞ ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። የኃይል ጥቃት ቢሰነዘርበትም አልፈራም። (ሉቃስ 4:28-30) ድካምና ረሃብ ተስፋ አላስቆረጡትም። (ዮሐንስ 4:5-16, 31-34) ወዳጆቹ ጥለውት ቢሸሹም ከዓላማው ፈጽሞ ወደኋላ አላለም።—ማቴዎስ 26:55, 56፤ ዮሐንስ 18:3-9

ለሰዎች በጥልቅ ያስብ ነበር። የተራቡ ሰዎችን መግቧል። (ዮሐንስ 6:10, 11) የተጨነቁትን አጽናንቷል። (ሉቃስ 7:11-15) ማየትና መስማት የተሳናቸውን እንዲሁም ሌሎች የጤና እክሎች ያሉባቸውን ሰዎች ፈውሷል። (ማቴዎስ 12:22፤ ሉቃስ 8:43-48፤ ዮሐንስ 9:1-6) ጠንክረው ይሠሩ የነበሩትን ሐዋርያቱን አበረታቷቸዋል። (ዮሐንስ ምዕራፍ 13 እስከ 17) በጎቹን የሚንከባከብ “መልካም እረኛ” ነበር።—ዮሐንስ 10:11-14

ለሥራ አይለግምም። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ አንድ አስፈላጊ ትምህርት ለመስጠት ሲል እግራቸውን አጥቧቸዋል። (ዮሐንስ 13:4-15) አቧራማ በሆኑት የእስራኤል መንገዶች እየተዘዋወረ ይሰብክ ነበር። (ሉቃስ 8:1) “ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ” ሄዶ ለማረፍ ባሰበበትም ጊዜ እንኳ ሕዝቡ እንዲያስተምራቸው ፈልገው ወደ እርሱ ሲመጡ ተቀብሏቸዋል። (ማርቆስ 6:30-34) ስለዚህ በትጋት ረገድ ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሆን አርዓያ ትቷል።—1 ዮሐንስ 2:6

ኢየሱስ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ሰማይ ሄዷል። ይሖዋ አምላክ ለዚህ የታማኝነት አቋሙ በሰማይ ንጉሥ ያደረገው ከመሆኑም በላይ ያለመሞትን ባሕርይ አላብሶታል። መጽሐፍ ቅዱስ ከትንሣኤው በኋላ ኢየሱስ ስላገኘው ሕይወት ሲናገር “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶአልና፣ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለንና፤ ሞት ከእንግዲህ በእርሱ ላይ ጉልበት አይኖረውም” ይላል። (ሮሜ 6:9) ኢየሱስ የሰው ዘር ሊያገኛቸው ከሚችላቸው መሪዎች ሁሉ የላቀ መሪ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ምድርን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠራት በኋላ ሌላ ሰው መሾምም ሆነ የአመራር ለውጥ ማድረግ አያስፈልግም። ማንም እርሱን በመግደል ከሥልጣኑ ሊያፈናቅለው አይችልም፤ እንዲሁም ብቃት የጎደለው መሪ በእርሱ እግር ተተክቶ ያከናወነውን መልካም ሥራ ሊያበላሽበት አይችልም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሰው ዘሮችን ለመጥቀም ምን ያደርጋል?

ይህ መሪ ምን ነገሮችን ያከናውናል?

መዝሙር 72 ፍጹም የሆነውና ያለመሞትን ባሕርይ የተላበሰው ይህ መሪ እንዴት እንደሚገዛ የሚገልጽ ትንቢታዊ ዘገባ ይዟል። በቁጥር 7 እና 8 ላይ እንዲህ ይላል፦ “በዘመኑ ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከታላቁም ወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ይገዛል።” ለሰው ልጆች ጥቅም በሚያስገኘው የግዛት ዘመኑ ወቅት የምድር ነዋሪዎች ሕይወት ዘላለማዊና የተረጋጋ ሁኔታ የሰፈነበት ይሆናል። በምድር ላይ የሚገኙ መሣሪያዎችን በሙሉ የሚያጠፋ ከመሆኑም በላይ ሰዎች ግጭት የመፍጠር ፍላጎት እንኳ እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ዛሬ እንደተራበ አንበሳ ወይም እንደተቆጣ ድብ ሌሎችን የሚያጠቁ ሰዎች አመለካከታቸው ሙሉ በሙሉ ይለወጣል። (ኢሳይያስ 11:1-9) በምድር ሁሉ ላይ ሰላም ይሰፍናል።

መዝሙር 72 ከቁጥር 12 እስከ 14 አክሎ እንዲህ ይላል፦ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል፤ ደማቸውም በእርሱ ፊት ክቡር ነው።” በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት ሥር ችግረኞች፣ ድኾችና ምስኪኖች የአንድ ደስተኛ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባላት ሆነው በኅብረት ይኖራሉ። ሕይወታቸው በሥቃይና በተስፋ መቁረጥ የተሞላ መሆኑ ይቀርና ደስተኞች ይሆናሉ።—ኢሳይያስ 35:10

ቁጥር 16 ደግሞ “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ” ይላል። ዛሬ በምድር ላይ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይራባሉ። አብዛኛውን ጊዜ በፖለቲካና በስግብግብነት ምክንያት ምግብ በተገቢው መንገድ ለሁሉም አይዳረስም። በዚህም የተነሳ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በተለይም ልጆች በረሃብ ይሞታሉ። በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ሥር ግን ይህ ችግር ይወገዳል። ምድር ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችን አትረፍርፋ ስለምትሰጥ የሰው ዘር በሙሉ ጠግቦ ያድራል።

ብቃት ያለው መሪ የሚያመጣቸውን እነዚህን በረከቶች ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ በቅርቡ ምድርን ሙሉ በሙሉ ስለሚቆጣጠረው መሪ እንድትማር እናበረታታሃለን። የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ በደስታ ይረዱሃል። ይሖዋ አምላክ ራሱ ስለ ልጁ ሲናገር “እኔ ግን በተቀደሰው ተራራዬ፣ በጽዮን ላይ የራሴን ንጉሥ ሾምሁ” ስላለ ይህ መሪ እንደጠበቅኸው ሳይሆን ቀርቶ አታዝንም።—መዝሙር 2:6

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በድንገት ከሥልጣን መውረድ

አብዛኛውን ጊዜ አንድ መሪ በአገሩ ውስጥ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሰላምና አስተማማኝ የኑሮ ሁኔታ እንዲሰፍን ካደረገ ዜጎቹ እንደሚያከብሩትና እንደሚደግፉት ሊጠብቅ ይችላል። ይሁን እንጂ በሆነ ምክንያት ሕዝቡ በእርሱ ላይ እምነት ካጣ ብዙም ሳይቆይ ሥልጣኑን ለሌላ ያስረክባል። አንዳንድ ጠንካራ መሪዎች በድንገት ሥልጣናቸውን እንዲያጡ ካደረጓቸው ምክንያቶች ጥቂቶቹ ለአብነት ያህል ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።

ሕዝቡ በኑሮው አለመርካቱ። በ18ተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ አብዛኞቹ የፈረንሳይ ዜጎች ከፍተኛ ቀረጥ እንዲከፍሉ ይገደዱ የነበረ ከመሆኑም በላይ በአገሪቱ የምግብ እጥረት ነበር። እነዚህ ችግሮች ለፈረንሳዩ አብዮት መፈንዳት ምክንያት ሆኑና ንጉሥ ሉዊ 16ተኛ በ1793 አንገታቸው በጊሎቲን ተቀንጥሶ ተገደሉ።

ጦርነት። አንደኛው የዓለም ጦርነት በታሪክ ውስጥ ኃያል ለሚባሉ አንዳንድ ንጉሠ ነገሥታት ከሥልጣን መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ለምሳሌ ያህል በቅዱስ ፒተርስበርግ፣ ሩስያ በጦርነት ሳቢያ በተከሰተው ረሃብ የተነሳ በ1917 የየካቲቱ አብዮት ፈነዳ። ይህ ዓመጽ የሩስያው ዛር ዳግማዊ ኒኮላስ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ ያደረገ ሲሆን በምትኩ ኮሚኒስቶች ሥልጣን ያዙ። በኅዳር ወር፣ 1918 ጀርመን ሰላም እንዲወርድ ትፈልግ የነበረ ቢሆንም የሕብረ ብሔሩ ጦር ግን የአመራር ለውጥ እስኪደረግ ድረስ ውጊያውን አላቆመም። በውጤቱም የጀርመኑ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ቪልኸልም ወደ ኔዘርላንድ ለመሰደድ ተገደዱ።

የፖለቲካው ሥርዓት እንዲለወጥ መፈለግ። በ1989 የምዕራቡንና የምሥራቁን ዓለም ከፍሎ የነበረው የብረት መጋረጃ ሲገለጥ እንደ ዓለት የጠነከሩ የሚመስሉ መንግሥታት ዜጎቻቸው ኮሚኒዝምን ትተው ለየት ያሉ ሥርዓቶችን በማቋቋማቸው ፈራረሱ።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሎይድ ጆርጅ፦ Photo by Kurt Hutton/Picture Post/Getty Images

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የተራቡትን መግቧል፣ የታመሙትን ፈውሷል እንዲሁም ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሆን ጥሩ ምሳሌ ትቷል