በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው!”

“እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው!”

ዕጹብ ድንቅ የሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት

“እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው!”

የምንኖረው በገጠርም ሆነ በከተማ፣ በተራራማ ቦታዎችም ሆነ በባሕር አካባቢ በዙሪያችን ዕጹብ ድንቅ የሆኑ ፍጥረታት ይገኛሉ። በመሆኑም የ2004 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ የይሖዋ አምላክን አስደናቂ ፍጥረታት በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንድንችል የሚያደርጉ ሥዕሎች ይዞ መውጣቱ ተገቢ ነው።

አድናቂ የሆኑ ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ትኩረት ይሰጡ ነበር። ለአብነት ያህል፣ “ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ” ጥበብ እንዳለው የተነገረለትን ሰሎሞንን እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “ከሊባኖስ ዝግባ አንሥቶ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ስለ ዕፀዋት ተናግሮአል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣ ስለ ወፎች፣ በሆዳቸው ስለሚሳቡ እንስሳትና ስለ ዓሦችም ተናግሮአል” ይላል። (1 ነገሥት 4:30, 33) የሰሎሞን አባት የሆነው ንጉሥ ዳዊትም ብዙውን ጊዜ በአምላክ ድንቅ ሥራዎች ላይ ያውጠነጥን ነበር። ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች” በማለት ፈጣሪውን ለማወደስ ተገፋፍቶ ነበር።—መዝሙር 104:24 a

እኛም የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች ትኩረት ሰጥተን ልንመለከታቸውና ልናሰላስልባቸው ይገባል። ለምሳሌ ዓይናችንን አንሥተን ወደ ሰማይ በመመልከት “እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው?” ብለን መጠየቅ እንችላለን። መልሱ ‘ታላቅ ኃይልና ብርታት’ ያለው ይሖዋ አምላክ ነው የሚል ይሆናል።—ኢሳይያስ 40:26

በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን ቢያንስ በሦስት መንገዶች ይጠቅመናል። እንዲህ ማድረጋችን (1) ሕይወታችንን ውድ እንደሆነ አድርገን እንድንመለከተው፣ (2) ሌሎች ከፍጥረት እንዲማሩ ለመርዳት እንድንነሳሳ እንዲሁም (3) ፈጣሪያችንን ይበልጥ እንድናውቀውና እንድናደንቀው ያደርገናል።

የሰው ልጆች ‘ልቦና ከሌላቸው አራዊት’ የላቅን በመሆናችን ተፈጥሮን መመልከትና ማድነቅ እንችላለን። (2 ጴጥሮስ 2:12) ዓይናችን ውብ የሆኑ መልክዓ ምድሮችን ለመመልከት፣ ጆሯችን ጣፋጭ የሆነውን የአእዋፍ ዝማሬ ለማድመጥ የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ ጊዜና ቦታዎችን ማስታወስ የምንችል መሆኑ አስደሳች ትዝታዎች እንዲኖሩን ያደርጋል። የአሁኑ ሕይወታችን ፍጹም የተስተካከለ ባይሆንም እንኳ በሕይወት መኖራችን ፈጽሞ የሚያስቆጭ አይደለም!

ወላጆች ልጆቻቸው በፍጥረት የመደሰት ዝንባሌ እንዳላቸው ይመለከታሉ። ልጆች በለመለመ መስክ ላይ ቢራቢሮዎችን ማባረር፣ ከቤት እንስሳት ጋር መጫወት ወይም ዛፍ ላይ መውጣት በጣም ያስደስታቸዋል። ልጆቹ የሚያዩአቸው ፍጥረታት ፈጣሪ እንዳላቸው እንዲገነዘቡ ወላጆች ሊረዷቸው ይገባል። እንዲህ ማድረጋቸው ልጆቹ ካደጉም በኋላ እንኳ ለይሖዋ ፍጥረታት አድናቆትና አክብሮት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።—መዝሙር 111:2, 10

ተፈጥሮን አድንቀን የዚህ ሥራ ባለቤት የሆነውን ፈጣሪ ሳናደንቅ ብንቀር የሚያሳዝን ይሆናል። ኢሳይያስ የተናገረው የሚከተለው ትንቢት በዚህ ጉዳይ ላይ እንድናስብ ይረዳናል:- “አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም።”—ኢሳይያስ 40:28

በእርግጥም የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ተወዳዳሪ የሌለው ጥበቡን፣ አቻ የማይገኝለት ኃይሉንና ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያሳያሉ። ዙሪያችንን ስንቃኝ የምንመለከተው ውበትና እነዚህን ሁሉ የሠራው ፈጣሪ ያሉት ባሕርያት እንደ ዳዊት “ጌታ ሆይ፤ . . . እንደ አንተ ያለ የለም፤ ከአንተም ሥራ ጋር የሚወዳደር ሥራ የለም” እንድንል ያነሳሱናል።—መዝሙር 86:8

ምንጊዜም ቢሆን ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች ማድነቃቸውን እንደሚቀጥሉ እርግጠኞች ነን። ለዘላለም ስንኖር ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለመማር ሰፊ አጋጣሚ እናገኛለን። (መክብብ 3:11) ይበልጥ ስለ እርሱ በተማርን መጠን ደግሞ ፈጣሪያችንን ይበልጥ እንወደዋለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በ2004 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ ኅዳር/ታኅሣሥ የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለፈጣሪ የቀረበ ውዳሴ

አድናቂ የሆኑ በርካታ ሳይንቲስቶች ፍጥረት የአምላክ እጅ እንዳለበት እንደሚያምኑ ተናግረዋል። እነዚህ ሳይንቲስቶች ከሰነዘሯቸው ሐሳቦች መካከል ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል:-

“በምሠራበት የሳይንስ መስክ አልፎ አልፎ አዲስ ነገር ሳገኝ ‘አሃ፣ አምላክ የሠራው በዚህ መንገድ ነው ማለት ነው’ ብዬ አስባለሁ። እነዚህ አጋጣሚዎች በሥራዬ ላይ ጉልህ ሥፍራ የሚይዙ ከመሆኑም በላይ ያስደስቱኛል። ጥረቴ ከአምላክ ዓላማ ውስጥ ትንሿን ክፍል ለማወቅ ነው።”—የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሄንሪ ሼፈር

“አጽናፈ ዓለሙ እየሰፋ ስለሚሄድበት ምክንያት አንባቢው የራሱ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይኖርበታል፤ ሆኖም በመደምደሚያችን ላይ እርሱን [አምላክን] ካላስገባን የተሟላ ግንዛቤ አይኖረንም።”—የሥነ ሕዋ ተመራማሪ የሆኑት እንግሊዛዊው ኤድዋርድ ሚለን

“ተፈጥሮን አለ በሚባለው የላቀ የሒሳብ ስሌት መግለጽ የተቻለው አምላክ ስለፈጠረው እንደሆነ እናውቃለን።”—አሌክሳንደር ፖልያኮቭ የተባሉ ሩስያዊ የሒሳብ ምሑር

“በተፈጥሯዊ አካላት ላይ በምናካሂደው ጥናት የፈጣሪን ሐሳብ እያጠናን፣ የእርሱን ንድፎች እያነበብንና የእርሱ እንጂ የእኛ ያልሆነውን ሥርዓት እየተነተንን ነው።”—የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት አሜሪካዊው ሉዊስ አጋዚ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀንቱ ፔንግዊን፣ አንታርክቲክ ባሕረ ገብ መሬት

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግራንድ ቴተን ብሔራዊ ፓርክ፣ ዋዮሚንግ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

[ምንጭ]

Jack Hoehn/Index Stock Photography