በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት አጋንንት የት ይሆናሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አይሰጥም። ሆኖም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት አጋንንት የት ሊሆኑ እንደሚችሉ አሳማኝ የሆነ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን።

ሐዋርያው ዮሐንስ በዚህ የሺህ ዓመት ግዛት መጀመሪያና ማብቂያ ላይ ስለሚፈጸሙት ነገሮች የተመለከተውን ራእይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የጥልቁን መክፈቻና ትልቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። እርሱም የጥንቱን እባብ፣ ዘንዶውን፣ ማለትም ዲያብሎስን ወይም ሰይጣንን ይዞ ሺህ ዓመት አሰረው። ሺሁ ዓመትም እስኪፈጸምም ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቦችን እንዳያስት ወደ ጥልቁ ጣለው፤ ዘጋውም፤ በእርሱም ላይ ማኅተም አደረገበት። ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ሊፈታ ይገባዋል።” (ራእይ 20:1-3) እዚህ ጥቅስ ላይ በጥልቁ ውስጥ እንደሚታሰርም ሆነ ከሺህ ዓመት በኋላ ለጥቂት ጊዜ እንደሚፈታ የተገለጸው ሰይጣን ብቻ ነው። ስለ አጋንንቱ ምንም የተገለጸ ነገር ባይኖርም የጥልቁ መክፈቻ ያለው መልአክ ማለትም ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎስን ይዞ ወደ ጥልቁ ሲጥለው በአጋንንቱም ላይ እንዲሁ ያደርጋል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል።—ራእይ 9:11

ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በሰማይ ሲነግሥ በሰይጣንም ሆነ በአጋንንቱ ላይ ከባድ እርምጃ ወስዷል። ራእይ 12:7-9 እንዲህ ይላል:- “በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም [አጋንንት] መልሰው ተዋጓቸው፤ ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ። ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።” ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰይጣንና አጋንንቱ ከምድር አካባቢ እንዳያልፉ ገደብ ተደርጎባቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ምድርን ከሰይጣን መጥፎ ተጽዕኖ ነጻ ለማድረግ ሲል እርሱን በጥልቁ ውስጥ በመጣል እንቅስቃሴውን የበለጠ ሲገድበው በአጋንንትም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ ማሰብ እንችላለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የምናገኘውን የመጀመሪያውን ትንቢትም እንመልከት። አምላክ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር:- “በአንተና [በሰይጣንና] በሴቲቱ [በሰማይ ባለችው የይሖዋ ድርጅት]፣ በዘርህና [በሰይጣን ዘርና] በዘሯ [በኢየሱስ ክርስቶስ] መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:15) የእባቡ ራስ መቀጥቀጥ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ሰይጣን በጥልቁ ውስጥ መታሰሩንም ይጨምራል። የእባቡን ራስ በሚቀጠቅጠው አካልና በሰይጣን ዘር መካከል ጠላትነት እንደሚኖር ትንቢቱ አክሎ ይናገራል። ይህ የሰይጣን ዘር ወይም ድርጅት ከሰብዓዊ እይታ ውጭ የሆኑትን ክፉ መላእክት ወይም አጋንንት ያቀፈ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ሰይጣንን ወደ ጥልቁ ሲጥለው አጋንንትንም አስሮ ወደ ጥልቁ ይጥላቸዋል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይሆናል። ክፉ መናፍስት ጥልቁን በጣም መፍራታቸው ወደፊት በዚህ ቦታ እንደሚታሰሩ የሚያውቁ መሆናቸውን ያመለክታል።—ሉቃስ 8:31

ይሁን እንጂ በራእይ 20:1-3 ላይ አጋንንት ያልተጠቀሱት ከሚታየው የሰይጣን ዘር ክፍል ጋር በአርማጌዶን ስለጠፉ ሊሆን ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሊሆን እንደማይችል ያሳያል። ስለ ሰይጣን የመጨረሻ ዕጣ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ያሳታቸው ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ።” (ራእይ 20:10) አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ፖለቲካዊ ድርጅቶች ሲሆኑ በዓይን የሚታየው የሰይጣን ድርጅት ክፍል ናቸው። (ራእይ 13:1, 2, 11-14፤ 16:13, 14) የአምላክ መንግሥት በአርማጌዶን የዓለምን መንግሥታት በሙሉ ጠራርጎ በሚያጠፋበት ጊዜ እነዚህ ፖለቲካዊ ድርጅቶችም ይጠፋሉ። (ዳንኤል 2:44) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ስለተዘጋጀው የዘላለም እሳት’ ይናገራል። (ማቴዎስ 25:41) ሰይጣንና አጋንንቱ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ‘የእሳትና የዲን ባሕር’ ይጣላሉ፤ ይህም ሲባል እነርሱም ለዘላለም ይጠፋሉ ማለት ነው። የሰይጣን ዘር ክፍል የሆኑት እነዚህ በዓይን የማይታዩ ኃያል አካላት በአርማጌዶን የሚጠፉ ቢሆን ኖሮ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ምሳሌያዊ በሆነው ባሕር ውስጥ እንዳሉ ሲገለጽ እነርሱም ይጠቀሱ ነበር። በራእይ 20:10 ላይ አጋንንት ከአውሬውና ከሐሰተኛው ነቢይ ጋር አለመጠቀሳቸው በአርማጌዶን እንዳልጠፉ ያሳያል።

አጋንንት ወደ ጥልቁ እንደተጣሉ በቀጥታ ስላልተገለጸ ከጥልቁ እንደሚፈቱም መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ይሁን እንጂ መጨረሻቸው ከዲያብሎስ የተለየ አይሆንም። ዲያብሎስ ከጥልቁ ሲለቀቅ አጋንንትም አብረውት ይፈታሉ፤ ከዚያም በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ለሰው ዘር በሚቀርበው የመጨረሻ ፈተና ከእርሱ ጋር ከተባበሩ በኋላ ወደ እሳቱ ባሕር ይጣሉና የዘላለም ጥፋት ይደርስባቸዋል።—ራእይ 20:7-9

እንግዲያው ራእይ 20:1-3 ምንም እንቅስቃሴ ወደማይደረግበት ጥልቅ ተይዞ እንደሚጣል የሚናገረው ስለ ሰይጣን ብቻ ቢሆንም መላእክቱም እንደሚታሰሩና ወደ ጥልቁ እንደሚጣሉ መደምደማችን ምክንያታዊ ነው። ሰይጣንም ሆነ አጋንንታዊ ጭፍሮቹ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት አምላክ ምድርን ወደ ገነትነት ለመለወጥና የሰውን ዘር ወደ ፍጽምና ለማድረስ ያለውን ዓላማ እንዲያደናቅፉ አይፈቀድላቸውም።