በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ መታመን

በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ መታመን

የሕይወት ታሪክ

በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ መታመን

አና ዴንትስ ተርፐን እንደተናገረችው

እናቴ ፈገግ ብላ “‘ለምን’ የሚለው ቃል መቼም ከአፍሽ አይጠፋም!” አለችኝ። እንደ ማንኛውም ልጅ ሁሉ ወላጆቼ ላይ የጥያቄ ናዳ አዥጎደጉድባቸው ነበር። እናቴም ሆነች አባቴ ጥያቄ ታበዣለሽ ብለው በፍጹም ተቆጥተውኝ አያውቁም። እንዲያውም በተቃራኒው ነገሮችን እንዳገናዝብና በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነው ኅሊናዬ ተጠቅሜ ውሳኔ እንዳደርግ አስተምረውኛል። ይህ ለቀሪው ሕይወቴ የሚጠቅም ግሩም ማሠልጠኛ ነበር! የ14 ዓመት ልጅ እያለሁ አንድ ቀን ናዚዎች ወላጆቼን ከእኔ ነጥለው ከወሰዷቸው በኋላ ዳግም አላየኋቸውም።

አባቴ ኦስካር ዴንትስ እና እናቴ አና ማሪያ በስዊስ ጠረፍ በምትገኘው ሎራክ በተባለች የጀርመን ከተማ ይኖሩ ነበር። ወጣት በነበሩበት ጊዜ በፖለቲካ ጉዳዮች ይካፈሉ የነበረ ሲሆን በሕዝብ ዘንድ ታዋቂና የተከበሩ ነበሩ። በ1922 ከተጋቡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ለፖለቲካ ያላቸው አመለካከት ከመቀየሩም በላይ በወደፊት ግቦቻቸው ላይ ማስተካከያ አደረጉ። እናቴ ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ከሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች፤ በጥናቷም ላይ የአምላክ መንግሥት ለምድር ሰላም እንደሚያመጣ መማሯ በጣም አስደሰታት። ብዙም ሳይቆይ አባቴ ከእናቴ ጋር አብሮ ማጥናት ከመጀመሩም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። በዛው ዓመት አባቴ የአምላክ በገና የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መጽሐፍ ለእናቴ የገና ስጦታ አድርጎ አበረከተላት። እኔ መጋቢት 25, 1923 የተወለድኩ ሲሆን ወላጆቼ ሌላ ልጅ አልወለዱም።

በቤተሰብ ሆነን በጣም አስደሳች ጊዜ እናሳልፍ ነበር፤ በበጋ ወራት ብላክ ፎረስት በተባለ እረጭ ያለ ጫካ ውስጥ የምናደርገው የእግር ጉዞ እንዲሁም እናቴ እንዴት የቤት አያያዝ ታስተምረኝ እንደነበረ ትዝ ይለኛል! እናቴ ወጥ ቤት ውስጥ ቆማ ምግብ ማብሰል ስታስተምረኝ አሁን ድረስ በዓይነ ኅሊናዬ ትታየኛለች። ከምንም ነገር በላይ ወላጆቼ ይሖዋ አምላክን እንድወድና በእርሱ እንድታመን አስተምረውኛል።

በጉባኤያችን 40 የሚያህሉ ትጉህ የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪዎች ነበሩ። ወላጆቼ ባገኙት አጋጣሚ ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ ልዩ ተሰጥኦ ነበራቸው። ቀደም ሲል በኅብረተሰቡ ውስጥ ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ከሌሎች ጋር በቀላሉ እንዲቀራረቡ አስችሏቸዋል፤ ሰዎችም በደንብ ያዳምጧቸው ነበር። ሰባት ዓመት ሲሞላኝ ከቤት ወደ ቤት የማገልገል ፍላጎት አደረብኝ። አገልግሎት በጀመርኩበት የመጀመሪያ ቀን አብራኝ ታገለግል የነበረችው እህት ጥቂት ጽሑፎች ሰጠችኝና አንድ ቤት አሳይታ “እስቲ ሂጂና ጽሑፎቹን ይፈልጉ እንደሆነ ጠይቂያቸው” አለችኝ። በ1931 በስዊዘርላንድ፣ ባዝል ከተማ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ባደረጉት የአውራጃ ስብሰባ ላይ በተገኘንበት ጊዜ ወላጆቼ ተጠመቁ።

ከብጥብጥ ወደ አምባገነናዊ አገዛዝ

በዚያን ጊዜ ጀርመን ውስጥ ብጥብጥ ነግሦ የነበረ ሲሆን በርካታ የፖለቲካ አንጃዎች በጎዳናዎች ላይ ግጭት ይፈጥሩ ነበር። አንድ ቀን ምሽት ከጎረቤት ጩኸት ሰምቼ ከእንቅልፌ ነቃሁ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወንዶች ወንድማቸው ከእነርሱ የተለየ ፖለቲካዊ አመለካከት ስላለው ብቻ በመንሽ ወግተው ገደሉት። በአይሁዳውያን ላይ ይደርስ የነበረው ጥላቻም በጣም ከፍቶ ነበር። አብራኝ የምትማር አንዲት ልጅ አይሁዳዊ በመሆኗ የክፍሉ ጠርዝ ላይ ብቻዋን እንድትቆም ይደረግ ነበር። መጠላት ምን ዓይነት ስሜት እንደሚያሳድር በራሴ ላይ ደርሶ እንደማየው በወቅቱ ባላውቅም ልጅቷ በጣም ታሳዝነኝ ነበር።

ጥር 30, 1933 አዶልፍ ሂትለር የጀርመን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ። ከእኛ ቤት ቀጥሎ ካሉት ሁለት ሕንጻዎች አልፎ በሚገኘው የከተማው ማዘጋጃ ቤት ላይ ናዚዎች የስዋስቲካን ባንዲራ በድል አድራጊነት ስሜት ሲሰቅሉ ተመለከትን። ሂትለር ሥልጣን በመያዙ በደስታ የፈነደቁት አስተማሪያችን “ሃይል ሂትለር!” ብለን ሰላምታ እንድንሰጥ አስተማሩን። ያን ዕለት ከሰዓት በኋላ ስለ ሁኔታው ለአባቴ ስነግረው በጣም ተጨነቀ። ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “አነጋገሩ ምንም ደስ አላለኝም፤ ምክንያቱም ‘ሃይል’ ማለት መዳን ማለት ነው። ስለዚህ ‘ሃይል ሂትለር’ ስንል የሚያድነን ይሖዋ ሳይሆን ሂትለር ነው ማለታችን ነው። ይሄ ደግሞ ትክክል አይደለም፤ ነገር ግን ምን ማድረግ እንዳለብሽ ራስሽ ወስኚ።”

አብረውኝ የሚማሩት ልጆች “ሃይል ሂትለር” በማለት ሰላምታ መስጠት እንደማልፈልግ ሲያውቁ አገለሉኝ። እንዲያውም አንዳንድ ወንዶች አስተማሪ ሳያያቸው ይመቱኝ ነበር። ቀስ በቀስ እንዲህ ማድረጋቸውን ቢያቆሙም ጓደኞቼ አባቶቻቸው አደገኛ መሆኔን በመግለጽ ከእኔ ጋር እንዳይጫወቱ እንደከለከሏቸው ነገሩኝ።

ናዚዎች በጀርመን ሥልጣን ከተቆናጠጡ ከሁለት ወራት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ለአገሪቱ አደገኛ ናቸው በማለት እገዳ ጣሉብን። የሂትለር ወታደሮች በማግደቡርግ የሚገኘውን ቤቴል ዘጉ እንዲሁም ስብሰባ እንዳናደርግ ታገድን። ሆኖም መኖሪያችን በጠረፍ አቅራቢያ ስለነበር አባቴ ወደ ባዝል፣ ስዊዘርላንድ አቋርጠን ለመሄድ የሚያስችል ፈቃድ አወጣና እሁድ እሁድ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርን። ብዙ ጊዜ አባቴ በጀርመን የሚገኙ ወንድሞቻችን ከፊታቸው የተጋረጠባቸውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችላቸው ብርታት እንዲያገኙ ይህን የመሰለ መንፈሳዊ ምግብ እንዲመገቡ ይመኝ ነበር።

አደገኛ ጉዞዎች

በማግደቡርግ ያለው ቢሮ ከተዘጋ በኋላ ቀድሞ የቤቴል ቤተሰብ አባል የነበረው ዩልየስ ሪፈል፣ በድብቅ ይከናወን የነበረውን የስብከት ሥራ ለማደራጀት ወደ ትውልድ መንደሩ ሎራክ መጣ። ወዲያውኑ አባቴ ሊረዳው እንደሚፈልግ ገለጸ። አባቴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከስዊዘርላንድ ወደ ጀርመን በማስገባት ለመርዳት እንደተስማማና ነገሩ በጣም አደገኛ በመሆኑ ከታወቀበት እንደሚታሰር ለእኔና ለእናቴ ነገረን። ጉዳዩ ለእኛም ቢሆን አስጊ ስለሚሆን እንድናግዘው አልገፋፋንም። እናቴም ወዲያው “እኔም እረዳሃለሁ” አለችውና ሁለቱም ያዩኝ ጀመር፤ ከዚያም “እኔም ከጎንህ ነኝ” አልኩት።

እናቴ በመጠበቂያ ግንብ ልክ የሚሆን የዳንቴል ቦርሳ ሠራች። ከዚያም ጽሑፉን በቦርሳው ውስጥ ትከትና ማስገቢያውን በኪሮሽ እየጠለፈች ትዘጋዋለች። እንዲሁም በአባቴ ልብሶች ውስጥ የምስጢር ኪሶች የሠራችለት ሲሆን ለእኔና ለእርሷ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያግዙ ትንንሽ ጽሑፎችን ደብቀን ለመያዝ የሚያስችሉ ሁለት መቀነቶች ሠራች። የምንደብቃቸውን እነዚህን ውድ ሀብቶች በሰላም ወደ ቤታችን ይዘን በገባን ቁጥር በደስታ ይሖዋን እናመሰግናለን። ከዚያም በኮርኒስ ውስጥ እንደብቃቸዋለን።

መጀመሪያ ናዚዎች ምንም ስላልጠረጠሩ ጥያቄ አቅርበውልንም ሆነ ቤታችንን ፈትሸው አያውቁም። የሆነ ሆኖ አንድ ችግር ቢፈጠር መንፈሳዊ ወንድሞቻችንን ለማስጠንቀቅ 4711ን ምስጢራዊ ቁጥር አድርገን ሰየምን፤ ይህ ቁጥር ኮሎኝ የሚባል ታዋቂ ሽቶ መለያ ስም ነው። ወንድሞች ወደ ቤታችን መምጣታቸው ችግር የሚያስከትልባቸው ከሆነ፣ በሆነ መንገድ ይህን ቁጥር በመጠቀም እናስጠነቅቃቸዋለን። በተጨማሪም ወደ ሕንጻው ከመግባታቸው በፊት የሳሎን መስኮታችንን እንዲያዩ አባቴ ነገራቸው። በስተ ግራ ያለው መስኮት ከተከፈተ አንድ ችግር አለ ማለት ስለነበር መመለስ አለባቸው።

በ1936 እና 1937 ጌስታፖዎች (የሂትለር የምስጢር ፖሊሶች) የይሖዋ ምሥክሮችን እያፈሱ ወደ እስር ቤትና ወደ ማጎሪያ ካምፖች ወሰዷቸው፤ ወንድሞችና እህቶች በእነዚህ ቦታዎች ከባድ ስቃይ ደርሶባቸዋል። በበርን፣ ስዊዘርላንድ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በካምፖቹ ውስጥ ናዚዎች የሚፈጽሙትን ወንጀል የሚያጋልጥ ክሮይትሱግ ጌይገን ዳስ ክርስተንቱም (በክርስትና ላይ የተከፈተ ጦርነት) የሚል መጽሐፍ ለማውጣት ከካምፕ እንደምንም የሚገኙትን ጨምሮ የተለያዩ ዘገባዎችን ማጠናቀር ጀመረ። እኛም እነዚህን ዘገባዎች ጠረፍ እያቋረጥን በምስጢር ወደ ባዝል ይዞ የመሄዱን አደገኛ ሥራ ተያያዝነው። ናዚዎች እነዚህን ሕገ ወጥ ሰነዶች ይዘን ቢያገኙን ወዲያውኑ እስር ቤት ይጨምሩን ነበር። ወንድሞቻችን የሚደርስባቸውን ስቃይ ሳነብ አለቅስ የነበረ ቢሆንም አልፈራሁም። እውነተኛ ወዳጆቼ የሆኑት ይሖዋና ወላጆቼ እንደሚጠብቁኝ እተማመን ነበር።

በ14 ዓመቴ ትምህርቴን አጠናቀቅኩና በአንድ የእቃ መሸጫ ሱቅ ውስጥ በጸሐፊነት ተቀጠርኩ። አባቴ አብዛኛውን ጊዜ ሥራ በማይገባበት ዕለት ማለትም ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ወይም እሁድ መልእክት ይዘን ወደ በርን እንጓዛለን። በአማካይ በየሁለት ሳምንቱ እንሄዳለን ለማለት ይቻላል። ጠረፍ ጠባቂዎቹ ልክ እንደ ሌሎቹ ቤተሰቦች የሳምንቱን መጨረሻ በመዝናናት ለማሳለፍ የምንጓዝ ስለሚመስላቸው ለአራት ዓመታት ያህል አስቁመውንም ሆነ ፈትሸውን አያውቁም ነበር። የካቲት 1938 ግን ሁኔታው ተለወጠ።

ታወቀብን!

በባዝል አቅራቢያ ባለ ጽሑፍ በምንረከብበት ቦታ ስንደርስ አባቴ ጽሑፎች ተከምረው ሲያይ ፊቱ እንዴት እንደተለዋወጠ መቼም አልረሳውም። እንደ እኛው ጽሑፍ የሚያሳልፍ ሌላ ቤተሰብ ተይዞ ስለነበረ ተጨማሪ መጽሐፎችን መያዝ ነበረብን። ጠረፍ ላይ ስንደርስ አንድ የጉምሩክ ባለ ሥልጣን ጠረጠረንና እንድንፈተሽ አዘዘ። መጽሐፎቹን ሲያገኝ ሽጉጥ ደግኖብን ወደ አንድ የፖሊስ መኪና ወሰደን። የፖሊስ መኮንኖቹ ይዘውን እየተጓዙ እያለ አባቴ እጄን ጭምድድ አድርጎ በመያዝ በሹክሹክታ “ከሐዲ እንዳትሆኚ። የማንንም ስም እንዳትሰጪ!” አለኝ። እኔም “የማንንም ስም አልሰጥም” ብዬ መልስ ሰጠሁት። ሎራክ ስንደርስ ውድ አባቴን ወሰዱት። የእስር ቤቱ በር ከተዘጋበት በኋላ በድጋሚ አላየሁትም።

አራት ጌስታፖዎች የወንድሞችንና የእህቶችን ስምና አድራሻ እንድነግራቸው ለአራት ሰዓታት ያህል ምርመራ አደረጉብኝ። የጠየቁኝን ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆኔ አንዱ ባለሥልጣን በቁጣ “በሌላ ዘዴ እናውጣጣሻለን!” በማለት አስፈራራኝ። አንዲትም ነገር አልነገርኳቸውም። እኔንና እናቴን ወደ ቤት ይዘውን ሄዱና ለመጀመሪያ ጊዜ ቤታችንን ፈተሹ። ከዚያም እናቴን ወደ ማረፊያ ቤት ወሰዷትና እኔን አክስቴ ጋር ይዘውኝ ሄዱ፤ ነገር ግን እርሷም የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች አላወቁም ነበር። ሥራ እንድሠራ የተፈቀደልኝ ቢሆንም አራት ጌስታፖዎች ከቤቱ ፊት ለፊት መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው የማደርገውን እያንዳንዱን ነገር ይከታተሉ ነበር፤ ሌላ ፖሊስ ደግሞ የእግር መንገዱ ላይ ወዲያ ወዲህ እያለ አካባቢውን ይጠብቅ ነበር።

ከጥቂት ቀናት በኋላ በምሳ ሰዓት ከቤት ወጣ ስል አንዲት ወጣት እህት በብስክሌት ወደ እኔ ስትመጣ አየኋት። ቀረብ ስትለኝ አንዲት ብጫቂ ወረቀት ልትወረውርልኝ እንደሆነ ገባኝ። ወረቀቷን ቀለብኩና የምስጢር ፖሊሶቹ አይተውኝ እንደሆነ ለማጣራት ዞር ብዬ ተመለከትኳቸው። የሚገርመው በዚያች ቅጽበት ሁሉም ወደ ላይ አንጋጠው እየተሳሳቁ ነበር!

እህት የሰጠችኝ ማስታወሻ ቀትር ላይ ወደ ወላጆቿ ቤት እንድሄድ የሚገልጽ ነበር። ነገር ግን የምስጢር ፖሊሶቹ እየተከታተሉኝ ስለነበር ወደዚያ ብሄድ እነርሱን አሳልፎ መስጠት ይሆንብኛል ብዬ ፈራሁ። አራቱን ጌስታፖዎችና መንገዱ ላይ ወዲያ ወዲህ የሚለውን ፖሊስ ተመለከትኩና ምን እንደማደርግ ግራ ስለገባኝ አጥብቄ ይሖዋ እንዲረዳኝ ለመንኩት። በድንገት መንገድ ላይ የነበረው ፖሊስ ወደ ምስጢር ፖሊሶቹ ሄዶ አነጋገራቸውና መኪናው ላይ ወጣ፤ ከዚያም መኪናቸውን አስነስተው ሄዱ!

ወዲያውኑ አክስቴ የመንገዱን ዳር ይዛ ስትመጣ አየኋት። በዚያ ጊዜ ቀትር አልፎ ነበር። ማስታወሻውን ካነበበች በኋላ ወንድሞች ወደ ስዊዘርላንድ ሊወስዱኝ እንዳሰቡ ስለጠረጠረች ወደተጠራሁበት ቤት እንድንሄድ ወሰነች። እንደደረስንም ባለቤቶቹ ሃይንሪሽ ራይፍ ከተባለ ከዚያ በፊት ከማላውቀው ሰው ጋር አስተዋወቁኝ። በሰላም መምጣት በመቻሌ እንደተደሰተ ከገለጸልኝ በኋላ ወደ ስዊዘርላንድ በድብቅ ይዞኝ ለመሄድ እንደመጣና በግማሽ ሰዓት ውስጥ በአንድ ጫካ ውስጥ እንድንገናኝ ነገረኝ።

የስደት ኑሮ

ወላጆቼን ጥሎ የመሄዱ ጉዳይ በጣም አሳዝኖኝ ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ ከወንድም ራይፍ ጋር በቀጠሯችን ቦታ ተገናኘን። ሁሉም ነገር በፍጥነት ተከናወነ። ለጥቂት ጊዜያት በስጋት ከተጓዝን በኋላ ከቱሪስቶች ጋር ተቀላቀልንና የስዊስን ጠረፍ በሰላም አቋረጥን።

በርን በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ስደርስ በዚያ የሚገኙ ወንድሞች ወደ ስዊዘርላንድ እንድመጣ የሚያስችሉኝን ነገሮች እንዳመቻቹልኝ ተረዳሁ። በደግነት የምኖርበትን ቦታ አዘጋጁልኝ። ከዚያም በጣም የምወደውን የወጥ ቤት ሥራ እንድሠራ ተመደብኩ። ሆኖም የሁለት ዓመት እስር የተበየነባቸው ወላጆቼ ምን እንደሚያጋጥማቸው ስለማላውቅ እዚያ መኖሩ በጣም ከብዶኝ ነበር! አንዳንድ ጊዜ ሐዘኑና ሐሳቡ ከአቅሜ በላይ ስለሚሆንብኝ መታጠቢያ ቤት እገባና በሩን ከውስጥ ቆልፌ ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ። ነገር ግን ከወላጆቼ ጋር ያለማቋረጥ ደብዳቤ እጻጻፍ ነበር፤ እነርሱም ከታማኝነቴ ፍንክች እንዳልል ያበረታቱኝ ነበር።

ወላጆቼ ጥሩ የእምነት ምሳሌ ስለሆኑኝ ራሴን ለይሖዋ በመወሰን ሐምሌ 25, 1938 ተጠመቅኩ። በቤቴል አንድ ዓመት ከቆየሁ በኋላ የስዊስ ቅርንጫፍ ቢሮ የገዛው እርሻ ላይ ለመሥራት ወደ ሻኔላ ተዛወርኩ፤ በዚያ ቦታ ለቤቴል ቤተሰብና በስደት ሸሽተው ለመጡ ወንድሞች የሚሆን ምግብ ይመረት ነበር።

ወላጆቼ የሁለት ዓመት ፍርዳቸውን በ1940 ካጠናቀቁ በኋላ እምነታቸውን ከካዱ ነጻ እንደሚወጡ ናዚዎች ገለጹላቸው። ሆኖም እምነታቸውን ለመተው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ እናቴ ወደ ዳካው አባቴ ደግሞ ወደ ራቬንስብሩክ ማጎሪያ ካምፖች ተወሰዱ። በ1941 የክረምት ወራት ማብቂያ ላይ እናቴና ሌሎች በካምፑ ውስጥ የሚገኙ እህቶች ከውትድርና አገልግሎት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሥራዎች ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ቀዝቃዛ ቦታ ላይ ለ3 ቀንና ለ3 ሌሊት እንዲቆሙ ተደረገ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ የማይረባ ምግብ እየተሰጣቸው በጨለማ ክፍል ውስጥ ለ40 ቀናት ታሰሩ። ከዚያም በላይ ይደበደቡ ነበር። እናቴ በጭካኔ ከተደበደበች ከሦስት ሳምንት በኋላ ጥር 31, 1942 ሕይወቷ አለፈ።

አባቴ ከዳካው ካምፕ ኦስትሪያ ወደሚገኘው ማውታውሰን ተዛወረ። ናዚዎች በዚህ ካምፕ ውስጥ ያሉትን እስረኞች በማስራብና በጣም ከባድ ሥራ በማሠራት በዘዴ ይገድሏቸው ነበር። አባቴን ግን እናቴ በሞተች በስድስተኛው ወር የሕክምና መሞከሪያ በማድረግ ለየት ባለ መንገድ ገደሉት። የካምፑ ዶክተሮች እስረኞችን ልክ እንደ ሕክምና መሞከሪያ አይጦች በሳምባ ነቀርሳ በሽታ ይበክሏቸዋል። ቀጥሎም የመርዝ መርፌ ልባቸው ላይ በመውጋት ይገድሏቸዋል። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ መዝገብ ላይ የሰፈረው ግን አባቴ “የልቡ ጡንቻ ደካማ በመሆኑ” ምክንያት እንደሞተ የሚናገር መግለጫ ነው። የ43 ዓመቱ አባቴ በጭካኔ መገደሉን የሰማሁት ከወራት በኋላ ነበር። እስከ አሁን ድረስ ውድ ወላጆቼን ባስታወስኩ ቁጥር አነባለሁ። ሆኖም በሰማይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ወላጆቼ በይሖዋ እቅፍ ውስጥ መሆናቸውን ማወቄ፣ በሞቱበት ጊዜም ሆነ አሁን እንድጽናና አስችሎኛል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኒው ዮርክ በሚገኘው ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 11ኛ ክፍል የመሠልጠን መብት አገኘሁ። ለአምስት ወራት ቅዱሳን ጽሑፎችን ማጥናት ምንኛ መታደል ነው! በ1948 ከትምህርት ቤቱ ከተመረቅኩ በኋላ ስዊዘርላንድ ውስጥ በሚስዮናዊነት እንዳገለግል ተመደብኩ። ብዙም ሳይቆይ በጊልያድ ትምህርት ቤት በአምስተኛው ክፍል ከተመረቀው ከጄምስ ተርፐን ጋር ተዋወቅኩ። ለመጀመሪያ ጊዜ በቱርክ ቅርንጫፍ ቢሮ ሲከፈት የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። በመጋቢት ወር 1951 ተጋባንና ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንዳረገዝኩ በማወቃችን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የተጓዝን ሲሆን በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ወር ውስጥ ሴት ልጃችንን ማርሊንን ወለድኩ።

ባለፉት ዓመታት ሁሉ እኔና ጄምስ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ ብዙ ደስታ አስገኝቶልናል። በተለይ ፔኒ የተባለች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጣም የምትወድ ቻይናዊት ሴት ትዝ ትለኛለች። ራሷን ወስና ከተጠመቀች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ እያገለገለ ያለውን ጋይ ፒርስን አገባች። እነዚህን የመሳሰሉ ውድ ወንድሞች ወላጆቼን በማጣቴ ምክንያት የሚሰማኝን የባዶነት ስሜት እንዳሸንፍ ረድተውኛል።

በ2004 መጀመሪያ ላይ በወላጆቼ የትውልድ ከተማ በሎራክ የሚገኙ ወንድሞች በስቲክ ጎዳና የመንግሥት አዳራሽ ገነቡ። የከተማው ምክር ቤት የይሖዋ ምሥክሮች ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለመዘከር የመንገዱን ስም ለወላጆቼ ክብር ዴንትስሽትራሰ (ዴንትስ ጎዳና) ተብሎ እንዲቀየር ወሰነ። በአካባቢው የሚታተመው ባዲሸ ጻይቱንግ የተሰኘው ጋዜጣ “ለተገደሉት ዴንትስ የተባሉ ባልና ሚስት መታሰቢያ የተሰጠ አዲስ የመንገድ ስም” በሚል ርዕስ ሥር ወላጆቼ “በእምነታቸው ምክንያት በሦስተኛው ራይክ [በሂትለር ዘመነ መንግሥት] በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ተገደሉ” በማለት ዘግቧል። የከተማው ምክር ቤት ያደረገው ይህ ነገር ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ቢሆንም ሁኔታዎች በዚህ መንገድ መለዋወጣቸው ግን በጣም ያስደስታል።

አባቴ ብዙውን ጊዜ ‘አርማጌዶን በእኛ ዘመን አይመጣም ብለን በማሰብ የረጅም ጊዜ ግብ እናውጣ፤ ሆኖም ሕይወታችንን አርማጌዶን ነገ ሊመጣ እንደሚችል እንደምናስብ በሚያሳይ መንገድ እንምራ’ ይል ነበር። ሁልጊዜ በዚህ ድንቅ ምክር ለመመራት ጥረት አደርጋለሁ። እርጅና ባስከተለብኝ የአቅም ገደብ ምክንያት እቤት መዋል ከጀመርኩ ወዲህ በትዕግሥትና በጉጉት አንድን ነገር መጠበቅ ቀላል አልሆነልኝም። ሆኖም ይሖዋ፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን . . . በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል” በማለት ለታማኝ አገልጋዮቹ የገባውን ቃል ፈጽሞ ተጠራጥሬ አላውቅም።—ምሳሌ 3:5, 6

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከተጻፉ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ያገኘኋቸው ድንቅ ደብዳቤዎች

ከሎራክ በጣም ርቆ በሚገኝ መንደር የምትኖር አንዲት ሴት በ1980ዎቹ ዓመታት ይቺን ከተማ ለመጎብኘት መጣች። በዚያን ጊዜ የከተማዋ ነዋሪዎች የማይፈልጓቸውን እቃዎች ከቤታቸው እያወጡ ሕዝብ በሚበዛበት ቦታ ይጥሉና አላፊ አግዳሚው ከተጣሉት እቃዎች ውስጥ የሚፈልገውን መርጦ ይወስድ ነበር። ይህች ሴት የልብስ ስፌት እቃዎች የሚቀመጡበት ትንሽ ሣጥን አግኝታ ወሰደች። ከዚያም በሣጥኑ ውስጥ የአንዲት ልጃገረድ ፎቶግራፎችና በማጎሪያ ካምፕ የጽሕፈት መሣሪያ የተጻፉ ደብዳቤዎች ታገኛለች። ሴትየዋ በደብዳቤዎቹ በጣም የተማረከች ከመሆኑም በላይ ፀጉሯን የተጎነጎነችውስ ልጅ ማን ትሆን? እያለች ትጠይቅ ነበር።

ይህች ሴት በ2000 በሎራክ ስለተዘጋጀው ታሪካዊ ኤግዚቢሽን የሚገልጽ ጋዜጣ አነበበች። ጋዜጣው የእኛን ቤተሰብ ጨምሮ በአጠቃላይ የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ የግዛት ዘመን ያሳለፉትን ታሪክ ዘግቦ ነበር። እንዲሁም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለሁ የተነሣሁትን ፎቶ ይዞ ወጥቶ ነበር። ጋዜጣው ላይ ያለው ታሪክ ካገኘችው ነገር ጋር እንደሚመሳሰል ስታይ ጋዜጠኛዋን ፈልጋ በማግኘት ስለ ደብዳቤው ትነግራታለች፤ በአጠቃላይ 42 ደብዳቤዎች ነበሩ! ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ደረሱኝ። ወላጆቼ ደብዳቤ እየጻፉ አክስቴን ስለ እኔ በተደጋጋሚ ይጠይቋት እንደነበር ተረዳሁ። ለእኔ የነበራቸው ፍቅራዊ አሳቢነት ፈጽሞ አልቀዘቀዘም ነበር። እነዚህ ደብዳቤዎች እስከ አሁን መቆየታቸውና ከ60 ዓመታት በላይ በኋላ እኔ እጅ መግባታቸው ተአምር ነው!

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደስተኛ የነበረው ቤተሰባችን ሂትለር ሥልጣን በያዘበት ወቅት ተበታተነ

[ምንጭ]

ሂትለር፦ U.S. Army photo

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. በማግደቡርግ የነበረው ቢሮ

2. ጌስታፖዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ሲያስሩ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ጄምስ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ ብዙ ደስታ አስገኝቶልናል