በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሰው ልጆች ብቻ የተሠጠ ችሎታ

ለሰው ልጆች ብቻ የተሠጠ ችሎታ

ለሰው ልጆች ብቻ የተሠጠ ችሎታ

ጆዲ የሞቱ ሰዎች ንብረት አሻሻጭ ነው። አንዲት ሴት የሟች እህቷን ንብረቶች በመልክ በመልኩ ለይታ መሸጥ እንድትችል እየረዳት ሳለ በአንድ አሮጌ ምድጃ አካባቢ የአሣ ማጥመጃ ዕቃዎች የሚቀመጡባቸው ሁለት የቆዩ ሣጥኖች አገኘ። ከሣጥኖቹ አንደኛውን ሲከፍት በተመለከተው ነገር በጣም ከመገረሙ የተነሳ ዓይኖቹን ማመን አልቻለም። በሣጥኑ ውስጥ በድምሩ 82,000 የአሜሪካ ዶላር የሚያህሉ ረብጣ የመቶ ዶላር ኖቶች ተቀምጠዋል። ጆዲ ገንዘቡን ሲያገኝ ማንም አላየውም። ታዲያ ምን ያድርግ? ምንም ሳይናገር ሣጥኑን ይውሰደው ወይስ ስላገኘው ገንዘብ ለደንበኛው ይንገራት?

ጆዲ ያጋጠመው ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ የሰው ልጆችን ከእንስሳት የተለዩ ከሚያደርጓቸው ባሕርያት አንዱን ጎላ አድርጎ ያሳያል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ “እኛ የሰው ልጆች ካሉን ልዩ ባሕርያት አንዱ ማድረግ ስለሚገባን ወይም ስለማይገባን ነገሮች ማሰባችን ነው” ይላል። አንድ የተራበ ውሻ ጠረጴዛ ላይ ሙዳ ሥጋ ተቀምጦ ቢመለከት መብላቴ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም ብሎ አያስብም። በሌላ በኩል ጆዲ የሚወስደው እርምጃ ትክክል መሆን አለመሆኑን የማመዛዘን ችሎታ አለው። ገንዘቡን ቢወስድ ሥርቆት ነው፤ ሌባ ተብሎ የመያዝ አጋጣሚው ግን ጠባብ ነው። በእርግጥ ገንዘቡ የእርሱ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ደንበኛው በዚያ ቦታ ገንዘብ መኖሩንም አታውቅም። ከዚህም በላይ ጆዲ ገንዘቡን ለሴትየዋ ቢሰጣት በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ አብዛኞቹ ሰዎች እንደ ሞኝ ይቆጥሩታል።

አንተ በጆዲ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ ሕይወትህን በምትመራበት የሥነ ምግባር መሥፈርት ላይ የተመሠረተ ይሆናል።

ሥነ ምግባር ምንድን ነው?

“ሥነ ምግባር” የሚለው ቃል “የሰውን ተግባር አስመልክቶ የጥሩና የመጥፎ፣ መሆን ያለበትና የሌለበት ወዘተ ሳይንስ” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። (ሐበሻ አማርኛ መዝገበ ቃላት) ኤሪክ ኢስተን የተባሉ ደራሲ እንደተናገሩት “ሥነ ምግባር” ተብሎ የተተረጎመው “ኤቲክስ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ባህልና ወግ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ” ያመለክታል።

በጥቅሉ ሲታይ ለበርካታ ዘመናት ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመሩባቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚወስነው ሃይማኖት ነበር። በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድር ነበር። ሆኖም በዓለም ዙሪያ ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ሰዎች ሃይማኖታዊ መሥፈርቶች ተግባራዊ ሊሆኑ እንደማይችሉና የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መመሪያዎችም ጊዜ እንዳለፈባቸው ይሰማቸዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች የትኛውን የሥነ ምግባር ደንብ እየተከተሉ ነው? ሥነ ምግባር በንግዱ ዓለም (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ “ከዚህ ቀደም ሃይማኖት ይዞት የነበረው ቦታ . . . በዓለማዊ እውቀት ተተክቷል” ይላል። ብዙ ሰዎች ሥነ ምግባራዊ መመሪያ ለማግኘት ወደ ሃይማኖት ዞር ከማለት ይልቅ ከግብረ ገብነት ጋር የተያያዘ ጥናት የሚያካሂዱ ባለሞያዎች ወደሚሰጡት ሐሳብ ያዘነብላሉ። ባዮኤቲክስ ተብሎ በሚጠራው የሕክምና ሥነ ምግባር መስክ ባለሞያ የሆኑት ፖል መክኒል እንዲህ ብለዋል:- “የግብረ ገብ ባለሞያዎች ቀሳውስት ያከናውኑት የነበረውን ሥራ እየሠሩ ይመስለኛል . . . ሰዎች በሃይማኖታዊ መሥፈርቶች መመራታቸው ቀርቶ ሰብዓዊ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን እየተከተሉ ነው።”

ውሳኔ የሚጠይቅ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥምህ ትክክል የሆነውን ከስህተቱ የምትለየው በምን መሥፈርት ነው? የምትከተለው የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ነው ወይስ የራስህን?