በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰሎሞን ስለምናነባቸው ነገሮች የሰጠው ጥበብ ያዘለ ምክር

ሰሎሞን ስለምናነባቸው ነገሮች የሰጠው ጥበብ ያዘለ ምክር

ሰሎሞን ስለምናነባቸው ነገሮች የሰጠው ጥበብ ያዘለ ምክር

“ብዙ መጻሕፍትን መጻፍ ማብቂያ የለውም፤ ብዙ ማጥናትም ሰውነትን ያደክማል።” (መክብብ 12:12) የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰሎሞን ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት እንዲህ ብሎ ሲጽፍ ማንበብ ጥቅም እንደሌለው መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መራጭ የመሆንን አስፈላጊነት መግለጹ ነበር። በዓለም ላይ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ጽሑፎች በሚታተሙበት በዚህ ዘመን ይህ ምክር በጣም አስፈላጊ ነው።

ሰሎሞን የገለጻቸው ‘ብዙ መጻሕፍት’ ጠቃሚና መንፈስን የሚያድሱ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህን መጻሕፍት ማንበቡ ዘላቂ ጥቅም ከማስገኘት ይልቅ “ሰውነትን ያደክማል” በማለት የተናገረውም ለዚህ ነው።

ይሁን እንጂ ሰሎሞን ለአንባቢው የሚበጅ አስተማማኝና ጠቃሚ መመሪያ የያዙ መጻሕፍት የሉም ማለቱ ነበር? በፍጹም፤ እርሱ ራሱ “የጠቢባን ቃላት እንደ ሹል የከብት መንጃ ናቸው፤ የተሰበሰቡ አባባሎቹም እጅግ ተቀብቅበው እንደ ገቡ ችንካሮች ሲሆኑ፣ ከአንድ እረኛ የተሰጡ ናቸው” በማለት ጽፏል። (መክብብ 12:11) በእርግጥም እንደ “ሹል የከብት መንጃ” ጠቃሚ እርዳታ የሚያበረክቱ መጻሕፍት አሉ። እንደዚህ ያሉት ጽሑፎች አንድን ሰው በትክክለኛው መንገድ እንዲሄድ የሚገፋፉት ከመሆኑም በላይ “ተቀብቅበው እንደ ገቡ ችንካሮች” አቋሙን ያጠናክሩለታል እንዲሁም ሚዛኑን እንዳይስት ይረዱታል።

እንደዚህ ያሉትን ጥበብ ያዘሉ ቃላት ከየት ማግኘት እንችላለን? ሰሎሞን እንደገለጸው እንደነዚህ ያሉት ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው መመሪያዎች የሚገኙት ከአንዱ እረኛ ከይሖዋ ነው። (መዝሙር 23:1) ስለዚህ ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ ለማግኘት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ መጽሐፍ የለም። አንድ ሰው ይህንን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ አዘውትሮ ማንበቡ “ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ” ያደርገዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17