በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ቶማስን እንዲነካው ሲፈቅድለት መግደላዊት ማርያምን ግን የከለከላት ለምንድን ነው?

አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ጥቅሱን ኢየሱስ መግደላዊት ማርያም እንዳትነካው እንደከለከላት አድርገው ተርጉመውታል። ለምሳሌ በአማርኛው አዲሱ መደበኛ ትርጉም ላይ “ገና ወደ አብ ስላላረግሁ፣ አትንኪኝ” ተብሎ ተተርጉሟል። (ዮሐንስ 20:17) ሆኖም ብዙውን ጊዜ “መንካት” ተብሎ የሚተረጎመው ግሪክኛ ግስ “መጠምጠም፣ ማቀፍ፣ አጥብቆ መያዝ፣ መጨበጥ እና ማገድ” የሚል ትርጉምም አለው። ኢየሱስ ከእርሷ ከተለየ በኋላ ሌሎች ሴቶች ‘እግሩን እንዲይዙት’ መፍቀዱ መግደላዊት ማርያም ጨርሶ እንዳትነካው እንዳልከለከላት ያስገነዝበናል።—ማቴዎስ 28:9

የ1980 ትርጉምን በመሳሰሉ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ቃሉ “አትያዥኝ” ተብሎ በመተርጎሙ ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደነበር መገንዘብ እንችላለን። ሆኖም የቅርብ ወዳጁ ለነበረችው ለመግደላዊት ማርያም እንዲህ ያለበት ምክንያት ምንድን ነው?—ሉቃስ 8:1-3

መግደላዊት ማርያም ኢየሱስ ጥሏት ወደ ሰማይ የሚያርግ ሳይመስላት አልቀረም። ከጌታዋ ጋር ለመቆየት ካላት ፍላጎት የተነሳ እንዳይሄድ ቀልጠፍ ብላ አጥብቃ ያዘችው። ኢየሱስ የሚሄድበት ጊዜ ገና እንደሆነ ለማረጋገጥ ሲል፣ ከምትይዘው ይልቅ ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት መነሳቱን እንድታበስር ነገራት።—ዮሐንስ 20:17

ኢየሱስ ከቶማስ ጋር ያደረገው ውይይት ግን ከዚህ የተለየ ነው። ኢየሱስ ለጥቂት ደቀ መዛሙርቱ በተገለጠበት ጊዜ ቶማስ በቦታው አልነበረም። ስለዚህ ቶማስ በምስማር የተበሳውን የኢየሱስን እጅ ካላየና በጦር በተወጋው ጎኑ ውስጥ ጣቱን ካላስገባ መነሳቱን እንደማያምን ተናገረ። ኢየሱስ እንደገና ከስምንት ቀናት በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠላቸው። በዚህን ጊዜ ቶማስ በቦታው ስለነበር ኢየሱስ ቁስሉን እንዲነካ ነገረው።—ዮሐንስ 20:24-27

በመሆኑም ኢየሱስ፣ መግደላዊት ማርያም ሊሄድ ነው በሚል ስሜት እንዳትይዘው እየከለከላት ሲሆን ቶማስን ግን ጥርጣሬ እንዳያድርበት እየረዳው ነበር። ኢየሱስ በሁለቱም ወቅቶች ያደረገው ምክንያታዊ የሆነ ነገር ነበር።