በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ለምን ያህል ዓመት መኖር ይችላሉ?

ሰዎች ለምን ያህል ዓመት መኖር ይችላሉ?

ሰዎች ለምን ያህል ዓመት መኖር ይችላሉ?

መጋቢት 3, 1513 ሁዋን ፖንሴ ዴ ሊዮን የተባለው ስፔይናዊ አሳሽ አንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዞ አድርጎ ነበር። ከፖርቶ ሪኮ በመርከብ የተነሳው ሁዋን ቢሚኒ ወደምትባለው ደሴት ለመድረስ ተስፋ በማድረግ ጉዞ ጀመረ። በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው የጉዞው ዓላማ ወጣትነትን መልሶ ያጎናጽፋል የሚባልለትን ተአምራዊ ጠበል ለማግኘት ነበር። ይሁን እንጂ የቢሚኒን ደሴት በማግኘት ፋንታ በዩናይትድ ስቴትስ በምትገኘው የአሁኗ የፍሎሪዳ ግዛት አረፈ። ተአምራዊው ጠበል ግን ቀድሞውንም ስላልነበረ ሊያገኘው አልቻለም።

በዛሬው ጊዜ የሰዎች ዕድሜ በአጠቃላይ ሲታይ ከ70ና ከ80 ዓመት ብዙም አይዘልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም ረዥም ዘመን የኖሩ ሰዎች እንዳሉ ቢገለጽም በ2002 የዓለማችን የድንቃድንቅ ነገሮች መዝገብ ላይ በሰፈረው ዘገባ መሠረት ረጅም ዘመን በመኖር የአንደኝነትን ደረጃ የያዙት ሴት ዕድሜያቸው 122 ዓመት ከ164 ቀናት ነው። (ዘፍጥረት 5:3-32) ይሁን እንጂ ባዮኤቲክስ ተብሎ በሚጠራው የሕክምና ሥነ ምግባር ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ጆን ሃሪስ “በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ ያሉ አዳዲስ ምርምሮች እርጅናና ሞት የማንጋፋቸው ባላጋራዎቻችን መሆናቸው የሚያከትምበት ዘመን ሊመጣ እንደሚችል ተስፋ እየሰጡ ነው” ብለዋል። በርካታ የ21ኛው መቶ ዘመን ተመራማሪዎች ወደፊት የሰው ልጆች “ያለመሞት ባሕርይ” እንደሚላበሱ፣ “በ2099 የሰዎች ዕድሜ ገደብ እንደማይኖረው” እንዲሁም “ሴሎቻችን አንዳቸው ሌላውን እየተኩ ለዘላለም የመቀጠል ብቃት እንደሚኖራቸው” እና እነዚህን የመሳሰሉ ተስፋዎች እየሰጡ ነው።

ማርክ ቤኔኬ የተባሉ ደራሲ ዘ ድሪም ኦቭ ኢተርናል ላይፍ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ ውስጥ መላው አካሉ ለማለት ይቻላል በየጊዜው ይታደሳል። . . . ከሰባት ዓመታት ገደማ በኋላ ቃል በቃል አዲስ ሰውነት ይኖረናል።” ይሁን እንጂ የሰውነታችን ሴሎች ለተወሰነ ጊዜ እየተከፈሉ ከተባዙ በኋላ መከፈላቸውን ስለሚያቆሙ ይህ ሂደት ለዘላለም አይቀጥልም። እንዲህ ባይሆን ኖሮ “የሰው አካል ራሱን በራሱ እያደሰ ለረጅም ጊዜ እንዲያውም ለዘላለም መቀጠል ይችል ነበር” በማለት ቤኔኬ ተናግረዋል።

አጭር በሆነው የሕይወት ዘመናችን ውስጥ ልንጠቀምበት ከምንችለው በጣም የላቀ መረጃ የማከማቸት ብቃት ያለውን አእምሯችንን ደግሞ እንመልከት። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚለው የሰዎች አእምሮ “አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ ሊጠቀምበት ከሚችለው በእጅጉ የበለጠ አቅም አለው።” (1976 እትም፣ ጥራዝ 12፣ ገጽ 998) በዴቪድ ሳውሳ የተጻፈው ሃው ዘ ብሬን ለርንስ የተባለው መጽሐፍ “አእምሮ ማንኛውንም ዓይነት መረጃ ለማከማቸት ያለው አቅም ገደብ የለውም” ይላል።—ገጽ 78, ሁለተኛ እትም፣ Copyright 2001

ከአፈጣጠራችን አንጻር የምናረጅበትንና የምንሞትበትን ምክንያት ተመራማሪዎች ለማወቅ ያልቻሉት ለምንድን ነው? የሰዎች አእምሮስ ይሄን ያህል ከፍተኛ መረጃ የማከማቸት ብቃት ያለው ለምንድን ነው? ለዘላለም እውቀት እየቀሰምን እንድንኖር ታስቦ የተዘጋጀ ይሆን? ደግሞስ ለዘላለም ስለመኖር ማሰብ የቻልነው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው” ይላል። (መክብብ 3:11 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ቃላት ለዘላለም የመኖርን ሐሳብ በውስጣችን የቀረጸው አምላክ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ስለ አምላክና ስለ ሥራዎቹ ሁልጊዜ አዳዲስ ነገሮችን እየተማርን መኖር እንችላለን። ኅልቆ መሳፍርት ለሌላቸው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ማለትም ለዘላለም መኖር ብንችል ስለ አምላክ ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች ሁልጊዜ ተጨማሪ እውቀት የመቅሰም አጋጣሚ እናገኛለን።

ኢየሱስ ክርስቶስም የሰው ልጆች ለዘላለም መኖር የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ተናግሯል። “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 17:3) አንተስ? ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁዋን ፖንሴ ዴ ሊዮን ወጣትነትን መልሶ ያጎናጽፋል የተባለለትን ጠበል ለማግኘት ይፈልግ ነበር

[ምንጭ]

ፖንሴ ዴ ሊዮን፦ Harper’s Encyclopædia of United States History