በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን መለየት የምትችለው እንዴት ነው?

ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን መለየት የምትችለው እንዴት ነው?

ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን መለየት የምትችለው እንዴት ነው?

ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር መሥፈርት የማውጣት ሥልጣን ያለው ማን ነው? ይህ ጥያቄ በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ተነስቶ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ እንደሚያሳየው አምላክ “መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ” ብሎ የሰየመው በኤድን የአትክልት ሥፍራ የሚገኝ ዛፍ ነበረ። (ዘፍጥረት 2:9) አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት ከዚህ ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ አዘዛቸው። ሆኖም የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ከፍሬው ከበሉ ‘ዐይናቸው እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ እንደ እግዚአብሔር እንደሚሆኑ’ ለአዳምና ለሔዋን ጠቆማቸው።—ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:1, 5፤ ራእይ 12:9

በዚህ ጊዜ አዳምና ሔዋን ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ ተደቀነባቸው፦ መልካምና ክፉ ስለሆነው ነገር አምላክ ያወጣውን መሥፈርት ይከተሉ ወይስ በራሳቸው መንገድ ይመሩ? (ዘፍጥረት 3:6) እነዚህ ባልና ሚስት የአምላክን ትእዛዝ ጥሰው ከዛፉ ለመብላት መረጡ። ይህ ቀላል የሚመስል እርምጃ ምን አንድምታ ነበረው? አዳምና ሔዋን አምላክ ካስቀመጠላቸው ገደብ በማለፋቸው እነርሱም ሆኑ ልጆቻቸው ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር የራሳቸውን መሥፈርት ቢያወጡ እንደሚበጃቸው መግለጻቸው ነበር። የሰው ልጅ የአምላክን ቦታ በመውሰድ የራሱን መሥፈርት ለማውጣት ያደረገው ጥረት ምን ያህል ተሳክቶለታል?

የተለያዩ አመለካከቶች

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ባለፉት ዘመናት ሁሉ የኖሩ ስመ ጥር ፈላስፎች የሰነዘሯቸውን ሐሳቦች ከዘረዘረ በኋላ፣ ከግሪካዊው ፈላስፋ ከሶቅራጥስ አንስቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ “ስለ ጥሩነት ትርጉም እንዲሁም ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች ለመለየት ስለሚያስችለው መሥፈርት ተደጋጋሚ ውዝግብ” እንደነበረ ገልጿል።

ለአብነት ያህል፣ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ሶፊስቶች የሚባሉ ታዋቂ የግሪክ መምህራን ነበሩ። እነዚህ ምሑራን ትክክልና ስህተት የሆነው ነገር የሚወሰነው በብዙኃኑ አመለካከት ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። ከእነዚህ መምህራን አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ከተማ ውስጥ ትክክልና ተቀባይነት ያለው እንደሆነ የሚታሰበውን ነገር [ሕዝቡ] እስከተስማማበት ድረስ ለዚያ ከተማ ትክክልና ተቀባይነት ያለው ይሆናል።” በዚህ መሥፈርት መሠረት በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ጆዲ በሚኖርበት ማኅበረሰብ ወይም “ከተማ” ውስጥ አብዛኛው ሰው የሚያደርገው ነገር ስለሆነ ገንዘቡን ሊወስድ ይገባል ማለት ነው።

ኢማኑኤል ካንት የተባለው ታዋቂ የ18ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋ ደግሞ ከዚህ የተለየ አመለካከት ነበረው። ሥነ ምግባርን የሚመለከቱ ጉዳዮች (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሔት “ኢማኑኤል ካንት እና እንደ እርሱ ያለ አመለካከት ያላቸው ሌሎችም . . . እያንዳንዱ ግለሰብ [ትክክልና ስህተት የሆነውን] ራሱ የመምረጥ ነጻነት እንዳለው ያምናሉ” ይላል። በካንት ፍልስፍና መሠረት ጆዲ የሌሎችን መብት እስካልጣሰ ድረስ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚወስነው ራሱ ይሆናል። የብዙኃኑ አመለካከት በውሳኔው ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግበት መፍቀድ አይኖርበትም።

ታዲያ ጆዲ ምን ውሳኔ አደረገ? ከላይ ከተገለጹት ከሁለቱ የተለየ ሦስተኛ አማራጭ ተጠቀመ። በክርስቲያኖችም ሆነ ክርስቲያን ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ ተደናቂነት ያተረፉትን የኢየሱስ ክርስቶስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተከተለ። ኢየሱስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” በማለት አስተምሯል። (ማቴዎስ 7:12) ጆዲ 82,000ውን ዶላር ሲሰጣት ደንበኛው በጣም ተገረመች። ጆዲ ገንዘቡን ለምን እንዳልወሰደው ሲጠየቅ የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ከገለጸ በኋላ “ገንዘቡም የእኔ አይደለም” በማለት መለሰ። ኢየሱስ በማቴዎስ 19:18 ላይ “አትስረቅ” በማለት የሰጠውን መመሪያ ጆዲ በቁም ነገር ተመልክቶታል።

የብዙኃኑ አመለካከት አስተማማኝ መመሪያ ሊሆን ይችላል?

አንዳንዶች ጆዲ የዚህን ያህል ታማኝ መሆኑ ሞኝነት እንደሆነ ይናገሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ የብዙኃኑ አመለካከት አስተማማኝ መመሪያ ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ ያህል፣ ባለፉት ዘመናት የነበሩ አንዳንድ ማኅበረሰቦች ያደርጉ እንደነበረው በምትኖርበት ኅብረተሰብ ውስጥ አብዛኞቹ ሰዎች ልጆችን መሥዋዕት ማድረግ ትክክል እንደሆነ የሚያምኑ ቢሆን ኖሮ ድርጊቱ ተገቢ ይሆን ነበር? (2 ነገሥት 16:3) የምትኖርበት ማኅበረሰብ የሰውን ሥጋ መብላት ትክክል እንደሆነ አድርጎ የሚያስብ ቢሆን ይህ ድርጊት ስህተት መሆኑ ይቀራል ማለት ነው? ከዚህ አንጻር ስንመለከተው አንድ ልማድ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑ ብቻ ትክክል አያደርገውም። መጽሐፍ ቅዱስ ከረጅም ጊዜ በፊት “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል” በማለት በዚህ ዓይነት አመለካከት እንዳንታለል አስጠንቅቆናል።—ዘፀአት 23:2

ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” እንደሆነ ሲናገር ትክክልና ስህተት የሆነውን በመለየት ረገድ የብዙኃኑን አመለካከት መከተል ተገቢ የማይሆንበትን ተጨማሪ ምክንያት ጠቁሟል። (ዮሐንስ 14:30፤ ሉቃስ 4:6) ሰይጣን በዚህ ሥልጣኑ በመጠቀም “ዓለምን ሁሉ” ያስታል። (ራእይ 12:9) እንግዲያው ትክክል የሆነውን ከስህተቱ ለመለየት የብዙኃኑን አመለካከት የምትከተል ከሆነ በሥነ ምግባር ረገድ የሰይጣንን አመለካከት እየተቀበልህ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ወደ ጥፋት እንደሚመራህ ግልጽ ነው።

በራስህ አመለካከት ልትመራ ትችላለህ?

እንግዲያው እያንዳንዱ ሰው ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር የራሱን መሥፈርት ማውጣት ይኖርበታል ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” ይላል። (ምሳሌ 3:5) ለምን? ምክንያቱም ሁላችንም ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አለፍጽምናን የወረስን ሲሆን ይህ ደግሞ የማመዛዘን ችሎታችንን ያዛባብናል። አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ሲያምጹ ራስ ወዳድ የሆነውን የከሃዲውን የሰይጣንን መሥፈርቶች በመከተል እርሱ መንፈሳዊ አባታቸው እንዲሆን መርጠዋል። በዚህም የተነሣ ለልጆቻቸው ያወረሷቸው ትክክል የሆነውን ማወቅ ቢችልም ስህተት የሆነውን ማድረግ የሚፈልግ ተንኰለኛ ልብ ነው።—ዘፍጥረት 6:5፤ ሮሜ 5:12፤ 7:21-24

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ሥነ ምግባርን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ከሥነ ምግባር አኳያ ሊያደርጉ የሚገባቸው ምን እንደሆነ ቢያውቁም እሱን ችላ ብለው ራሳቸው የሚፈልጉትን ነገር የሚያደርጉ መሆኑ አያስገርምም። እንደዚህ ያሉት ሰዎች ትክክል የሆነውን ለመከተል እንዲነሳሱ ማድረግ በምዕራቡ ዓለም ዋነኛ ችግር ሆኗል።” መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሁኔታ እንዲህ በማለት በትክክል አስቀምጦታል፦ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” (ኤርምያስ 17:9 የ1954 ትርጉም) ተንኰለኛና ክፉ እንደሆነ የምታውቀውን ሰው እምነት ትጥልበታለህ?

በአምላክ የማያምኑ ሰዎችም እንኳ ከሥነ ምግባር አንጻር ትክክል የሆነውን እንደሚያደርጉና ግሩምና ጠቃሚ የሆኑ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንደሚያወጡ አይካድም። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የሚያወጧቸው የላቁ መሥፈርቶች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መመሪያዎች ያንጸባርቃሉ። እነዚህ ሰዎች የአምላክን ሕልውና ቢክዱም የሚያፈልቋቸው ሐሳቦች የአምላክን ባሕርያት የማንጸባረቅ ተፈጥሯዊ ሥጦታ እንዳላቸው ያሳያሉ። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው የሰው ዘር በመጀመሪያ የተፈጠረው “በእግዚአብሔር መልክ” መሆኑን ያረጋግጣል። (ዘፍጥረት 1:27፤ የሐዋርያት ሥራ 17:26-28) ሐዋርያው ጳውሎስም “የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ” ብሏል።—ሮሜ 2:15

እርግጥ ነው፣ ትክክል የሆነውን ማወቅ እና ያንን ለማድረግ የሚያስፈልገውን የሞራል ጥንካሬ ማዳበር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። አንድ ሰው ትክክል የሆነውን ለማድረግ የሚያስፈልገውን የሞራል ጥንካሬ ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው? አንድን ነገር እንድናደርግ የሚያነሳሳን ልባችን በመሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ፍቅር ማዳበር እንዲህ ያለውን ጥንካሬ ለማግኘት ያስችላል።—መዝሙር 25:4, 5

መልካም የሆነውን ለማድረግ የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ማግኘት

አምላክን ለመውደድ የመጀመሪያው እርምጃ ትእዛዛቱ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉና ጠቃሚ መሆናቸውን መገንዘብ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” ብሏል። (1 ዮሐንስ 5:3) ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን፣ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን መውሰድን ወይም ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸምን አስመልክቶ ወጣቶች ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳቸው ጠቃሚ ምክር ይዟል። በትዳር ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ሐሳቦች እንዲሁም በልጆች አስተዳደግ ረገድ ለወላጆች መመሪያ የሚሆኗቸው ምክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። a ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች፣ ምንም ዓይነት የትምህርት ደረጃ ቢኖራቸው ወይም የሚኖሩበት ማኅበረሰብም ሆነ ባህላቸው ምንም ይሁን ምን የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ ይጠቀማሉ።

የተመጣጠነ ምግብ መብላት ለመሥራት የሚያስፈልግህን ኃይል እንደሚሰጥህ ሁሉ የአምላክን ቃል ማንበብም እርሱ ባወጣቸው መሥፈርቶች ሕይወትህን ለመምራት የሚያስችልህን ጥንካሬ ይሰጥሃል። ኢየሱስ የአምላክን ቃል በሕይወት ለመኖር አስፈላጊ ከሆነው እንጀራ ጋር አወዳድሮታል። (ማቴዎስ 4:4) እንዲሁም “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግ . . . ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:34) ኢየሱስ የአምላክን ቃል መመገቡ ፈተናዎችን ለመቋቋምና ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ ማድረግ እንዲችል አስታጥቆታል።—ሉቃስ 4:1-13

የአምላክን ቃል ማንበብና እርሱ ባወጣቸው መሥፈርቶች መመራት መጀመሪያ ላይ ይከብድህ ይሆናል። ሆኖም ልጅ እያለህ ጠቃሚ ቢሆኑም የማትወዳቸው ምግቦች እንደነበሩ ማስታወስ ትችላለህ። ጠንካራ ሆነህ እንድታድግ እነዚህን ጠቃሚ ምግቦች መብላትን መልመድ ነበረብህ። በተመሳሳይም የአምላክን መሥፈርቶች ለመውደድ ጊዜ ይወስድብህ ይሆናል። ሆኖም ጥረት ማድረግህን ከቀጠልክ እነዚህን ሥርዓቶች ትወዳቸውና በመንፈሳዊ ጠንካራ ትሆናለህ። (መዝሙር 34:8፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:15-17) እንዲሁም በይሖዋ መታመንንና ‘መልካም ማድረግን’ ትማራለህ።—መዝሙር 37:3

ጆዲ እንደገጠመው ዓይነት ሁኔታ አንተን ላያጋጥምህ ይችላል። ያም ቢሆን በየዕለቱ ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ ቀላልም ይሁን ከባድ ውሳኔዎች ታደርጋለህ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል” በማለት ይመክርሃል። (ምሳሌ 3:5, 6) በይሖዋ መታመንን መማርህ በዛሬው ጊዜ የሚጠቅምህ ከመሆኑም በላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይከፍትልሃል፤ ምክንያቱም ለይሖዋ አምላክ መታዘዝ ወደ ሕይወት ይመራል።—ማቴዎስ 7:13, 14

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በእነዚህና በሌሎች ዐበይት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሠጠውን ጠቃሚ ምክር ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች እንዲሁም ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባሉትን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ መጻሕፍት ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው አመለካከት የሰይጣንና የአጋንንቱ ተጽዕኖ ሊኖርበት ይችላል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለፉት ዘመናት ሁሉ ፈላስፎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በሚመለከት ሲወዛገቡ ኖረዋል

ሶቅራጥስ

ካንት

ኮንፊዩሽየስ

[ምንጭ]

ካንት፦ ዘ ሂስቶሪያንስ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ፤ ሶቅራጥስ፦ ኤ ጀነራል ሂስትሪ ፎር ኮሌጅስ ኤንድ ሃይ ስኩልስ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ፤ ኮንፊዩሽየስ፦ ሰንግ ካያን ክዋን ዩኒቨርሲቲ፣ ሴኦል፣ ኮሪያ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል የሆነውን ከስህተቱ ለመለየት እንድንችል የሚረዳን ከመሆኑም በላይ ትክክል የሆነውን እንድናደርግ ይገፋፋናል