በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የክርስቲያን ጉባኤ ሆዳምነትን እንዴት ይመለከተዋል?

የአምላክ ቃል ሰካራምነትም ሆነ ሆዳምነት የይሖዋ አገልጋዮች ሊያስወግዷቸው የሚገቡ ባሕርያት እንደሆኑ በመግለጽ እነዚህን ልማዶች ያወግዛል። ስለዚህ የክርስቲያን ጉባኤ ሆዳም መሆኑ በተደጋጋሚ የታየንና ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነን ሰው ከሰካራም ለይቶ አያየውም። ሰካራሞችም ሆኑ ሆዳሞች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቦታ የላቸውም።

ምሳሌ 23:20, 21 እንዲህ ይላል:- “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ፣ ሥጋ ከሚሰለቅጡ ጋር አትወዳጅ፤ ሰካራሞችና ሆዳሞች ድኾች ይሆናሉና፤ እንቅልፋምነትም ቡትቶ ያለብሳቸዋል።” በዘዳግም 21:20 ላይ “እልከኛና ዐመፀኛ” ሰው በሙሴ ሕግ መሠረት ሞት እንደሚፈረድበት ተገልጿል። በዚህ ጥቅስ መሠረት ንስሓ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆነው ይህ ዐመፀኛ ሰው “አባካኝና [“ሆዳምና፣” NW] ሰካራም” ነበር። በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው በጥንቷ እስራኤል አምላክን ለማገልገል በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ ሆዳምነት ተቀባይነት የሌለው ነገር ነበር።

ይሁን እንጂ ሆዳምነት ምንድን ነው? የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ? ሆዳም የሚለው ቃል “ጠገብኩ የማያውቅ፤ ስግብግብ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ስለዚህ ሆዳም ሰው ስግብግብ ነው ማለት ነው፤ የአምላክ ቃል ደግሞ “ስግብግቦች” የይሖዋን መንግሥት እንደማይወርሱ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ፊልጵስዩስ 3:18, 19፤ 1 ጴጥሮስ 4:3) ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ‘ከሥጋ ሥራ’ እንዲርቁ ሲያስጠነቅቅ ‘ስካርን፣ ዘፋኝነትን እንዲሁም እነዚህን የመሰሉትን’ ድርጊቶች እንዲያስወግዱ ነግሯቸዋል። (ገላትያ 5:19-21) አብዛኛውን ጊዜ ከመጠን በላይ መብላት ከስካርና ከፈንጠዝያ ጋር የተያያዘ ነው። በተጨማሪም ጳውሎስ ‘እነዚህን የመሰሉትን’ በማለት ከገለጻቸው ነገሮች መካከል ሆዳምነትም እንደሚገኝበት አያጠራጥርም። በብዙዎች ዘንድ በሆዳምነቱ የሚታወቅና ይህንን የስግብግብነት ባሕርይ ለማስወገድ ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ ክርስቲያን ሌሎቹን ‘የሥጋ ሥራዎች’ ቢፈጽም እንደሚደረገው ሁሉ ከጉባኤው መወገድ አለበት።—1 ቆሮንቶስ 5:11, 13 a

የአምላክ ቃል ሰካራምነትን ከሆዳምነት ለይቶ የማያየው ቢሆንም አንድ ሰው ሆዳም መሆን አለመሆኑን መለየት ሰካራም የሆነን ሰው እንደመለየት ቀላል አይደለም። የሰከረን ሰው በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። ሆኖም አካላዊ ሁኔታውን ብቻ በመመልከት አንድ ሰው ሆዳም መሆኑን ማወቅ ያስቸግራል። በመሆኑም የጉባኤ ሽማግሌዎች እንደዚህ ያሉ ጉዳዮችን በሚይዙበት ወቅት በጣም መጠንቀቅና አስተዋዮች መሆን ያስፈልጋቸዋል።

ለምሳሌ ከመጠን በላይ መፈወር የሆዳምነት ምልክት ሊሆን ቢችልም ወፍራም ሰው ሁሉ ግን ሆዳም ነው ማለት አይቻልም። አንድ ሰው በጣም የወፈረው በሕመም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ውፍረት ከቤተሰብ ሊወረስም ይችላል። ከዚህም በላይ ከመጠን በላይ መወፈር በሰውነታችን ላይ የሚታይ ነገር ሲሆን ሆዳምነት ግን ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል። ከመጠን በላይ መወፈር በሰውነት ውስጥ ብዙ ስብ በመከማቸቱ የተነሳ የሚከሰት ሲሆን ሆዳምነት ግን ‘አልጠግብ ባይነት ወይም ስግብግብነት’ ነው። በመሆኑም አንድ ሰው ሆዳም መሆኑ የሚታወቀው በክብደቱ ሳይሆን ለምግብ ባለው አመለካከት ነው። አንድ ሰው መካከለኛ ሰውነት እያለው እንዲያውም ቀጭን ሆኖም እንኳ ሆዳም ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም መጠነኛ ክብደት ወይም የተስተካከለ የሰውነት ቅርጽ የሚባለው ከቦታ ቦታ ይለያያል።

ሆዳምነት የሚታወቀው በምንድን ነው? ሆዳም ሰው በምግብ ረገድ ራሱን መግታት የማይችል ከመሆኑም በላይ ቁንጣን እስኪይዘው ወይም እስኪያመው ድረስ ከልክ በላይ ይበላል። ራሱን መግዛት አለመቻሉ፣ ድርጊቱ በይሖዋም ሆነ በሕዝቦቹ መልካም ስም ላይ የሚያመጣው ነቀፋ እንደማያሳስበው ያሳያል። (1 ቆሮንቶስ 10:31) በሌላ በኩል ግን በተወሰኑ አጋጣሚዎች ከመጠን በላይ የበላ ሰው ወዲያው እንደ “ስግብግብ” አይቆጠርም። (ኤፌሶን 5:5) ሆኖም በገላትያ 6:1 በ1980 ትርጉም ላይ በተገለጸው መሠረት እንደዚህ ያለው ግለሰብ እርዳታ ያስፈልገዋል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ወንድሞች ሆይ! ሰው ማናቸውንም ስሕተት አድርጎ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁት እናንተ እንዲህ ዐይነቱን ሰው በገርነት አቅኑት።”

መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ የመብላትን ልማድ እንድናስወግድ የሚሰጠው ምክር በተለይ በዛሬው ጊዜ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ እኛ ስለምንኖርበት ዘመን ሲናገር የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ በመስጠቱ ነው:- “በመብልና በመጠጥ ብዛት በስካርም በመባከንና ስለ ዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ። አለበለዚያ ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይመጣባችኋል።” (ሉቃስ 21:34, 35 የ1980 ትርጉም) መንፈሳዊነታችንን ሊጎዳ ከሚችል አኗኗር መራቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ ከልክ በላይ የመብላትን ልማድ በማስወገድ ነው።

ልከኝነት ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባ ባሕርይ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 11) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በአመጋገብና በመጠጥ ረገድ ልከኞች እንድንሆን የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ከልባቸው የሚጥሩትን ሁሉ ይሖዋ እንደሚረዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ዕብራውያን 4:16

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በግንቦት 1, 1986 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።