ይሖዋ የሚሰጥህን እርዳታ ትቀበላለህ?
ይሖዋ የሚሰጥህን እርዳታ ትቀበላለህ?
“ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም።”—ዕብራውያን 13:6
1, 2. በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን እርዳታና አመራር መቀበላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አንድ ቀጭን መንገድ ተከትለህ ተራራ እየወጣህ ነው እንበል። ይሁንና መንገዱን የሚያሳይህ ሰው አብሮህ ለመሄድ ፈቃደኛ ስለሆነ ብቻህን አይደለህም። ሰውየው ደግሞ ከማንም የተሻለ መሪ ነው። ከአንተ የበለጠ ልምድና ጥንካሬ ቢኖረውም በትዕግሥት ከአጠገብህ ሳይርቅ ይጓዛል። አልፎ አልፎ እንደምትደናቀፍ አስተውሏል። አንድ አደገኛ ቦታ ላይ ስትደርሱ ለአንተ ደኅንነት በማሰብ እጁን ዘረጋልህ። እርዳታ አያስፈልገኝም ትለዋለህ? ቦታው ለሕይወትህ አስጊ ስለሆነ እንደዚያ እንደማትል ግልጽ ነው!
2 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እኛም በጣም አስቸጋሪ ጉዞ አለብን። ቀጭኑን መንገድ ለብቻችን መጓዝ ይኖርብናል? (ማቴዎስ 7:14) በጭራሽ። ከማንም በተሻለ ሊመራን የሚችለው ይሖዋ አምላክ ሰዎች ከእርሱ ጋር እንዲሄዱ ፈቃደኛ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 5:24፤ 6:9) ይሖዋ አገልጋዮቹን በጉዟቸው ይረዳቸዋል? እንዲህ ይላል:- “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና።” (ኢሳይያስ 41:13) በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሰው መንገድ መሪ ሁሉ ይሖዋም ከእርሱ ጋር ለመጓዝ ለሚፈልጉ ሰዎች ለእርዳታ እጁን በደግነት የዘረጋላቸው ከመሆኑም ሌላ ከእርሱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ጋብዟቸዋል። ማናችንም ብንሆን እርዳታውን አንፈልግም እንደማንል የታወቀ ነው!
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚብራሩት የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?
3 በፊተኛው ርዕስ ላይ ይሖዋ በጥንት ዘመን ሕዝቦቹን የረዳበትን አራት መንገዶች ተመልክተን ነበር። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹን በተመሳሳይ መንገዶች ይረዳቸዋል? ታዲያ እርሱ ከሚሰጠን እርዳታ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋ በእርግጥ ረዳታችን መሆኑን ከበፊቱ በበለጠ እንድናምን ያስችለናል።—ዕብራውያን 13:6
መላእክት የሚሰጡት እርዳታ
4. በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች መላእክት እንደሚረዷቸው በእርግጠኝነት ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው?
4 መላእክት በዛሬው ጊዜ ያሉትን የይሖዋ አገልጋዮች ይረዳሉ? አዎ፣ ይረዳሉ። እርግጥ፣ በዚህ ዘመን እውነተኛ አምላኪዎችን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲመጡ ሰዎች ሊያዩዋቸው አይችሉም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ቢሆን መላእክት የታዩባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂት ናቸው። እንደ ዛሬው ሁሉ ያኔም የሚያደርጓቸው አብዛኞቹ ነገሮች ከሰው ዓይን የተሰወሩ ነበሩ። ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋዮች መላእክት ከጎናቸው ሆነው እንደሚረዷቸው ማወቃቸው በጣም አጽናንቷቸዋል። (2 ነገሥት 6:14-17) እኛም እንደዚህ እንዲሰማን የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት አለን።
5. በዛሬው ጊዜ መላእክት በስብከቱ ሥራ እንደሚሳተፉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?
5 የይሖዋ መላእክት እኛ ለምንሳተፍበት አንድ ልዩ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ። ሥራው ምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ራእይ 14:6 ላይ እናገኛለን:- “ከዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር።” ይህ “የዘላለም ወንጌል” ኢየሱስ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ . . . በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ሲል ከተነበየው “የመንግሥት ወንጌል” ጋር የተያያዘ መሆኑ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 24:14) እርግጥ መላእክት በቀጥታ ለሰዎች አይሰብኩም። ኢየሱስ ይህን ከባድ ተልእኮ የሰጠው ለሰዎች ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህን ተልእኮ በምንወጣበት ጊዜ ጥበበኛና ብርቱ የሆኑ ቅዱሳን መላእክት እንደሚረዱን ማወቁ አያበረታታም?
6, 7. (ሀ) መላእክት የስብከቱ ሥራችንን እንደሚደግፉ እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) የይሖዋን መላእክት ድጋፍ እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
6 የስብከቱን ሥራ ስናከናውን መላእክት እንደሚረዱን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎት ላይ ሳሉ እውነቱን ለማወቅ እንዲረዳቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት ወደ አምላክ ጸልየው የነበሩ ሰዎች እንዳገኙ ሲነገር ብዙ ጊዜ እንሰማለን። እንዲህ ዓይነት ተሞክሮ በተደጋጋሚ የሚከሰት ከመሆኑ የተነሳ እንዲያው የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ብለን ልናልፈው አንችልም። እንዲህ የመሰለ የመላእክት እርዳታ በመኖሩ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች ‘በሰማይ መካከል የሚበረው መልአክ’ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት” ሲል ያወጀውን ትእዛዝ ለመፈጸም በመማር ላይ ናቸው።—ራእይ 14:7
7 የይሖዋ ኃያላን መላእክት እንዲረዱህ ትፈልጋለህ? ከሆነ አቅምህ የሚፈቅድልህን ያህል በአገልግሎት ተካፈል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ከይሖዋ በተቀበልነው በዚህ ልዩ የአገልግሎት ምድብ ራሳችንን ሳንቆጥብ ስንሠራ የይሖዋ መላእክት እንደሚረዱን እርግጠኛ መሆን እንችላለን።
ከመላእክት አለቃ የሚገኝ እርዳታ
8. ኢየሱስ በሰማይ ምን ዓይነት ከፍተኛ ቦታ አለው? ይህስ እኛን የሚያበረታታን ለምንድን ነው?
8 ይሖዋ በሌላም መንገድ በመልአክ ይረዳናል። ራእይ 10:1 “ፊቱ እንደ ፀሓይ” ስለሚያበራ “ብርቱ መልአክ” ይናገራል። በራእይ የታየው ይህ አስደናቂ መልአክ በሰማይ ሥልጣን የያዘውንና ክብር የተላበሰውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። (ራእይ 1:13, 16) ኢየሱስ በእርግጥ መልአክ ነው? የመላእክት አለቃ ስለሆነ መልአክ ነው ሊባል ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 4:16) ኢየሱስን ከይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች መካከል በኃይል የሚተካከለው የለም። ይሖዋ በመላእክት ሠራዊቱ ላይ አዛዥ አድርጎ ሾሞታል። በእርግጥም ይህ የመላእክት አለቃ ከፍተኛ የእርዳታ ምንጭ ነው። እርዳታ የሚሰጠን በምን መንገዶች ነው?
9, 10. (ሀ) ኢየሱስ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ረዳት የሚሆነን እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከተወልን ምሳሌ ምን ዓይነት እርዳታ ማግኘት እንችላለን?
9 አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ “ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:1) ዮሐንስ በተለይ ‘ኃጢአት ስንሠራ’ ኢየሱስ የእኛ “ጠበቃ” ወይም ረዳት እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው? በየቀኑ ኃጢአት እንሠራለን፤ ኃጢአት ደግሞ ለሞት ይዳርጋል። (መክብብ 7:20፤ ሮሜ 6:23) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የእኛን ኃጢአት ለመደምሰስ ሲል ሕይወቱን ሰውቷል። እንዲሁም ስለ እኛ ለመማጸን በይቅር ባዩ አባታችን ጎን ተቀምጧል። ሁላችንም እንዲህ ዓይነት እርዳታ ያስፈልገናል። ከእርዳታው ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ለፈጸምነው ኃጢአት ንስሐ መግባትና በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ምሕረት መጠየቅ ይኖርብናል። በተጨማሪም ኃጢአቱን ላለመድገም መጠንቀቅ ይኖርብናል።
10 ኢየሱስ ለእኛ ሲል ከመሞቱም በተጨማሪ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) እርሱ የተወልን ምሳሌ መመሪያ ይሆነናል እንዲሁም በማስተዋል በመኖር ከባድ ኃጢአት ከመፈጸም እንድንርቅና ይሖዋ አምላክን እንድናስደስት ይረዳናል። እንዲህ ዓይነት እርዳታ በማግኘታችን ደስተኞች አይደለንም? ኢየሱስ ተከታዮቹ ሌላም ረዳት እንደሚያገኙ ቃል ገብቶላቸዋል።
መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው እርዳታ
11, 12. የይሖዋ መንፈስ ምንድን ነው? ምን ያህልስ ኃይል አለው? በዛሬው ጊዜ የሚያስፈልገንስ ለምንድን ነው?
11 ኢየሱስ “እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም . . . ሊቀበለው አይችልም” በማለት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። (ዮሐንስ 14:16, 17) ይህ “የእውነት መንፈስ” ወይም መንፈስ ቅዱስ አካል ሳይሆን ኃይል ነው። ይሖዋ የሚጠቀምበት ኃይል ከመሆኑም ሌላ ምንም ገደብ የሌለው ብርቱ ኃይል ነው። ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን ለመፍጠር፣ አስደናቂ ተአምራት ለማከናወንና ፈቃዱን በራእይ ለመግለጽ የተጠቀመበት ኃይል ነው። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ መንፈሱን በእነዚህ መንገዶች ስለማይጠቀምበት መንፈሱ አያስፈልገንም ማለት ይቻላል?
12 በጭራሽ! በዚህ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” የይሖዋ መንፈስ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ያስፈልገናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ፈተናዎችን ችለን እንድናሳልፍ ብርታት ይሰጠናል። ወደ ይሖዋ እንዲሁም ወደ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይበልጥ እንድንቀርብ የሚያስችሉ ግሩም ባሕርያት እንድናፈራ ይረዳናል። (ገላትያ 5:22, ) ታዲያ ከይሖዋ ከምናገኘው ከዚህ ግሩም እርዳታ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? 23
13, 14. (ሀ) ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ለሕዝቦቹ በደስታ እንደሚሰጥ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንዳናገኝ የሚያደርገን ምን ዓይነት ድርጊት ነው?
13 በመጀመሪያ ደረጃ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል። ኢየሱስ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይስጥ!” ብሏል። (ሉቃስ 11:13) አዎ፣ ከይሖዋ የተሻለ አባት ሊኖር አይችልም። መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን አጥብቀን በእምነት ከጠየቅነው ይከለክለናል ብሎ ማሰቡ የማይመስል ነገር ነው። ታዲያ እንዲሰጠን እንለምናለን? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። በየቀኑ በምናቀርበው ጸሎት ላይ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቅ ይኖርብናል።
14 በሁለተኛ ደረጃ ከመንፈሱ ጋር ተስማምተን በመኖር መንፈሱን ማግኘት እንችላለን። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት:- አንድ ክርስቲያን የብልግና ምስሎችን ከማየት ለመራቅ እየታገለ ነው እንበል። ይህን መጥፎ ልማድ ማሸነፍ እንዲችል የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ለማግኘት ጸልዮአል። ከጉባኤ ሽማግሌዎች ምክር ጠይቆ፣ እንዲህ ወዳለው እርኩስ ነገር ዝር እንዳይል በማሳሰብ ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ መክረውታል። (ማቴዎስ 5:29) የሰጡትን ምክር ችላ ብሎ በፈተናው ቢሸነፍስ? ይህ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ለማግኘት ካቀረበው ጸሎት ጋር ተስማምቶ እየኖረ ነው? ወይስ የአምላክን መንፈስ የማሳዘንና ይህን ስጦታ የማጣት አደጋ ተደቅኖበታል? (ኤፌሶን 4:30) በእርግጥም፣ ከይሖዋ የምናገኘው ይህ ከፍተኛ እርዳታ እንዳይቋረጥብን የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።
ከአምላክ ቃል የምናገኘው እርዳታ
15. መጽሐፍ ቅዱስን አቅልለን እንደማንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ለሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ለበርካታ መቶ ዘመናት የእርዳታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ተራ መጽሐፍ ከመቁጠር ይልቅ ከፍተኛ የእርዳታ ምንጭ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። ከመጽሐፉ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሕይወታችን ክፍል ልናደርገው ይገባል።
16, 17. (ሀ) መዝሙር 1:2, 3 የአምላክን ሕግ ማንበብ የሚያስገኘውን ጥቅም የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) መዝሙር 1:3 ተግቶ የመሥራትን አስፈላጊነት የሚጠቁመው እንዴት ነው?
16 መዝሙር 1:2, 3 የአምላክን መመሪያ ስለሚያከብር ሰው ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ [“በውኃ ፈሳሾች፣” የ1954 ትርጉም] ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” የዚህ ጥቅስ ሐሳብ ገብቶሃል? ጥቅሱን አንብቦ ደስ ስለሚል አካባቢ ማለትም ወንዝ ዳር ስለተተከለ ጥላ የሚሰጥ ዛፍ ይገልጻል ብሎ መደምደም ቀላል ነው። ቀትር ላይ በእንደዚህ ዓይነት ቦታ ጋደም ማለት መንፈስ ያድሳል! ይህ መዝሙር ግን እያሳሰበን ያለው ስለ እረፍት እንድናስብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መዝሙሩ በትጋት መሥራትን የሚያበረታታ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
17 እዚህ ላይ የተጠቀሰው ዛፍ ጥላ ከመስጠት ያለፈ ፋይዳ የሌለው ወፍ ዘራሽ ዛፍ አለመሆኑን ልብ በል። ከዚህ ይልቅ “በውኃ ፈሳሾች ዳር” በዓላማ ‘የተተከለ’ ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ ነው። ታዲያ አንድ ዛፍ በብዙ የውኃ ፈሳሾች ዳር ሊያድግ የሚችለው እንዴት ነው? ወንዝ ዳር የፍራፍሬ እርሻ ያለው አንድ ገበሬ ዛፎቹን ውኃ ለማጠጣት በርካታ የመስኖ ቦዮችን ይቆፍር ይሆናል። አሁን ነጥቡ ግልጽ ነው! በመንፈሳዊ ሁኔታ እኛም እንደ ዛፉ ተመችቶን የምናድገው አንድ ሰው እኛን ለመርዳት ብዙ ደክሞልን ነው። አባል የሆንበት ድርጅት የእውነትን ንጹሕ ውኃ ያለንበት ድረስ ያመጣልናል፤ ውኃውን መጠጣት ግን የእኛ ፋንታ ነው። የአምላክ ቃል እውነት ወደ አእምሯችንና ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ ተገቢውን ምርምር በማድረግና በማሰላሰል ከዚህ ውድ ውኃ መጠቀም እንድንችል አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ በማድረግ እኛም ጥሩ ፍሬ ማፍራት እንችላለን።
18. ለጥያቄዎቻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
18 መጽሐፍ ቅዱስ ተዘግቶ መደርደሪያ ላይ መቀመጡ በራሱ የሚያስገኝልን አንዳች ፋይዳ የለም። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፉ አንድ ዓይነት ምትሐት ያለው ይመስል ዓይናችንን ጨፍነን ያገኘነው ቦታ ገልጠን በማንበብ ለጥያቄያችን መልስ እናገኛለን ብለን መጠበቅ የለብንም። ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች ሲያጋጥሙን የተቀበረ ሀብት ለማግኘት የምንቆፍረውን ያህል ‘የአምላክን እውቀት’ ለማግኘት መጣር ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:1-5) የእኛን ሁኔታ በቀጥታ የሚመለከት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለማግኘት ትጋትና ማስተዋል የተሞላበት ምርምር ማድረግ አስፈላጊ ነው። ምርምር ለማድረግ የሚረዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ጽሑፎች አሉን። በእነዚህ ጽሑፎች አማካኝነት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እንደ ዕንቁ የከበረ ጥበብ ለማግኘት በትጋት የምንቆፍር ከሆነ በእርግጥ ይሖዋ ከሚሰጠን እርዳታ እንደምንጠቀም ያሳያል።
ከእምነት ባልንጀሮቻችን የምናገኘው እርዳታ
19. (ሀ) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ላይ የሚወጡ ትምህርቶች የእምነት ባልንጀሮቻችን የሰጡን እርዳታ ተደርገው ሊታዩ የሚችሉት ለምንድን ነው? (ለ) ከመጽሔቶቻችን በአንዱ ላይ ከወጣ ትምህርት ምን ያገኘኸው እርዳታ አለ?
19 በምድር ላይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ባለፉት ዘመናት ሁሉ አንዳቸው ለሌላው የብርታት ምንጭ ሆነው ቆይተዋል። በዚህ ረገድ ይሖዋ ተለውጧል? በፍጹም። ከእምነት ጓደኞቻችን የሚያስፈልገንን እርዳታ በተገቢው ጊዜ ያገኘንበት ሁላችንም የምናስታውሰው ሁኔታ እንደሚኖር ምንም ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ ያህል በአስፈላጊው ጊዜ ማጽናኛ ወይም ለአንድ ችግር መፍትሔ ያገኘህበት አሊያም በእምነትህ ላይ የተደቀነብህን ፈተና እንድትወጣ የረዳህ መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! ላይ የወጣ ትዝ የሚልህ ርዕስ አለ? ‘በተገቢው ጊዜ ምግብ’ እንዲያቀርብ በተሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ይህን እርዳታ የሰጠህ ይሖዋ ነው።—ማቴዎስ 24:45-47
20. የጉባኤ ሽማግሌዎች ‘ሥጦታ የሆኑ ወንዶች’ መሆናቸውን የሚያሳዩት በምን መንገድ ነው?
20 አብዛኛውን ጊዜ ግን ከእምነት ባልንጀሮቻችን የምናገኘው እርዳታ በቀጥታ የሚመጣ ነው። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የሰጠው ንግግር ለተግባር አነሳስቶን ወይም ያደረገልን የእረኝነት ጉብኝት የደረሰብንን ችግር እንድንቋቋም ረድቶን ወይም የሰጠን ደግነት የተሞላበት ምክር ድክመታችንን አውቀን እንድናሸንፍ አስችሎን ይሆናል። አንዲት አመስጋኝ የሆነች ክርስቲያን አንድ ሽማግሌ ስለሰጣት እርዳታ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “አገልግሎት ላይ እያለን ጊዜ ወስዶ የሚሰማኝን እንድነግረው አበረታታኝ። ከዚያ በፊት በነበረው ምሽት ጭንቀቴን የማካፍለው ሰው እንዲልክልኝ ወደ ይሖዋ ጸልዬ ነበር። ልክ በነጋታው ይህ ወንድም አሳቢነት በተሞላበት መንገድ አነጋገረኝ። ለበርካታ ዓመታት ይሖዋ እንዴት ሲረዳኝ እንደቆየ እንድገነዘብ ረዳኝ። ይሖዋ ይህን ሽማግሌ ስለላከልኝ አመሰግነዋለሁ።” የጉባኤ ሽማግሌዎች በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ለመርዳት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከይሖዋ ያገኘናቸው ‘ሥጦታ የሆኑ ወንዶች’ መሆናቸውን በእነዚህና በሌሎች መንገዶች ማሳየት ይችላሉ።—ኤፌሶን 4:8 NW
21, 22. (ሀ) የጉባኤ አባላት ፊልጵስዩስ 2:4 ላይ የሚገኘውን ምክር መከተላቸው ምን ውጤት ያስገኛል? (ለ) የተደረገልን የደግነት ድርጊት ትንሽም ቢሆን እንኳ ከፍተኛ ጥቅም የሚኖረው ለምንድን ነው?
21 የጉባኤ ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ታማኝ ክርስቲያኖች “እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መመሪያ በተግባር ማዋል ይፈልጋሉ። (ፊልጵስዩስ 2:4) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች ይህን ምክር በሥራ ሲያውሉ ግሩም የደግነት መግለጫዎች ይታያሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ቤተሰብ በድንገት ተደራራቢ ችግሮች ደረሱበት። አባትየው ሴት ልጁን ይዞ ወደ ገበያ አዳራሽ ሄዶ ነበር። ወደ ቤት እየተመለሱ ሳለ የመኪና አደጋ አጋጠማቸው። ልጅቷ ሕይወቷን ያጣች ሲሆን አባትየው ደግሞ ከባድ ጉዳት ደረሰበት። አባትየው ከሆስፒታል ከወጣ በኋላም ራሱን የሚረዳበት አቅም አልነበረውም። ሚስትየው በጭንቀት ከመዋጧ የተነሳ እርሱን ለብቻዋ መንከባከብ አልቻለችም። ስለዚህ በጉባኤያቸው ውስጥ ያሉ አንድ ባልና ሚስት እነዚህን በሐዘን የተደቆሱ ወንድምና እህት ቤታቸው ወስደው ለበርካታ ሳምንታት እንክብካቤ አደረጉላቸው።
22 እርግጥ ሁልጊዜ እንደዚህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጥማል ወይም ይህን የመሰለ የራስን ጥቅም የመሰዋት መንፈስ እንድናሳይ ይጠየቅብናል ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ የሚሰጠን እርዳታ አነስተኛ ሊሆን ይችላል። የደግነት መግለጫው ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን እርዳታውን በአድናቆት መመልከት አይኖርብንም? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ደግነት የተሞላበት ቃል በመናገራቸው ወይም አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት በመፈጸማቸው የሚያስፈልግህን እርዳታ ያገኘህበት ጊዜ አለ? ይሖዋ ብዙ ጊዜ የሚረዳን እንዲህ ባሉ መንገዶች ነው።—ምሳሌ 17:17፤ 18:24
23. ይሖዋ አንዳችን ሌላውን ለማበረታታት የምናደርገውን ጥረት እንዴት ይመለከተዋል?
23 ይሖዋ ሌሎችን ለመርዳት አንተን መሣሪያ አድርጎ እንዲጠቀምብህ ትፈልጋለህ? ይህ ልዩ አጋጣሚ ለአንተም ክፍት ነው። እንዲያውም ይሖዋ በዚህ ረገድ የምታደርገውን ጥረት በአድናቆት ይመለከታል። ቃሉ “ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል” ይላል። (ምሳሌ 19:17) ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ራሳችንን መስጠታችን ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ሆን ብለው ራሳቸውን የሚያገልሉ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ መስጠት የሚያስገኘው ደስታም ሆነ መቀበል የሚያስገኘው ማበረታቻ ያመልጣቸዋል። (ምሳሌ 18:1) በመሆኑም አንዳችን ሌላውን ማበረታታት እንድንችል በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር በታማኝነት እንገኝ።—ዕብራውያን 10:24, 25
24. ይሖዋ ከዚህ ቀደም የፈጸማቸውን አስደናቂ ተአምራት ባለማየታችን የቀረብን ነገር እንዳለ ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው?
24 ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች እንደሚረዳን ማሰቡ አያስደስትም? የምንኖረው ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም አስደናቂ ተአምራት በሚያከናውንበት ጊዜ ውስጥ ባይሆንም እንኳ የቀረብን ነገር እንዳለ ሊሰማን አይገባም። ዋናው ቁም ነገር፣ ይሖዋ በታማኝነት መጽናት እንድንችል የሚያስፈልገንን ማንኛውንም እርዳታ የሚሰጠን መሆኑ ነው። ደግሞም አንድ ላይ በእምነት ከጸናን በታሪክ ዘመን በሙሉ ታይቶ የማያውቀውን የይሖዋን አስደናቂ ድርጊት ለማየት እንበቃለን! “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” ከሚለው ለ2005 ከተመረጠው ጥቅስ ጋር ተስማምተን መኖር እንድንችል የይሖዋን ፍቅራዊ እርዳታ ለመቀበልና ከእርዳታው በሚገባ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—መዝሙር 121:2 NW
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚያስፈልገንን እርዳታ
• በመላእክት
• በመንፈስ ቅዱስ
• በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ
• በእምነት ባልንጀሮቻችን አማካኝነት የሚሰጠን እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መላእክት የስብከቱን ሥራ እንደሚደግፉ ማወቁ ያበረታታል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በአንድ የእምነት ባልንጀራችን አማካኝነት የሚያስፈልገንን ማጽናኛ ሊሰጠን ይችላል