በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ቃል በድፍረት ተናገር

የአምላክን ቃል በድፍረት ተናገር

የአምላክን ቃል በድፍረት ተናገር

“ሂድና ለሕዝቤ . . . ትንቢት ተናገር።”—አሞጽ 7:15

1, 2. አሞጽ ማን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ምን ይላል?

 ስለ ይሖዋ የሚመሠክር አንድ ሰው በአገልግሎት ተሰማርቶ እንዳለ አንድ ካህን ተቃወመው። ካህኑ ‘ሁለተኛ ስትሰብክ እንዳላይህ! ከዚህ አካባቢ ጥፋ!’ በማለት ጮኸበት። ታዲያ ምሥክሩ ምን አደረገ? ለካህኑ ማስፈራሪያ ተሸነፈ ወይስ የአምላክን ቃል በድፍረት መናገሩን ቀጠለ? ይህ ምሥክር ያጋጠሙትን ነገሮች በስሙ በተጠራው መጽሐፍ ውስጥ መዝግቦ ስላቆየ ምን እንዳደረገ ማወቅ ትችላለህ። መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው ትንቢተ አሞጽ ነው። ይሁንና አሞጽ ከካህኑ ጋር ስላጋጠመው ፍጥጫ በዝርዝር ከማየታችን በፊት ስለ እርሱ ማንነት አንዳንድ ሁኔታዎችን እንመልከት።

2 አሞጽ ማን ነበር? የኖረውስ መቼና የት ነበር? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ አሞጽ 1:1 ላይ የምናገኝ ሲሆን ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በቴቁሔ ከነበሩት እረኞች መካከል አንዱ የሆነው አሞጽ፣ ዖዝያን የይሁዳ ንጉሥ በነበረ ጊዜ እንዲሁም የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም የእስራኤል ንጉሥ በነበረ ጊዜ . . . የተናገረው ቃል ይህ ነው።” አሞጽ ይኖር የነበረው ይሁዳ ውስጥ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ 16 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቴቁሔ ነበር። የኖረበት ዘመንም ንጉሥ ዖዝያን በይሁዳ፣ ዳግማዊ ንጉሥ ኢዮርብዓም ደግሞ በአሥሩ ነገድ የእስራኤል ሕዝብ ላይ ይገዙ በነበረበት በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። አሞጽ የበግ እረኛ ነበር። እንዲያውም አሞጽ 7:14 “እረኛ” ብቻ ሳይሆን “የባሉጥ ፍሬ ለቃሚ [“ወጊ፣” NW]” እንደነበረም ይናገራል። ስለዚህ በዓመቱ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ መከር በመሰብሰብ ሥራ ይሰማራ ነበር። የባሉጥ ፍሬ ይወጋ ወይም ይበሳ ነበር። እንዲህ የሚደረገው ፍሬው ቶሎ እንዲበስል ለማድረግ ነው። ይህ ሥራ በጣም አድካሚ ነበር።

‘ሂድ ትንቢት ተናገር’

3. ለመስበክ ብቃቱ እንደሌለን ከተሰማን ስለ አሞጽ ሁኔታ ማወቃችን እንዴት ሊረዳን ይችላል?

3 አሞጽ “ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም” በማለት ሐቁን ተናግሯል። (አሞጽ 7:14) አሞጽ የነቢይ ልጅ ወይም የነቢይነት ሥልጠና የተሰጠው ሰው አልነበረም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በይሁዳ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ለሥራው የመረጠው አሞጽን ነበር። በወቅቱ አምላክ ኃያል የሆነ ንጉሥ፣ የተማረ ካህን ወይም ባለጠጋ የሕዝብ አለቃ አልመረጠም። ይህም ለሁላችንም የሚያጽናና ትምህርት ይዞልናል። የኑሮ ደረጃችን ወይም የተከታተልነው መደበኛ ትምህርት በጣም ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህ የአምላክን ቃል ለመስበክ ብቃት እንደሌለን ሆኖ እንዲሰማን ሊያደርግ ይገባል? በፍጹም! ይሖዋ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ የአገልግሎት ክልሎች እንኳን ሳይቀር መልእክቱን ለማወጅ የሚያስችለንን ብቃት ሊሰጠን ይችላል። ይሖዋ ለአሞጽ ያደረገለት ይህንኑ ስለነበረ የአምላክን ቃል በድፍረት የመናገር ፍላጎት ያለን ሁሉ አሞጽ የተወልንን ምሳሌ ብንመረምር ጥሩ ትምህርት እናገኛለን።

4. አሞጽ እስራኤል ውስጥ ትንቢት መናገር በጣም አስቸጋሪ የሆነበት ለምን ነበር?

4 ይሖዋ “ሂድና ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር” በማለት ለአሞጽ ትእዛዝ ሰጠው። (አሞጽ 7:15) ይህ በጣም አስቸጋሪ ሥራ ነበር። በወቅቱ የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት በሰላምና በጸጥታ ተረጋግቶ ይኖር የነበረ ሲሆን ነዋሪዎቹም ባለጠጎች ነበሩ። ብዙዎቹ ተራ በሆነ የጭቃ ጡብ ሳይሆን ውድ በሆነ “በተጠረበ ድንጋይ” የተሠሩ ‘የክረምትና የበጋ ቤቶች’ ነበሯቸው። አንዳንዶቹ በዝሆን ጥርስ የተሸለሙ የቤት ዕቃዎች ነበሯቸው። “ባማሩ የወይን ተክል ቦታዎች” የተመረተ ወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር። (አሞጽ 3:15፤ 5:11) ከዚህ የተነሣ አብዛኛው ሕዝብ ግድየለሽ ሆኗል። በእርግጥም ለአሞጽ የተሰጠው የአገልግሎት ክልል አንዳንዶቻችን ከምናገለግልበት አካባቢ ጋር ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም።

5. አንዳንድ እስራኤላውያን ምን ዓይነት በደል ይፈጽሙ ነበር?

5 እስራኤላውያን ሀብታም መሆናቸው በራሱ ምንም ስህተት አልነበረውም። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ሀብት ያከማቹት በተለያዩ የማታለያ ዘዴዎች ነበር። ባለጠጎቹ ‘ድኾችን ይጨቁኑና ችግረኞችን ያስጨንቁ’ ነበር። (አሞጽ 4:1) ታላላቅ ነጋዴዎች፣ ዳኞችና ካህናት ድሆችን ለመዝረፍ አሲረዋል። አሁን ወዳለፈው ዘመን መለስ እንበልና እነዚህ ሰዎች ምን ያደርጉ እንደነበረ እስቲ እንመልከት።

የአምላክ ሕግ ተጣሰ

6. እስራኤላውያን ነጋዴዎች ሌሎችን ይበዘብዙ የነበሩት እንዴት ነው?

6 በመጀመሪያ በገበያ ቦታ የሚፈጸመውን እንመልከት። አታላይ ነጋዴዎች ‘መስፈሪያውን ያሳንሱ፣ ዋጋውን ከፍ ያደርጉ’ ይባስ ብሎም “ግርዱን” በስንዴ ዋጋ ይሸጡ ነበር። (አሞጽ 8:5, 6) ነጋዴዎቹ መጠኑን በማሳነስ፣ ዋጋውን በጣም በማስወደድና መናኛ ምርቶችን በመሸጥ ደንበኞቻቸውን ያታልሉ ነበር። ነጋዴዎቹ ድሆቹን በዝብዘው ካራቆቷቸው በኋላ እነዚህ ምስኪን ሰዎች ራሳቸውን ለባርነት ለመሸጥ ይገደዳሉ። ከዚያ በኋላ ነጋዴዎቹ “በጥንድ ጫማ” ዋጋ ይገዟቸዋል። (አሞጽ 8:6) እስቲ አስበው፣ እነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎች ወገናቸው የሆነውን እስራኤላዊ ከጫማ የበለጠ ዋጋ እንደሌለው አድርገው ይቆጥሩ ነበር! በእርግጥም፣ ችግረኞችን እጅግ ያዋርዱና የአምላክን ሕግ ይጥሱ ነበር! ይሁንና እነዚሁ ነጋዴዎች “ሰንበት” ያከብሩ ነበር። (አሞጽ 8:5) አዎን፣ ለይምሰል ሆነ እንጂ ሃይማኖተኞች ነበሩ።

7. የእስራኤል ነጋዴዎች የአምላክን ሕግ እንዲጥሱ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ምንድን ነው?

7 ነጋዴዎቹ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ትእዛዝ ተላልፈው እያለ እንዴት ከቅጣት ማምለጥ ቻሉ? (ዘሌዋውያን 19:18) ሕጉን ማስከበር የነበረባቸው ዳኞች የወንጀላቸው ተባባሪዎች በመሆናቸው ነበር። ችሎት በሚቀመጡበት የከተማው በር ላይ ዳኞቹ ‘ጉቦ ይቀበላሉ እንዲሁም ከድኻው ፍትሕ ይነጥቃሉ።’ የድሆቹን መብት ከማስከበር ይልቅ በጉቦ አሳልፈው ይሰጧቸው ነበር። (አሞጽ 5:10, 12) በመሆኑም ዳኞቹም የአምላክን ሕግ ይተላለፉ ነበር።

8. ክፉዎቹ ካህናት አይተው እንዳላዩ ያለፉት ምን ዓይነቱን ድርጊት ነበር?

8 በዚህ ጊዜ ታዲያ የእስራኤል ካህናት ምን ያደርጉ ነበር? ይህን ለማወቅ ትኩረታችንን ወደ ሌላ ቦታ እናዙር። ካህናቱ “በአምላካቸው ቤት” ምን ዓይነት ኃጢአት ሲፈጸም ዝም ብለው እንደሚያዩ ተመልከት! አምላክ በአሞጽ አማካኝነት “አባትና ልጅ ከአንዲት ሴት ጋር ይተኛሉ፤ እንዲህም እያደረጉ ቅዱስ ስሜን ያረክሳሉ” ብሏል። (አሞጽ 2:7, 8) እስቲ አስበው፣ አንድ እስራኤላዊ አባትና ልጁ ሁለቱም አንዲት የቤተ መቅደስ ጋለሞታ ጋር ሄደው የፆታ ብልግና ይፈጽማሉ! እነዚያ ክፉ ካህናት ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ብልግና አይተው እንዳላዩ ሆነው ያልፉ ነበር!—ዘሌዋውያን 19:29፤ ዘዳግም 5:18፤ 23:17

9, 10. እስራኤላውያን ጥፋተኛ የሆኑት የትኛውን የአምላክ ሕግ በመጣሳቸው ነው? በዛሬው ጊዜስ ምን ዓይነት ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል?

9 ይሖዋ የፈጸሙትን ተጨማሪ ኃጢአት በተመለከተ “በመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ፣ በየመሠዊያው ሥር ይተኛሉ፤ በአምላካቸው ቤት፣ በመቀጫነት የተወሰደውን የወይን ጠጅ ይጠጣሉ” ብሏል። (አሞጽ 2:8) አዎን፣ ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ በአጠቃላይ በመያዣነት የተወሰደ ልብስ ፀሐይ ከመግባቱ በፊት ለባለቤቱ መመለስ እንዳለበት የሚያዝዘውን የዘፀአት 22:26, 27ን ሕግም ይተላለፋሉ። ልብሱን ከመመለስ ይልቅ ለሐሰት አማልክት አምልኮ በሚያቀርቡበት ጊዜ መሬት ላይ አንጥፈው ይበሉበትና ይጠጡበት ነበር። ከድሆች በሚወስዱት የመቀጫ ገንዘብ ደግሞ በሐሰት ሃይማኖት ክብረ በዓላት ላይ የሚጠጡትን የወይን ጠጅ ይገዙበት ነበር። ከእውነተኛው የአምልኮ ጎዳና በጣም ርቀዋል!

10 እስራኤላውያን ይሖዋንና ባልንጀሮቻቸውን እንዲወድዱ የተሰጧቸውን ሁለት ታላላቅ ትእዛዛት በግልጽ ጥሰዋል። በዚህም ምክንያት አምላክ የክህደት አካሄዳቸውን እንዲያወግዝ አሞጽን ላከው። ዛሬም የሕዝበ ክርስትና ተከታዮችን ጨምሮ የቀረው የዚህ ዓለም ክፍል የጥንቷን እስራኤል ምግባረ ብልሹነት ያንጸባርቃሉ። አንዳንዶች በሀብት ሲበለጽጉ አብዛኛው ሕዝብ ግን የትላልቅ ንግድ ድርጅቶች እንዲሁም የፖለቲካና የሐሰት ሃይማኖት አጭበርባሪ መሪዎች በሚፈጽሙት ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ተግባር የተነሳ ደህይቶ የገንዘብና የስሜት ኪሳራ ደርሶበታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ መከራ ለሚደርስባቸውና እርሱን ለመፈለግ ለሚነሳሱ ሁሉ ያስባል። በዚህም ምክንያት በዚህ ዘመን ላሉ አገልጋዮቹ ልክ እንደ አሞጽ ቃሉን በድፍረት የመስበክ ሥራ ሰጥቷቸዋል።

11. ከአሞጽ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

11 ለአሞጽና ለእኛ የተሰጠው ሥራ በጣም ስለሚመሳሰል የአሞጽን ምሳሌ በመመርመር ከፍተኛ ጥቅም እናገኛለን። እንዲያውም ከአሞጽ ታሪክ (1) ምን መስበክ እንዳለብን፣ (2) እንዴት መስበክ እንዳለብን እና (3) ተቃዋሚዎች የስብከቱን ሥራችንን ማስቆም የማይችሉት ለምን እንደሆነ እንማራለን። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመርምር።

አሞጽን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

12, 13. ይሖዋ በእስራኤላውያን አለመደሰቱን የገለጸው እንዴት ነው? የእነርሱስ ምላሽ ምን ነበር?

12 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን የሚያተኩረው የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ማርቆስ 13:10) ይሁንና አሞጽ፣ ይሖዋ በክፉዎች ላይ የቅጣት ፍርድ እንደሚያመጣ እንደተናገረ ሁሉ እኛም የአምላክን ማስጠንቀቂያ እንሰብካለን። ለምሳሌ ያህል፣ አሞጽ 4:6-11 ይሖዋ በእስራኤል ማዘኑን በተለያዩ መንገዶች በግልጽ ማሳወቁን ያሳያል። ይሖዋ ለሕዝቡ ‘የሚበሉት እንዳሳጣቸው፣’ ‘ዝናብ እንደከለከላቸው፣’ “በዋግና በአረማሞም” እንደመታቸው እንዲሁም “መቅሰፍትን” እንደሰደደባቸው ገልጿል። እነዚህ ሁኔታዎች እስራኤላውያንን ንስሐ እንዲገቡ አድርገዋቸዋል? አምላክ “እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም” ብሏል። በእርግጥም፣ እስራኤላውያን ይሖዋን በተደጋጋሚ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

13 ይሖዋ ንስሐ ለመግባት እንቢተኛ የሆኑትን እስራኤላውያን ቀጥቷቸዋል። ከዚያ በፊት ግን ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ መሠረት አምላክ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ ምንም ነገር አያደርግም” ብሏል። (አሞጽ 3:7) ይሖዋ ለኖኅ የጥፋት ውኃ እንደሚመጣና ሕዝቡንም እንዲያስጠነቅቅ እንደነገረው ሁሉ ለአሞጽም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ ነገረው። የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን ይህን መለኮታዊ መልእክት ሳይቀበሉና ትክክለኛውን እርምጃ ሳይወስዱ ቀሩ።

14. በአሞጽ ዘመንና በእኛ ዘመን መካከል ምን ተመሳሳይነት ይታያል?

14 በአሞጽ ዘመንና በእኛ ዘመን መካከል አንዳንድ አስገራሚ ተመሳሳይነት መኖሩን እንደምትቀበል ግልጽ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው ዘመን ብዙ መቅሰፍቶች እንደሚኖሩ ተንብዮ ነበር። በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚካሄድ የስብከት ሥራ እንደሚኖር ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3-14) ይሁን እንጂ እንደ አሞጽ ዘመን ሁሉ ዛሬም አብዛኞቹ ሰዎች ለዘመኑ ምልክቶችም ሆነ የአምላክ አገልጋዮች ለሚሰብኩት መልእክት ትኩረት አልሰጡም። እነዚህ ሰዎች ንስሐ ባልገቡት እስራኤላውያን ላይ የደረሰው ዓይነት መከራ ይደርስባቸዋል። ይሖዋ በአሞጽ ዘመን የነበሩትን ሰዎች “አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ” ሲል አስጠንቅቋቸው ነበር። (አሞጽ 4:12) እስራኤላውያን በአሦር ሠራዊት ድል ተደርገው የቅጣት ፍርዱን በተቀበሉ ጊዜ ከአምላክ ጋር ተገናኝተዋል። ዛሬም ይህ አምላክ የለሽ ዓለም ይሖዋን በአርማጌዶን ‘ይገናኛል።’ (ራእይ 16:14, 16) ሆኖም የይሖዋ ትዕግሥት እስከቀጠለ ድረስ የተቻለንን ያህል ብዙ ሰዎች ‘ይሖዋን እንዲፈልጉና በሕይወት እንዲኖሩ’ እንመክራለን።—አሞጽ 5:6

እንደ አሞጽ ተቃውሞን መጋፈጥ

15-17 (ሀ) አሜስያስ ማን ነበር? አሞጽ ለሚያውጀው የፍርድ መልእክትስ ምን ምላሽ ሰጠ? (ለ) አሜስያስ በአሞጽ ላይ ምን ክስ አቀረበ?

15 አሞጽ ካሳለፈው ተሞክሮ ምን እንደምንሰብክ ብቻ ሳይሆን መልእክቱን እንዴት እንደምንሰብክ ጭምር እንማራለን። ይህ ጉዳይ በመግቢያችን ላይ ስለተጠቀሰው ካህን በሚናገረው በምዕራፍ 7 ላይ በሚገባ ተገልጿል። ይህ ሰው “የቤቴል ካህን አሜስያስ” ነበር። (አሞጽ 7:10) ቤቴል የጥጃ አምልኮን የሚያካትተው የእስራኤል የክህደት ሃይማኖት ማዕከል ነበረች። ስለዚህ አሜስያስ የአገሩ ብሔራዊ ሃይማኖት ካህን ነበር። አሞጽ በድፍረት ለሚናገረው መልእክት ምን ስሜት አደረበት?

16 አሜስያስ አሞጽን እንዲህ አለው፦ “አንተ ባለ ራእይ ከዚህ ሂድ! [ወደ] ይሁዳ ምድር ሽሽ፤ እዚያም እንጀራህን ብላ፤ በዚያም ትንቢት ተናገር። ከእንግዲህ ወዲያ ግን በቤቴል ትንቢት አትናገር፤ የንጉሡ መቅደስ፣ የመንግሥቱም መኖሪያ ነውና።” (አሞጽ 7:12, 13) አሜስያስ ‘ወደ አገርህ ሂድ! እኛ የራሳችን ሃይማኖት አለን’ ብሎ የተናገረ ያህል ነበር። በተጨማሪም አሜስያስ ለዳግማዊ ንጉሥ ኢዮርብዓም “አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል በአንተ ላይ እያሤረ ነው” ብሎ በመንገር መንግሥት የአሞጽን እንቅስቃሴ እንዲያግድ ጥረት አድርጓል። (አሞጽ 7:10) አሜስያስ፣ አገር የመክዳት ወንጀል ፈጽሞአል ብሎ አሞጽን ከሰሰው! ለንጉሡ እንዲህ አለው፦ “አሞጽ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበርና፤ ‘ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፤ እስራኤልም በእርግጥ ከትውልድ አገሩ ተማርኮ ይሄዳል።’”—አሞጽ 7:11

17 አሜስያስ በዚህ ንግግሩ ብቻ ሦስት አሳሳች ነገሮችን ተናግሯል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ “አሞጽ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበርና” አለ። አሞጽ ግን ትንቢቱን እርሱ እንዳመነጨው አድርጎ ተናግሮ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በማለት ነበር የሚናገረው። (አሞጽ 1:3) በተጨማሪም “ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል” ብሏል በማለት አሞጽን ከሶታል። ይሁን እንጂ በአሞጽ 7:9 ላይ ማየት እንደሚቻለው አሞጽ የተነበየው “[እኔ ይሖዋ] በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፌ እነሣለሁ” ብሎ ነው። አምላክ እንዲህ ዓይነት ጥፋት እንደሚያመጣ ያስነገረው በኢዮርብዓም “ቤት” ማለትም በዝርያዎቹ ላይ ነው። በመጨረሻም አሜስያስ “እስራኤልም በእርግጥ ከትውልድ አገሩ ተማርኮ ይሄዳል” ብሏል ሲል አሞጽን ከሶታል። ይሁንና አሞጽ ወደ አምላክ የሚመለስ ማንኛውም እስራኤላዊ በረከት እንደሚያገኝ ጭምር ተናግሯል። በእርግጥም አሜስያስ መንግሥት በአሞጽ የስብከት ሥራ ላይ እገዳ እንዲጥል ለማድረግ እውነቱን አዛብቶና ቀናንሶ አቅርቧል።

18. አሜስያስ በተጠቀመባቸውና በዛሬ ጊዜ ቀሳውስት በሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

18 አሜስያስ የተጠቀመባቸው ዘዴዎች ዛሬ የይሖዋ ሕዝብ ጠላቶች ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ጋር በጣም እንደሚመሳሰሉ አስተውለሃል? አሜስያስ አሞጽን ዝም ለማሰኘት እንደሞከረ ሁሉ አንዳንድ የዘመናችን ቀሳውስት፣ ጳጳሳትና ፓትርያርኮች የይሖዋ አገልጋዮችን የስብከት ሥራ ለማስቆም ይሞክራሉ። አሜስያስ አሞጽን ከሃዲ እንደሆነ አድርጎ በሐሰት ከስሶት ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ አንዳንድ ቀሳውስት የይሖዋ ምሥክሮችን ለአገር ደኅንነት አስጊ ናቸው በማለት በሐሰት ይከስሳሉ። አሜስያስ አሞጽን ለማጥቃት ከንጉሡ እርዳታ እንደጠየቀ ሁሉ ቀሳውስቱም የይሖዋ ምሥክሮችን ለማሳደድ አብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ አጋሮቻቸውን ድጋፍ ይጠይቃሉ።

ተቃዋሚዎች የስብከት ሥራችንን ሊያስቆሙ አይችሉም

19, 20. አሞጽ፣ አሜስያስ ለሰነዘረበት ተቃውሞ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?

19 አሞጽ አሜስያስ ለሰነዘረበት ተቃውሞ ምን ምላሽ ሰጠ? በመጀመሪያ ካህኑን “‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር’ ነው የምትለኝ?” [NW] ሲል ጠየቀው። ደፋሩ የአምላክ ነቢይ አሞጽ፣ አሜስያስ ፈጽሞ መስማት የማይፈልገውን ነገር ምንም ሳያመነታ ተናገረ። (አሞጽ 7:16, 17) አሞጽ ምንም አልፈራም። ይህ ለሁላችንም እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! እኛም ዘመናዊ አሜስያሶች ጭካኔ የተሞላበት ስደት በሚቆሰቁሱባቸው አገሮች እንኳ ሳይቀር የአምላክን ቃል የመናገር ግዴታችንን ለድርድር አናቀርብም። እኛም እንደ አሞጽ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ብለን መልእክቱን ማወጃችንን እንቀጥላለን። ደግሞም ‘የይሖዋ እጅ’ ከእኛ ጋር ስለሆነ ተቃዋሚዎች የስብከት ሥራችንን ፈጽሞ ሊያስቆሙ አይችሉም።—የሐዋርያት ሥራ 11:19-21

20 አሜስያስ የሚሰነዝረው ማስፈራሪያ ከንቱ መሆኑን ማወቅ ይገባው ነበር። አሞጽ በምድር ላይ ማንም ቢሆን መልእክቱን እንዳያውጅ ሊከለክለው የማይችልበትን ምክንያት ቀደም ብሎም ቢሆን ገልጿል። የምንመረምረው ሦስተኛ ነጥብም ይህ ነው። በአሞጽ 3:3-8 ላይ እንደተገለጸው አሞጽ በርካታ ጥያቄዎችንና ምሳሌዎችን በመጠቀም እያንዳንዱ ክስተት መንስዔ እንዳለው አስረድቷል። ከዚያም “አንበሳ አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?” በማለት የምሳሌውን ትርጉም ገለጸ። በሌላ አባባል አሞጽ አድማጮቹን ‘አንበሳ ሲያገሳ ስትሰሙ መፍራታችሁ እንደማይቀር ሁሉ እኔም ይሖዋ ስበክ ብሎ ሲያዘኝ የአምላክን ቃል ከመስበክ ወደኋላ ማለት አልችልም’ ማለቱ ነበር። አሞጽን እንዲናገር የገፋፋው ለአምላክ ያለው ፍርሃት ማለትም ለእርሱ ያለው ጥልቅ አክብሮት ነበር።

21. አምላክ ምሥራቹን እንድንሰብክ ለሰጠን ትእዛዝ ምላሻችን ምንድን ነው?

21 እኛም ይሖዋ ስበኩ ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ሰምተናል። የምንሰጠው ምላሽ ምንድን ነው? እንደ አሞጽና እንደ መጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ እኛም ይሖዋ በሚሰጠን እርዳታ ቃሉን በድፍረት እንሰብካለን። (የሐዋርያት ሥራ 4:23-31) ተቃዋሚዎች የሚቆሰቁሱት ስደትም ሆነ የምንሰብክላቸው ሰዎች የሚያሳዩት ግድየለሽነት ዝም አያሰኘንም። በመላው ዓለም የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የአሞጽን የመሰለ ቅንዓት በማሳየት ምሥራቹን በድፍረት መስበካቸውን ለመቀጠል ይገፋፋሉ። ስለ መጪው የይሖዋ ፍርድ ሰዎችን የማስጠንቀቅ ኃላፊነት ተጥሎብናል። ይህ ፍርድ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እናገኛለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• አሞጽ አምላክ የሰጠውን ተልእኮ የፈጸመው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ነው?

• እንደ አሞጽ ሁሉ እኛም መስበክ ያለብን ምንድን ነው?

• የስብከቱን ሥራችንን ማከናወን ያለብን በምን ዓይነት ዝንባሌ ነው?

• ተቃዋሚዎች የምሥክርነቱን ሥራችንን ማስቆም የማይችሉት ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ የባሉጥ ፍሬ የመውጋት ሥራ የነበረውን አሞጽን ፍርዱን እንዲያውጅ መርጦታል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ አሞጽ ሁሉ አንተም የይሖዋን መልእክት በድፍረት እያወጅህ ነው?