በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በጣም ግሩም” የትርጉም ሥራ

“በጣም ግሩም” የትርጉም ሥራ

“በጣም ግሩም” የትርጉም ሥራ

በአንድ አኃዛዊ ግምት መሠረት ከ1952 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት ውስጥ 55 አዳዲስ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ታትመዋል። ተርጓሚዎቹ በሥራቸው ላይ የየራሳቸው ምርጫ ስለሚኖራቸው በአንድ ዓይነት መንገድ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች የሉም። በፍላግስታፍ፣ አሪዞና ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ኖርዘርን አሪዞና ዩኒቨርሲቲ በሃይማኖት ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄሰን ቤዱን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ጨምሮ ስምንት ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን በማነጻጸር ይበልጥ ትክክለኛ የሆነውን ለማወቅ ሞክረው ነበር። ውጤቱ ምን ሆነ?

ቤዱን በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ላይ አንዳንድ ሐሳቦች የተቀመጡበትን መንገድ ባይስማሙበትም ይህ ትርጉም ከተመለከቷቸው ከሌሎቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ጋር ሲወዳደር “በጣም ግሩም” እና “እጅግ የተሻለ” እንደሆነ እንዲሁም ‘አብዛኞቹን ጥቅሶች በትክክል በመተርጎም ረገድ የተሻለ’ መሆኑን ገልጸዋል። ቤዱን ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም “በአሁኑ ወቅት ካሉት በትክክለኛነታቸው የላቁ ከሚባሉት የአዲስ ኪዳን የእንግሊዝኛ ትርጉሞች መካከል አንዱ መሆኑን” እንዲሁም “ካነጻጸሯቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሁሉ ይበልጥ ትክክለኛ እንደሆነ” ጽፈዋል።—ትሩዝ ኢን ትራንስሌሽን፤ አኪዩሬሲ ኤንድ ባያስ ኢን ኢንግሊሽ ትራንስሌሽንስ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት

ከዚህም በላይ ቤዱን በርካታ ተርጓሚዎች “መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ከዘመናዊዎቹ አንባቢዎች ፍላጎት ጋር ለማስማማት ሲባል በቀላል አገላለጽ እንዲተረጉሙት ወይም እንዲያብራሩት” ግፊት የሚደረግባቸው መሆኑን ከተናገሩ በኋላ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ግን ከእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች የተለየ እንደሆነ ገልጸዋል። ለዚህም ምክንያቱን ሲናገሩ “የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የጥንቶቹ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የተጠቀሙባቸውን አገላለጾች ቃል በቃልና በጥንቃቄ ማስቀመጡ [ከሌሎች ትርጉሞች] ይበልጥ ትክክለኛ ያደርገዋል” ብለዋል።

የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንደገለጸው ቅዱሳን ጽሑፎችን መጀመሪያ ከተጻፉበት ቋንቋ ወደ ዘመናዊው ቋንቋ መተርጎም “በጣም ከፍተኛ ኃላፊነት” ነው። ኮሚቴው አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ ያዘጋጁት ተርጓሚዎች የቅዱሳን ጽሑፎች ደራሲ የሆነውን አምላክ የሚፈሩትና የሚወድዱት ከመሆኑም በላይ የእርሱን ሐሳቦችና ሕግጋት በተቻለ መጠን በትክክል የማስተላለፍ ልዩ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ይሰማቸዋል።”

የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1961 ከታተመበት ጊዜ አንስቶ ሁለት የብሬይል ቋንቋዎችን ጨምሮ በ34 ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በተለምዶ “አዲስ ኪዳን” የሚባለው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ደግሞ በተጨማሪ 18 ቋንቋዎች እንዲሁም በአንድ የብሬይል ቋንቋ ተዘጋጅቷል። ይህ ዘመናዊና “በጣም ግሩም” የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አንተ በምትረዳው ቋንቋ የሚገኝ ከሆነ እንድታነብበው እንጋብዝሃለን።