የይሖዋ ትሕትና ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
የይሖዋ ትሕትና ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
ዳዊት መከራ ምን ማለት እንደሆነ አሳምሮ የሚያውቅ ሰው ነበር። አማቹ የነበረው ንጉሥ ሳኦል በቅናት ተነሳስቶ ብዙ በደል አድርሶበታል። ሦስት ጊዜ በጦር ወግቶ ሊገድለው የሞከረ ሲሆን ለዓመታት እግር በእግር ይከታተለው ስለነበር የስደት ኑሮ ለመኖር ተገድዷል። (1 ሳሙኤል 18:11፤ 19:10፤ 26:20) ቢሆንም ይሖዋ ዳዊትን አልተወውም። ከሳኦል ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጠላቶቹም ታድጎታል። በመሆኑም ዳዊት “እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤ . . . የድል ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች፤ ዝቅ ብለህም ከፍ አደረግኸኝ” ብሎ እንዲዘምር የገፋፋውን ስሜት ለመረዳት እንችላለን። (መዝሙር 18:2, 35) ዳዊት በእስራኤል ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ አግኝቶ ነበር። ሆኖም የይሖዋ ትሕትና ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው እንዴት ነው?
ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ ትሑት እንደሆነ ሲናገሩ የአቅም ገደብ እንዳለበት ወይም የሌሎች የበታች እንደሆነ መግለጻቸው አይደለም። ከዚያ ይልቅ ይህ ልዩ ባሕርይ ይሖዋ ሞገሱን ለማግኘት ልባዊ ጥረት ለሚያደርጉ ሰዎች እንደሚራራና ምሕረቱን እንደሚያሳያቸው ይጠቁማል። መዝሙር 113:6, 7 “በሰማይና በምድር ያሉትንስ ለማየት፣ ራሱን ወደ ታች ዝቅ የሚያደርግ ማን ነው? ድኻውን ከትቢያ ያነሳል” በማለት ስለ ይሖዋ ይናገራል። ‘ራሱን ወደ ታች ዝቅ ያደርጋል’ ሲባል “ወደ ታች ለመመልከት ይጎነበሳል” ወይም “ለመመልከት ራሱን ዝቅ ያደርጋል” ማለት ነው። (ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን፤ ያንግስ ሊትራል ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ሆሊ ባይብል) ስለዚህ ይሖዋ ፍጹም ያልሆነውን ሆኖም እርሱን የማገልገል ፍላጎት የነበረውን ትሑቱን ዳዊትን ለመመልከት ‘ተጎንብሶ’ ወይም ‘ራሱን ዝቅ አድርጎ’ ነበር። በመሆኑም ዳዊት “እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል” በማለት ሊናገር ችሏል። (መዝሙር 138:6) ይሖዋ ዳዊትን በምሕረት፣ በትዕግሥትና በርኅራኄ መያዙ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ የሚያበረታታ ነው።
ይሖዋ ሉዓላዊ እንደመሆኑ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የላቀውን ቦታ ቢይዝም ከእያንዳንዳችን ጋር ዝምድና ለመመሥረት ፈቃደኛ ነው። ይህም ከባድ ችግር ቢያጋጥመን እንኳን በእርሱ እርዳታ መተማመን እንደምንችል ያረጋግጥልናል። ይሖዋ ይረሳናል ብለን የምንፈራበት መዝሙር 136:23
ምንም ምክንያት የለም። ከጥንቱ የእስራኤል ብሔር ጋር በተያያዘ ይሖዋ ‘በውርደታቸው ጊዜ ያሰባቸው፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና’ ተብሎ ተነግሮለታል።—በጊዜያችን የይሖዋ አገልጋዮች የሆንን ሁሉ እንደ ዳዊት መከራ ሊደርስብን ይችላል። አምላክን የማያውቁ ሰዎች ያፌዙብን ይሆናል፤ እንዲሁም በጤና እክል እንሠቃይ ወይም የምንወደውን ሰው በሞት በማጣታችን እናዝን ይሆናል። ያጋጠመን ሁኔታ ምንም ዓይነት ይሁን ቅን ልብ ካለን ይሖዋን በጸሎት ቀርበን ምሕረቱን እንዲያሳየን ልንለምነው እንችላለን። ይሖዋ ‘ራሱን ወደ ታች ዝቅ አድርጎ’ የሚመለከተን ከመሆኑም በላይ ጸሎታችንንም ይሰማል። መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት “የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 34:15) በይሖዋ ልዩ የትሕትና ባሕርይ ላይ ስታሰላስል ልብህ በጥልቅ አይነካም?
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የዳዊትን ጸሎት እንደሰማ ሁሉ የእኛንም ጸሎት ለመስማት ፈቃደኛ ነው