በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልብን የሚመረምረውን ይሖዋን ፈልጉ

ልብን የሚመረምረውን ይሖዋን ፈልጉ

ልብን የሚመረምረውን ይሖዋን ፈልጉ

“እኔን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ።”—አሞጽ 5:4

1, 2. ይሖዋ “ልብን ያያል” የሚለው አባባል ምን ትርጉም አለው?

 ይሖዋ አምላክ ለነቢዩ ሳሙኤል “ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” ብሎት ነበር። (1 ሳሙኤል 16:7) ይሖዋ ‘ልብን የሚያየው’ እንዴት ነው?

2 በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ልብ የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ማለትም ፍላጎቱን፣ ሐሳቡን፣ ስሜቱንና የሚወደውን ነገር ለማመልከት ብዙ ጊዜ በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ልብን ያያል ሲል ከአንድ ሰው ውጫዊ ማንነት አልፎ በእውነተኛ ማንነቱ ላይ ያተኩራል ማለት ነው።

አምላክ እስራኤልን መረመረ

3, 4. በአሞጽ 6:4-6 መሠረት በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ ይታይ ነበር?

3 ልብን የሚመረምረው አምላክ በአሞጽ ዘመን የነበረውን ባለ አሥር ነገዱን የእስራኤል መንግሥት ሲመለከት ምን አየ? አሞጽ 6:4-6 ‘በዝሆን ጥርስ ባጌጠ ዐልጋ ላይ ስለሚተኙና በድንክ ዐልጋቸው ላይ ስለሚዝናኑ’ ሰዎች ይናገራል። እነዚህ ሰዎች “ከበጎች መንጋ ጠቦትን፣ ከጋጣም ጥጃን” ይበሉ ነበር። በተጨማሪም ‘የሙዚቃ መሣሪያ’ አዘጋጅተዋል እንዲሁም “በፋጋ የወይን ጠጅ” ይጠጡ ነበር።

4 ይህ ትዕይንት እንዲሁ ከላይ ሲታይ አስደሳች ሊመስል ይችላል። ባለጠጎቹ በተንቆጠቆጡ ቤቶቻቸው ተቀምጠው ምርጥ የሆነውን እየበሉና እየጠጡ ጥራት ባላቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች ይዝናናሉ። ‘በዝሆን ጥርስ ያጌጠ ዐልጋም’ ነበራቸው። የመሬት ቁፋሮ አጥኚዎች የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ በነበረችው በሰማርያ በሚያምር ሁኔታ የተቀረጹ የዝሆን ጥርሶች አግኝተዋል። (1 ነገሥት 10:22) ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በቤት ውስጥ ዕቃዎች ላይ የተለበጡ እንዲሁም ግድግዳ ለማስጌጥም የሚያገለግሉ ሳይሆኑ አይቀሩም።

5. አምላክ በአሞጽ ዘመን በነበሩት እስራኤላውያን ያዘነው ለምን ነበር?

5 ይሖዋ የተቃወመው እስራኤላውያን ተንደላቀው መኖራቸውን፣ ጣፋጭ ምግብ መመገባቸውን፣ ጥሩ የወይን ጠጅ መጠጣታቸውንና ደስ የሚል ሙዚቃ መስማታቸውን ነበር? እንዳልነበረ የተረጋገጠ ነው! እንዲያውም የሰው ልጆች እንዲደሰቱ ለማድረግ እነዚህን ነገሮች አትረፍርፎ ሰጥቷል። (1 ጢሞቴዎስ 6:17) ይሖዋን ያሳዘነው ነገር የሕዝቡ መጥፎ ፍላጎት፣ የልባቸው ክፋት፣ ለአምላክ የነበራቸው ንቀት እንዲሁም ወገኖቻቸው ለሆኑት እስራኤላውያን ፍቅር አለማሳየታቸው ነበር።

6. በአሞጽ ዘመን በእስራኤል የነበረው መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

6 ‘በድንክ ዐልጋ ላይ የሚዝናኑ፣ ከበጎች መንጋ ጠቦትን የሚበሉ፣ ወይን የሚጠጡና የሙዚቃ መሣሪያ የሚያዘጋጁ’ እስራኤላውያን ያልጠበቁት ነገር ሊመጣባቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ‘ክፉውን ቀን የሚያርቁት’ ለምን እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። በእስራኤል በነበሩት ሁኔታዎች በጣም ማዘን ሲገባቸው እነርሱ ግን ‘ስለ ዮሴፍ መከራ አላዘኑም።’ (አሞጽ 6:3-6) ብሔሩ በኢኮኖሚ የበለጸገ ቢሆንም እንኳ አምላክ፣ ዮሴፍ ወይም እስራኤል በጣም አሳዛኝ በሆነ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተመልክቷል። ይሁንና ሕዝቡ ምንም ግድ ሳይሰጠው የዕለት ተዕለት ተግባሩን ያከናውን ነበር። ዛሬም ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ ያሳያሉ። የምንኖርበት ጊዜ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ያምኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነርሱን በግል እስካልነካቸው ድረስ በሌሎች ላይ የሚደርሰው ችግር ቅንጣት ታክል እንኳ አያሳስባቸውም፤ እንዲሁም ለመንፈሳዊ ጉዳዮች አንዳች ፍላጎት የላቸውም።

እስራኤል—በመፈራረስ ላይ ያለ ብሔር

7. የእስራኤል ነዋሪዎች የተሰጣቸውን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ካላከበሩ ምን ይደርስባቸዋል?

7 የአሞጽ መጽሐፍ ብሔሩ ከላይ ሲታይ ባለጠጋ ቢመስልም እየፈራረሰ እንደነበር ያመለክታል። የእስራኤል ሕዝብ የአምላክን ማስጠንቀቂያ ለመቀበል እንቢተኛ በመሆናቸውና አመለካከታቸውን ሳያስተካክሉ በመቅረታቸው ይሖዋ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸዋል። አሦራውያን በዝሆን ጥርስ ካጌጠው አልጋቸው ላይ ጎትተው በኃይል ወደ ግዞት ይወስዷቸዋል። ከዚያ በኋላ ምቾት የሚባል ነገር አያዩም!

8. የእስራኤል ብሔር አስከፊ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ የቻለው እንዴት ነው?

8 እስራኤላውያን እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊደርስባቸው የቻለው እንዴት ነው? ይህ ሁኔታ የተከሰተው በ997 ከክርስቶስ ልደት በፊት ንጉሥ ሰሎሞን በልጁ ሮብዓም በተተካበትና አሥሩ የእስራኤል ነገዶች ከይሁዳና ከብንያም ነገድ በተገነጠሉበት ጊዜ ነበር። የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት የመጀመሪያው ንጉሥ “የናባጥ ልጅ” ቀዳማዊ ኢዮርብዓም ነበር። (1 ነገሥት 11:26) ኢዮርብዓም በግዛቱ ያሉት ሕዝቦች ይሖዋን ለማምለክ ኢየሩሳሌም ድረስ መጓዝ እንደማያስፈልጋቸው አሳመናቸው። ይሁን እንጂ ይህን ያደረገው ለሕዝቡ ደኅንነት አስቦ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት እያደረገ ነበር። (1 ነገሥት 12:26) ኢዮርብዓም እስራኤላውያን በዓመታዊዎቹ ክብረ በዓላት ላይ ይሖዋን ለማምለክ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ መጉረፋቸውን ከቀጠሉ ልባቸው ወደ ይሁዳ ይሸፍታል የሚል ስጋት አደረበት። ኢዮርብዓም ይህን ለማስቀረት ሲል ሁለት የወርቅ ጥጃዎች አሠርቶ አንዱን በዳን ሁለተኛውን ደግሞ በቤቴል አቆመ። በዚህ መንገድ የጥጃ አምልኮ የእስራኤል ብሔር ሃይማኖት ሆነ።—2 ዜና መዋዕል 11:13-15

9, 10. (ሀ) ቀዳማዊ ንጉሥ ኢዮርብዓም የትኞቹ በዓላት እንዲከበሩ ዝግጅት አድርጎ ነበር? (ለ) አምላክ በዳግማዊ ንጉሥ ኢዮርብዓም ዘመን ይከበሩ የነበሩትን በዓላት እንዴት ይመለከታቸው ነበር?

9 ኢዮርብዓም አዲስ ያቋቋመውን ሃይማኖት እውነተኛ ለማስመሰል ሙከራ አድርጓል። በኢየሩሳሌም ይከበሩ ከነበሩት በዓላት ጋር የሚመሳሰሉ ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲከበሩ ዝግጅት አደረገ። በ1 ነገሥት 12:32 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በይሁዳ እንደሚደረገው ሁሉ [ኢዮርብዓም] በስምንተኛው ወር ዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል እንዲሆን ወሰነ፤ በመሠዊያውም ላይ መሥዋዕት አቀረበ። . . . እንዲህ ያለውን ድርጊት በቤቴል ፈጸመ።”

10 ይሖዋ እንደዚህ ያሉ የሐሰት ሃይማኖት በዓላትን ፈጽሞ አልደገፈም። ከአንድ መቶ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ በ844 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ንጉሥ በነበረው በዳግማዊ ኢዮርብዓም የንግሥና ዘመን በነቢዩ አሞጽ አማካኝነት ስለ ጣዖት አምልኮ ያለውን አመለካከት በማያሻማ ሁኔታ ገልጿል። (አሞጽ 1:1) አሞጽ 5:21-24 እንደሚያሳየው አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “ዓመት በዓላችሁን ተጸይፌአለሁ፤ ጠልቼውማለሁ፤ ጉባኤዎቻችሁ ደስ አያሰኙኝም። የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን ብታቀርቡልኝም፣ እኔ አልቀበለውም፤ ከሰቡ እንስሶቻችሁ የኅብረት መሥዋዕት ብታቀርቡልኝም፣ እኔ አልመለከተውም። የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ አርቅ፤ የበገናህንም ዜማ አልሰማም። ነገር ግን ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ።”

በዘመናችን የሚታዩ ተመሳሳይ ሁኔታዎች

11, 12. በጥንቷ እስራኤል ይካሄድ በነበረው አምልኮና ሕዝበ ክርስትና በምታካሂደው አምልኮ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

11 ይሖዋ በእስራኤል በዓላት ላይ የሚካፈሉትን ሰዎች ልብ ከመረመረ በኋላ እነዚህን በዓላትና በዚያ ወቅት የሚቀርቡትን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች እንዳልተቀበለ ግልጽ ነው። ዛሬም በተመሳሳይ እንደ ገናና ፋሲካ ያሉትን የሕዝበ ክርስትና አረመኔያዊ በዓላት ይጸየፋል። ለይሖዋ አምላኪዎች በጽድቅና በዓመጽ፣ በብርሃንና በጨለማ መካከል ምንም ዓይነት ዝምድና የለም።—2 ቆሮንቶስ 6:14-16

12 ጥጃ አምላኪዎቹ እስራኤላውያን ያከናውኑት የነበረው አምልኮና በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለው አምልኮ የሚመሳሰሉባቸውን ሌሎች መንገዶችም ማየት ይቻላል። አንዳንድ ክርስቲያን ነን ባዮች የአምላክ ቃል እውነት መሆኑን ቢቀበሉም እንኳ የሕዝበ ክርስትና አምልኮ ለአምላክ ካላት እውነተኛ ፍቅር የሚመነጭ አይደለም። ቢሆን ኖሮ ይሖዋ የሚደሰተው “በመንፈስና በእውነት” በሚቀርብ አምልኮ ስለሆነ እርሱን በዚህ መንገድ ለማምለክ ቁርጥ ያለ አቋም ትወስድ ነበር። (ዮሐንስ 4:24) ከዚህ በተጨማሪ ሕዝበ ክርስትና “ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ” እንዲፈስ አላደረገችም። ይልቁንም የአምላክን የሥነ ምግባር ብቃቶች ስትበርዝና ስትከልስ ኖራለች። ዝሙትንና ሌሎች ከባድ ኃጢአቶችን በዝምታ ታልፋለች፤ ይባስ ብሎም ግብረ ሰዶማዊ ጋብቻዎችን እስከ መፍቀድ ደርሳለች!

‘መልካሙን ውደዱ’

13. ከአሞጽ 5:15 ቃላት ጋር ተስማምተን መኖር ያለብን ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ እርሱ በሚፈልገው መንገድ አምልኮ ለማቅረብ ለሚፈልጉ ሁሉ “ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ” ብሏል። (አሞጽ 5:15) ፍቅርና ጥላቻ ከምሳሌያዊው ልብ የሚመነጩ ጠንካራ ስሜቶች ናቸው። ልብ ተንኮለኛ ስለሆነ አቅማችን በሚፈቅደው መጠን ልባችንን መጠበቅ ይኖርብናል። (ምሳሌ 4:23፤ ኤርምያስ 17:9) ልባችን መጥፎ ምኞቶች እንዲያዳብር ከፈቀድንለት መጥፎ የሆነውን መውደድና ጥሩ የሆነውን መጥላት ልንጀምር እንችላለን። ኃጢአት በመሥራት እነዚህን ምኞቶቻችንን መፈጸም ከጀመርን የቱንም ያህል ቀናተኛ አገልጋዮች መስለን ብንታይ እንኳ የአምላክን ሞገስ መልሰን ማግኘት አንችልም። ስለዚህ ‘ክፉውን መጥላትና መልካሙን መውደድ’ እንድንችል አምላክ እንዲረዳን እንጸልይ።

14, 15. (ሀ) በእስራኤል መልካም ነገር ከሚሠሩት መካከል እነማን ይገኙ ነበር? ይሁንና አንዳንዶቹ ምን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል? (ለ) በዛሬው ጊዜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሠማሩትን ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?

14 በይሖዋ ዓይን መጥፎ የሆነውን ያደርጉ የነበሩት ሁሉም እስራኤላውያን አልነበሩም። ለምሳሌ ያህል፣ ሆሴዕና አሞጽ ‘መልካሙን ይወድዱ’ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ነቢይ ሆነው በታማኝነት አገልግለውታል። ሌሎች ደግሞ በናዝራዊነት ለመኖር ስዕለት ተስለዋል። ናዝራውያን ሆነው በኖሩባቸው ዘመናት ከወይን ተክል ውጤቶች በሙሉ በተለይም ከወይን ጠጅ ራሳቸውን ጠብቀዋል። (ዘኍልቁ 6:1-4) ሌሎቹ እስራኤላውያን መልካም ነገር የሚያከናውኑትን የእነዚህን ሰዎች የመሥዋዕትነት ኑሮ እንዴት ተመለከቱት? ለዚህ ጥያቄ የተሰጠው አስደንጋጭ መልስ ብሔሩ ምን ያህል በመንፈሳዊ ነቅዞ እንደነበር ያሳየናል። አሞጽ 2:12 “እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም ትንቢት እንዳይናገሩ አዘዛችኋቸው” ይላል።

15 እነዚህ እስራኤላውያን የናዝራውያኑንና የነቢያቱን የታማኝነት ምሳሌ ሲመለከቱ እፍረት ተሰምቷቸው አካሄዳቸውን ለመለወጥ መነሳሳት ነበረባቸው። ከዚህ ይልቅ እስራኤላውያኑ ታማኞቹ አገልጋዮች ለአምላክ ክብር እንዳይሰጡ ለማዳከም ሞከሩ። እኛም አቅኚዎች፣ ሚስዮናውያን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሆኑ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን የሙሉ ጊዜ አገልግሎታቸውን አቋርጠው ለራሳቸው እንዲኖሩ ማበረታታት አይገባንም። ከዚህ ይልቅ በዚህ በጎ ሥራቸው እንዲቀጥሉ እናበረታታቸው!

16. እስራኤላውያን ከአሞጽ ዘመን ይልቅ በሙሴ ዘመን የተሻለ መንፈሳዊ ሁኔታ የነበራቸው ለምንድን ነው?

16 በአሞጽ ዘመን የነበሩ በርካታ እስራኤላውያን በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ተሟልቶላቸው የነበረ ቢሆንም እንኳ “በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም” አልነበሩም። (ሉቃስ 12:13-21) አባቶቻቸው ለ40 ዓመት በምድረ በዳ የተመገቡት መና ብቻ ነበር። የሰባ ሰንጋ አርደው አልበሉም ወይም በዝሆን ጥርስ በተለበጠ አልጋ ላይ አልተንፈላሰሱም። ይሁን እንጂ ሙሴ እንዲህ ሲል በትክክል ነግሯቸዋል፦ “አምላካችሁ እግዚአብሔር በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኮአችኋል፤ . . . በእነዚህ አርባ ዓመታት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።” (ዘዳግም 2:7) አዎን፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ እያሉ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አጥተው አያውቁም። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአምላክን ፍቅር፣ ጥበቃና በረከት አግኝተዋል!

17. ይሖዋ የጥንቶቹን እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ያስገባቸው ለምን ነበር?

17 ይሖዋ በአሞጽ ዘመን የነበሩትን ሰዎች አባቶቻቸውን ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳስገባቸውና ጠላቶቻቸውን ከምድሪቱ እንዲያስወግዱ እንደረዳቸው አስታወሳቸው። (አሞጽ 2:9, 10) ይሁንና ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ያስገባቸው ለምን ነበር? የቅንጦት ኑሮ እንዲኖሩና ፈጣሪያቸውን እንዲተዉ ነበር? በጭራሽ! ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያደረገው ከባርነት ተላቅቀውና በመንፈሳዊ ንጹሕ ሕዝብ ሆነው እርሱን ማምለክ እንዲችሉ ነው። ሆኖም አሥር ነገዶችን ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ነዋሪዎች ክፉውን አልጠሉም፣ መልካሙንም አልወደዱም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ አምላክ ሳይሆን ለተቀረጹ ምስሎች ክብር መስጠት ጀመሩ። እንዴት የሚያሳፍር ነገር ነው!

ይሖዋ ሊቀጣቸው ነው

18. ይሖዋ በመንፈሳዊ ሁኔታ ነፃ ያወጣን ለምንድን ነው?

18 አምላክ እስራኤላውያን ያሳዩትን አሳፋሪ ባሕርይ በቸልታ አያልፈውም። “ስለ ሠራችሁት ኀጢአት ሁሉ፣ እኔ እቀጣችኋለሁ” ሲል አቋሙን በግልጽ አስፍሯል። (አሞጽ 3:2) እነዚህ ቃላት ከዘመናዊቷ ግብጽ ማለትም ከዚህ ክፉ ሥርዓት ባርነት ነፃ ስለመውጣታችን እንድናስብ ሊያደርጉን ይገባል። ይሖዋ በመንፈሳዊ ሁኔታ ነፃ ያወጣን የስስትና የራስ ወዳድነት ግቦችን እንድንከታተል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ይህን ያደረገው በንጹሕ አምልኮ የምንሳተፍ ነፃ ሰዎች ሆነን ከልብ የመነጨ ክብር እንድንሰጠው ነው። ደግሞም ሁላችንም ይህን ነፃነታችንን ስለተጠቀምንበት መንገድ ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።—ሮሜ 14:12

19. በአሞጽ 4:4, 5 መሠረት አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለምን ነገር ፍቅር አድሮባቸው ነበር?

19 የሚያሳዝነው ግን አብዛኞቹ እስራኤላውያን አሞጽ ላስተላለፈው ጠንካራ መልእክት ጆሯቸውን አልሰጡም። ነቢዩ በአሞጽ 4:4, 5 ላይ ልባቸው በመንፈሳዊ የታመመ መሆኑን እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “ወደ ቤቴል ሂዱና ኀጢአትን ሥሩ፤ ወደ ጌልገላም ሂዱና ኀጢአትን አብዙ፤ . . . እናንት እስራኤላውያን . . . ማድረግ የምትወዱት ይህን ነውና።” እስራኤላውያኑ ትክክለኛ ዝንባሌዎችን አላዳበሩም። ልባቸውን አልጠበቁም። በዚህም የተነሣ አብዛኞቹ ክፉውን መውደድ፣ ጥሩውን መጥላት ጀምረው ነበር። እነዚህ አንገተ ደንዳና ጣዖት አምላኪዎች ፈጽሞ አልተለወጡም። ይሖዋ ይቀጣቸዋል፤ በኃጢአታቸው እንደተተበተቡም ይሞታሉ!

20. አንድ ሰው ከአሞጽ 5:4 ጋር የሚስማማ አካሄድ መከተል የሚችለው እንዴት ነው?

20 በዚያ ዘመን ለሚኖር ለማንኛውም ሰው ቢሆን ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መኖር ቀላል አልነበረም። በመካከላችን ያላችሁ ወጣቶችም ሆናችሁ ጎልማሶች በሚገባ እንደምታውቁት የአብዛኛውን ሕዝብ ዝንባሌ በሚቃረን መንገድ መመላለስ ቀላል አይደለም። ይሁንና አንዳንድ እስራኤላውያን አምላክን ስለሚወዱና እርሱን የማስደሰት ፍላጎት ስለነበራቸው እውነተኛውን አምልኮ ለመፈጸም ተነሳስተዋል። ይሖዋ በአሞጽ 5:4 ላይ የሚገኘውን “እኔን ፈልጉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ” የሚለውን ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦላቸዋል። በዛሬው ጊዜም አምላክ የቃሉን ትክክለኛ እውቀት በመቅሰምና ከዚያም ፈቃዱን በማድረግ ንስሐ ለሚገቡና እርሱን ለሚፈልጉ ሰዎች ምሕረት ያደርግላቸዋል። በዚህ ጎዳና መመላለስ ቀላል ባይሆንም እንዲህ ማድረግ ግን የዘላለም ሕይወት ያስገኛል።—ዮሐንስ 17:3

መንፈሳዊ ረሃብ እያለም የተገኘ ብልጽግና

21. እውነተኛውን አምልኮ የማይከተሉ ሰዎች ምን ዓይነት ረሃብ ይደርስባቸዋል?

21 እውነተኛውን አምልኮ የማይደግፉ ሁሉ ምን ይጠብቃቸዋል? ከረሃብ ሁሉ የከፋ ረሃብ ማለትም መንፈሳዊ ረሃብ ያጋጥማቸዋል! ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “በምድር ላይ ረሐብን የምሰድበት ዘመን ይመጣል፤ ይኸውም የእግዚአብሔርን ቃል የመስማት ረሐብ እንጂ፣ እንጀራን የመራብ ወይም ውሃን የመጠማት አይደለም።” (አሞጽ 8:11) ሕዝበ ክርስትና እንዲህ ባለው መንፈሳዊ ረሃብ ተይዛለች። ይሁን እንጂ በመካከሏ የሚገኙ ቅን ሰዎች የአምላክን ሕዝቦች መንፈሳዊ ብልጽግና ማየት የሚችሉ ከመሆኑም በላይ ወደ ይሖዋ ድርጅት እየጎረፉ ናቸው። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በሚታየው ሁኔታና በአምላክ አገልጋዮች ዘንድ ባለው ሁኔታ መካከል ያለው ልዩነት ይሖዋ በተናገራቸው በሚከተሉት ቃላት በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል፦ “ባሮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ ባሮቼ ይጠጣሉ፤ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ ባሮቼ ደስ ይላቸዋል፤ እናንተ ግን ታፍራላችሁ።”—ኢሳይያስ 65:13

22. ደስተኛ የምንሆንበት ምን ምክንያት አለን?

22 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ለተደረጉልን መንፈሳዊ ዝግጅቶችና ላገኘናቸው በረከቶች በግለሰብ ደረጃ አድናቆት እናሳያለን? መጽሐፍ ቅዱስንና መንፈሳዊ ጽሑፎችን ስናጠና እንዲሁም በጉባኤ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በምንገኝበት ጊዜ ሁሉ ከልባችን ደስታ የተነሣ እልል ብለን ለመጮህ ይቃጣናል። በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአሞጽን ትንቢት ጨምሮ ስለ አምላክ ቃል ጥርት ያለ ማስተዋል በማግኘታችን ደስተኞች ነን።

23. አምላክን የሚያከብሩ ሰዎች ምን ያገኛሉ?

23 አምላክን ለሚወዱና ለእርሱ ክብር መስጠት ለሚፈልጉ ሁሉ የአሞጽ ትንቢት የተስፋ መልእክት ይዟል። አሁን ያለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታ ወይም በዚህ በችግር በተሞላ ዓለም የሚያጋጥመን መከራ ምንም ይሁን ምን እኛ አምላክን የምንወድ ሰዎች መለኮታዊ በረከትና ምርጥ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ አግኝተናል። (ምሳሌ 10:22፤ ማቴዎስ 24:45-47) ለእኛ ጥቅም ሲል ሁሉንም ነገር አትረፍርፎ ለሚሰጠን አምላክ ክብር ሊቀርብለት ይገባል። ስለዚህ ለእሱ ልባዊ ውዳሴያችንን ለዘላለም ማቅረብ ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን። ልብን የሚመረምረውን ይሖዋን የምንፈልግ ከሆነ ይህን አስደሳች መብት ማግኘት እንችላለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በአሞጽ ዘመን እስራኤል ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ ይታይ ነበር?

• በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ላይ የታየው ዓይነት ሁኔታ በማን ላይ ደርሷል?

• በአሁኑ ጊዜ አስቀድሞ የተተነበየ ምን ዓይነት ረሃብ ተከስቷል? ሆኖም በረሃቡ የማይጠቁት እነማን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ እስራኤላውያን የቅንጦት ኑሮ ቢኖሩም መንፈሳዊ ብልጽግና ግን አላገኙም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች መልካም ሥራ መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸው

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ደስተኛ ሕዝቦች በመንፈሳዊ አይራቡም