በአምላካዊ ጥበብ አማካኝነት ልጆቻችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
በአምላካዊ ጥበብ አማካኝነት ልጆቻችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
ሰውነታችን ምንጊዜም ቢሆን ውጊያ ላይ ነው። ረቂቅ ተሕዋስያንን፣ ጥገኛ ነፍሳትንና ቫይረሶችን መታገል ይገባዋል። ደግነቱ አብዛኞቻችን እንዲህ ያሉትን ጥቃቶች እንድንመክትና በእነዚህ ሕዋሳት ምክንያት በሚመጡት በሽታዎች እንዳንያዝ የሚረዳን በተፈጥሮ ያገኘነው መከላከያ አለን።
በተመሳሳይም እኛ ክርስቲያኖች ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ አስተሳሰቦችና የአቋም ደረጃዎች እንዳንመራ መታገል እንዲሁም መንፈሳዊ ጤንነታችን እንዲታወክ የሚደረጉብንን ግፊቶች መቋቋም ይገባናል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) በየዕለቱ በአእምሯችንና በልባችን ላይ የሚሰነዘረውን እንዲህ ያለውን ጥቃት ለመቋቋም መንፈሳዊ መከላከያዎችን መገንባት ይገባናል።
በተለይ ልጆቻችን የዓለምን መንፈስ ለመመከት የሚያስችሉትን መንፈሳዊ መከላከያዎች ይዘው ስላልተወለዱ እንዲህ ያሉት መከላከያዎች ያስፈልጓቸዋል። (ኤፌሶን 2:2) ወላጆች ልጆቻቸው እያደጉ ሲሄዱ የራሳቸውን መከላከያ እንዲያበጁ መርዳታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህ መከላከያዎች በምን ላይ የተመሠረቱ ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ . . . የታማኞቹንም አካሄድ ያጸናል” ይላል። (ምሳሌ 2:6, 8) መለኮታዊ ጥበብ ወጣቶችን ከክፉ ባልንጀርነት፣ ከእኩዮች ተጽዕኖና ጎጂ ከሆኑ መዝናኛዎች እንዲርቁ በመርዳት አካሄዳቸው ቀና እንዲሆን ይረዳቸዋል። ወላጆች የይሖዋን አመራር መከተልና በልጆቻቸው ውስጥ አምላካዊ ጥበብ መትከል የሚችሉት እንዴት ነው?
ጥሩ ባልንጀሮችን ማፍራት
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች በእነርሱ የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው፤ ነገር ግን ጓደኝነታቸው ከእነዚህ ብዙም ተሞክሮ ከሌላቸው እኩዮቻቸው ጋር ብቻ ከሆነ አምላካዊ ጥበብን ማግኘትና በዚያም መመራት አይችሉም። የምሳሌ መጽሐፍ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 22:15) አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በጓደኛ ምርጫ ረገድ በአምላካዊ ጥበብ እንዲመሩ መርዳት የቻሉት እንዴት ነው?
ዶን a የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሏል:- “ወንዶች ልጆቻችን ከጓደኞቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የሚገናኙት በእኛ ቤት ሲሆን እኛም አብረናቸው እንሆናለን። በማንኛውም ሰዓት ቤታችን ክፍት ስለነበር ሁልጊዜ በወጣቶች እንደተሞላ ነው፤ የሚመጡትን ወጣቶች ምግብ ከመጋበዛችንም በላይ በመምጣታቸው እንደተደሰትን እንዲሰማቸው እናደርግ ነበር። ልጆቻችንን የሚያስደስት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ስለምንፈልግ በቤታችን ውስጥ የሚኖረውን ጫጫታና ረብሻ ከምንም አንቆጥረውም ነበር።”
ብራየን እና ማሪ ሦስት ጥሩ ጥሩ ልጆች አሏቸው፤ ሆኖም እነርሱን ማሠልጠን ሁልጊዜ ቀላል እንዳልነበረ በግልጽ ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል:- “በጉባኤያችን ውስጥ ልጃችን ጄን ጓደኛ ልታደርጋቸው የምትችላቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች አልነበሩም። ሆኖም ተግባቢና ፍልቅልቅ የሆነች ሱዛን የተባለች አንድ ጓደኛ ነበረቻት። የሱዛን ወላጆች የእኛን ያህል ጥብቅ አልነበሩም። ሱዛን ውጪ እንድታመሽ፣ አጫጭር ቀሚሶች እንድትለብስ፣ አጠያያቂ ሙዚቃዎችን እንድታዳምጥና ተገቢ ያልሆኑ ፊልሞችን እንድታይ ይፈቀድላት የነበረ ሲሆን ጄን ግን እንዲህ እንድታደርግ አንፈቅድላትም ነበር። ጄን ለረጅም ጊዜያት እኛ ያለን አመለካከት አስፈላጊነት አይገባትም ነበር። ጄን የሱዛን ቤተሰቦች የልጃቸውን ስሜት የሚረዱ፤ እኛ ደግሞ ፈጽሞ የማናፈናፍን እንደሆንን አድርጋ ትመለከት ነበር። ጥብቅ የምንሆንባት እርሷን ለመጠበቅ መሆኑን የተረዳችው ሱዛን ችግር በገጠማት ጊዜ ነበር። ለልጃችን ይጠቅማታል ብለን ያሰብነውን ነገር በተመለከተ ያለንን አቋም ባለማላላታችን በጣም ደስተኞች ነን።”
ልክ እንደ ጄን ሁሉ በርካታ ወጣቶችም ይህን ዓይነቱን ባልንጀርነት በተመለከተ ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን ምክር ማዳመጥ ጥበብ እንደሆነ ተገንዝበዋል። የምሳሌ መጽሐፍ “ሕይወት ሰጪ የሆነውን ተግሣጽ የሚሰማ፣ በጠቢባን መካከል ይኖራል” ይላል። (ምሳሌ 15:31) አምላካዊ ጥበብ ወጣቶች ጥሩ ባልንጀሮች እንዲያፈሩ ይረዳቸዋል።
እኩዮቻቸውን እንዲመስሉ የሚደረግባቸውን ተጽዕኖ መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ጓደኝነትና የእኩዮች ተጽዕኖ የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። በየዕለቱ ልጆቻችን ከሌሎች ጋር ተመሳስለው እንዲኖሩ ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል። ብዙውን ጊዜ ወጣቶች በእኩዮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ስለሚፈልጉ፣ የእኩዮቻቸው ተጽዕኖ ዓለም ትክክል ነው ብሎ በሚያምንበት መንገድ ሊቀርጻቸው ይችላል።—ምሳሌ 29:25
መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸው በዚህ ዓለም አስተሳሰብ ሲሸነፉ ዝም ብለው ማየት የለባቸውም። ወላጆች ልጆቻቸው ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
“ሴት ልጄ ሁልጊዜ እንደ ሌሎች ወጣቶች መልበስ ትፈልጋለች” በማለት ሪቻርድ ይናገራል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ስለዚህ እንዲደረግላት የምትጠይቀው እያንዳንዱ ነገር ያለውን ጥቅምና ጉዳት በትዕግሥት እናስረዳት ነበር። ምንም ችግር የለባቸውም ብለን ስለምናምንባቸው ፋሽኖች እንኳን ከረጅም ዓመታት በፊት የሰማነውን ‘ጥበበኛ ሰው አዲስ ፋሽን ለመከተል የመጀመሪያው አይሆንም፤ ጊዜ ያለፈበትንም ይዞ ሙጭጭ አይልም’ የሚለውን ምክር እንከተላለን።”
ፖሊን የተባለች እናት ደግሞ ልጆቿ የእኩዮቻቸውን ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ የረዳቻቸው በሌላ መንገድ ነው። እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “የልጆቼ ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማወቅ ስል ሁልጊዜ ወደ መኝታ ክፍላቸው ሄጄ አጫውታቸዋለሁ።
በእነዚህ ወቅቶች ከልጆቼ ጋር የማደርገው ረዘም ያለ ውይይት አስተሳሰባቸውን ለመቅረጽና ነገሮችን ለየት ባለ መንገድ እንዲመለከቱ ለመርዳት አስችሎኛል።”የእኩዮች ተጽዕኖ ስለማያቋርጥ ወላጆች የዓለምን ‘ሐሳብ በማፍረስ’ የልጆቻቸውን አእምሮ ‘እየማረኩ ለክርስቶስ እንዲታዘዙ’ ለማድረግ የማያቋርጥ ትግል ይጠይቅባቸው ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 10:5) ሆኖም ወላጆችም ሆኑ ልጆች ‘በጸሎት በመጽናት’ ይህን በጣም አስፈላጊ ትግል በድል ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ ማግኘት ይችላሉ።—ሮሜ 12:12፤ መዝሙር 65:2
መዝናኛ ያለው የመሳብ ኃይል
ወላጆች መመሪያ ለመስጠት የሚቸገሩበት ሦስተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ ደግሞ መዝናኛ ነው። ልጆች በተፈጥሯቸው የመጫወት ፍላጎት አላቸው። ዕድሜያቸው ከፍ ያለ ልጆችም ቢሆኑ መጫወትና መዝናናት ይፈልጋሉ። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ነገር ግን ይህን ፍላጎታቸውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለማርካት ከሞከሩ መንፈሳዊ የመከላከል ኃይላቸው ሊዳከም ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ አደጋው በሁለት መንገዶች ሊከሰት ይችላል።
በመጀመሪያ አብዛኞቹ መዝናኛዎች ያዘቀጠውን የዓለም ሥነ ምግባር የሚያንጸባርቁ ናቸው። (ኤፌሶን 4:17-19) ሆኖም እነዚህ መዝናኛዎች ስሜትን በሚቀሰቅስና በሚማርክ መልኩ መቅረባቸው የተለመደ ነው። ይህ ሁኔታ ወጥመዱ በማይታያቸው ወጣቶች ላይ ከባድ አደጋ ያስከትልባቸዋል።
ሁለተኛው ችግር ደግሞ በመዝናኛ የሚጠፋው ጊዜ ነው። አንዳንዶች መዝናናት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚያሟጥጥባቸው ቢሆንም እንኳን ለሕይወታቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ነገር አድርገው ይመለከቱታል። የምሳሌ መጽሐፍ “ከመጠን በላይ ማር መብላት ጥሩ አይደለም” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 25:27) በተመሳሳይ ከልክ በላይ መዝናናት የመንፈሳዊ ምግብ ፍላጎትን ሊዘጋና የአእምሮ ስንፍና ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 21:17፤ 24:30-34) ወጣቶች በዚህ ዓለም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም መፈለጋቸው “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት ‘አጥብቀው እንዳይዙ’ ጋሬጣ ይሆንባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19) ወላጆች ፈተናውን እንዴት ሊቋቋሙት ቻሉ?
የሦስት ሴቶች ልጆች እናት የሆነችው ማሪ ካርሜን እንዲህ ብላለች:- “ልጆቻችን ጠቃሚ በሆኑ መዝናኛዎች ራሳቸውን እንዲያስደስቱ እንፈልግ ነበር። ስለዚህ በቤተሰብ ሆነን ወጣ እንላለን፤ እንዲሁም በጉባኤያችን ካሉ ወጣት ጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ ያሳልፉ ነበር። ነገር ግን መዝናኛው ከልክ እንዳያልፍ እንጠነቀቅ ነበር። መዝናኛን የምንመለከተው ከምግብ በኋላ እንደሚቀርብ ጣፋጭ ነገር እንጂ እንደዋነኛው ምግብ አድርገን አይደለም። በቤት፣ በትምህርት ቤትና በጉባኤ ውስጥ ሥራ መሥራትንም ተምረዋል።”
ዶን እና ሩት የሚዝናኑት እንዲያው ባጋጣሚ ሳይሆን ጊዜ መድበው ነበር። “ቅዳሜን ‘የቤተሰብ ቀን’ አድርገን መድበን ነበር” በማለት ገልጸዋል። አክለውም “ጠዋት በመስክ አገልግሎት እንካፈላለን፤ ከሰዓት በኋላ ዋና እንሄዳለን፤ ምሽቱን አስደሳች ለማድረግ ደግሞ ከወትሮው ለየት ያለ ምግብ እንመገባለን” ብለዋል።
እነዚህ ወላጆች የሰጡት አስተያየት ጠቃሚ በሆኑ መዝናኛዎች ጊዜ በማሳለፍ ረገድ ሚዛናዊ የመሆንን አስፈላጊነት እንዲሁም መዝናኛ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ተገቢው ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ያጎላል።—መክብብ 3:4፤ ፊልጵስዩስ 4:5
በይሖዋ መታመን
መንፈሳዊ መከላከያችንን መገንባት በርካታ ዓመታት ሊፈጅ ይችላል። ልጆች በሰማያዊ አባታቸው እንዲታመኑ የሚያስችላቸውን አምላካዊ ጥበብ በውስጣቸው የሚያሰርጽ ተዓምራዊ መድኃኒት የለም። አምላካዊ ጥበብ ሊሰርጽባቸው የሚችለው ወላጆች ‘በጌታ ምክርና ተግሣጽ ካሳደጓቸው’ ነው። (ኤፌሶን 6:4) ይህ በቀጣይነት የሚሰጥ “ምክር” ልጆች አምላክ ለነገሮች ያለውን አመለካከት እንዲይዙ ይረዳቸዋል። ወላጆች ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
ቋሚ የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ መዝሙር 119:18) ዚዬጎ የቤተሰብ ጥናቱን በቁም ነገር ይመለከት የነበረ በመሆኑ ልጆቹ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ችለዋል። “ለጥናታችን በሚገባ እዘጋጃለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው በተዘጋጁ ጽሑፎች ተጠቅሜ ምርምር በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ባሕርያት ለልጆቼ እውን እንዲሆኑላቸው ለማድረግ ችያለሁ። በእነርሱና በታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ምን ተመሳሳይነት እንዳለ እንዲያነጻጽሩ አበረታታቸው ነበር። ይህም ልጆቼ ይሖዋን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ በግልጽ እንዲረዱ አስችሏቸዋል” በማለት ተናግሯል።
ለስኬት ዋነኛው ቁልፍ ነው። ይህ ጥናት ‘ከሕግ ድንቅ ነገሮችን እንዲያዩ ዐይኖቻቸው እንዲከፈቱ’ ያደርጋቸዋል። (ልጆች መደበኛ ባልሆነም መንገድ መማር ይችላሉ። ሙሴ፣ ወላጆች የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ‘በቤታቸው ሲቀመጡ፣ በመንገድ ሲሄዱ፣ ሲተኙና ሲነሱ’ ለልጆቻቸው እንዲነግሩ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ዘዳግም 6:7) አንድ አባት እንዲህ ብሏል:- “ልጄ የልቡን አውጥቶ የሚናገርበትና ስሜቱን የሚገልጽበት ጊዜ ይፈልግ ነበር። የእግር ጉዞ በምናደርግበትና አብረን ሥራ በምንሠራበት ጊዜ መግቢያ መንገድ ይፈልግና ችግሩን ግልጽልጽ አድርጎ ይነግረኛል። በእነዚህ ጊዜያት ሁለታችንንም የሚጠቅሙ ጥሩ ጥሩ ሐሳቦችን እንለዋወጣለን።”
ወላጆች የሚያቀርቡት ጸሎትም እንዲሁ በልጆች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያደርጋል። ልጆች ወላጆቻቸው አምላክ እንዲረዳቸውና ይቅር እንዲላቸው በትሕትና ሲጸልዩ መመልከታቸው ‘እግዚአብሔር መኖሩን እንዲያምኑ’ ያስችላቸዋል። (ዕብራውያን 11:6) የተሳካላቸው ብዙ ወላጆች ቤተሰቡ በአንድ ላይ መጸለዩ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አጥብቀው ይናገራሉ፤ እንዲህ ባለ ጸሎት ላይ የትምህርት ቤት ጉዳዮችንና ልጆቻቸውን የሚያስጨንቁ ሌሎች ነገሮችን ማካተት ይቻላል። አንድ አባት ልጆቹ ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት ከእናታቸው ጋር እንደሚጸልዩ ተናግሯል።—መዝሙር 62:8፤ 112:7
“በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት”
ሁሉም ወላጆች ይሳሳታሉ፤ በመሆኑም አንዳንድ ሁኔታዎችን በተመለከተ ያደረጉት ውሳኔ ይጸጽታቸው ይሆናል። የሆነ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በጎ ነገር ከማድረግ ሳንታክት’ ትግላችንን መቀጠል እንዳለብን ይገልጻል።—ገላትያ 6:9
ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ወላጆች የልጆቻቸው ጉዳይ ግራ ሲያጋባቸው ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ወጣቱ ትውልድ ለየት ያለና አስቸጋሪ ነው ብሎ መደምደም ቀላል ነው። ሕግ እንዲጥሱ የሚደረግባቸው ግፊት እየጨመረ ቢሆንም እንደ እውነቱ ከሆነ የዛሬ ልጆች ቀደም ሲል ከነበረው ትውልድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድክመትና ፍላጎት አላቸው። ስለዚህ አንድ አባት ለልጁ እርማት ከሰጠ በኋላ “ልብህ ማድረግ የሚፈልገው እኔ በአንተ ዕድሜ በነበርኩበት ጊዜ ማድረግ እፈልግ የነበረውን ነገር ነው” በማለት ቀድሞ የሰጠውን ተግሣጽ ለዘብ የሚያደርጉ ቃላት ሊናገር ይችላል። ወላጆች ዘመናዊ ስለሆኑ ነገሮች የወጣቶችን ያህል ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ባይኖራቸውም ፍጹም ስላልሆነው ሥጋችን ዝንባሌ በደንብ ያውቃሉ።—ማቴዎስ 26:41፤ 2 ቆሮንቶስ 2:11
ምሳሌ 22:6፤ 23:22-25) አሁን በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እያገለገለ ያለው ማቲው የተባለ ወጣት ክርስቲያን እንዲህ ብሏል:- “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለሁ ወላጆቼ የሚጥሉብኝ እገዳ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማኝ ነበር። ከዚህም በላይ ‘የጓደኞቼ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚፈቅዱላቸውን ነገር የእኔ ወላጆች የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። በታንኳ መጓዝ እወድ ስለነበር አንዳንድ ጊዜ ወላጆቼ ለቅጣት ብለው እንዳልሄድ ሲከለክሉኝ በጣም እበሳጭ ነበር። ሆኖም አሁን መለስ ብዬ ሳስበው ወላጆቼ ይሰጡኝ የነበረው ተግሣጽ በጣም ውጤታማና አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። የሚያስፈልገኝን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ስለሰጡኝ በጣም አመሰግናቸዋለሁ።”
ምናልባት አንዳንድ ልጆች ወላጆቻቸው የሚሰጧቸውን መመሪያዎች እሺ ብለው ላይቀበሉ አልፎ ተርፎም እርማት ሲሰጣቸው ሊቃወሙ ይችላሉ። በዚህም ጊዜ ቢሆን ትዕግሥት ያስፈልጋል። ብዙ ልጆች መጀመሪያ ላይ ቅር ቢላቸውም ወይም ለተወሰነ ጊዜ በእምቢተኝነታቸው ቢቀጥሉም ውለው አድረው አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ። (ምንም እንኳን ልጆቻችን አንዳንድ ጊዜ ጤናማ መንፈሳዊ ሁኔታ ባልሰፈነበት አካባቢ ለመኖር ቢገደዱም ጥሩ ክርስቲያን ሆነው ሊያድጉ እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ጥበብ መንፈሳዊ መከላከያ እንደሚያስገኝላቸው ተስፋ ይሰጣል። እንዲህ ይላል:- “ጥበብ ልብህ ውስጥ ትገባለችና፤ ዕውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለች፤ የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ ማስተዋልም ይጠብቅሃል። ጥበብ. . . ከክፉዎች መንገድ ታድንሃለች።”—ምሳሌ 2:10-12
አንድን ልጅ ለዘጠኝ ወራት በማሕፀን መሸከም ቀላል አይደለም። ከዚያ በኋላ ያሉት 20 ዓመታት በበኩላቸው ደስታና ኃዘንን ይዘው ይከተላሉ። ሆኖም ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ስለሚወዱ በአምላካዊ ጥበብ አማካኝነት እነርሱን ለመጠበቅ የተቻላቸውን ጥረት ሁሉ ያደርጋሉ። እነርሱም አረጋዊው ሐዋርያው ዮሐንስ መንፈሳዊ ልጆቹን በተመለከተ ይሰማው የነበረውን ስሜት ይጋራሉ:- “ልጆቼ በእውነት የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም።”—3 ዮሐንስ 4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በማንኛውም ሰዓት ቤታችን ክፍት ስለነበር ሁልጊዜ በወጣቶች እንደተሞላ ነው”
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የልጆቻችሁ ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አድርጉ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ለጥናታችን በሚገባ እዘጋጃለሁ”