በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብዙዎች ሃይማኖት ለሰው ዘር አንድነት ሊያስገኝ መቻሉን የሚጠራጠሩት ለምንድን ነው?

ብዙዎች ሃይማኖት ለሰው ዘር አንድነት ሊያስገኝ መቻሉን የሚጠራጠሩት ለምንድን ነው?

ብዙዎች ሃይማኖት ለሰው ዘር አንድነት ሊያስገኝ መቻሉን የሚጠራጠሩት ለምንድን ነው?

“ጎረቤትህን . . . ውደድ።” (ማቴዎስ 22:39) በርካታ ሃይማኖቶች ይህንን መሠረታዊ የሥነ ምግባር መመሪያ ይደግፋሉ። እነዚህ ሃይማኖቶች ምዕመኖቻቸው ጎረቤቶቻቸውን እንዲወድዱ በማስተማር ረገድ ቢሳካላቸው ኖሮ አባሎቻቸው አንድነት ይኖራቸው ነበር። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለ አንድነት ተመልክተሃል? ሃይማኖቶች አንድነት የሚያስገኝ ተጽዕኖ ማሳደር ችለዋል? በቅርቡ በጀርመን በተካሄደ አንድ ጥናት ላይ “ሃይማኖቶች ሰዎች አንድነት እንዲኖራቸው ማድረግ ችለዋል ወይስ እርስ በርስ እንዲከፋፈሉ እያደረጉ ነው?” የሚል ጥያቄ ለተሳታፊዎቹ ቀርቦላቸው ነበር። በጥናቱ ከተካፈሉት መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት ሃይማኖት አንድነት እንደሚያስገኝ የሚሰማቸው ሲሆን 52 በመቶ የሚሆኑት ግን መለያየትና ክፍፍል እንደሚፈጥር ተሰምቷቸዋል። ምናልባት አንተ በምትኖርበት አገር ያሉ ሰዎችም ተመሳሳይ ስሜት ይኖራቸው ይሆናል።

ብዙ ሰዎች ሃይማኖት ለሰው ዘር አንድነት ሊያስገኝ መቻሉን የሚጠራጠሩት ለምንድን ነው? እንደዚህ ዓይነት ስሜት ያደረባቸው በታሪክ ዘመናት ከተመለከቷቸው ነገሮች በመነሳት ይሆናል። ሃይማኖት ሰዎች አንድነት እንዲኖራቸው ከማድረግ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ሲከፋፍላቸው ይታያል። አንዳንድ ጊዜም በሃይማኖት ሽፋን በጣም ዘግናኝ የሆኑ የጭካኔ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ተስተውሏል። ባለፈው ምዕተ ዓመት ብቻ የተከናወኑ አንዳንድ ክስተቶችን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

ሃይማኖት የሚያሳድረው ተጽዕኖ

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በባልካን አገሮች በሚገኙት የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታዮች በሆኑ ክሮአቶችና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባላት በሆኑ ሰርቦች መካከል ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ ነበር። ሁለቱም ወገኖች ደቀ መዛሙርቱ ጎረቤታቸውን እንዲወድዱ ያስተማረው የኢየሱስ ተከታዮች ነን የሚሉ ነበሩ። ሆኖም በመካከላቸው የተፈጠረው ጦርነት “በታሪክ ዘመናት ሁሉ በንጹሐን ዜጎች ላይ ከተፈጸሙት በጣም ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች” መካከል የሚመደብ እልቂት እንዳስከተለ አንድ ተመራማሪ ገልጸዋል። ከ500,000 የሚበልጡ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ሕይወት የቀጠፈው ይህ ውጊያ የዓለምን ሕዝብ ያስደነገጠ ነበር።

በ1947 ሕንድ 400 ሚሊዮን ነዋሪዎች (ከዓለም ሕዝብ መካከል አንድ አምስተኛ የሚሆነው ማለት ነው) የነበሯት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሂንዱዎች፣ ሙስሊሞችና የሲክ ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ። ሕንድ ስትከፋፈል ፓኪስታን የተባለች የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች አገር ተፈጠረች። በዚህ ወቅት በሃይማኖት ስም በተፈጸመ ጭፍጨፋ ከሁለቱም አገሮች የተሰደዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተቃጥለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶባቸዋል እንዲሁም በጥይት ተገድለዋል።

ከላይ የተጠቀሱት ዘግናኝ እልቂቶች የማይበቁ ይመስል በ21ኛው መቶ ዘመን ደግሞ ዓለም የሽብርተኝነት ስጋት አጥልቶበታል። በዛሬው ጊዜ ሽብርተኝነት መላውን ዓለም ስጋት ላይ የጣለው ሲሆን አብዛኞቹ ሽብርተኛ ቡድኖች ከሃይማኖታዊ ድርጅቶች ጋር ትስስር እንዳላቸው ይናገራሉ። ሃይማኖት አንድነት ሊያስገኝ እንደሚችል ተደርጎ መታየቱ ቀርቶ አብዛኛውን ጊዜ ከዓመጽና ከመከፋፈል ጋር እየተዛመደ ነው። በመሆኑም ፎከስ የተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ እንደ ቡድሂዝም፣ ክርስትና፣ ኮንፊሺያኒዝም፣ ሂንዱይዝም፣ እስልምና፣ ጁዳይዝምና ታኦይዝም ያሉትን የዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች ከባሩድ ጋር ማመሳሰሉ አያስገርምም።

የውስጥ ሽኩቻ

አንዳንድ ሃይማኖቶች የሚጋጩት ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ በራሳቸው ሃይማኖት ውስጥ በተፈጠሩ ውዝግቦች እየታመሱ ነው። ለአብነት ያህል፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በመሠረተ ትምህርቶች ላይ በተነሳ ማባሪያ የሌለው ውዝግብ ሳቢያ ተከፋፍለዋል። ቀሳውስቱም ሆኑ ምዕመናኑ የወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም ይፈቀዳል? ጽንስ ማስወረድስ? ሴቶች ቀሳውስት ሆነው መሾም አለባቸው? ቤተ ክርስቲያኗ ግብረ ሰዶምን እንዴት ልትመለከተው ይገባል? ሃይማኖት ለጦርነት ቡራኬ መስጠት አለበት? እንደሚሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ ይወዛገባሉ። አንዳንዶች እነዚህን የመሳሰሉ ልዩነቶችን ሲመለከቱ ‘አንድ ሃይማኖት የራሱ አባላት እንኳ አንድነት እንዲኖራቸው ማድረግ ካልቻለ ለሰው ዘር እንዴት አንድነት ሊያስገኝ ይችላል?’ ብለው ይጠይቃሉ።

በጥቅሉ ሲታይ ሃይማኖት አንድነት ማስገኘት እንዳልቻለ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የዚህ ዓይነት ችግር ያላቸው ሁሉም ሃይማኖቶች ናቸው? ለሰው ዘር አንድነት ሊያስገኝ የሚችል ለየት ያለ ሃይማኖት ይኖር ይሆን?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1947 በሕንድ በሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ የቆሰሉ ፖሊሶች

[ምንጭ]

Photo by Keystone/Getty Images