በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በምግብ ሰዓት አስደሳች ጭውውት ማድረግ ይቻላል

በምግብ ሰዓት አስደሳች ጭውውት ማድረግ ይቻላል

በምግብ ሰዓት አስደሳች ጭውውት ማድረግ ይቻላል

ሁሉም ሰው ጣፋጭ ምግብ መመገብ ያስደስተዋል። ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ሞቅ ያለ አስደሳች ጭውውት እያደረግን መመገብ ደግሞ ረሃባችንን ከማስታገስ አልፎ መንፈሳችንንም ያረካል። በርካታ ቤተሰቦች በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ ተሰባስበው የመመገብ ልማድ አላቸው። በምግብ ሰዓት የቤተሰብ አባላት በዕለቱ ውስጥ የሚያከናውኗቸውን ነገሮች ወይም ያጋጠሟቸውን ሁኔታዎች ለመወያየት የሚያስችል አጋጣሚ ያገኛሉ። ወላጆች ልጆቻቸው የሚናገሯቸውን ሐሳቦች የሚያዳምጡ ከሆነ አስተሳሰባቸውንና ስሜታቸውን የሚጠቁም ፍንጭ ያገኛሉ። ዘና ባለ ሁኔታ በአንድ ላይ ምግብ እየተመገቡ አስደሳች ወቅት ማሳለፍ በጊዜ ሂደት በቤተሰቡ መካከል የመረጋጋት ስሜት፣ መተማመንና ፍቅር እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን ይህም አስተማማኝ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በዛሬው ጊዜ ብዙ የቤተሰብ አባላት በሥራ የተጠመዱ ስለሆኑና ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ስለሚዘዋወሩ በአንድ ላይ ተሰባስቦ ምግብ መመገብ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች የአካባቢው ባሕል ቤተሰቦች በአንድ ላይ ተሰባስበው መመገባቸውን ወይም በማዕድ ላይ ማውራታቸውን ይከለክላል። ሌሎች ቤተሰቦች ደግሞ በምግብ ሰዓት ቴሌቪዥን ስለሚመለከቱ እርስ በርስ ጠቃሚ ጭውውት ማድረግ የሚችሉበት አጋጣሚ ያመልጣቸዋል።

ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወላጆች በቤተሰባቸው መካከል ያለውን ቅርርብ ለማጠናከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በንቃት ይከታተላሉ። (ምሳሌ 24:27) ከረጅም ጊዜ በፊት ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ አምላክ ቃል መንገር ከሚችሉባቸው ግሩም አጋጣሚዎች አንዱ ‘በቤት ሲቀመጡ’ እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 6:7) ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አዘውትረው መመገባቸው በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ለይሖዋ እና ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጥልቅ ፍቅር መትከል የሚችሉበት እድል ይሰጣቸዋል። ዘና ያለና ደስ የሚል መንፈስ እንዲኖር በማድረግ የምግብ ሰዓት ሁሉም የቤተሰብህ አባላት የሚደሰቱበትና የሚታነጹበት ወቅት እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ። አዎን፣ በምግብ ሰዓት እንዲያው የቀረበውን ምግብ ብቻ ተመግቦ ከመለያየት ይልቅ አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ ይቻላል።