በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን አገዛዝ በጽናት ደግፈናል

የአምላክን አገዛዝ በጽናት ደግፈናል

የሕይወት ታሪክ

የአምላክን አገዛዝ በጽናት ደግፈናል

ሚካል ዝሆብራክ እንደተናገረው

ለአንድ ወር ያህል ብቻዬን ከታሰርኩ በኋላ እየተገፈተርኩ ወደ መርማሪው ተወሰድኩ። መርማሪውም ፊቱ ደም መስሎ “እናንተ ሰላዮች! የአሜሪካ ሰላዮች!” ሲል ጮኸብኝ። እንዲህ ያናደደው ምን ነበር? ሃይማኖትህ ምንድን ነው ብሎ በጠየቀኝ ጊዜ “የይሖዋ ምሥክር ነኝ” ብዬ ስለመለስኩለት ነበር።

ህ ነገር ከተፈጸመ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖታል። በምኖርባት አገር በወቅቱ የኮሚኒስት አገዛዝ ሰፍኖ ነበር። ከዚህ ቀደም ብሎም ቢሆን በክርስቲያናዊ የስብከት ሥራችን ምክንያት ከባድ ተቃውሞ ደርሶብናል።

የጦርነትን መራራ ጽዋ ቀመስን

አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 ሲፈነዳ እኔ የስምንት ዓመት ልጅ ነበርኩ። በዚያን ጊዜ መንደራችን ዛሉዝሂፅ፣ በኦስትሮ-ሃንጋሪ ንጉሣዊ አገዛዝ ሥር ነበረች። ጦርነቱ ዓለምን ከማመሳቀሉም በላይ ገና በልጅነቴ ከባድ ኃላፊነት እንድሸከም አስገድዶኛል። ወታደር የነበረው አባቴ የሞተው ገና ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በመጀመሪያው ዓመት ነበር። ይህም እኔን፣ እናቴንና ሁለት ታናናሽ እህቶቼን ለከፋ ድህነት ዳረገን። ለቤቱ የመጀመሪያና ብቸኛ ወንድ ልጅ በመሆኔ ትንሿን እርሻችንን መቆጣጠርና ሌሎች የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን መሸከም ግድ ሆነብኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ አጥባቂ ሃይማኖተኛ ነበርኩ። እንዲያውም ቀደም ሲል አባል የነበርኩበት ሃይማኖት ማለትም የሪፎርምድ (የካልቪኒስት) ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በማይኖሩበት ጊዜ እሳቸውን ተክቼ አብረውኝ የሚማሩትን ልጆች እንዳስተምር ይጠይቁኝ ነበር።

በ1918 ታላቁ ጦርነት በማብቃቱ ይህ ነው የማይባል የእፎይታ ስሜት ተሰማን። በዚያን ጊዜ የኦስትሮ-ሃንጋሪ ንጉሣዊ አገዛዝ ወድቆ ስለነበር መንደራችን የቼኮዝሎቫኪያ ግዛት ሆነች። ብዙም ሳይቆይ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰድደው ከነበሩት የመንደራችን ነዋሪዎች መካከል ብዙዎቹ ተመልሰው መጡ። ከእነዚህም ውስጥ በ1922 የተመለሰው ሚካል ፔትሪክ ይገኝበታል። በአቅራቢያችን የሚኖር አንድ ቤተሰብ እርሱን በጋበዘበት ዕለት እኔንና እናቴንም ጠራን።

የአምላክ አገዛዝ ሕያው ሆነልን

ሚካል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (የይሖዋ ምሥክሮች በወቅቱ የሚጠሩበት ስም ነው) የነበረ ሲሆን የዚያን ዕለት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን አንስቶ አወያየን። ቀልቤን ከሳቡት ነገሮች አንዱ ስለ ይሖዋ መንግሥት መምጣት የነገረን እውነት ነው። (ዳንኤል 2:44) በዛሆር መንደር ከፊታችን በነበረው እሁድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ እንዳለ ሲነግረን ለመሄድ ቆረጥኩ። ያን ዕለት ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ላይ ተነስቼ ከአንድ የቅርብ ዘመዴ ብስክሌት ለመዋስ 8 ኪሎ ሜትር ተጓዝኩ። የብስክሌቱ ጎማ ተንፍሶ ስለነበር አስተካከልኩትና 24 ኪሎ ሜትር ተጉዤ ዛሆር ደረስኩ። ስብሰባው የት እንደሚካሄድ ስለማላውቅ በመንገድ ዳር ቀስ እያልኩ እየተጓዝኩ ሳለ ከአንዱ ቤት ውስጥ የመንግሥቱ መዝሙር ሲዘመር ሰማሁ። ልቤ በደስታ ዘለለች። ወደ ቤቱ ገብቼ ለምን እንደመጣሁ ነገርኳቸው። ከዚያም አብሬያቸው ቁርስ እንድበላ ጋበዙኝና ወደ ስብሰባ ይዘውኝ ሄዱ። ወደ ቤት ለመመለስ በብስክሌትና በእግሬ ተጨማሪ 32 ኪሎ ሜትር የተጓዝኩ ቢሆንም በፍጹም አልደከመኝም።—ኢሳይያስ 40:31

የይሖዋ ምሥክሮች በሚያስተምሩት ግልጽና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት በጣም ተደነቅሁ። በአምላክ አገዛዝ ሥር ስለሚሰፍነው የተደላደለና አርኪ ኑሮ የሚገልጸው የምሥራች ልቤን ማረከው። (መዝሙር 104:28) እኔና እናቴ አባል ለነበርንበት ቤተ ክርስቲያን የስንብት ደብዳቤ ለማስገባት ወሰንን። በዚያ ሰሞን ጉዳዩ የመንደራችን ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ለጥቂት ጊዜ እኛን ማነጋገር አቁመው የነበረ ቢሆንም በአካባቢያችን ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ጥሩ ወዳጅነት ነበረን። (ማቴዎስ 5:11, 12) ብዙም ሳይቆይ በኡህ ወንዝ ውስጥ ተጠመቅኩ።

አገልግሎት የሕይወታችን ክፍል ሆነ

ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ስለ ይሖዋ መንግሥት እንሰብክ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) በተለይ በደንብ በተደራጀ መልክ በየሳምንቱ እሁድ ለሚደረገው የስብከት ዘመቻ ትኩረት እንሰጥ ነበር። በዚያን ጊዜ ሰዎች በሌሊት የመነሳት ልማድ ስለነበራቸው የስብከቱን ሥራ በማለዳ እንጀምራለን። ከዚያም ቀን ላይ ሕዝባዊ ስብሰባ እናደርጋለን። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎቹ ብዙውን ጊዜ ንግግራቸውን የሚያቀርቡት ምንም ጽሑፍ ሳይዙ በቃላቸው ነበር። ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ብዛት፣ ሃይማኖታዊ አመለካከትና ትኩረታቸውን የሚስቡ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ያስገባሉ።

የምንሰብከው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልበ ቅን የሆኑ ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ብርሃን እንዲበራላቸው አድርጓል። ከተጠመቅኩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በትርሆቪሽቴ መንደር ማገልገል ጀመርኩ። በአንድ ቤት ውስጥ ካገኘኋቸው ሚስስ ሱዛን ሞስካል ከተባሉ ደግና ተግባቢ ሴት ጋር ተወያየሁ። ቤተሰቡ በሙሉ እኔ እከተለው የነበረው የካልቪኒስት ቤተ ክርስቲያን አባል ነበር። ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ቢያውቁም መልስ ያላገኙላቸው በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ነበሯቸው። ለአንድ ሰዓት ያህል ከተወያየን በኋላ የአምላክ በገና የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ሰጠኋቸው። a

የሚስስ ሞስካል ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን በሚያነቡበት በተለመደው ሰዓት ይህን መጽሐፍ ጨምረው ማንበብ ጀመሩ። በዚያ መንደር የሚኖሩ ሌሎች በርካታ ቤተሰቦችም ፍላጎት ከማሳየታቸውም በላይ በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ጀመሩ። ስለዚህ የካልቪኒስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ስለ እኛና ስለ ጽሑፎቻችን ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጡ። በዚህ ጊዜ አንዳንድ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች፣ አገልጋዩ በምንሰበሰብበት ቦታ ተገኝተው ትምህርቶቻችን ሐሰት መሆናቸውን በማስረጃ እንዲያረጋግጡ ጠየቋቸው።

አገልጋዩ በስብሰባው ላይ የተገኙ ቢሆንም ለትምህርታቸው ድጋፍ የሚሆን አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሊያቀርቡ ባለመቻላቸው እንዲህ ሲሉ ሰበብ አቀረቡ፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ማመን አንችልም። የተጻፉት በሰዎች ነው፤ ስለዚህ ለሃይማኖታዊ ጥያቄዎች በተለያየ መንገድ መልስ መስጠት ይቻላል።” ይህም ለብዙ ሰዎች አዲስ ምዕራፍ ከፈተ። አንዳንዶቹ አገልጋዩ በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምኑ ከሆነ ዳግም ቤተ ክርስቲያን ሄደው ስብከታቸውን እንደማይሰሙ ነገሯቸው። ከዚያም 30 የሚያህሉ የመንደሩ ነዋሪዎች የካልቪኒስት ቤተ ክርስቲያን አባልነታቸውን በመሰረዝ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በጽናት ደግፈዋል።

የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ የኑሯችን ክፍል በመሆኑ በመንፈሳዊ ጠንካራ ከሆኑ ቤተሰቦች መሃል የትዳር ጓደኛ የምትሆነኝን ሴት መፈለግ ጀመርኩ። አብረውኝ ከሚያገለግሉት ወንድሞች መካከል እውነትን በዩናይትድ ስቴትስ የሰማው ያን ፔትሩሽካ አንዱ ነበር። ልጁ ማሪያ ልክ እንደ እርሱ ለሁሉም ሰው ለመስበክ ያላት ተነሳሽነት ይማርከኝ ነበር። በ1936 ከማሪያ ጋር የተጋባን ሲሆን ሕይወቷ እስካለፈበት እስከ 1986 ድረስ ለ50 ዓመታት ታማኝ አጋሬ ነበረች። በ1938 ብቸኛ ልጃችን ኤድዋርድ ተወለደ። በዚያን ጊዜ በአውሮፓ ሌላ ጦርነት አንዣቦ ነበር። ጦርነቱ በስብከቱ ሥራችን ላይ ምን ውጤት አስከተለ?

ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችን ተፈተነ

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት ወቅት ከቼኮዝሎቫኪያ የተገነጠለችው ስሎቫኪያ በናዚ አገዛዝ ሥር ነበረች። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ በድርጅት ደረጃ ለማገድ የተወሰደ መንግሥታዊ እርምጃ አልነበረም። በእርግጥ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን በድብቅ ማከናወን የነበረብን ሲሆን ጽሑፎቻችንም ሳንሱር ይደረጉ ነበር። የሆነ ሆኖ ሥራችንን በጥበብ መሥራት ቀጠልን።—ማቴዎስ 10:16

ዕድሜዬ ከ35 ዓመት በላይ የነበረ ቢሆንም ጦርነቱ እየበረታ ሲመጣ ለውትድርና ተመለመልኩ። በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሜ ምክንያት በጦርነቱ ለመካፈል ፈቃደኛ አልሆንኩም። (ኢሳይያስ 2:2-4) ደስ የሚለው፣ ባለ ሥልጣኖቹ ምን እርምጃ እንደሚወስዱብኝ ከመወሰናቸው በፊት በእኔ ዕድሜ የሚገኙ ምልምሎች በሙሉ ወደ ጦርነቱ መሄዳቸው ቀረ።

የኑሮ ችግር በገጠር ከምንኖረው ይልቅ በከተማ በሚኖሩ ወንድሞቻችን ላይ የባሰ እንደሆነ ተገነዘብን። በመሆኑም ያለንን ለማካፈል ወሰንን። (2 ቆሮንቶስ 8:14) መያዝ የቻልነውን የምግብ ዓይነት በሙሉ ይዘን ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ወደሚገኘው ብራቲስላቫ ተጓዝን። በጦርነቱ ዓመታት የመሠረትነው ጠንካራ ክርስቲያናዊ ወዳጅነትና ፍቅር ከፊታችን ይጠብቁን ለነበሩት አስቸጋሪ ጊዜያት ጠቅሞናል።

አስፈላጊውን ማበረታቻ ማግኘት

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ስሎቫኪያ እንደገና ከቼኮዝሎቫኪያ ጋር ተቀላቀለች። ከ1946 እስከ 1948 በነበሩት ዓመታት በቡርኖ ወይም በፕራግ የይሖዋ ምሥክሮች አገር አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ሲካሄድ ቆይቷል። በምሥራቅ ስሎቫኪያ የምንገኘው፣ ለልዑካኖች በተዘጋጁ ልዩ ባቡሮች ወደ ስብሰባው ቦታ እንጓዝ ነበር። እዚያ እስክንደርስ ድረስ እየዘመርን እንጓዝ ስለነበር ባቡሮቹ የመዝሙር ባቡሮች ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ።—የሐዋርያት ሥራ 16:25

በተለይ ከዋናው መሥሪያ ቤት የመጡት ወንድም ናታን ኤች ኖርና ሌሎች ሁለት የበላይ ተመልካቾች የተገኙበትን በ1947 በቡርኖ የተደረገውን የአውራጃ ስብሰባ መቼም አልረሳውም። አብዛኞቻችን የሕዝብ ንግግሩን ለማስተዋወቅ ጭብጡን የያዘ ማስታወቂያ አንገታችን ላይ አንጠልጥለን ከተማውን ዞርን። በዚያን ጊዜ የዘጠኝ ዓመቱ ልጃችን ኤድዋርድ ማስታወቂያ እንዲይዝ ስላልተሰጠው ቅር አለው። ስለዚህ ወንድሞች ለሌሎች ልጆችም ጭምር ትንንሽ ማስታወቂያዎችን አዘጋጁላቸው። እነዚህ ትንንሽ ልጆች ጥሩ አድርገው ስብሰባውን አስተዋውቀዋል!

ከዚያም ኮሚኒስቶች በየካቲት 1948 ሥልጣን ተቆናጠጡ። ይዋል ይደር እንጂ መንግሥት ሥራችን ላይ እገዳ መጣሉ እንደማይቀር አውቀን ነበር። መስከረም 1948 በፕራግ የአውራጃ ስብሰባ ያደረግን ሲሆን ለሦስት ዓመታት በነፃነት ከተሰበሰብን በኋላ እንደገና ይህን መብታችንን የሚገፍፍ ሕግ እንደሚወጣ ተሰምቶን ስለነበር የስብሰባውን ጊዜ ሞቅ ባለ መንፈስ አሳለፍን። የአውራጃ ስብሰባውን ከመጨረሳችን በፊት የአቋም መግለጫ አጸደቅን፤ መግለጫው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “እኛ እዚህ የተሰበሰብነው የይሖዋ ምሥክሮች . . . አርኪ የሆነውን ይህን አገልግሎታችንን በይበልጥ ለማከናወን እንዲሁም ከጌታ ባገኘነው ሞገስ እየታገዝን በአስቸጋሪ ጊዜያትም ቢሆን ያለመታከት የመንግሥቱን ወንጌል በበለጠ ቅንዓት ለማወጅ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።”

“የአገር ጠላቶች”

ይህን የአውራጃ ስብሰባ ካደረግን ከሁለት ወራት በኋላ የምስጢር ፖሊሶች በዚያው በፕራግ አቅራቢያ የሚገኘውን ቤቴል በድንገት ወረሩ። ማግኘት የቻሏቸውን ጽሑፎችና ሌሎች የቤቴል ንብረቶችን በሙሉ ወረሱ፤ አንዳንድ ወንድሞችን ጨምሮ ቤቴላውያንን ሁሉ አሰሩ። ሆኖም ከዚህ የባሰ ሁኔታ ይጠብቀን ነበር።

የካቲት 3, 1952 ሌሊት ላይ የፀጥታ ኃይሎች አገሩን እያሰሱ ከ100 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችን አሰሩ። እኔም ከተያዙት መካከል ነበርኩ። ፖሊሶች ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ከእንቅልፋችን ቀሰቀሱን። ለምን እንደፈለጉኝ እንኳን ሳይናገሩ አብሬያቸው እንድሄድ ጠየቁኝ። እጆቼን በካቴና አሥረውና ዓይኔን በጨርቅ ሸፍነው ከሌሎች ሰዎች ጋር በአንድ የጭነት መኪና ከወሰዱኝ በኋላ በአንዲት ክፍል ውስጥ ለብቻዬ ታሰርኩ።

ያለ ምንም ጥያቄ አንድ ወር ሙሉ ታሰርኩ። የማየው ሰው ቢኖር በበሩ ትንሽ ክፍተት መናኛ ምግብ የሚያቀብለኝን ጠባቂ ብቻ ነበር። ከዚያም በመጀመሪያ ላይ እንደገለጽኩት መርማሪው ፊት ቀረብኩ። ሰላይ ነህ ካለኝ በኋላ “ሃይማኖት ድንቁርና ነው። አምላክም የለም! ላብአደሮቻችንን እንድታታልል አንፈቅድልህም። ወይ ትንጠለጠላለህ አሊያም እዚችው እስር ቤት ትበሰብሳታለህ። አምላክህ ቢመጣ እንኳ እንገድለዋለን!” አለኝ።

ባለ ሥልጣናቱ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንን የሚከለክል በግልጽ የተቀመጠ ሕግ አለመኖሩን ስለሚያውቁ “የአገር ጠላቶች” እና የሌላ አገር ሰላዮች እንደሆንን አድርገው በመወንጀል ሥራችንን ሕገ ወጥ ለማስመሰል ፈልገው ነበር። ለዚህም ሲሉ ቁርጥ አቋማችንን ለማዳከምና የተመሠረተብንን የሐሰት ክስ “እንድናምን” ለማድረግ ሞከሩ። በዚያን ዕለት ምሽት ምርመራ ከተደረገብኝ በኋላ መተኛት ተከለከልኩ። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ እንደገና ምርመራው ቀጠለ። በዚህን ጊዜ መርማሪው እንዲህ በሚለው መግለጫ ላይ እንድፈርም ጠየቀኝ፦ “እኔ የሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ቼኮዝሎቫኪያ ጠላት እንደመሆኔ መጠን አሜሪካኖች መጥተው ነጻ እንዲያወጡኝ ስለምጠባበቅ [የገበሬ ማኅበር] አባል አልሆንኩም።” ይህን በመሰለው ውሸት ተስማምቼ ለመፈረም ፈቃደኛ ባለመሆኔ ወደ ፀባይ ማረሚያ ክፍል ተወሰድኩ።

እዚያም መቆም ወይም ወዲያ ወዲህ መንጎራደድ ካልሆነ በስተቀር እንዳልተኛ፣ ጋደም እንዳልል አልፎ ተርፎም እንዳልቀመጥ እንኳን ተከልክዬ ነበር። በመሆኑም በጣም ስለደከመኝ በሲሚንቶ ወለሉ ላይ ተዘረርኩ። በዚህን ጊዜ ጠባቂዎቹ ወደ መርማሪው ቢሮ መልሰው ወሰዱኝ። መርማሪውም “አሁንስ አትፈርምም?” ብሎ ጠየቀኝ። እንደማልፈርም በድጋሚ ስገልጽለት በጥፊ መታኝ። በዚህ ጊዜ ደም ይፈስሰኝ ጀመር። ጠባቂዎቹን በጩኸት “ይሄ ሰው ራሱን መግደል ስለሚፈልግ ሕይወቱን እንዳያጠፋ ጠብቁት!” አላቸው። ከዚያም ብቻዬን ታስሬ ወደ ነበረበት ቦታ ተመለስኩ። ከዚህ በኋላ ለስድስት ወራት ያህል ይህን የመሰሉ ምርመራዎች ለተደጋጋሚ ጊዜያት ቀጠሉ። የአገሪቱ ጠላት እንደሆንኩ እንዳምን ለማግባባት የተደረጉት ሙከራዎች ለይሖዋ ያለኝን የታማኝነት አቋም እንዳላላ አላደረጉኝም።

ለፍርድ ከመቅረቤ አንድ ወር አስቀድሞ ከፕራግ የመጣ አቃቤ ሕግ የታሰርነውን 12 ወንድሞች በየተራ መረመረን። “ምዕራባውያን ኢምፔሪያሊስቶች አገራችን ላይ ጥቃት ቢሰነዝሩ ምን ታደርጋለህ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም “የማደርገው ነገር ቢኖር ይህች አገር ከሂትለር ጋር በመተባበር ሶቪየት ሕብረትን ባጠቃችበት ወቅት ያደረግኩትን ነው። በዚያን ጊዜ በውጊያው አልተካፈልኩም ነበር፤ አሁንም ቢሆን ክርስቲያን በመሆኔና በገለልተኝነት አቋሜ ምክንያት አልዋጋም” ስል መልስ ሰጠሁት። እርሱም “የይሖዋ ምሥክሮችን መታገስ አንችልም። ምዕራባውያን ኢምፔሪያሊስቶች ምናልባት ጥቃት ቢሰነዝሩብን ለመከላከል እንድንችልና በምዕራቡ ዓለም ያሉትን ላብአደር ጓዶቻችንን ነጻ ለማውጣት ወታደሮች ያስፈልጉናል” አለኝ።

ሐምሌ 24, 1953 ወደ ፍርድ ቤት ተወሰድን። አሥራ ሁለታችንም ተራ በተራ ዳኞች ፊት ቀረብን። ይህን አጋጣሚ ስለ እምነታችን ለመናገር ተጠቀምንበት። ለቀረቡብን የሐሰት ክሶች ምላሽ ከሰጠን በኋላ ጠበቃው ቆመና “እዚህ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ መጥቻለሁ። ብዙ ሰዎች ስህተታቸውን ሲያምኑና ሲፀፀቱ እንዲሁም ሲያለቅሱ ተመልክቻለሁ። እነዚህ ሰዎች ግን እዚህ ከገቡ በኋላ ይበልጥ ብሶባቸው ይወጣሉ” ብሎ ተናገረ። ቀጥሎም አሥራ ሁለታችንም በመንግሥት ላይ አድማችኋል ተብለን ተወነጀልን። እኔም ንብረቴ ሁሉ በመንግሥት እንዲወረስና ለሦስት ዓመት እንድታሰር ተፈረደብኝ።

የዕድሜ መግፋት አላገደኝም

ከእስር ነጻ ብወጣም ፖሊሶች በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉኝ ነበር። እንዲህም ሆኖ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዬን እንደገና የጀመርኩ ሲሆን በጉባኤያችን ያለውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በበላይነት የመከታተል ኃላፊነት ተሰጠኝ። በተወረሰው ቤታችን እንድንኖር የተፈቀደልን ቢሆንም ሕጋዊ በሆነ መንገድ የተመለሰልን ከ40 ዓመታት በኋላ የኮሚኒዝም ሥርዓት በወደቀበት ጊዜ ነበር።

ከቤተሰባችን ውስጥ የታሰርኩት እኔ ብቻ አይደለሁም። ከእስር ከተለቀቅኩ ከሦስት ዓመት በኋላ ኤድዋርድ በውትድርና እንዲያገለግል ተመለመለ። በመጽሐፍ ቅዱስ በሰለጠነ ሕሊናው ምክንያት በውትድርና ለማገልገል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ታሰረ። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ደግሞ የልጄ ልጅ ፒተር ጤነኛ ባይሆንም እንኳን ተመሳሳይ ችግር ገጥሞታል።

የቼኮዝሎቫኪያ ኮሚኒስት አገዛዝ በ1989 ወደቀ። ከአራት አሥርተ ዓመታት እገዳ በኋላ በነጻነት ከቤት ወደ ቤት መስበክ መቻሌ እንዴት እንዳስደሰተኝ ልትገምቱ ትችላላችሁ! (የሐዋርያት ሥራ 20:20) ጤንነቴ እስከፈቀደልኝ ድረስ በዚህ አገልግሎት በደስታ ተካፍያለሁ። አሁን 98 ዓመት ሞልቶኛል፤ እንደበፊቱ ጥሩ ጤንነት ባይኖረኝም ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጠንን አስደሳች ተስፋ ለሰዎች መስበክ እችላለሁ።

የተወለድኩባትን ከተማ ያስተዳደሩ የአምስት አገሮችን 12 መሪዎች አይቻለሁ። ከነዚህም መካከል አምባገነን መሪዎች፣ ፕሬዚዳንቶችና ንጉሥ ይገኙበታል። አንዳቸውም ቢሆኑ ለተገዢዎቻቸው ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ አላመጡም። (መዝሙር 146:3, 4) ይሖዋ ገና በልጅነቴ እሱን እንዳውቅ ስለፈቀደልኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። ይህም በመሲሐዊው መንግሥቱ አማካኝነት ስለሚያመጣው መፍትሄ እንዳውቅና ከእርሱ አገዛዝ ውጪ የሆነ ከንቱ ሕይወት እንዳልመራ ረድቶኛል። መልካሙን የምሥራች ከ75 ለሚበልጡ ዓመታት በንቃት መስበኬ ዓላማ ያለውና አርኪ ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል፤ እንዲሁም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ብሩህ ተስፋ እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ከዚህ ሌላ ምን እፈልጋለሁ? b

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

b የሚያሳዝነው ወንድም ሚካል ዝሆብራክ በመጨረሻ ጤንነቱ ክፉኛ ተቃወሰ። ይህ ጽሑፍ ለሕትመት እየተዘጋጀ ሳለ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነቱን እንደያዘ በታማኝነት በሞት አንቀላፍቷል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከተጋባን ከጥቂት ጊዜ በኋላ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከኤድዋርድ ጋር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1947 በቡርኖ ይደረግ የነበረውን የአውራጃ ስብሰባ ስናስተዋውቅ