በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ

የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ

የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ

“የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በእነዚህ የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።”—ምሳሌ 20:1

1. መዝሙራዊው ከይሖዋ ላገኛቸው በጎ ስጦታዎች የተሰማውን አድናቆት የገለጸው እንዴት ነው?

 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 1:17) መዝሙራዊው ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው የአምላክ በጎ ስጦታዎች ያለውን አድናቆት ሲገልጽ “ከምድር ምግብን ታወጣ ዘንድ፣ ለእንስሳት ሣርን፣ ለሰው ልጆች ሥራ ዕፀዋትን ታበቅላለህ፤ የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ ወይን፣ ፊቱን የሚያወዛ ዘይት፣ ልቡን የሚያበረታ እህል በዚህ ይገኛል” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 104:14, 15) እንደ ዕፅዋት፣ እህልና ዘይት ሁሉ ወይን ጠጅን ጨምሮ ሌሎች የአልኮል መጠጦችም የአምላክ በጎ ስጦታዎች ናቸው። ታዲያ እንዴት ልንጠቀምባቸው ይገባል?

2. የአልኮል መጠጥን በሚመለከት የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 አንድ ጥሩ ስጦታ አስደሳች ሊሆን የሚችለው በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውል ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል ማር “መልካም” ነው፤ ሆኖም “ከመጠን በላይ ማር መብላት ጥሩ አይደለም።” (ምሳሌ 24:13፤ 25:27) “ጥቂት የወይን ጠጅ” መጠጣት አስደሳች ሊሆን ቢችልም ከመጠን በላይ መጠጣት ግን ከባድ ችግር ያስከትላል። (1 ጢሞቴዎስ 5:23) መጽሐፍ ቅዱስ “የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በእነዚህ የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 20:1) ይሁን እንጂ በአልኮል መጠጥ መሳት ሲባል ምን ማለት ነው? a አንድ ሰው ከመጠን በላይ ጠጥቷል የሚባለው ምን ያህል ቢጠጣ ነው? በዚህ ረገድ ሊኖረን የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት ምንድን ነው?

አንድ ሰው በአልኮል መጠጥ ‘የሚስተው’ እንዴት ነው?

3, 4. (ሀ) እስኪሰክሩ ድረስ መጠጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዘ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ የስካር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

3 በጥንቷ እስራኤል አንድ ልጅ ሆዳምና ሰካራም ሆኖ ከተገኘና ከዚህ አመሉ የማይታረም ከሆነ በድንጋይ ተወግሮ ይገደል ነበር። (ዘዳግም 21:18-21) ሐዋርያው ጳውሎስ “‘ወንድም ነኝ’ እያለ ከሚሴስን ወይም ከሚስገበገብ ወይም ጣዖትን ከሚያመልክ ወይም ከሚሳደብ ወይም ከሚሰክር ወይም ከሚቀማ ጋር እንዳትተባበሩ . . . ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጋር ምግብ እንኳ አትብሉ” በማለት ክርስቲያኖችን መክሯል። ከዚህ በግልጽ እንደምናየው እስኪሰክሩ ድረስ መጠጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈጽሞ የተወገዘ ነው።—1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 6:9, 10

4 መጽሐፍ ቅዱስ የስካር ምልክቶችን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “መልኩ ቀይ ሆኖ፣ በብርጭቆ ውስጥ ሲያንጸባርቅ፣ ሰተት ብሎ በሚወርድበትም ጊዜ፣ ወደ ወይን ጠጅ ትክ ብለህ አትመልከት። በመጨረሻው እንደ እባብ ይነድፋል፤ እንደ እፉኝትም መርዙን ይረጫል። ዐይኖችህ እንግዳ ነገር ያያሉ፤ አእምሮህም ይቀባዥራል።” (ምሳሌ 23:31-33) አንድ ሰው ከመጠን በላይ ከጠጣ መጠጡ እንደ መርዛማ እባብ በመንደፍ ለሕመም ይዳርገዋል፣ ናላውን ያዞረዋል አልፎ ተርፎም ራሱን እስከመሳት ያደርሰዋል። የሰከረ ሰው ‘እንግዳ ነገር ሊያይ’ ማለትም በቁሙ ሊቃዥ ይችላል። እንዲሁም ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል እንደሚባለው ሌላ ጊዜ መናገር የማይፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ መናገር ወይም መቀባዠር ይጀምራል።

5. የአልኮል መጠጥን አዘውትሮ የመውሰድ ልማድ ጎጂ የሚሆነው እንዴት ነው?

5 አንድ ሰው የስካር ምልክት እንዳይታይበት እየተጠነቀቀ የመጠጣት ልማድ ቢኖረውስ? አንዳንዶች ብዙ ጠጥተውም እንኳ የስካር ምልክት ላይታይባቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ልማድ ራስን ማሞኘት ነው። (ኤርምያስ 17:9) አንድ ሰው እንዲህ ያለ ልማድ ካለው ይዋል ይደር እንጂ የአልኮል ጥገኛና ‘ሱሰኛ’ መሆኑ አይቀርም። (ቲቶ 2:3) ካሮላይን ናፕ የተባሉ ጸሐፊ የአልኮል ሱሰኛ ወደመሆን የሚያደርሰውን ሒደት በተመለከተ ሲናገሩ “አንድ ሰው የአልኮል ሱሰኛ የሚሆነው ቀስ በቀስና ምንም ሳይታወቀው ነው” ብለዋል። በእርግጥም የአልኮል መጠጥ አደገኛ ወጥመድ ሊሆን ይችላል!

6. አንድ ሰው ብዙ የመጠጣትና የመብላት ልማድ እንዳይጠናወተው መጠንቀቅ ያለበት ለምንድን ነው?

6 በተጨማሪም ኢየሱስ “በመብልና በመጠጥ ብዛት በስካርም በመባከንና ስለ ዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ። አለበለዚያ ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይመጣባችኋል። ምክንያቱም ያ ቀን በምድር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ በድንገት ያጠምዳቸዋል” ሲል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በል። (ሉቃስ 21:34, 35 የ1980 ትርጉም) አንድ ሰው ባይሰክርም እንኳ የአልኮል መጠጥ በመጠጣቱ ምክንያት በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሊደብተውና ሊጫጫነው ይችላል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ላይ እያለ የይሖዋ ቀን ቢደርስበትስ?

ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ምን ሊያስከትል ይችላል?

7. የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ በ2 ቆሮንቶስ 7:1 ላይ ከሚገኘው መመሪያ ጋር የሚጋጨው እንዴት ነው?

7 የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ በርካታ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። ከሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች መካከል የተለያዩ የጉበት በሽታዎች እንዲሁም የነርቭና የአእምሮ መታወክ ይገኙበታል። በተጨማሪም አንድ ሰው ለረጅም ዓመታት የአልኮል መጠጥ ከጠጣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ እንዲሁም አንዳንድ የልብና የሆድ ዕቃ በሽታዎች ሊይዙት ይችላሉ። የአልኮል መጠጥን አብዝቶ የመጠጣት ልማድ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር እንደሚጋጭ ግልጽ ነው።—2 ቆሮንቶስ 7:1

8. በምሳሌ 23:20, 21 መሠረት የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ምን ሊያስከትል ይችላል?

8 የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ብኩን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ከሥራ ሊያፈናቅል ይችላል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ፣ ሥጋ ከሚሰለቅጡ ጋር አትወዳጅ” ሲል አስጠንቅቋል። ለምን? “ሰካራሞችና ሆዳሞች ድኾች ይሆናሉና፤ እንቅልፋምነትም ቡትቶ ያለብሳቸዋል” በማለት አክሎ ተናግሯል።—ምሳሌ 23:20, 21

9. አንድ ሰው የሚያሽከረክር ከሆነ የአልኮል መጠጥ ከመጠጣት መቆጠቡ ጥበብ የሚሆነው ለምንድን ነው?

9 ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ አልኮሆሊዝም የአልኮል መጠጥ የሚያስከትለውን ሌላ አደጋ ሲጠቁም “ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአልኮል መጠጥ እርምጃ የመውሰድ ፍጥነትን፣ ቅልጥፍናን፣ ትኩረትንና ንቃትን እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታን በማዛባት የአንድን ሰው የማሽከርከር ብቃት ይቀንሳል” ይላል። ጠጥቶ ማሽከርከር የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ የከፋ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ እንኳ ጠጥቶ ማሽከርከር ከሚያስከትለው አደጋ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ይቆስላሉ። በተለይ ለዚህ በእጅጉ የተጋለጡት በማሽከርከርም ሆነ በመጠጣት ብዙም ልምድ የሌላቸው ወጣቶች ናቸው። አንድ ሰው የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ የሚያሽከረክር ከሆነ የይሖዋ አምላክ ውድ ስጦታ ለሆነው ሕይወት አክብሮት አለኝ ሊል ይችላል? (መዝሙር 36:9) ሕይወት ቅዱስ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ማንም ሰው የሚያሽከረክር ከሆነ ፈጽሞ የአልኮል መጠጥ ባይጠጣ ይመረጣል።

10. የአልኮል መጠጥ በአእምሮ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው? ይህስ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ከመጠን በላይ መጠጣት አካላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ጉዳት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል” በማለት ይናገራል። (ሆሴዕ 4:11 የ1954 ትርጉም) የአልኮል መጠጥ በአእምሮ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የአሜሪካ ብሔራዊ የአደገኛ ዕፅ መቆጣጠሪያ ተቋም የሚያሳትመው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው የአልኮል መጠጥ ሲጠጣ ወደ ሰውነቱ ገብቶ በደም ሥሩ አማካኝነት ቶሎ አናቱ ላይ ይወጣል። ከዚያም አስተሳሰብንና ስሜትን የሚቆጣጠረውን የአእምሮ ክፍል ያፈዝዘዋል። በዚህ ጊዜ ግለሰቡ ራሱን መቆጣጠር ይሳነዋል።” እዚህ ደረጃ ላይ ከደረስን ‘ልንስት፣’ የማይፈለጉ ነገሮችን ለማድረግ ድፍረት ልናገኝና ራሳችንን ለብዙ ፈተና ልናጋልጥ እንችላለን።—ምሳሌ 20:1

11, 12. በአልኮል መጠጥ ረገድ ልከኛ አለመሆን ምን መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል?

11 ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” የሚል መመሪያ ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 10:31) የአልኮል መጠጥ አብዝቶ መጠጣት ለአምላክ ክብር ያመጣል? አንድ ክርስቲያን በምንም ዓይነት ጠጪ ነው የሚል ስም ማትረፍ አይኖርበትም። እንዲህ ያለው ስም ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ሳይሆን ስሙን የሚያሰድብ ነው።

12 አንድ ክርስቲያን በአልኮል መጠጥ ረገድ ልከኛ አለመሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖችን ምናልባትም አንድን አዲስ ደቀ መዝሙር ቢያሰናክልስ? (ሮሜ 14:21) ኢየሱስ “በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሰው፣ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥሎ ቢሰጥም ይሻለዋል” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 18:6) ከመጠን በላይ መጠጣት በጉባኤ ውስጥ ያሉንን መብቶች ሊያሳጣን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-3, 8) የአልኮል መጠጥ ከመጠን በላይ መጠጣት በቤተሰብ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው ግጭትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ከአደጋው መሸሽ የሚቻለው እንዴት ነው?

13. የአልኮል መጠጥ ከሚያስከትለው አደጋ ለመራቅ የሚረዳው ወሳኝ ነገር ምንድን ነው?

13 የአልኮል መጠጥ ከሚያስከትለው አደጋ መሸሽ የሚቻልበት ዋነኛው መንገድ እንዲያው ከስካር ብቻ መሸሽ ሳይሆን ብዙ ከመጠጣት ወይም ልማደኛ ጠጪ ከመሆን መራቅ ነው። ታዲያ በዚህ ረገድ ልኩ ይህ ነው ብሎ ገደብ ሊያበጅልን የሚችለው ማን ነው? ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው በርካታ ነገሮች ስላሉ ከዚህ በላይ ከሆነ ከልክ አልፏል ብሎ ቁርጥ ያለ ገደብ ማውጣት አይቻልም። እያንዳንዱ ሰው የራሱን መጠን አውቆ ከዚያ ላለማለፍ መጠንቀቅ አለበት። መጠንህን እንድታውቅ ምን ሊረዳህ ይችላል? ይህን ለመወሰን የሚረዳ መሠረታዊ መመሪያ ይኖራል?

14. መጠንህን ለማወቅ የሚረዳህ መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ “ትክክለኛ ፍርድንና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤ እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤ ለነፍስህ ሕይወት፣ ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ” ይላል። (ምሳሌ 3:21, 22) እንግዲያው ልንመራበት የምንችለው መሠረታዊ ሥርዓት ይህ ነው፦ የወሰድከው የአልኮል መጠጥ መጠን ምንም ይሁን ምን የማሰብና የማመዛዘን ችሎታህን ካዛባ ከመጠን አልፏል ማለት ነው። ሆኖም መጠንህን በማወቅ ረገድ ራስህን እንዳታታልል መጠንቀቅ አለብህ!

15. የአልኮል መጠጥ ጭራሽ አለመጠጣቱ የሚመረጥባቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

15 ይሁንና ጭራሽ መጠጥ አለመቅመሱ የሚመረጥበት ሁኔታም ሊኖር ይችላል። አንዲት ነፍሰ ጡር ለጽንሱ ደኅንነት ስትል ፈጽሞ የአልኮል መጠጥ ላለመጠጣት ልትወስን ትችላለች። እንዲሁም የአልኮል ሱስ የነበረበት ወይም ኅሊናው መጠጣትን የማይፈቅድለት ሰው አብሮን ካለ ከመጠጣት መቆጠቡ አሳቢነት አይሆንም? ይሖዋ በማደሪያው ድንኳን የክህነት አገልግሎት ለሚፈጽሙ ሰዎች “እንዳትሞቱ . . . ወደ መገናኛው ድንኳን በምትገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 10:8, 9) በመሆኑም ስብሰባ የምትሄድ፣ አገልግሎት የምትወጣ እንዲሁም ሌላ መንፈሳዊ ሥራ የምታከናውን ከሆነ ፈጽሞ መጠጣት አይኖርብህም። ከዚህም በላይ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ጨርሶ በታገደባቸው ወይም የዕድሜ ገደብ በተጣለባቸው አገሮች የአገሩን ሕግ ማክበር ግድ ነው።—ሮሜ 13:1

16. የአልኮል መጠጥ ሲቀርብልህ ምን ማድረግ እንዳለብህ መወሰን የምትችለው እንዴት ነው?

16 የአልኮል መጠጥ ስትጋበዝ ወይም ሲቀርብልህ በመጀመሪያ ‘መጠጣት ይኖርብኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ለመጠጣት ከወሰንክ መጠንህ ምን ያህል እንደሆነ ማስታወስና ከዚያ ላለማለፍ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። የጋበዘህ ሰው ስለገፋፋህና ግድ ስላለህ ብቻ መጠጣት የለብህም። የአልኮል መጠጥ እንደልብ በሚቀርብባቸው እንደ ሠርግ በመሳሰሉ ድግሶች ላይ በምትገኝበት ጊዜ ከመጠንህ እንዳታልፍ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግሃል። በብዙ አገሮች ልጆች የአልኮል መጠጥ እንዳይጠጡ የሚከለክል ሕግ የለም። እንዲህ ባሉ አገሮች የአልኮል መጠጥ አወሳሰድን በተመለከተ መመሪያ የመስጠትና የመቆጣጠር ኃላፊነት የወላጆች ነው።—ምሳሌ 22:6

ችግሩን ማሸነፍ ይቻላል

17. ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለብህና እንደሌለብህ ለመወሰን ምን ሊረዳህ ይችላል?

17 የአልኮል መጠጥ በብዛት የመጠጣትና አዘውትሮ የመውሰድ ችግር አለብህ? የአልኮል መጠጥ ያለ አግባብ መውሰድ ስውር ኃጢአት ከሆነብህ ይዋል ይደር እንጂ መጋለጥህ እንደማይቀር ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብህም። ራስህን በሐቀኝነት መመርመሩ ይበጅሃል። እንደሚከተለው እያልህ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ያለ ወትሮዬ ብዙ የመጠጣት ልማድ እያዳበርኩ ነው? በአንድ ጊዜ የምወስደው የመጠጥ መጠን እየጨመረ ነው? ካለብኝ ጭንቀት፣ ውጥረት ወይም ችግር ለመሸሽ ስል የአልኮል መጠጥ እጠጣለሁ? ከቤተሰቤ አባላት መካከል አንዱ ወይም የቅርብ ጓደኛዬ የመጠጥ አወሳሰዴን በተመለከተ አነጋግሮኛል? የመጠጥ ልማዴ በቤተሰቤ ውስጥ ችግር እያስከተለ ነው? የአልኮል መጠጥ ሳልቀምስ ለሳምንት፣ ለወር ወይም ለወራት መቆየት ይከብደኛል? የምጠጣውን የአልኮል መጠጥ መጠን ከሌሎች ለመደበቅ እሞክራለሁ?’ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዳንዶቹ የምትሰጠው መልስ አዎን የሚል ቢሆንስ? ከሆነ ‘ፊቱን በመስተዋት አይቶ ወዲያው ምን እንደሚመስል እንደሚረሳ ሰው’ መሆን የለብህም። (ያዕቆብ 1:22-24) ችግሩን ለማስተካከል ቁርጥ ያለ እርምጃ ውሰድ። ታዲያ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

18, 19. ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ የመውሰድ ልማድህን ማቆም የምትችለው እንዴት ነው?

18 ሐዋርያው ጳውሎስ “በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና” በማለት ክርስቲያኖችን አጥብቆ መክሯል። (ኤፌሶን 5:18) በአልኮል መጠጥ አወሳሰድ ረገድ ለአንተ ከመጠን በላይ ነው የምትለው ምን ያህል እንደሆነ መወሰንና ተገቢውን ገደብ ማበጀት ይኖርብሃል። ከዚያ ገደብ ላለማለፍና ራስህን ለመግዛት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። (ገላትያ 5:22, 23) ብዙ እንድትጠጣ ወይም የመጠጣት ልማድ እንዲኖርህ የሚገፋፉ ጓደኞች አሉህ? ከሆነ መጠንቀቁ ይበጅሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጒዳት ያገኘዋል” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 13:20

19 ከችግር ለመሸሽ የአልኮል መጠጥ የምትወስድ ከሆነ የሚበጅህ በቀጥታ ችግሩን መጋፈጥ ነው። ደግሞም አንዳንድ ችግሮችን የአምላክን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ማሸነፍ ይቻላል። (መዝሙር 119:105) እምነት የሚጣልባቸውን የጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። መንፈሳዊነትህን ለመገንባት ይሖዋ ባደረጋቸው ዝግጅቶች በሚገባ ተጠቀም። ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር። ዘወትር ወደ እርሱ ጸልይ፤ በተለይ ድክመትህን ንገረው። አምላክ ‘ኩላሊትህንና ልብህን እንዲያጠራልህ’ ተማጸነው። (መዝሙር 26:2 NW) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተብራራው በጽኑ አቋም መሄድህን ለመቀጠል የተቻለህን ሁሉ አድርግ።

20. የተቸገርክበትን የአልኮል መጠጥ የመጠጣት ልማድ ለማሸነፍ ምን እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግህ ይችላል?

20 ጥረት አድርገህም እንኳ የአልኮል መጠጥ የመጠጣት ልማድህ ቢያስቸግርህስ? “እጅህ ብታሰናክልህ ቁረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመሄድ፣ ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለብህ። (ማርቆስ 9:43) መፍትሔው ጭራሹን የአልኮል መጠጥ የሚባል ነገር አለመቅመስ ነው። አይሪን የምትባል ሴት የወሰደችው ቁርጥ ያለ እርምጃ ይህ ነበር። “ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል ምንም የአልኮል መጠጥ ሳልቀምስ ከቆየሁ በኋላ አንድ ብቻ ጠጥቼ እስቲ ራሴን ልየው ብዬ አሰብኩ። እንደ በፊቱ የመጠጣት ስሜት ሲሰማኝ ወዲያው ስለ ሁኔታው ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ከዚያ በኋላ እስከ አዲሱ ሥርዓት ድረስ መጠጥ የሚባል ነገር ላለመቅመስ ወሰንኩ። እዚያም ከገባሁ በኋላ ላልጠጣ እችላለሁ” በማለት ተናግራለች። አንድ ሰው አምላክ በሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት ለማግኘት ሲል ከአልኮል መጠጥ ሙሉ በሙሉ ቢታቀብ ምንም ማለት አይደለም።—2 ጴጥሮስ 3:13

“ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ”

21, 22. ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ የመጨረሻውን መስመር እንዳናልፍ ምን ነገር እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል? ይህንንስ እንዴት ማስወገድ እንችላለን?

21 ሐዋርያው ጳውሎስ የአንድን ክርስቲያን የሕይወት ጉዞ ከውድድር ጋር በማነጻጸር እንዲህ ብሏል፦ “በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ። ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል እነርሱ ዐላፊ ጠፊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ይደክማሉ፤ እኛ ግን ለዘላለም የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት እንደክማለን። ስለዚህ እኔ ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ደግሞም ነፋስን እንደሚጎስም ሰው እንዲያው አልታገልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር፣ ሰውነቴን እየጎሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 9:24-27

22 ሽልማቱን የሚያገኙት ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ የፈጸሙ ብቻ ናቸው። የአልኮል መጠጥ ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ እስከ መጨረሻው መስመር ድረስ እንዳንሮጥ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር ይኖርብናል። ‘ያለ ልክ እየጠጡ’ መሮጥ እንደማይቻል የታወቀ ነው። (1 ጴጥሮስ 4:3) ከዚህ ይልቅ በማንኛውም ነገር ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር ያስፈልገናል። የአልኮል መጠጥ ከመጠጣት ጋር በተያያዘ “በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፣ በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት” መኖራችን አስፈላጊ ነው።—ቲቶ 2:12

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ ርዕስ ውስጥ “የአልኮል መጠጥ” ስንል ቢራን፣ ወይን ጠጅን፣ ጠላን፣ አረቄን፣ ጠጅንና ሌሎች ኃይለኛ መጠጦችን ማለታችን ነው።

ታስታውሳለህ?

• የአልኮል መጠጥን ያለ አግባብ መውሰድ ሲባል ምን ማለት ነው?

• የአልኮል መጠጥን ያለ አግባብ መውሰድ ምን ጉዳቶች ያስከትላል?

• የአልኮል መጠጥ ከሚያስከትለው አደጋ መሸሽ የሚቻለው እንዴት ነው?

• አንድ ሰው ያለበትን የአልኮል መጠጥ የመውሰድ ልማድ ማሸነፍ የሚችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወይን ‘የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል’

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጠናችንን ማወቅና ከዚያ ላለማለፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገደብህን አስቀድመህ ወስን

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ድክመቶችህን በተመለከተ አዘውትረህ ወደ ይሖዋ ጸልይ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ወላጆች ለልጆቻቸው መመሪያ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው