የኢያሱ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የኢያሱ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
በ1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት በሞዓብ ሜዳ የሰፈሩት እስራኤላውያን “ስንቃችሁን አዘጋጁ፤ ከአሁን ጀምሮ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ትወርሳላችሁ” የሚሉትን ቃላት ሲሰሙ ምን ያህል ተደስተው ይሆን! (ኢያሱ 1:11) በምድረ በዳ ማሳለፍ የነበረባቸው 40 ዓመት ወደ ማብቃቱ ተቃርቧል።
ይህ ከሆነ ከሁለት አሥርተ ዓመታት ገደማ በኋላ ኢያሱ በተስፋይቱ ምድር እምብርት ላይ ሆኖ ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ አላቸው፦ “ከዮርዳኖስ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ በሙሉ ካሸነፍኋቸው ሕዝቦች ያልወረሳችሁትን ቀሪ ምድር ርስት እንዲሆን ለየነገዶቻችሁ እንዴት አድርጌ በዕጣ እንዳከፋፈልኋችሁ አስታውሱ። ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ከፊታችሁም ያሉበትን ስፍራ ያስለቅቃቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።”—ኢያሱ 23:4, 5
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1450 ኢያሱ ራሱ የጻፈው መጽሐፈ ኢያሱ በ22 ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙ አስደናቂ ታሪካዊ ክንውኖችን ይዟል። እኛም ቃል ወደተገባልን አዲስ ዓለም ለመግባት ደፍ ላይ በመሆናችን ተስፋይቱን ምድር ለመውረስ ከተዘጋጁት እስራኤላውያን ጋር እንመሳሰላለን። በመሆኑም እስቲ የኢያሱን መጽሐፍ ትኩረት ሰጥተን እንመርምር።—ዕብራውያን 4:12
ወደ “ኢያሪኮ ሜዳ”
ይሖዋ ለኢያሱ “እነሆ፤ ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ እንግዲህ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሡ፤ ለእሥራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ” በማለት ከባድ ኃላፊነት ሰጠው። (ኢያሱ 1:2) ኢያሱ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያቀፈውን ይህን ብሔር እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊጓዝ ነው። ለዝግጅት እንዲረዳው መጀመሪያ ወደሚቆጣጠረው ከተማ ወደ ኢያሪኮ ሁለት ሰላዮችን ላከ። በዚህች ከተማ ውስጥ ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል ያከናወናቸውን ታላላቅ ሥራዎች የሰማች ረዓብ የተባለች ጋለሞታ ትኖር ነበር። ይህች ሴት ሰላዮቹን ደበቀቻቸው እንዲሁም አስፈላጊውን እርዳታ አደረገችላቸው፤ በዚህ ምክንያት እንደማትጠፋ ቃል ገቡላት።
ሰላዮቹ ሲመለሱ ኢያሱና ሕዝቡ ጉዞ ለመጀመርና የዮርዳኖስን ወንዝ ለማቋረጥ ተዘጋጁ። ወንዙ ከአፍ እስከ ገደፉ መሙላቱ እስራኤላውያን ተሻግረው እንዳይሄዱ አላገዳቸውም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከላይ የሚወርደውን ውኃ ገድቦ አቆመው፤ ቁልቁል የሚወርደው ውኃ ደግሞ ተጠቃልሎ ወደ ሙት ባሕር እንዲገባ አደረገ። እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ ኢያሪኮ አቅራቢያ ባለው ጌልገላ ሰፈሩ። ከአራት ቀናት በኋላ ማለትም በአቢብ ወር 14ኛ ቀን ምሽት ላይ በኢያሪኮ ሜዳ የማለፍን በዓል አከበሩ። (ኢያሱ 5:10) በማግሥቱ የምድሪቱን ፍሬ መብላት የጀመሩ ሲሆን መና መውረዱንም አቆመ። በዚህን ጊዜ ኢያሱ በምድረ በዳ የተወለዱትን ወንዶች በሙሉ ገረዛቸው።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
2:4, 5—ረዓብ ሰላዮቹን እንዲይዙ ንጉሡ የላካቸውን ሰዎች በተሳሳተ መንገድ የመራቻቸው ለምንድን ነው? ረዓብ ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላ ሰላዮቹን የደበቀቻቸው በይሖዋ ላይ እምነት እያዳበረች በመምጣቷ ነው። ስለዚህ የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት ይፈልጉ ለነበሩ ሰዎች ሰላዮቹን አሳልፎ የመስጠት ግዴታ የለባትም። (ማቴዎስ 7:6፤ 21:23-27፤ ዮሐንስ 7:3-10) እንዲያውም፣ ረዓብ ‘የጸደቀችው’ የንጉሡን መልእክተኞች በተሳሳተ አቅጣጫ በመምራቷ ጭምር ነው።—ያዕቆብ 2:24-26
5:14, 15—“የእግዚአብሔር ሰራዊት አለቃ” ማን ነው? ኢያሱ የተስፋይቱን ምድር ነዋሪዎች ድል እያደረገ አካባቢውን መቆጣጠር በጀመረበት ጊዜ እርሱን ለማበረታታት የመጣው አለቃ፣ ሰው ከመሆኑ በፊት “ቃል” ይባል ከነበረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 1:1፤ ዳንኤል 10:13) ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች በሚያደርጉት መንፈሳዊ ውጊያ እንደሚያግዛቸው ማወቁ እንዴት ያበረታታል!
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:7-9፦ በመንፈሳዊ ለማደግ የምናደርገው ጥረት እንዲሳካልን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ፣ ባነበብነው ላይ ማሰላሰል እንዲሁም ያነበብነውን በሥራ ላይ ማዋል የግድ ያስፈልጋል።
1:11፦ ኢያሱ እስራኤላውያን እጃቸውን አጣጥፈው ቁጭ ብለው አምላክ እንዲመግባቸው እንዲጠብቁ ከማድረግ ይልቅ ስንቅ እንዲያዘጋጁ ነገራቸው። ኢየሱስ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለብን ከመከረን በኋላ “እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” ብሎ ቃል ገብቷል፤ እንዲህ ሲል ግን እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ምንም ጥረት እንዳናደርግ መናገሩ አልነበረም።—ማቴዎስ 6:25, 33
2:4-13፦ ረዓብ የይሖዋን ታላላቅ ሥራዎች ከሰማችና ከፊቷ እንዴት ያለ አስቸጋሪ ጊዜ እንደሚጠብቃት ከተገነዘበች በኋላ የእርሱን አምላኪዎች ለመደገፍ ቆርጣ ተነሳች። መጽሐፍ ቅዱስን ለተወሰነ ጊዜ ስታጠና ከቆየህና በጥናትህ አማካኝነት “በመጨረሻው ዘመን” ላይ እንደምንኖር ከተገነዘብክ አምላክን ለማገልገል እርምጃ መውሰዱ የተሻለ አይመስልህም?—2 ጢሞቴዎስ 3:1
3:15፦ ወደ ኢያሪኮ ተልከው የነበሩት ሰላዮች ጥሩ ዜና ይዘው በመመለሳቸው ኢያሱ የዮርዳኖስ ወንዝ እስኪጎድል ሳይጠብቅ በፍጥነት አስፈላጊውን እርምጃ ወስዷል። እኛም በተመሳሳይ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዙ ተግባሮችን ለማከናወን፣ ሁኔታዎች ይበልጥ አመቺ እስከሚሆኑ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ በድፍረት ሥራችንን መፈጸም ይገባናል።
4:4-8, 20-24፦ እስራኤላውያን ከዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ 12 ድንጋዮችን ያወጡት ለመታሰቢያ እንዲሆኗቸው ነበር። ይሖዋ በዚህ ዘመን ያሉት አገልጋዮቹን ከጠላቶቹ ነጻ ለማውጣት የወሰዳቸው እርምጃዎች እርሱ ከሕዝቡ ጋር እንዳለ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።
ድል ማድረጋቸውን ቀጠሉ
ኢያሪኮ ከተማ ‘ፈጽማ ተዘግታለች፤ ወደ ውጭ የሚወጣም ሆነ ወደ ውስጥ የሚገባ የለም።’ (ኢያሱ 6:1) ታዲያ ከተማዋን እንዴት ድል ማድረግ ይችላሉ? ይሖዋ ለኢያሱ አንድ ዘዴ ነገረው። ብዙም ሳይቆይ ግንቦቿ ፈራርሰው ከተማዋ ጠፋች። ረዓብና ቤተሰቦቿ ብቻ ከጥፋቱ ተረፉ።
ቀጥሎ የምትያዘው የነገሥታት ከተማ የሆነችው ጋይ ናት። የተላኩት ሰላዮች የከተማዋ ነዋሪዎች ጥቂት ስለሆኑ ብዙ ተዋጊዎች መሄድ እንደማያስፈልጋቸው አስታወቁ። ከዚያም 3,000 ወታደሮች ከተማይቱን እንዲወጉ ተላኩ፤ ነገር ግን የጋይ ሰዎች አሳደዷቸው። ለምን ይሆን? ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር ሳላልነበረ ነው። ምክንያቱም ኢያሪኮን በወረሩበት ወቅት የይሁዳ ነገድ አባል የነበረው አካን ኃጢአት ሠርቶ ነበር። ኢያሱ ለችግሩ እልባት ካበጀ በኋላ ከጋይ ሰዎች ጋር ጦርነት ከፈተ።
የጋይ ንጉሥ እስራኤላውያንን በመጀመሪያው ጦርነት ድል ስላደረገ በድጋሚ ለመግጠም በሙሉ ልብ ተዘጋጅቶ ነበር። ኢያሱ የጋይ ሰዎች ከልክ በላይ በራሳቸው መተማመናቸውን ተመለከተና በዚሁ ድክመታቸው በመጠቀም ከተማቸውን ያዘ።ገባዖን ‘ታላቅ ከተማ፣ በስፋቷም ከጋይ የምትበልጥና ሰዎቿም ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ።’ (ኢያሱ 10:2) ሆኖም ገባዖናውያን፣ እስራኤላውያን ኢያሪኮንና ጋይን ድል ማድረጋቸውን ሲሰሙ ኢያሱን በማታለል የሰላም ቃል ኪዳን አስገቡት። በአካባቢው የነበሩት ብሔራት ገባዖናውያን ከእስራኤላውያን ጋር በተናጠል የሰላም ስምምነት ማድረጋቸው አስደነገጣቸው። የእነዚህ ብሔራት አምስት ነገሥታት ግንባር ፈጥረው ገባዖንን ለማጥቃት ተነሱ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ገባዖናውያንን በመርዳት ነገሥታቱን ድል አደረጓቸው። በተጨማሪም በኢያሱ መሪነት በደቡብና በምዕራብ የሚገኙ ከተሞችን እንዲሁም በሰሜን በኩል የሚገኙ ጥምር ነገሥታትን ድል አድርገዋል። ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ የነበሩ በአጠቃላይ 31 ነገሥታት ድል ተነሱ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
10:13—ይህ ያልተለመደ ክስተት እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሰማይና የምድር ፈጣሪ ለሆነው “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?” (ዘፍጥረት 18:14) ይሖዋ ከፈለገ ምድር እንዳትንቀሳቀስ በማድረግ ከምድር ሆኖ ለሚመለከት ሰው ፀሐይና ጨረቃ የቆሙ መስለው እንዲታዩት ማድረግ ይችላል። ወይም ደግሞ የምድርና የጨረቃ እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል ከፀሐይና ከጨረቃ የሚመጣውን ብርሃን አቅጣጫ በማስቀየር ምድር ብርሃን እንድታገኝ ማድረግ ይችላል። ፀሐይ እንድትቆም የተደረገበት መንገድ ምንም ይሁን ምን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ “እንደዚያ ያለ ዕለት . . . አልነበረም።”—ኢያሱ 10:14
10:13—የያሻር መጽሐፍ ምንድን ነው? ይህ መጽሐፍ ለእስራኤል ንጉሥ ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ስለተጻፈው “የቀስት እንጉርጉሮ” በሚያወሳው በ2 ሳሙኤል 1:18 ላይም ተገልጿል። መጽሐፉ ታሪካዊ ይዘት ባላቸው ክንውኖች ላይ ያተኮሩ መዝሙሮችን እና ግጥሞችን የያዘና ዕብራውያን በደንብ የሚያውቁት ሊሆን ይችላል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
6:26፤ 9:22, 23፦ ኢያሱ ኢያሪኮ ስትጠፋ የተናገረው እርግማን ከ500 ዓመታት በኋላ ተፈጽሟል። (1 ነገሥት 16:34) ኖኅ የልጅ ልጁን ከነዓንን የረገመው እርግማንም እንዲሁ ገባዖናውያን ባሮች በሆኑበት ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ዘፍጥረት 9:25, 26) ይህም ይሖዋ የተናገረው ቃል ምንጊዜም ሳይፈጸም እንደማይቀር ማረጋገጫ ይሆነናል።
7:20-25፦ አንዳንዶች አካን ማንንም እንዳልጎዳ በማሰብ የፈጸመውን ስርቆት እንደ ቀላል ነገር ይቆጥሩት ይሆናል። ጥቃቅን ነገሮችን በመስረቅና ቀላል ስህተቶችን በመፈጸም የመጽሐፍ ቅዱስን ሕግ መጣስንም እንዲሁ አቅልለው ይመለከቱ ይሆናል። እኛ ግን ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጸም ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ነገር ሲደረግ ካየን እንደ ኢያሱ ጥብቅ አቋም ልንይዝ ይገባናል።
9:15, 26, 27፦ የገባነውን ውል በቁም ነገር መጠበቅና ቃላችንን ማክበር ይገባናል።
ኢያሱ ለመጨረሻ ጊዜ ከባድ ኃላፊነት ተቀበለ
ወደ 90 ዓመት ዕድሜው እየተጠጋ የነበረው አዛውንቱ ኢያሱ ለየነገዶቹ ርስት ማከፋፈል ጀመረ። ይህ በእርግጥ ከባድ ኃላፊነት ነበር! የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ቀደም ሲል ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን መሬት ወርሰው ነበር። የቀሩት ነገዶች ደግሞ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለውን ርስት በዕጣ ሊከፋፈሉ ነው።
የማደሪያው ድንኳን በኤፍሬም ነገድ ግዛት በሴሎ ተተከለ። ካሌብ ኬብሮን የምትባለው ከተማ ስትደርሰው ኢያሱ ደግሞ ተምናሴራን ወሰደ። ሌዋውያን 6 የመማጸኛ ከተሞችን ጨምሮ 48 ከተሞች ተሰጧቸው። ከዚያም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ምድር የወረሱት የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ተዋጊዎች ወደ ርስታቸው ሲመለሱ “ግዙፍ” መሠዊያ ሠሩ። (ኢያሱ 22:10) ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ የሚገኙ ነገዶች ይህን ጉዳይ እንደ ሃይማኖታዊ ክህደት በመቁጠራቸው ምክንያት ከባድ የጎሳ ጦርነት ሊነሳ ተቃረበ፤ ሆኖም ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት በማድረጋቸው ከደም መፋሰስ ሊጠበቁ ችለዋል።
ኢያሱ በተምናሴራ መኖር ከጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ መሪዎች፣ ፈራጆችና ሹማምንት ሰብስቦ እንዲበረቱና እስከመጨረሻው ድረስ ለይሖዋ ታማኝ እንዲሆኑ አሳሰባቸው። ቆየት ብሎም የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ በሴኬም ሰበሰበ። በዚያም ይሖዋ ከአብርሃም ዘመን አንስቶ ያደረገላቸውን ነገር ከተረከላቸው በኋላ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ታማኝነትም ተገዙለት” በማለት በድጋሚ አጥብቆ አሳሰባቸው። ሕዝቡም “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እንታዘዝለታለንም” ብለው መልስ ሰጡት። (ኢያሱ 24:14, 15, 24) እነዚህ ክንውኖች ከተፈጸሙ በኋላ ኢያሱ በ110 ዓመቱ ሞተ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
13:1—ይህ አነጋገር በኢያሱ 11:23 ላይ ከተገለጸው ሐሳብ ጋር አይጋጭም? አይጋጭም፤ ምክ ንያቱም ተስፋይቱን ምድር ድል አድርገው የያዙበት መንገድ በሁለት ይከፈላል። መጀመሪያ፣ ብሔሩ በኅብረት 31 የከነዓን ነገሥታትን ድል በማድረግ ኃይላቸውን አንኮታኮተ፤ ቀጥሎም እስራኤላውያን ውርሳቸውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ በየነገዱና በተናጠል ከነዓናውያንን ተዋጉ። (ኢያሱ 17:14–18፤ 18:3) እስራኤላውያን ከመካከላቸው ፈጽሞ ሊያባርሯቸው ያልቻሏቸው ከነዓናውያን ግን ለደኅንነታቸው ያን ያህል አስጊ አልነበሩም። (ኢያሱ 16:10፤ 17:12) ኢያሱ 21:44 “እግዚአብሔር . . . በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው” ይላል።
24:2—የአብርሃም አባት ታራ ጣዖት አምላኪ ነበር? ታራ በመጀመሪያ ይሖዋን አያመልክም ነበር። ሲን የተባለው የዑር ከተማ ተወዳጅ የጨረቃ አምላክ አምላኪ የነበረ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የአይሁዳውያን አፈ ታሪክ እንደሚገልጸው ታራ ጣዖት ሠሪ ሳይሆን አይቀርም። ነገር ግን አብርሃም በአምላክ ትእዛዝ ዑርን ለቅቆ ሲወጣ ታራ ወደ ካራን አብሮት ተጉዟል።—ዘፍጥረት 11:31
ምን ትምህርት እናገኛለን?
14:10-13፦ ካሌብ 85 ዓመት የሞላው ቢሆንም እንኳ የኬብሮንን ነዋሪዎች ከከተማው የማስወጣት ከባድ ሥራ እንዲሰጠው ጠየቀ። በዚህ ስፍራ በጣም ረጃጅም የሆኑት ዔናቃውያን ይኖሩ ነበር። ይህ ልምድ ያለው ተዋጊ በይሖዋ እርዳታ ተሳክቶለት ኬብሮንን በእጁ ያስገባ ሲሆን በኋላም ቦታው የመማጸኛ ከተማ ሆነ። (ኢያሱ 15:13-19፤ 21:11-13) ይህ የካሌብ ታሪክ ከባድ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን እንዳንሸሽ ያበረታታናል።
22:9-12, 21-33፦ እዚህ ላይ የሰፈረው ዘገባ ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር በተሳሳተ መንገድ እንዳንረዳ መጠንቀቅ እንዳለብን ያስተምረናል።
‘ከሰጣችሁ ተስፋ አንዲቱን እንኳ አላስቀረባችሁም’
ኢያሱ በሸመገለ ጊዜ በእስራኤል ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ . . . ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 23:14) ይህ እውነት መሆኑን ኢያሱ የመዘገበው ታሪክ በግልጽ ያሳያል!
ሐዋርያው ጳውሎስ “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 15:4) በመሆኑም አምላክ በሰጠን ተስፋዎች ላይ የምናምነው በከንቱ እንዳልሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አንዱም ቃል አይወድቅም፤ ሁሉም ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
እስራኤላውያን በኢያሱ መሪነት ምድሪቱን ድል አድርገው ያዙ
ባሳን
ገለዓድ
ዓረባ
ኔጌብ
የዮርዳኖስ ወንዝ
የጨው ባሕር
የያቦቅ ሸለቆ
የአርኖን ሸለቆ
አሦር (አጾር)
ማዶን
ለሸሮን
ሺምሮን
ዮቅንዓም
ዶር
መጊዶ
ቃዴስ
ታዕናክ
ኦፌር
ቲርሳ
አፌቅ
ታጱዋ
ቤቴል
ጋይ
ጌልገላ
ኢያሪኮ
ጌዝር
ኢየሩሳሌም
መቄዳ
የርሙት
ዓዶላም
ልብና
ለኪሶ
ዔግሎን
ኬብሮን
ዳቤር
ዓራድ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጋለሞታይቱ ረዓብ የጸደቀችው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢያሱ እስራኤላውያንን “እግዚአብሔርን ፍሩ . . . ተገዙለት” በማለት በጥብቅ አሳስቧቸዋል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአካን ስርቆት ቀላል ጥፋት ባለመሆኑ ምክንያት ከባድ መዘዝ አስከትሏል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘የኢያሪኮ ግንብ በእምነት ወደቀ።’—ዕብራውያን 11:30