በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፉዎች ከይሖዋ ፍርድ አያመልጡም

ክፉዎች ከይሖዋ ፍርድ አያመልጡም

ክፉዎች ከይሖዋ ፍርድ አያመልጡም

“አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ።”—አሞጽ 4:12

1, 2. አምላክ ክፋትን እንደሚያስወግድ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

 ይሖዋ ክፋትንና ሥቃይን ከዚህች ምድር ያስወግድ ይሆን? ይህ ጥያቄ በተለይ በዚህ በሃያ አንደኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ መነሳቱ በጣም ተገቢ ነው። የትም ብንሄድ ሰው በሰው ላይ የሚፈጽመውን አረመኔያዊ ድርጊት እንመለከታለን። ከዓመጽ፣ ከሽብርተኝነትና ከምግባረ ብልሹነት የጸዳች ዓለም ለማየት በጣም እንናፍቃለን!

2 ደስ የሚለው ግን ይሖዋ ክፋትን እንደሚያስወግድ ሙሉ በሙሉ መተማመን መቻላችን ነው። አምላክ ክፋትን እንደሚያጠፋ ባሕርይው ራሱ ያረጋግጣል። ይሖዋ ጻድቅና ፍትሐዊ ነው። በመዝሙር 33:5 ላይ ቃሉ “እርሱ ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል” በማለት ይናገራል። አንድ ሌላ መዝሙር ደግሞ “ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች” ይላል። (መዝሙር 11:5) በእርግጥም፣ አንዳች የማይሳነውና ጽድቅንና ፍትሕን የሚወድደው አምላክ የሚጠላውን ነገር ለዘላለም ታግሦ አይኖርም።

3. የአሞጽን ትንቢት መመርመራችንን ስንቀጥል ጎላ ብለው የሚብራሩት ነገሮች ምንድን ናቸው?

3 ይሖዋ ክፋትን እንደሚያስወግድ እርግጠኛ መሆን የምንችልበት ሌላም ምክንያት አለ። ከአሁን በፊት ያደረጋቸው ነገሮች ለዚህ ዋስትና ይሰጡናል። ይሖዋ በክፉዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የሚያሳይ ምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በአሞጽ መጽሐፍ ውስጥ እናገኛለን። በአሞጽ ትንቢት ላይ የምናደርገው ቀጣይ ምርምር ስለ መለኮታዊ ፍርድ ሦስት ነገሮችን ያስተምረናል። አንደኛ የይሖዋ ፍርድ ምንጊዜም ተገቢ ነው። ሁለተኛ ከይሖዋ ፍርድ ማምለጥ አይቻልም። ሦስተኛ ፍርዱ የሚፈጸመው ጥፋት በሚገባቸው ሰዎች ላይ ብቻ ነው። ይህም የሆነው ይሖዋ በክፉዎች ላይ የጥፋት ፍርድ ሲያመጣ ንስሐ ለሚገቡና ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ላላቸው ግለሰቦች ግን ምሕረቱን ስለሚዘረጋ ነው።—ሮሜ 9:17-26

መለኮታዊ ፍርድ ምንጊዜም ተገቢ ነው

4. ይሖዋ አሞጽን የላከው ወዴት ነበር? ለምን ዓላማስ?

4 በአሞጽ ዘመን የእስራኤል ብሔር ለሁለት መንግሥት ተከፍሎ ነበር። አንደኛው በስተ ደቡብ የሚገኘው ሁለት ነገድ ያቀፈው የይሁዳ መንግሥት ሲሆን ሌላው ደግሞ በስተ ሰሜን የሚገኘው አሥር ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ነበር። ይሖዋ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል አሞጽን ከአገሩ ከይሁዳ ወደ እስራኤል ምድር ላከው። በዚያም አሞጽ መለኮታዊውን ፍርድ በማወጅ አምላክን ያገለግላል።

5. አሞጽ በመጀመሪያ ትንቢት የተናገረው በየትኞቹ ብሔራት ላይ ነበር? መለኮታዊ የጥፋት ፍርድ የሚገባቸው ሆነው የተገኙበት አንደኛው ምክንያትስ ምን ነበር?

5 አሞጽ ሥራውን የጀመረው ዓመጸኛ በሆነው በሰሜናዊው መንግሥት ላይ የሚወርደውን መለኮታዊ ፍርድ በማወጅ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መልእክቱን የጀመረው በእስራኤል አቅራቢያ በሚገኙ ስድስት ብሔራት ላይ ማለትም በሶርያ፣ በፍልስጥኤም፣ በጢሮስ፣ በኤዶም፣ በአሞንና በሞዓብ ላይ የሚመጣውን የቅጣት ፍርድ በማወጅ ነበር። ይሁንና እነዚህ ብሔራት በእርግጥ የአምላክን የቅጣት ፍርድ ሊቀበሉ የሚገባቸው ነበሩ? በእርግጥ ይገባቸዋል። አንደኛ ነገር የአምላክ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላቶች ነበሩ።

6. አምላክ በሶርያ፣ በፍልስጥኤምና በጢሮስ ላይ ጥፋት ለማምጣት የወሰነው ለምን ነበር?

6 ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ‘ገለዓድን የብረት ጥርስ ባለው ማሄጃ ስላሄዱ’ ሶርያውያንን አውግዟቸዋል። (አሞጽ 1:3) ሶርያውያን የእስራኤል ግዛት ከሆነችው ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ከምትገኘው ከገለዓድ ላይ መሬት ወስደዋል። ከዚህም ሌላ በዚያ በሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። ፍልስጥኤምና ጢሮስስ ጥፋታቸው ምንድን ነው? ፍልስጥኤማውያን እስራኤላውያን ምርኮኞችን ወይም ግዞተኞችን ለኤዶማውያን በመሸጣቸው በደለኞች ሆነዋል። አንዳንድ እስራኤላውያን ደግሞ የባሪያ ነጋዴ በሆኑ ጢሮሳውያን እጅ ወድቀዋል። (አሞጽ 1:6, 9) የይሖዋን ሕዝቦች ለባርነት መሸጥ እንዴት ያለ ድፍረት ነው! ይሖዋ በሶርያ፣ በፍልስጥኤም እና በጢሮስ ላይ ጥፋት የሚያመጣ መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም።

7. ኤዶም፣ አሞንና ሞዓብ ከእስራኤል ጋር የሚዛመዱት በምን ነበር? ሆኖም በእስራኤላውያን ላይ የፈጸሙት ነገር ምንድን ነው?

7 ኤዶም፣ አሞንና ሞዓብ ከእስራኤልም ሆነ አንዳቸው ከሌላው ጋር የሚገናኙበት አንድ የጋራ ባሕርይ ነበራቸው። ሦስቱም ከእስራኤላውያን ጋር የሥጋ ዝምድና ነበራቸው። ኤዶማውያን የያዕቆብ መንትያ ወንድም ከሆነው ከዔሳው የተወለዱ የአብርሃም ዝርያዎች ነበሩ። ስለዚህ የእስራኤል ወንድሞች ነበሩ ማለት ይቻላል። አሞናውያንና ሞዓባውያንም የአብርሃም ወንድም ልጅ የነበረው የሎጥ ዝርያዎች ናቸው። ይሁንና ኤዶም፣ አሞንና ሞዓብ ዘመዶቻቸው የሆኑትን እስራኤላውያንን በወንድምነት ተቀብለዋቸው ነበር? በፍጹም! ኤዶም አለምንም ርኅራኄ “ወንድሙን” በሰይፍ አሳዶታል። አሞናውያን ደግሞ በእስራኤላውያን ግዞተኞች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ፈጽመዋል። (አሞጽ 1:11, 13) አሞጽ፣ ሞዓብ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የፈጸመውን ግፍ በቀጥታ ባይገልጽም ሞዓባውያን እስራኤላውያንን በመቃወም ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ አስመዝግበዋል። በእነዚህ ሦስት ዘመዳማች ብሔራት ላይ የሚወርደው ቅጣት እጅግ አስከፊ ይሆናል። ይሖዋ እንደ እሳት ያለ ጥፋት እንደሚያመጣባቸው ተናግሯል።

ክፉዎች ከመለኮታዊ ፍርድ አያመልጡም

8. በእስራኤል አቅራቢያ የነበሩት ስድስቱ ብሔራት ከአምላክ ፍርድ ሊያመልጡ የማይችሉት ለምንድን ነው?

8 በአሞጽ ትንቢት ላይ በመጀመሪያ የተጠቀሱት እነዚህ ስድስት ብሔራት ጥፋት እንደሚገባቸው ምንም አያጠያይቅም። ከዚህ በተጨማሪ ከጥፋቱ ማምለጥ የሚችሉበት አንዳች መንገድ አልነበረም። ይሖዋ ከአሞጽ ምዕራፍ 1 ቁጥር 3 እስከ ምዕራፍ 2 ቁጥር 1 ድረስ ስድስት ጊዜ ያህል “ቊጣዬን አልመልስም” ብሏል። ልክ እንደተናገረውም በእነዚያ ብሔራት ላይ እጁን ከመዘርጋት አልመለሰም። በእነዚህ ሁሉ ብሔራት ላይ ጥፋት መድረሱን የታሪክ መዝገብ ያረጋግጣል። እንዲያውም ቢያንስ አራቱ ማለትም ፍልስጥኤም፣ ሞዓብ፣ አሞንና ኤዶም ከጊዜ በኋላ ከሕልውና ውጪ ሆነዋል!

9. የይሁዳ ነዋሪዎች ምን መቀበል ይገባቸዋል? ለምንስ?

9 የአሞጽ ትንቢት ቀጥሎ በሰባተኛ ብሔር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን ይህም የአሞጽ የትውልድ አገር የሆነው የይሁዳ ምድር ነው። በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ይኖሩ የነበሩት ሰዎች አሞጽ በይሁዳ መንግሥት ላይ የጥፋት ፍርድ ሲያውጅ በመስማታቸው ሳይገረሙ አይቀሩም። የይሁዳ ነዋሪዎች የቅጣት ፍርድ የሚገባቸው የሆኑት ለምን ነበር? አሞጽ 2:4 “የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋል” ይላል። ይሖዋ ሰዎች ሕጉን እንዲህ ሆን ብለው ችላ ሲሉ ዝም ብሎ አላለፋቸውም። በአሞጽ 2:5 ላይ እንደተገለጸው “የኢየሩሳሌምን ምሽጎች እንዲበላ፣ በይሁዳ ላይ እሳት እሰዳለሁ” ሲል ተንብዮአል።

10. ይሁዳ ከሚመጣባት ወዮታ ማምለጥ የማትችለው ለምንድን ነው?

10 ከዳተኛይቱ ይሁዳ ከሚመጣባት ወዮታ ማምለጥ አትችልም። ይሖዋ ለሰባተኛ ጊዜ “ቊጣዬን አልመልስም” ብሏል። (አሞጽ 2:4) ይሁዳ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በባቢሎናውያን ስትጠፋ ይህን የተተነበየባትን ቅጣት ተቀብላለች። ከዚህም ቢሆን ክፉዎች ከመለኮታዊ ፍርድ ሊያመልጡ እንደማይችሉ እንረዳለን።

11-13. አሞጽ በዋነኝነት የፍርድ ትንቢት ያወጀው በየትኛው ብሔር ላይ ነበር? በዚያስ ምን ዓይነት ጭቆና ይታይ ነበር?

11 ነቢዩ አሞጽ በሰባት ብሔራት ላይ የሚመጣውን የይሖዋን ፍርድ አውጆ መጨረሱ ነበር። ይሁን እንጂ፣ አሞጽ የሚናገረው ገና ብዙ ነገር ስላለ ትንቢት መናገሩን ጨርሷል ብሎ ተስፋ ያደረገ ሰው ካለ በጣም ተሳስቷል! አሞጽ በዋነኝነት የታዘዘው በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ላይ ጠንካራ የፍርድ መልእክት እንዲያሰማ ነበር። የብሔሩ ሥነ ምግባራዊና ሃይማኖታዊ ዝቅጠት አስከፊ ደረጃ ላይ ስለደረሰ እስራኤል መለኮታዊ ፍርድ መቀበል ይገባት ነበር።

12 አሞጽ የሚያውጀው ትንቢት በእስራኤል መንግሥት ተንሰራፍቶ የነበረውን ጭቆና አጋልጧል። ይህን በተመለከተ አሞጽ 2:6, 7 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ሦስቱ የእስራኤል ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም፤ ጻድቁን ስለ ጥሬ ብር፣ ችግረኛውንም ስለ ጥንድ ጫማ ይሸጡታልና። የድኾችን ራስ፣ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ ፍትሕንም ከጭቊኖች ይነጥቃሉ።’”

13 ጻድቃን “ስለ ጥሬ ብር” ይሸጣሉ። ይህም ዳኞች የብር ጉቦ ተቀብለው በንጹሐን ሰዎች ላይ ይፈርዱ ነበር ማለት ሊሆን ይችላል። አበዳሪዎች ለትንሽ ዕዳ ሲሉ ሳይሆን አይቀርም ድሆችን ‘በጥንድ ጫማ’ ዋጋ ለባርነት ይሸጡ ነበር። ጨካኝ ሰዎች ‘ድኾችን’ የማዋረድ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ምስኪኖቹ ማዘናቸውን፣ መጨነቃቸውንና መዋረዳቸውን ለማሳየት በገዛ ራሳቸው ላይ ትቢያ ይነሰንሳሉ። ሙስና በጣም የተስፋፋ ከመሆኑ የተነሣ ‘ጭቁኖች’ ምንም ዓይነት ፍትሕ እናገኛለን ብለው ተስፋ አያደርጉም ነበር።

14. በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ ግፍ ይፈጸምባቸው የነበሩት እነማን ናቸው?

14 ግፍ የሚፈጸምባቸው እነማን እንደነበሩ ልብ በል። በምድሪቱ የሚኖሩ ጻድቃን፣ ችግረኞች፣ ድሆችና ቅኖች ነበሩ። ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የገባው የሕጉ ቃል ኪዳን ችግረኛና ድሃ የሆኑ ሰዎች በርኅራኄ እንዲያዙ ያዝዝ ነበር። ይሁን እንጂ በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ግዛት ውስጥ ለሚኖሩ እንደዚህ ላሉ ግለሰቦች ሁኔታው በጣም አስከፊ ነበር።

“አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ”

15, 16. (ሀ) እስራኤላውያን “አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ” የሚል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ለምን ነበር? (ለ) አሞጽ 9:1, 2 ክፉዎች መለኮታዊውን ፍርድ ማምለጥ እንደማይችሉ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ሐ) አሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ምን ደረሰበት?

15 በእስራኤል ውስጥ የሥነ ምግባር ብልግናም ሆነ ሌሎች ኃጢአቶች በሰፊው ይፈጸሙ ስለነበር ነቢዩ አሞጽ ዓመጸኛውን ብሔር “አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ” ሲል ማስጠንቀቁ ተገቢ ነበር። (አሞጽ 4:12) ይሖዋ ለስምንተኛ ጊዜ “ቊጣዬን አልመልስም” በማለት ስለገለጸ ከዳተኛይቱ እስራኤል ከሚመጣባት መለኮታዊ ፍርድ ልታመልጥ አትችልም። (አሞጽ 2:6) ለመደበቅ የሚሞክሩ ኃጢአተኛ ሰዎችን በተመለከተ አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “ከእነርሱ አንድም ሰው አይሸሽም፤ ቢሸሽም የሚያመልጥ የለም። መቃብር በጥልቀት ቈፍረው ቢወርዱም፣ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይ ቢወጡም፣ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ።”—አሞጽ 9:1, 2

16 ክፉዎች “መቃብር በጥልቀት ቈፍረው” ማለትም በታችኛው የምድር ክፍል ለመሸሸግ ጥረት ቢያደርጉ እንኳ ከይሖዋ የቅጣት ፍርድ ሊያመልጡ አይችሉም። “ወደ ሰማይ ቢወጡም” ማለትም ረጅም በሆኑ ተራሮች ቢመሸጉም ከመለኮታዊ ፍርድ ሊሰወሩ አይችሉም። የይሖዋ ማስጠንቀቂያ ግልጽ ነው፦ እርሱ ሊደርስበት የማይችልበት መሸሸጊያ የለም። የእስራኤል መንግሥት ለፈጸመው የክፋት ድርጊት ብድራቱን እንዲከፍል መለኮታዊ ፍትሕ ያስገድዳል። ይህ ፍርድ አሞጽ ትንቢቱን ከመዘገበ ከ60 ዓመታት በኋላ ማለትም በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት በአሦራውያን እጅ ሲወድቅ ተፈጽሟል።

መለኮታዊ ፍርድ በጅምላ አይጨርስም

17, 18. አሞጽ ምዕራፍ 9 ስለ አምላክ ምሕረት ምን የሚገልጸው ነገር አለ?

17 መለኮታዊ ፍርድ ምንጊዜም በሚገባቸው ላይ እንደሚደርስና ከፍርዱም ማምለጥ እንደማይቻል ከአሞጽ ትንቢት ተመልክተናል። ይሁን እንጂ የአሞጽ መጽሐፍ የይሖዋ ፍርድ ክፉዎችንና ጻድቃንን በጅምላ እንደማያጠፋም ይገልጻል። አምላክ ክፉዎችን የገቡበት ገብቶ ሊያገኛቸውና የቅጣት ፍርዱን ሊያወርድባቸው ይችላል። ንስሐ የሚገቡና ቅን በመሆናቸው የተነሳ ምሕረት የሚገባቸው ሰዎችንም ማግኘት ይችላል። ይህ ትምህርት በአሞጽ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ግሩም በሆነ መንገድ ተገልጿል።

18 በአሞጽ ምዕራፍ 9 ቁጥር 8 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ “የያዕቆብን ቤት ግን፣ ሙሉ በሙሉ አልደመስስም” ብሏል። ከቁጥር 13 እስከ 15 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ “የተሰደደውን ሕዝቤን . . . እመልሳለሁ” ሲል ቃል ገብቷል። እነዚህ ሰዎች ምሕረት ይደረግላቸዋል እንዲሁም የተረጋጋ ሕይወትና ብልጽግና ያገኛሉ። ይሖዋ “ዐጫጁ ዐጭዶ ሳይጨርስ፣ ዐራሹ በላዩ የሚደርስበት፣ . . . ጊዜ ይመጣል” ሲል ቃል ገብቷል። እስቲ አስቡት፣ ምርቱ በጣም ከመብዛቱ የተነሣ እህሉ ገና ተሰብስቦ ሳያልቅ ቀጣዩ የእርሻና የዘር ወቅት ይደርሳል!

19. የእስራኤልና የይሁዳ ቀሪዎች ምን ዓይነት ሁኔታ አጋጠማቸው?

19 በይሁዳና በእስራኤል በሚኖሩ ክፉዎች ላይ የተላለፈው የይሖዋ የቅጣት ፍርድ ንስሐ የገቡትንና ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን የማይጨምር በመሆኑ ፍርዱ ጅምላ ጨራሽ አልነበረም ማለት ይቻላል። አሞጽ ምዕራፍ 9 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው የመልሶ ማቋቋም ትንቢት መሠረት ንስሐ የገቡ የእስራኤልና የይሁዳ ቀሪዎች በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከባቢሎን ግዞት ተመልሰዋል። ወደሚወዷት ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ንጹሑን አምልኮ ዳግመኛ አቋቁመዋል። ተረጋግተው መኖር ከጀመሩ በኋላ ደግሞ ቤታቸውን መልሰው የገነቡ ከመሆኑም ሌላ ወይንና ሌሎች ተክሎችን አልምተዋል።

የይሖዋ የቅጣት ፍርድ ይፈጸማል!

20. አሞጽ ያወጀውን የፍርድ መልእክት መመርመራችን ምን ማረጋገጫ ሊሰጠን ይገባል?

20 አሞጽ በተናገረው የመለኮታዊ ፍርድ መልእክት ላይ ያደረግነው ጥናት ይሖዋ ክፋትን በእኛ ዘመንም ቢሆን እንደሚያስወግድ ዋስትና ይሰጠናል። ይህን ማመን የምንችለው ለምንድን ነው? አንደኛ፣ አምላክ በክፉዎች ላይ የፈጸማቸው እነዚህ የቀድሞ ድርጊቶች በዘመናችን ምን እርምጃ እንደሚወስድ የሚጠቁሙ ናቸው። ሁለተኛ፣ በከዳተኛው የእስራኤል መንግሥት ላይ የተፈጸመው መለኮታዊ ፍርድ አምላክ የዓለም ሐሰት ሃይማኖት ግዛት ማለትም ‘የታላቂቷ ባቢሎን’ ዋነኛ ክፍል በሆነችው በሕዝበ ክርስትና ላይ ጥፋት እንደሚያመጣ ያረጋግጣል።—ራእይ 18:2

21. ሕዝበ ክርስትና የአምላክ የቅጣት ፍርድ የሚገባት ለምንድን ነው?

21 ሕዝበ ክርስትና መለኮታዊ ፍርድ ልትቀበል የሚገባት መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። በውስጧ የሚታየው ቀፋፊ ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ ለዚህ ግልጽ ማስረጃ ነው። ሕዝበ ክርስትናና የተቀረው የሰይጣን ዓለም የይሖዋን ፍርድ መቀበላቸው የተገባ ነው። ከፍርዱ ማምለጥም አይቻልም። ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ጊዜ ሲደርስ የአሞጽ ምዕራፍ 9 ቁጥር 1 ቃላት ይፈጸማሉ፦ “ከእነርሱ አንድም ሰው አይሸሽም፤ ቢሸሽም የሚያመልጥ የለም።” አዎን፣ ክፉዎች የትም ይደበቁ የት፣ ይሖዋ ያገኛቸዋል።

22. መለኮታዊ ፍርድን በተመለከተ በ2 ተሰሎንቄ 1:6-8 ላይ ግልጽ የሆኑት የትኞቹ ነጥቦች ናቸው?

22 መለኮታዊ ፍርድ ምንጊዜም ቢሆን ተገቢ ነው፤ እንዲሁም ክፉዎች ከዚህ የቅጣት ፍርድ ማምለጥ የማይችሉ ሲሆን የሚፈጸመው ደግሞ በጅምላ አይደለም። ይህን ከሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት መረዳት ይቻላል፦ “እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤ መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው። በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።” (2 ተሰሎንቄ 1:6-8) “እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ” በቅቡዓን አገልጋዮቹ ላይ መከራ ለሚያመጡ ሰዎች የሚገባቸውን የቅጣት ፍርድ ይከፍላቸዋል። ‘ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር በሚገለጥበት ጊዜ’ ክፉዎች በሕይወት ስለማይተርፉ ከዚህ ፍርድ ማምለጥ አይቻልም። ኢየሱስ የበቀል እርምጃ የሚወስደው ‘እግዚአብሔርን በማያውቁትና ለወንጌል በማይታዘዙት’ ላይ ስለሆነ ከዚህ አንጻርም ቢሆን መለኮታዊ ፍርድ በጅምላ የሚጨርስ አይደለም። ደግሞም የመለኮታዊ ፍርድ መፈጸም አምላክን ለሚፈሩና መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች መጽናኛ ያስገኝላቸዋል።

ቅኖች ያላቸው ተስፋ

23. ከአሞጽ መጽሐፍ ላይ ምን ተስፋና ማጽናኛ ማግኘት ይቻላል?

23 የአሞጽ ትንቢት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ላላቸው ግለሰቦች ግሩም የሆነ የማጽናኛና የተስፋ መልእክት ይዟል። በአሞጽ መጽሐፍ ላይ በትንቢት ተነግሮ እንደነበረው ይሖዋ የጥንት ሕዝቦቹን ሙሉ በሙሉ አላጠፋቸውም። ከጊዜ በኋላ የእስራኤልንና የይሁዳን ግዞተኞች ወደ አገራቸው መልሶ በታላቅ ሰላምና ብልጽግና ባርኳቸዋል። ይህ ለዘመናችን ምን ትርጉም ይኖረዋል? መለኮታዊ የቅጣት ፍርድ በሚፈጸምበት ጊዜ ይሖዋ ክፉዎችን የትም ቢሸሸጉ ሊያገኛቸው እንደሚችል ሁሉ የእርሱ ምሕረት የሚገባቸው ሰዎችም በየትኛውም የምድር ክፍል ቢሆኑ ያሉበትን እንደሚያውቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

24. በዚህ ዘመን ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ምን በረከቶች አግኝተዋል?

24 ይሖዋ በክፉዎች ላይ የሚያመጣው ፍርድ የሚፈጸምበትን ጊዜ ስንጠባበቅ ታማኝ አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን ምን እናገኛለን? ይሖዋ ከፍተኛ መንፈሳዊ ብልጽግና አጎናጽፎናል! የሕዝበ ክርስትና የሐሰት ትምህርቶች ካመነጯቸው የውሸትና የተጣመሙ እምነቶች የጸዳ አምልኮ አግኝተናል። በተጨማሪም ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በመስጠት ባርኮናል። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ያገኘናቸው እነዚህ በረከቶች ትልቅ ኃላፊነት እንደሚያስከትሉብን ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ ሌሎች ሰዎችን ስለ መጪው ፍርድ እንድናስጠነቅቅ ይጠብቅብናል። ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ሰዎችን ለማግኘት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን። (የሐዋርያት ሥራ 13:48) አዎን፣ የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎች እኛ የምንደሰትበትን መንፈሳዊ ብልጽግና እንዲያገኙና በቅርቡ በክፉዎች ላይ ከሚመጣው መለኮታዊ ፍርድ እንዲድኑ መርዳት እንፈልጋለን። እርግጥ ነው፣ እነዚህን በረከቶች ማግኘት ከፈለግን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። ይህም በአሞጽ ትንቢት ውስጥ ጎላ ተደርጎ መገለጹን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የአሞጽ ትንቢት የይሖዋ የቅጣት ፍርድ ምን ጊዜም ተገቢ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

• አሞጽ ከመለኮታዊ ፍርድ ማምለጥ እንደማይቻል ለማሳየት ምን ማስረጃ አቅርቧል?

• የአምላክ የቅጣት ፍርድ በጅምላ እንደማያጠፋ የአሞጽ መጽሐፍ የሚያሳየው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእስራኤል መንግሥት ከመለኮታዊ ፍርድ አላመለጠም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት የእስራኤልና የይሁዳ ቀሪዎች ከባቢሎን ግዞት ተመልሰዋል